አዲስ ዘመን ድሮ

ቆየት ካሉ የአዲስ ዘመን ትውስታዎች ከተለያዩ ዓመተ ምህረት እትሞች መርጠን ለዛሬ አቅርበናል:: አምስት አንበሶች ሁለት ሰው ገደሉ፣ የሎተሪ ቲኬት ስለሰረቀው ግለሰብ፣ ከነጭ ጋር አብራችሁ ተሳፍራችኃል በሚል ተይዘው ስለታሰሩት የጥቁሮች ጉዳይ፣ እንዲሁም ከፊታችን ስለሚከበረው ስለ መስቀል በዓል(መስከረምና የመስቀል በዓል) በተጨማሪ ደግሞ “አንድ ጥያቄ አለኝ” ከተሰኘው ገጽ ላይ አንባቢያን ስለ መፍትሔ ሲሉ ያቀረቡትን ጉዳዮች መለስ ብለን እንመለከታቸዋለን::

አምስት አንበሶች ሁለት ሰው ገደሉ

በወለጋ ክፍለ ሀገር በሆሮ ጉድሩ አውራጃ በእመራ ቀበሌ ውስጥ 5 የአንበሳ መንጋዎች ሁለት ሰዎችና አንድ በሬ ገድለው አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ማቁሰላቸው ተገለጠ:: እነኚሁ የአንበሳ መንጋዎች በዚሁ አካባቢ ካለው በረሃ ውስጥ በመውጣት የአቶ ታዬ ቶሌራን አንድ በሬ ይዘው ከበሉ በኋላ ለርዳታ የደረሱትን የበሬውን ባለቤትና አንድ ሌላ ሰው ነክሰው መግደላቸው ታውቋል::

ከዚህም በቀር የቀበሌው የሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ጓድ አባሎች ከሥፍራው ደርሰው ርዳታ ለማድረግ በመጣር ላይ እንዳሉ፤ አንደኛው አባል በአንበሶቹ ከተነከሰ በኋላ ይዞት የነበረውም ጠመንጃ አንደኛው አንበሳ አስጥሎት በጥርሱ ንክሻ በመሸሽ ላይ እንዳለ በአንድ ሌላ ሰው በተተኰሰ ጥይት ተገድሏል::

የቀሩት አራቱ አንበሶች ግን ሸሽተው ወደ ጫካ መግባታቸውን የወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል:: በሌላ በኩል ደግሞ፤ በነቀምቴ አውራጃ በዋማ ሀገሎ ወረዳ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙት አርሶ አደሮች፤ ፀረ ሰብል የሆኑትን 280 አውሬዎች መግደላቸውን ጽሕፈት ቤቱ ጨምሮ አስታውቋል::

(አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 1969 ዓ.ም)

የሎቶሪ ቲኬት ሰረቀ የተባለ ተከሰሰ

ከሥራ ጓደኛው ኪስ 25 የሎቶሪ ቲኬት ሰርቆ በሚደርሰው የብሔራዊ ሎቶሪ ዕድል ለመጠቀም የሞከረው ታደሰ ወርቁ ተከሶ አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ::

ተከሳሹ ቲኬቱን ወሰደ የተባለው፤ አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ፖሊስ ሆስፒታል አጠገብ እየተባለ ከሚጠራው ቀበሌ መሆኑን ከፍርድ ቤቱ የተከፈተበት የዐቃቤ ሕግ ክስ ይገልጣል:: ተከሳሹ በሌላ ሰው ዕድል ለመጠቀም ሞክሯል የተባለው አቶ መሐሪ ንዳ የገዙትን የሎቶሪ ቲኬት ግንቦት 1 ቀን 1966ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ ከቤታቸው ሰርቆ መሆኑን ተገልጧል::

(አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 1966ዓ.ም)

ፈንጣጣ በ 6 ወር ውስጥ ከቁጥጥር ስር ይውላል

የፈንጣጣ በሽታ በሚቀጥሉት ስድስት ወሮች ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ይቻላል ተብሎ በመገመቱ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለዚህ ተግባር ተባባሪ ሆኖ መገኘት እንዳለበት ዶክተር ኬኤል ዊትሐለር የፈንጣጣ ማጥፊያ ፕሮግራም ዳሬክተር ትናንት በተከፈተው ሴሚናር ላይ አስገነዘቡ::

ዶክተር ዊትሐለር፤ በፈንጣጣ የተጠቃው ቀበሌ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በጌምድርን፣ ጎጃምን፣ ምዕራባዊ ወሎንና ሰሜናዊ ሸዋን እንደሆነና በሌሎች ጠ/ግዛቶች በሽታውን የማጥፋት ሥራ በደንበኛው በመካሔድ ጨርሶ ለማጥፋት የሚያስፈልገው ጊዜ ጥቂት ወሮች እንደሆነ አስረድተዋል::

(አዲስ ዘመን ግንቦት 13 ቀን 1966ዓ.ም)

ተይዘው ታሠሩ

ሃያ አምስት የሆኑ ጥቁር አሜሪካኖችና ሁለት ነጮች ከሞንት ጎሞሪ ወደ ጃክሶም ሚስፒ በአውቶብስ ተሳፍረው መጥተው ባረፉ ጊዜ ለምን አብራችሁ ሄዳችሁ በማለት በከተማው ፖሊሶች ተይዘው ታስረዋል:: እነኚህ ጥቁሮች አንታሰርም በማለት ፖሊሶቹን በማሰራቸው ሰዓት እላፊ ጭምር በእሥር ቤት ቆይተው እንደገና ወደ ፍርድ ቤት በነጋታው እንዲቀርቡ ተደርጓል::

(አዲስ ዘመን መስከረም 24 1955ዓ.ም)

የመስቀል በዓልና መስከረም

በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከበሩት ታላላቅ በዓሎች በተለይ የዘመን መለወጫን በዓል ተከትሎ የሚውለው የመስቀል በዓል አከባበር፤ ከማናቸውም በዓሎች ይልቅ ብሔራዊና መንፈሳዊ በዓል በመሆኑ ትልቁም ትንሹም በታላቅ ክብር ሲያከብረው አያሌ ዘመን ሆኗል::

በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የመስቀል ዋዜማ ከሆነው ከበዓለ ደመራው ጀምሮ እስከ ማግስቱ 17 ቀን ድረስ የሚከበረው ይህ ብሔራዊና መንፈሳዊ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በወሰነችው መሠረት ነው:: የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል፤ የሕዝቡንም መንፈሳዊ ስሜት ለማወቅና ለመረዳት፤ ብዙዎች የውጭ ሀገር ጎብኚዎች(ቱሪስቶች)ፊልም አንሺዎች፣ ታሪክ አጠናቃሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የመስከረሙን የመስቀል በዓልና የጥሩና የጥምቀቱን የቃና ዘገሊላን ብሔራዊ መንፈሳዊ በዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ለመመልከት መሆኑ ግልጽ ነው::

(አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 1966ዓ.ም)

አንድ ጥያቄ አለኝ

ለጳውሎስ ኞኞ

አዲስ አበባ

*ባለኝ የጠጉር ማስተካከያ ሱቄ ውስጥ የሚሰሩት ሠራተኞች እኔ ለሥራ የምገዛቸውን ቅባቶች እንዳስፈለጋቸው ሲቀቡትና ሲታጠቡበት ከመዋላቸውም በላይ እንዲሁም ልጆቻቸውን በነጻ ያስተካክላሉ:: ልጄና እኔ በምንላጭበት ጊዜ ግን እንድንከፍል እንጠየቃለን:: ለመሆኑ እኔ በገዛኋቸው ቅባቶችና በምከፍለው የቤት ኪራይ እነርሱ እንዳስፈለጋቸው ሲጠቀሙበት ይሉኝታ እየፈራሁ ዝም ስል እነርሱ ግን ልጄንና እኔን በምንላጭበት ጊዜ ማስከፈል ተገቢ ነውን?

ኪዳነ ማርያም አባይ (ከአዲስ አበባ)

-እንደ ውለታችሁ ነው:: ስትዋዋሉ ተነጋግራችሁበት እንደሆነ በንግድ ይሉኝታ የለም:: ባይሆን ልጅዎን በነጻ ቢያስተካክሉልዎ አይከፋም::

(አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 1966ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016

Recommended For You