የአፈር አሲዳማነትን የሚቀንሰው የወጣቶቹ የማዳበሪያ ምርምር ውጤት

የአፍሪካ ሀገራትን ልማትና እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑ መካከል የውጪ ምንዛሬ አንዱ ነው። ይሁን እንጂ እድገቱን እውን ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ጥሬ እቃዎችንና ልዩ ልዩ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በአህጉሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ይታያል። ይህንን ችግር ለመፍታት ሲባል ለእርዳታና ብድር ደጅ መጥናት የግድ ይላል። ይህ አካሄድ ደግሞ ብድርና እርዳታ አቅራቢ ሀገራት የእርዳታ ጠያቂ ሀገሮችን ሉአላዊነት በሚጥስ መልኩ በውስጥ ጉዳዮችና በፖሊሲ ውሳኔዎች ላይ እጃቸውን እንዲያስገቡ በር ይከፍታል።

አፍሪካውያን አሁን ላይ የወጪና ገቢ ንግድ በአግባቡ ተፈጻሚ እንዳይሆን ፈተና ከሆኑባቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑን እየገነዘቡት መጥተዋል ማለት ይቻላል:: ለዚህም በርካታ አገራት ከምእራባውያን የእጅ አዙር ተፅእኖ ለመላቀቅ የሚያስችሉ የፖሊሲ አማራጮችን እየወሰዱ ይገኛሉ። ከእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ አንዱ ምርትን ማሳደግ ሀገር በቀል የፈጠራ ክህሎትን መጨመር፣ ተኪ ምርቶች ላይ መስራት የሚሉት ይገኙበታል። ይሄ አማራጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ያስገቧቸው የነበሩ ምርቶችን በራሳቸው አቅም እንዲሸፍኑ ከማድረጉም በላይ ከላይ ያነሳነውንት ተፅእኖ ያስቀራል::

በእርግጥ ሁሉም ሀገራት ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ይሸፍኑ ማለት አይቻልም:: በኢኮኖሚና በስልጣኔ ጫፍ የደረሱት ሀገራትም ይህንን የማድረግ አቅም የላቸውም፤ የተፈጥሮም ሆነ የመልከዓ ምድር አቀማመጥ ይህንን የሚፈቅድ አይደለም። ለምሳሌ እጅግ ቀዝቃዛማ በሆነ ቦታ ቡናን ማምረት አይቻልም፤ ደረቃማ በሆነ ቦታም ሩዝን ማምረት ያስቸግራል። በዚህ ምክንያት በራስ አቅም መሸፈን የማይቻል ምርት የግዴታ ከውጪ በውጭ ምንዛሬ በግዢ ማስገባት ማስፈለጉ አይቀርም።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት የምርት ፍላጎትን ከውጪ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማስገባት የሚገደዱበት ሌላኛው ምክንያት የተፈጥሮ ማእድናት አለመኖር፣ ሀብቶቹ ኖረውም ማልማት የሚቻልበት ሁኔታ አለመመቻቸት ይጠቀሳሉ:: ለምሳሌ ያህል ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች አገር አይደለችም። በዚህ ምክንያት የውስጥ ፍላጎትን ለመሸፈን የግዴታ በውጪ ምንዛሬ ገዝታ ማስገባት የግድ ይላታል። ነዳጅ በአገር ውስጥ የማምረት ጅምር ጥረቱን ብታጠናክርና ውጤታማ ብትሆን ግን ይህንን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት ትችላለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከላይ ያነሳናቸውን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ቀርፆ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ አንዱ በግብርናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር አመት መሪ እቅድ በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ::

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ በ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በስፋት እየተሰራ ነው:: በተፈጥሮ ጋዝ፣ ነዳጅ፣ ማእድን ዘርፍም እንዲሁ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረት ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ናቸው።

በተለይ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሥራ ፈጠራ፣ በኢንተርፕረነር ሺፕ (ስታርት አፕ) በኩል ወጣቶችና የግል ዘርፉ ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው እየተሰራ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ይፋ እያደረገ ይገኛል። ይህ እንቅስቃሴም በራስ አቅም መተካት የሚቻሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን በማምረት ከውጭ ተጽእኖ ለመላቀቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ይጠበቃል::

የውጭ ምንዛሬ ወጪን መቀነስ ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ የወጣቶችን የፈጠራና ምርምር ብቃት ማሳደግ የሚለው ይገኝበታል። ወጣቶች ክህሎታቸውን አሳድገውና እውቀታቸውን አዳብረው በርካታ የሥራ እድል የሚፈጥሩ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የሚሸፍኑ ቴክኖሎጂዎችንና የምርምር ውጤቶችን ማቅረብ ይችላሉ። ይህ ጥረት ራሳቸውን ከመለወጥ አልፎ የኢትዮጵያ የእድገት መሰረትና የችግሮች ቁልፍ መፍቻ ይሆናል።

መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን በራስ አቅም በሀገር ውስጥ ግብዓት ተጠቅሞ ማምረት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። ከዚህ አኳያ የወጣቱን የፈጠራ ችሎታና አቅም መጠቀም በእጅጉ ያስፈልጋል:: በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የላቀ ብቃት ያላቸው የብሩህ አእምሮ ባለቤቶችን “የአእምሮ ውጤት” ማቀናጀት እና ትርጉም ባለው መልኩ መሬት ላይ አውርዶ ጥቅም ላይ ማዋል ለእድገት፣ ብልፅግና እና ስልጣኔ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያም ይህንን ፍላጎትና ሀገራዊ እቅድ ሊያሳኩ የሚችሉ የበርካታ ወጣቶች እናት ነች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ወጣቶች ችግር ፈች የሆኑ ሃሳቦችን ሲያፈልቁና የፈጠራ ሥራዎችን እውን እያደረጉ ሲያስተዋውቁ እየተመለከትን ነው:: መንግስትም ወጣቶች የፈጠራ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትና ችሎታቸውን የሚያሳድጉበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን (ማእከላትን) እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን እየገነባ ወደ ስራ እያስገባ ይገኛል። የወጣቱን የፈጠራ ክህሎት አቅም አቀናጅቶ ለሀገር ልማት ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተመዘገቡ ውጤቶችም ተስፋ ሰጪ ናቸው።

በጥረቶቻቸው የተገኙ የፈጠራ ውጤቶች በተለያዩ መድረኮች ለውድድር ሲቀርቡ፣ በኢግዚቢሽንና ባዛር ሲተዋወቁ፣ የአንዳንዶቹም የፈጠራ ውጤቶች ከአልሚዎች ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ምርት እንዲገቡ ሲደረጉ እየታየ ነው::

መንግሥት የምርምርና የፈጠራ ክህሎትን ለማሳደግና ፍላጎቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከሚወስደው እርምጃና ከሚያደጋቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች ባሻገር “ተሰጦና ክህሎት” ያላቸው ወጣቶች በግል የሚያደርጉት ጥረት የሚያበረታታ እየሆነ ነው።

ይህንን ጉዳይ በምሳሌ ለመመልከት እንዲያስችለን በቅርቡ ሁለት ወጣቶች ያበረከቱትን የፈጠራ ውጤት እንመለከታለን። እነዚህ ወጣቶች ልክ እንደ መሰል የፈጠራ ሙያ ጓደኞቻቸው ከትምህርት ጎን ለጎን “ችግር ፈቺ ነው” ያሉትን የመፍትሄ ሀሳብ በማፍለቅና ምርምር በማድረግ የድርሻቸውን ለማበርከት የሞከሩ ናቸው።

የወጣቶቹ ምርምርና ውጤታቸው ያተኮረው በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የአፈር ማለስለሻ “ማዳበሪያ” ላይ ነው። ወጣቶቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያደረገ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በሚያስችል የምርምር ውጤት ላይ ያተኮረ የምስራች እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል።

ተመራማሪዎቹ ወጣት ጌታሁን ምናለ እና ወጣት በአምላኩ ፈንታሁን ይባላሉ:: ባሳለፍነው ዓመት በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት መስክ በ2014 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል:: በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቄራ ተረፈ ምርት በሆነው “አጥንት” የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያን መስራት ችለዋል:: ወጣት ባለሙያዎቹ የአፈር ማለስለሻ ማዳበሪያ ላይ ለመመራመር ፍላጎት ያደረባቸው በኢትዮጵያ 43 በመቶ የሚሆነው የሚታረስ መሬት የአፈር አሲዳማነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ችግር ምርታማነት ከዓመት ዓመት እየቀነሰና የአቅርቦት እጥረት እየተፈጠረ መሆኑን ተገንዝበዋል:: በዚህም ምክንያት ችግሩን ሊፈታ የሚችል ምርምር ለመስራት መነሳሳታቸውን ይናገራሉ::

የምርምር ሂደቱ በጣም ፈታኝ እንደነበር የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ ምርምሩን ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን ያስኬዱት እንደነበር ይገልጻሉ:: ውጤታማ የአፈር ማዳበሪያ ምርት ለማግኘት በርካታ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን እንዳሳለፉና ሂደቱ አድካሚ እንደነበር ያስታውሳሉ። የምርምር ስራውንም ለማጠናቀቅና ከአጥንት ተረፈ ምርት በሀገር ውስጥ የሚመረት ማዳበሪያ ለመስራት በጥቅሉ ሁለት ዓመታትን እንደወሰደባቸው ይገልፃሉ::

ወጣት በአምላኩ እንደሚናገረው፤ ጠቃሚ የሆኑ ቀደም ብለው የተሰሩ ጥናቶችን በመዳሰስና በማንበብ የተጀመረው ጥናት ወደ ሀሳብ ማበለፀግ ግብአቶችን በመሰብሰብ፣ የንጥረ ነገር ይዘታቸውን በመመርመር፣ በመፍጨት፣ (ሳይዝ ሪዳክሽን) በማመጣጠን ሃሳቡ ወደ ተግባር ሊያድግ ችሏል::

ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ ሁሉንም ከቄራዎች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን መጠቀም የሚቻል መሆኑን ጠቅሰው፣ እነሱ ግን በአሁኑ ሰዓት በዋናነት አጥንቶችን ነው የሚጠቀሙት:: የእንስሳት አጥንት በባህሪው ከፍተኛ “የፎስፈረስ” ክምችት ስላለው ያንን በከፍተኛ ሙቀት (እሳት) በማፍላት ለመፍጨት ቀላል እንዲሆንና በላዩ ላይ ያሉ ሞራዎች በቀላሉ እንዲወገዱ ይደረጋል:: በዚህም 42 እስከ 52 በመቶ የሚሆን ፎስፈረስ የተባለ ንጥረ ነገር ማግኘት ተችሏል::

“የአፈር ማዳበሪያው ከተፈጥሯዊ ግብዓት ለተፈጥሮ የሚዘጋጅ በመሆኑ ለከባቢ አየሩና ለግብርና ምርት ተስማሚ ነው” የሚለው ወጣት በአምላኩ፤ እርጥበትን የመምጠጥ አቅሙም ከፍተኛ በመሆኑ በልዩ ሁኔታም ለበረሀማ ቦታዎች ተስማሚ እንደሆነ ይናገራል:: ይህም የአፈር አሲዳማነትን በመቀነስ ምርትን ማሳደግ እንደሚያስችል ይገልፃል።

የምርምር ባለሙያውና የበአምላኩ ባልደረባ ወጣት ጌታሁን በበኩሉ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎች በቀላሉ ስለሚሟሙ በውሃ ታጥበ በቀላሉ ወደ ወንዞች ውስጥ እንደሚገቡ ይገልፃል። በወንዞቹም ውስጥ እንደ እንቦጭ ያሉ አረሞች እንዲራቡና እንዲስፋፉ ምክንያት ይሆናል:: የእነሱ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ግን በአንድ ጊዜ የማይሟሟ በመሆኑ በቀላሉ በውሃ አይታጠብም ፤ለእጽዋቱም በሂደት በመሟሟት ለእድገታቸው እና ለምርታማነታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል::

ወጣቶቹ የፈጠራ ውጤታቸው በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት መገምገሙን ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያው ውጤታማነትን ለመገምገም የዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀምና ያለምንም የአፈር ማዳበሪያ ተመሳሳይ ሰብሎችን በመዝራት ሙከራዎችን አድርገዋል:: በሙከራው የተገኘው ውጤት በወጣቶቹ ምርምር የተገኘው የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ የተሻለ ምርት እንደሚያስገኝ አረጋግጧል::

ወጣት ጌታሁን የምርምር ውጤት እስከአሁን ከተለመደው ዩሪያ እና ዳፕ ማዳበሪያዎች የሚለየውም የመጀመሪያውና ዋናው ነገር ገበያ ላይ ካለው ማዳበሪያ በተለየ መልኩ ፖታሲየም ኒውትረንት (NPK ፈልትራይዘር) ስላለው ነው ይላል:: ይህም የመሬትን አሲዳማነት ለመቀነስና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያስችልም ይገልጻል:: በኢትዮጵያ ይህ የማዳበሪያ ምርምር ውጤት በሰፊው ተመርቶ ገበያ ላይ ቢውልና አርሶ አደሩ እንዲጠቀምበት ማድረግ ቢቻል የላቀ ጥቅም እንደሚያስገኝም ይጠቁማል:: ምርቱ ወደ ገበያ መሰራጨት ቢጀምር በሀገር ውስጥ ግብዓትና በሀገር ልጆች የሚመረት በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሬን እንደሚቀንስም ይናገራሉ።

“የአፈር ማዳበሪያው የማዳበሪያ እጥረትን በመቀነስ የገበያ መረጋጋትን ይፈጥራል” የሚለው ወጣት ጌታሁን፤ የሚመረትበት ግብዓትም ከቄራዎች የሚገኝ በመሆኑ አላስፈላጊ ተረፈ ምርቶችን ወደ ልማት በመቀየር የአካባቢ ንጽህናን ለመጠበቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ይገልፃል:: ለአፈር ማዳበሪያው ዋናው ግብዓቱ የሚገኘው ከተረፈ ምርት በመሆኑ ምክንያት የግዢ ዋጋውን በመቀነስ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል እድል እንደሚፈጥርም ይናገራል::

“የአፈር ማዳበሪያው ምርታማነትን ከመጨመርና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማስመዝገብ አንፃር ፋይዳውም የጎላ ነው” የሚለው ወጣት በአምላኩ፤ ለሙከራ የቀረበው የአፈር ማዳበሪያ ተፈጥሯዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ፤ ምርታማነትን እንዲጨምር እንደሚያስችል ይገልፃል:: ይህም ምርት የማይሰጡ መሬቶችን ምርት እንዲሰጡ እንደሚያደርግ፣ ከዋጋ እና ከተደራሽነት አንፃር ውጤታማ በመሆኑ ዜጎች አምራች እንዲሆኑ እንደሚያበረታታም ያብራራል። በተጨማሪ አርሶ አደሩ በቂ የአፈር ማዳበሪያ ስለሚያገኝ ሙሉ አቅሙን ማምረት እንዲችል ያደርገዋል:: ይህም የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት ባሻገር በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን መጠን በመጨመርና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የወጪ ንግዱ እንዲሻሻል በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬን ለሀገሪቱ ለማስገኘት እንደሚያግዝ ይናገራል::

“ወጣቶች ይህንንና መሰል የምርምር ስራዎችን መስራታቸውና የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ለሀገር ማበርከታቸው ያለው ፋይዳ በርካታ ነው” ሲል ወጣት ጌታሁን ያመለክታል። በሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ቁሶች አብዛኛዎቹ ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ይህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲዳከም አስተዋጾኦ ማድረጉን ይጠቁማል:: ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ዋነኛው መፍትሄ መሆኑን ያስረዳል።

የአፈር ማዳበሪያ ምርምሩን በሚሰሩበት ወቅት ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች እንደነበሩ ወጣቶቹ ገልጸዋል:: ከተግዳሮቶቹ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የመስሪያ እቃዎችና የኬሚካል እጥረት እንደነበር ወጣት ጌታሁን ይናገራል:: ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግም እነዚህ እና መሰል የፈጠራ ስራዎችን ወደ መሬት ማውረድ እና ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ይገልፃል። ለአዳዲስ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች የግብዓት አቅርቦትን ከማመቻቸት አንስቶ ልዩ ድጋፍ ማድረግም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ይገልፃል።

ሌላው ተግዳሮት የተገኘውን የምርምር ውጤት በማባዛትና ወደ ገበያ እንዲገባ ለማድረግ የመነሻ ኢንቨስትመንት ካፒታል እጥረት መኖሩ መሆኑን ጠቅሶ፣ እንደዚህ አይነት የምርምር ውጤቶችን ከመደገፍ አንፃር መንግስት፤ በቀላሉ ከፈጠራ ውጤት ባለቤቶች ጋር ሊገናኝ የሚችል እንዲሁም ፈጠራዎች ወደ ምርት የሚቀየሩበትን መንገድ የሚያመቻች ተቋም ቢመሰርት መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ::

ወጣቶቹ የአፈር አሲዳማነትን የሚቀንሰው በሀገር ውስጥ የተመረተው ማዳበሪያ እውቅና እንዲያገኝና ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ የሚሰሩበትን መንገድ እየተነጋገሩ እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል:: እንዲሁም ሌሎች አጋር ድርጅቶችን አብረው ለመስራት ማቀዳቸውንም ነግረውናል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016

Recommended For You