አዲሱን ዓመት በአዲስ ልብ

አዲስ አመትን በአዲስ ልብ ካልተቀበልነው አሮጌ ነው። አዲስ አመት አዲስ የሚሆነው እኛ በአስተሳሰብ ስንልቅና አዲስ ስንሆን ብቻ ነው። የሰው ልጅ ታሪክ አለው..ታሪክ ደግሞ በጊዜና በዘመን ውስጥ ያልፋል። የእያንዳንዳችን ታሪክ ከውልደት የሚጀምር በሞት የሚጠናቀቅ የዘመን ሀቅ ነው። ይህ ተፈጥሮአዊ እውነት ደግሞ የሰውን ልጅ ማረፊያ አድርጎ በተቀመጠለት የሥርዓት አውድ ውስጥ እየመጣ የሚሄድ ነው።

ጊዜ ሀጂውን እየሸኘ..መጪውን እየተቀበለ በማይዛነፍ ፍጹም እውነት ውስጥ ይጓዛል..የሰውን ልጅ ጉዳይ አድርጎ። ጊዜ ጌታ ነው..ጊዜ ፈራጅ ነው። ጊዜ መጽናናት መሻርም ሁሉንም ነገር ነው። በተፈጥሮ እውነት የጸና..በሚዛናዊነት ምህዋር ውስጥ ሳይንገዳገድ የቆመ መለኮታዊ ጽኑ ቃል ነው።

የጊዜ ጌትነት ግን በራሱ የሚሆን ሳይሆን በሰው ልጅ የማሰብ አቅም የሚወሰን የአእምሮ ነጸብራቅ ነው። የእያንዳንዳችን ትናንት የእያንዳንዳችን ዛሬና ነገ፣ የእያንዳንዳችን ድሮና ዘንድሮ፣ አምናና ካቻምና በዚህ በጊዜና በሰው ልጅ የጋርዮሽ መስተጋብር የተቃኘ ነው።

የሰው ልጅ በጊዜ ውስጥ ባለታሪክ ነው። ጊዜ በሰው ልጅ ውስጥ ጉልበታም ነው። የጊዜና የሰው ልጅ ቁርኝት ታሪክን እየደገመ፣ ተፈጥሮን እያጣቀሰ የሚያዘግም ነው። ጊዜ የታሪክ መፈጠሪያ፣ የህልምና ምኞት ካዝና ነው። የምንፈልጋቸው ነገሮች በጊዜ ውስጥ አልፈው የእኛ የሚሆኑ ናቸው።

ካለጊዜ ሰው፣ ካለሰው ጊዜ ምንም ናቸው። ጊዜና የሰው ልጅ እጅና ጓንት፣ መዳፍና አይበሉባ፣ መረብና አሳ ናቸው። ሁለት አካል አንድ ገጸ ሰብ፣ ሁለት ገላ አንድ አይነት መልክ። በተፈጥሮ እውቀትና ጥበብ ተሰናስለው የተደሩ የዳበሩም ናቸው።

ለዚህም ነው አዲስ አመት በመጣ ቁጥር አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ነፍስና ስጋ ፍለጋ የምንዋትተው። ለዚህ ነው አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ከአምናው የተለየን ለመሆን በአዲስ እቅድና በአዲስ ምኞት የምንሳበው። ለዚህ ነው እድሜአችን የሚያሳስበን፣ ሞታችን የሚያስጨንቀን።

ትልቁ የዘመን መለወጥ ፋይዳው በአስተሳሰቡ ለተቀየረና ተሀድሶን መሰረት ላደረገ አእምሮ ነው። ለለውጥ ካልተጠቀምንበት ጊዜ መጥቶ ከመሄድ ባለፈ ትርጉም የለውም። ትርጉም ያለው ሆኖ እንዲያልፍ የምናደርገው እኛ ነን።

አዲስ አመት እንደ ትርጉሙ አዲስ ነው። በውስጡ አንዳች ሀይልና ብርታት አለው። ለሰው ልጅ ሁሉ የሚሆን የመታደስ፣ የመበርታት መንፈስን በውስጡ ይዟል። ብዙዎቻችን ይሄን ሀይል እንፈልገዋለን። በዚህ ሀይል ውስጥ መኖር እንፈልጋለን። ለዚህም አመት ጠብቀን የምናቅድ፣ አመት ጠብቀን የምንጀምር፣ አመት ሲመጣ የምንበረታ ባጠቃላይ ለምንም ነገር አዲስ አመት የምንል ብዙዎች ነን።

የአዲስነት ስሜት የሚያድርብን አዲስ አመት ሲመጣና ሲቃረብ ነው። የመስራት የመለወጥ ፍላጎታችን የሚነሳሳው መስከረም ሊጠባ ጥቂት ሲቀረው ነው። ህልሞቻችን የሚታወሱን የአበቦቹን ሽታ ተከትለን ነው። ከአሮጌነት የምንወጣው፣ ከድሮነት የምንሸሸው ጻጉሜን ተሻግረን አበባየ ሆይ ሲባል የሚመስለን እልፍ ነን።

ህይወታችን፣ መኖራችን ትርጉም ያሚያገኝ የሚመስለን በዚህ ጊዜ ነው። ለአዲስ ህይወት የምንዘጋጀው ይሄን አዲስ ዘመን ታከን ነው። ሁሉ ነገራችንን ለአዲስ አመት አሳልፈን የሰጠን ነን።

ይሄ ስህተት ነው የሰው ልጅ የጊዜ ባሪያ መሆን የለበትም። ዛሬን ለለውጥና ለስኬት መጠቀም ይኖርበታል። የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር ከዛሬ በመጀመር፣ ከአሁን በማቀድ ማሳካት እንችላለን። ብዙዎቻችን ዛሬን አናውቀውም። የአሁንን ሀይል አልተረዳነውም።

የቆምንባት ቅጽበት የሀይል የለውጥ መጀመሪያ እንደሆነች ገና አልደረስንበትም። አዲስ አመት የምንም ነገር መጀመሪያ እንደሆነ አምነን የተቀበልን ነን። በአዲስ አመት ሰሞን ከሞት የምንነቃ፣ ካንቀላፋንበት የምንባንን ብዙ ነን።

በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ለውጥ የለም። በዚህ እምነት ውስጥ ስኬት የለም። ስኬት መነሻውም መድረሻውም አዲስ አመት ሳይሆን አዲስ አስተሳሰብ ነው። አዲስ አስተሳሰብ ደግሞ ዛሬን ከመጠቀም አሁንን ከመኖር የሚጀምር ነው። አዲስ አመት ሲያልፍ ምኞታችን አብሮ የሚያልፍ ከሆነ፣ አዲስ አመት ሲመጣ ምኞታችን ከሞተበት የሚነቃ ከሆነ የአዲስ አመትን ትርጉም አልተረዳነውም ማለት ነው።

ጊዜና ለውጥን አስታከው የተጻፉ ብዙ የስኬት መጽሀፎች አሉ። አንዳቸውም ለውጥ ከአዲስ ዘመን እንደሚጀምር አልጻፉም። የሁሉም የጋራ ሀሳብ ለውጥ ያለው ከዛሬና ከአሁን የሚል ነው።

በአስተሳሰቡ ላልተቀየረ ማህበረሰብ አዲስ አመት ምኑ ነው? ከመጠበቅና ተስፋ ከማድረግ ላልወጣ ሰውነት አዲስ አመት ዋጋው ስንት ነው? ፍቅርን ለማያውቅ ይቅርታን ላልተማረ ልብ ጊዜ ዘመን ምኑ ነው? ለማይሰሩ እጆች፣ ለማያስቡ ጭንቅላቶች መጠበቅ ፋይዳው ምንድነው?።

በብሄር፣ በጎሳ ለሚባላ ሀገርና ህዝብ የዘመን መቀየር ፋይዳው ምንድነው? ከወንድሞቹ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ ለሚኖር፣ ተነጋግሮ መግባባት፣ ተወያይቶ መስማማት ላቃተው ፖለቲካና ፖለቲከኛ፣ ትውልድና ዜጋ መሻገር ምንድነው? እኚህ ጥያቄዎች አሁን ላለንው እኛ መሰረታዊ ናቸው። የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ስናውቅና ስንረዳ ብቻ ነው የአዲስ አመትን ዋጋ ልንረዳው የምንችለው።

ያለፈውን አመት እንዲህ እንደአሁኑ ለመነቃቃት ተጠቅመንው ነበር። አምናን እኮ በእልልታና በፌሽታ ተቀብለነው ነበር። ካቻምናን እኮ የደስታና የሰላም ዘመን ብለንው ነበር። ያለፈውን አመት ብዙ ልንሰራበት ብዙ ልናተርፍበት አውርተን ነበር። 2015 እኮ እንደ ሀገር፣ እንደግለሰብ ብዙ ያቀድንበት ብዙ ያሰብንበት ዘመን ነበር ፤ግን እንደሀሳባችን አልተጠቀምንበትም። እንደምኞታችን አላዋልንውም። ምክንያቱም ከዘመን ጋር የተቀየረ አእምሮ ስላልነበረን ነው ፡

በተቃራኒው አመቱ መጥፎና እድለ ቢስ እንደነበር አወራን። ምንም ያላተረፍኩበት አመት ነው ስንል ነቀፍነው። ዘመን የሚዘወረው በሰው ልጅ አስተሳሰብ ነው። ያለፉት አመታቶች ጥሩ ያልነበሩት ዘመኑ ጥሩ ስላልነበር ሳይሆን እኛ ጥሩ ስላልነበርን ነው። እኛ ስላልተቀየርን ዘመኑም አልተቀየረም።

የሰው ልጅ ልቡና አእምሮው፣ ሀሳቡና ምኞቱ ካልተቀየረ አዲስ አመት ምንም ነው። ሀሳባችንን ሳናድስ፣ ከድሮነት ሳንወጣ ሰኔና ሀምሌ ገመገም ላይ ቆመን 2015 ለኔ ጥሩ ጊዜ አልነበረም፣ ለሀገራችን መልካም አልነበረም ብንል ልክ አይደለንም።

ዘመን ለሰው ልጅ ሎሌ እንጂ ሰው ለዘመን ሎሌ አይደለም። ሁሉን ነገር ለአዲስ አመት ትተን መቀመጣችን የዘመን ጥገኞች መሆናችንን ከማሳየቱ ባለፈ እያንዳንዱን ቀን ዋጋ ለመስጠት የምናደርገው የበረታ እንቅስቃሴ እንደሌለም የሚያሳይ ነው። ዘመን በእኛ ስር ነው። አዲስ አመት አዲስ የሚሆነው በእኛ አዲስ ልብ ነው። ልቦቻችንን አሳድፈን፣ መንፈሳችንን አስነውረን፣ ፍቅርና ይቅርታን ሳንማር፣ በመነጋገር ሳንግባባ፣ በእርቅ አንድ ሳንሆን ብንቀበለው ያው ነው እንደ ድሮው..እኛም ከእርግማን አንወጣም።

ተስፋ ያደረግንው አዲሱ አመት ያሰብንውን እንደሚሰጠን ዋስትናችን ምንድነው? የሚመጣው አዲስ አመት የምንመኘውን እርቅ፣ የምንፈልገውን አንድነት፣ የራቀንን ሰላም እንደሚሰጠን መተማመኛችን ምንድነው? ምንም መተማመኛ የለንም። ልንተማመንበት የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ራሳችን ነን። ራሳችንን ለፍቅር፣ ለይቅርታ፣ ለመነጋገር ዝግጁ ካደረግን እንዳሰብንው አዲስ አመት አዲስ ይሆናል። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ አዲስ አመትን አዲስ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው ።

ታሪኮቻችን ውብ እና ጋፍ የሚሆኑት በእኛ ነው። ጊዜ እኛ ተኝተን የሚያነቃ ሀይል የለውም። ለምንፈልገው ሰላም፣ ለምንፈልገው አንድነት፣ ለምንፈልገው እድገት ዘመን አስተዋጽኦ የለውም። ለዚህ ምስክር የሚሆኑን ያለፉ በአዲስ ምኞት ተቀብለናቸው አዲስነትን ያልሰጡን ዘመኖች ናቸው።

ተስፋዎቻችን ሀሳቦቻችን በኩል የሚያብቡ እንጂ በመስከረም መጥባት በኩል የሚታዩ አይደሉም። እንደዚህ አይነት መለማመዶች ለማንም አይጠቅሙም። ዘመን ያው እንደትላንቱ ነው። የተፈጥሮን እውነት ጠብቆ መጥቶ የሚሄድ ነው። አትምጣ ብንለውም፣ ና ብንለውም በእኛ ፍቃድ ስር አይደለም። መጥቶ መሄድ ተፈጥሮአዊ ግብሩ ነው።

ከዚህ እውነት በመነሳት አዲስ አመት ሲመጣም ሆነ ሲሄድ የተለየ ተፈጥሮ እንደሌለው መተማመን ላይ መድረስ አለብን ። አዲስም ሆነ አሮጌ የሚሆነው በሰዎች ተጽዕኖ ነው። ቀን ሳንጠብቅ፣ ጊዜ ሳናሰላ፣ አዲስ አመት ሳንል የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር አሁን ላይ መፍጠር እንችላለን። ሰላም ከሆነ የምንሻው፣ አንድነት ከሆነ ፍላጎቶቻችን ሰላምና አንድነት በሚያመጡ ሀሳቦች ላይ በማተኮር የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን።

ባልተለወጠ እምነት የተለወጠች ሀገር አትኖርም። ለውጥ ሁልጊዜም መነሻው አእምሮ ነው። በአእምሯችን ስንለወጥ ብቻ ነው ባለውም በሚመጣውም ዘመን ላይ ጀግና የምንሆነው። ከጊዜ ባርነት መውጣት ይኖርብናል። ለምንም ነገር ነገን መጠበቃችን፣ ለምንም ነገር አዲስ አመትን መሻታችን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው።

ሰላም ሊሰጡን የሚችሉ፣ ህልምና ራዕዮቻችንን ልናሳካባቸው የሚችሉ ብዙ ቀናት፣ ብዙ ጊዜዎች አብረውን አሉ። ራሳችንን ማንቃት ከቻልን ወደትላንት ሳንሄድ፣ ወደነገም ሳናዘግም መለወጥ እንችላለን። ችግሩ ከአዲስ አመት አስተሳሰብ አልወጣንም። ችግሩ ከዛሬ ይልቅ ነገን ተስፋ የምናደርግ መሆናችን ነው። ከቻልን ጊዜ የእኛ ባሪያ እንዲሆን እንቆጣጠረው። ከቻልን እያንዳንዱን ቀናችንን የምንም ነገር አዲስ አመታችን አድርገን እንቀበለው።

በጊዜ ባርነት ውስጥ ልዕልና የለም። በመጠበቅ ውስጥ ንግስናና ክብር ምንም ናቸው። ሰው ከትጋት ሲጎድል፣ ከጥረት ሲላላ ለምንም ነገር ጊዜን መጠበቅ ይጀምራል። ጊዜን የመጠበቃችን ምክንያት ስንፍናና አጉል የኑሮ ዘየቤ መልመዳችን ነው። በእውቀትና በእቅድ መኖር ብንጀምር እያንዳንዷ ቀን አዲስ አመታችን ትሆን ነበር ወይም ደግሞ ከአዲስ አመት በበለጠ ምን ያክል ለለውጥና ለስኬት አውፈላጊ እንደሆነች እንረዳ ነበር።

በትጋት ስንሞላ ለምንም ነገር ጊዜ እኛን መጠበቅ ይጀምራል። በትጋት ስንሞላ ምንም ነገር ከአሁን እንጀምራለን። ጊዜን መጠበቅና በጊዜ መጠበቅ ሁለት የተለያዩ እውነቶች ናቸው። ልክ ለምንም ነገር አዲስ አመትን እንደሚጠብቁት እና ለምንም ነገር ዛሬ የተሻለ ቀን ነው ብለው እንደሚያምኑት ሁለት ጉራማይሌ ነፍሶች አይነት።

ትጉ ነፍሶች የሚፈልጉትን ዘመን ዛሬ ላይ ይፈጥሩታል። ታካች ነፍሶች ደግሞ በመንቀፍ፣ በመሰልቸት፣ በስንፍና፣ በአይሆንልኝም፣ በማመንታት፣ በመወላወል፣ ቆይ ነገ በሚል እሳቤ በመጠበቅ ውስጥ ይቆማሉ። ብዙ ዛሬዎችን፣ ብዙ አሁኖችን፣ ብዙ ነገዎችን ዘለን አዲስ አመትን መጠበቃችን ስንፍናና ስልቹነት ምን ያክል ስር እንደሰደደብን አመላካች ነው።

ብልህ ሰው በብሩህ ሀሳቡ በኩል ዛሬን አዲስ አመት ማድረግ ይችላል። ጠንካራ ሰው ወደ ነገ ሳይሄድ፣ ወደ አምና ሳይሳብ አሁንን ለለውጥና ለስኬት መጠቀም ይቻለዋል።ለተጋ ልብ፣ ለበረታ አእምሮ ሁሌም ስኬት፣ ሁሌም አዲስ አመት አለ። አዲስ አመት ለእኛ ብሎ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም። መጥቶ እንዲሄድ የተፈጥሮ ግዳጁን እየተወጣ ነው።

እኛ ነን ከተፈጥሮ የራቅንው። እኛ ነን ማስተዋል የጎደለን..በጊዜ ሀቅ ውስጥ ቆመን እንኳን መማር አልቻልንም። ለመማር ዝግጁ ብንሆን ጊዜ የሚያስተምረን ብዙ ነበረው። አምናን በጉጉት ጠብቀንው የምንፈልገውን ሰላምና አንድነት ካልሰጠን፣ 2015 ለነበሩብን ችግሮች መፍትሄ አድርገንው ቃሉን ከበላ ችግሩ ከጊዜው ሳይሆን ከእኛ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። አዲሱን 2016 በአምና ልብ ሳይሆን በታደሰና በተቀየረ ልብ ልንቀበለው ይገባል። ያኔ ያለጥርጥር የምንፈልገውን እናገኛለን..እንደምኞታችንም ዘመኑ አዲስ መሆን ይጀምራል።

የሚሰማ ጆሮ የሚያስተውል ልብ ቢኖረን ኖሮ የጊዜን ሹክሹክታ እናደምጠው ነበር። ጊዜ ህላዊ ኖሮት መናገር ቢችል ኖሮ ‹..እባካችሁ አትጠብቁኝ እኔ ለሰው ልጅ የሚሆን ምንም የለኝም፣ ለበረቱ እየመጣሁ የምሄድ፣ ለጠንካሮች ሚዛኔን የደፋሁ ነኝ› የሚለን ይመስለኛል። በዚህ አያበቃም ፦

‹ከኔ ይልቅ ዛሬና ነገ የላቀ ዋጋ አላቸው። አስራ ሁለት ወራትን አልፋችሁ፣ ሀምሳ ሁለት ሳምንታትን ትታችሁ፣ ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናትን ሽራችሁ የምትጠብቁኝ ምናችሁ ሞኝ ነው? ሲል የሚያላግጥብን ይመስለኛል። መች በዚህ ያበቃና ‹ልቦቻችሁን ሳታድሱ፣ አመለካከታችሁን ሳትቀይሩ ጥሩ ነው መጥፎ ነው እያላችሁ አትሙኝ። እኔ ጥሩና መጥፎ የመሆን ስልጣን የለኝም። መጥቼ እንድሄድ የታዘዝኩ የተፈጥሮ መንገደኛ ነኝ እናም አትጠብቁኝ በአሁናችሁ ላይ በርትታችሁና ተልቃችሁ ቁሙ› ይለን ነበር።

ምኞታችን መልካም ጊዜ ከሆነ እጆቻችንን በስራ፣ ልቦቻችሁን በትጋት እናጥመድ። ምኞታችን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት ከሆነ ደግሞ ለነዚህ የሚሆን የተግባቦት ሰውነት እንፍጠር ። ካልሰራንበት፣ ካልበረታንበት አዲሱ አመትም እንደ አምናና ካቻምና ርባና ቢስ ሆኖ ነው የሚያልፈው።

አዲስ አመት የዛሬ አብራክ ነው። ብዙ ዛሬዎች ተቆጥረው ነው አዲስ አመት የሰጡን። ለምንድነው ዛሬአችንን አዲስ አመት አድርገን የማንቀበለው? ለምንድነው አዲስ አመት ሲመጣ የምናገኘውን ሀይልና ብርታት በቆምንባት ዛሬ ላይ የማንፈጥረው?

አዲስ አመት የቀናት ጥርቅም ነው። አዲስ አመት የሳምንታት የወራት ሂደት ነው። ለመለወጥ ካልተጋን የሚሰጠን አንዳች ነገር የለውም። እኛ እስካልተለወጥን ድረስ የአዲስ አመት መምጣት ምንም ነው..ቤስቲ ቤስታ የለውም።

ጊዜ በተለይም አዲስ ዘመን በእያንዳንዳችን ህይወት ላይ ዋጋ የሚኖረው የአሁንን ወይም ደግሞ የዛሬን ዋጋ ስናውቅ ብቻ ነው። አምና አዲስ ያልንው ዘንድሮ አሮጌ ብለን ሸኝተንዋል። ብዙም አላተረፍንበትም። ስለዚህ ከዘመን ቁራኛነት ወጥተን ዛሬን አዲስ አመት እናድርግ። በተለወጠ ልብ በተለወጠ ሀሳብ የተለወጠ ሀገርና ህዝብ እንፍጠር።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You