የቤተሰብ ጫና ከሙዚቃ ያራቃቸው ድምጸ መረዋ

ሕይወት ፈርጇ ብዙ ነው።አንዳንዶች ከጅምሩ በአንድ የሙያ ዘርፍ ተክነው በዛው ታውቀው ወደሌላ ሳያማትሩ ሰጥመው ይቀራሉ።አንዳንዶች ሕይወትን ለማሸነፍ በተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው የሙያ መስካቸውን ለመቀያየር ይገደዳሉ።በዛሬው የዝነኞች ገፅ አምዳችን ልንመለከታቸው የወደድነው የዝናው ዓለም ሰው ምንም እንኳን ከሁሉ የላቀውን ስምና ዝና በድምጻዊነቱ ቢቀዳጁም ጋዜጠኝነት፣ የሽያጭ ባለሙያነት እንዲሁም ሹፍርና ከተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

‹‹ከጣትም ጣት ይበልጣል›› እንዲሉ ከሳቸው የሙዚቃ ሥራዎች የኔ ሃሳብ የተሰኘው ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ደግሞ የ 62 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ቢሆንም ዛሬም እንደጥንቱ ከልጅ እስከአዋቂው እንዲታወሱና እንዲወደዱ ያደረጋቸው አንኳር ሥራቸው ነው።ድምጻዊ እንዲሁም ጋዜጠኛ ግርማ ነጋሽ 80 ዓመትን ቢሻገሩም ድምጻቸው አሁንም አልተለያቸውም።በሙያም በእድሜም አንጋፋ ናቸውና ከስማቸው ፊት ጋሼን ማስቀደም መርጠናል።

የተወለዱት አዲስ አበባ ፊት በር ነው።የአሁኑ ሸራተን ሆቴል ያረፈበት አካባቢ የሳቸው የልጅነትና የወጣትነት እድሜ የተቀለሰበት ሰፈር ነው።ታዲያ ሰፈሩ በሕብረት የታወቀ ነውና ከእኩዮቻቸው ጋር ሰብሰብ ብለው ማውጋትና ዘፈን መሞከር መለያቸው ነበር።በተለይ በበዓል ወቅት ዋነኛ የሰፈሩ አድማቂዎች ናቸው።የጥምቀት ሰሞን ከእኩዮቻቸው ጋር ጃንሜዳ ከትመው ታዳሚ ሲያዝናኑ ይሰነብታሉ። ይሄ ስብስብ ማርኳቸው ከተቀላቀሉ ሰዎች መካከል እውቁ ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ ይገኝበታል፡፡

ያኔ እሱ በሬዲዮ የሚሰማ ስሙ የታወቀና የተወደደ ድምጻዊ ቢሆንም በመልክ አያውቁትም።ወደእነሱ ሰፈር አመጣጡ አያቱ እዛ አካባቢ መኖር በመጀመራቸው ስለሆነ ስለማንነቱም ጠለቅ ያለ እውቀት አልነበራቸውም።እሱን የሚያውቁት በዘፋኝነቱ ሳይሆን ሰፈራቸው በገባ ዘናጭ ሰውነቱ ነበር።ስለዚህም እሱ ባለበት የሰፈር ልጆች በሙሉ ያለመሳቀቅ ያዜማሉ።ያኔ ቀረብ ብሎ አስተያየት ሲሰጣቸው ከሰፈር ልጅነት በዘለለም ማንነቱ ስለተገለጸላቸው የእሱን አስተያየት ከቁምነገር ይወስዱት ጀመር፡፡

ፊት በር በሰፈር ጓደኝነት የተመሠረተ ወዳጅነት ዳብሮ የያኔ ተማሪና ወጣቱ ጋሽ ግርማ ጥላሁንን ፍለጋ ጃንሜዳ የክብር ዘበኛ የኪነት ቡድን ጋር ሲሄዱ ከትዝታው ንጉሥ መሀሙድ አሕመድን፣ ከድምጻዊ እሳቱ ተሰማ፣ ከድምጻዊ ተፈራ ካሳና ባጠቃላይ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አባላትን መተዋወቃቸውን ያወሳሉ።ድምጻዊ ወዳጃቸው ጥላሁንን ብለው ሲሄዱ ካገኙት ድምጻዊ መሀሙድ አሕመድ ጋር የተመሠረተው ወዳጅነት ሰምሮ ብዙ ክፉ ደጎችን አብረው አሳልፈዋል።ከጥላሁን ጋር የተጀመረው ወዳጅነትም በ1964 ዓ.ም ትዳር ሲመሰርቱ አንደኛ ሚዜያቸው በመሆን ታጅቧል።በሰርጋቸው ምኒልክ ወስናቸው ከሌሎች ሁለት የሰፈር አብሮ አደጎቻቸው ጋር ሚዜዎቻቸው ነበሩ፡፡

ሙዚቃና ጋሽ ግርማ ቁርኝታቸው ለመንፈስ ምግብነት ነበር።ያለምንም ትርፍ ፍላጎት ይዘፍናሉ በምትኩ ከሷ ምንም አይጠብቁም።የሰፈር ድግሱን እነሱ አሉለት፤ ደግሞም የመስቀል ደመራም ሆነ ጥምቀት ሲደርስ ከዘፈኑም ከመዝሙሩም እያጣቀሱ ያስነኩታል። ሰፈራቸው ለጃንሜዳ ቅርብ በመሆኑ በየዓመቱ ለጥምቀት የጃንሜዳ ድምቀቶች ነበሩ።ሆኖም ለሙዚቃ መስመራቸው ፈር መያዝ ከጥላሁን ገሰሰ ጋር መወዳጀታቸውን ዋና ምክንያት ያደርጉታል።እሱ ያኔ የሰፈር ወዳጃቸው ሲሆን በቃኘው ሬዲዮ ጣቢያ ዘፈኖቹን የሚሰሙ ብሎም የሚያደንቁት ድምጻዊ ቢሆንም በአካል ስለማያውቁት በነጻነት ወዳጅነት መስርተዋል።ያለመሳቀቅ ከሰፈር ልጆች ጋር አብረው ያዜማሉ፤ በሂደት ማንነቱን ሲያውቁ ፈር የሚያሲዝ ምክር ለግሷቸዋል፤ ከዛም አልፎ በርካታ የሙዚቃ ሰዎችን እንዲያውቁ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

የጥላሁን ምክር ለሙዚቃ ቢያቀርባቸውም የሰፈር አብሮአደጎቻቸው የፖሊስ ኦርኬስትራን መቀላቀል ጋሽ ግርማንም ሥራቸው ሙዚቃ እንዲሆን አነሳስቷቸዋል።ነገሩ እንዲህ ነው፤ ከዕለታት አንድ ቀን አባይ በለጠ እና አረጋይ ተስፋዬ የተሰኙ የሰፈር ልጆች የፖሊስ ኦርኬስትራን ተቀላቅለዋል የሚል ወሬ በሰፈራቸው ፊትበር ናኘ።እነሱ ገብተው እኔ እንዴት እቀራለሁ ሲሉ የተቆጩት ጋሽ ግርማ ኦርኬስትራው ወደሚገኝበት ኮልፌ የሚወስዳቸውን መኪና መፈለግ ጀመሩ።በዚህ ፍለጋ ላይ እያሉ አሸዋ የጫነ የጓጋደኛቸው አባት ይመጣል።ቀረብ ብለው “እባኮት ወደኮልፌ ከሆኑ ይሸኙኝ” ይላሉ።“ና ውጣ” የሚል ፈቃድ እንደተቸራቸው አሸዋው ላይ ወጥተው ጉዞ ወደ ኮልፌ።

በቦታው ያረጋገጡት እውነትም ጓደኞቻቸው ኦርኬስትራውን ተቀላቅለዋል።ጋሽ ግርማም ሰፈር ውስጥ አብሮአቸው የሚያደምቅ ድምጸ መረዋ ነበርና ለአለቃቸው ሻለቃ ደመቀ ስለብቃቱ ይመሰክራሉ።ሻለቃውም ቆፍጠን ባለ የወታደር ትእዛዝ “አንተ ና እስቲ ዘፈን ታውቃለህ አሉ እስቲ ዝፈን” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ቢያሰሙም ከሰፈሩ በአሸዋ መኪና ተጭነው እንዳልሄዱ ተግደረደሩ።ከአፍታ ማፈር በኋላ ሰፈር ውስጥ ከሚዘፍኗቸው ዘፈኖች አንዱን ቢዘፍኑ ወዲያው ተቀጠሩ።

ከሰፈር ጓደኞቻቸው እኩል የ50 ብር ደሞዝተኛ ሆኑ።መጀመሪያ ከዛ ሃምሳ ብር ደሞዝ ላይ እየተቆረጠ እዛው ለፖሊስ አባላት የሚዘጋጅ ምግብ እየበሉ በልምምድ ይውላሉ።በሂደት ለሙዚቀኛ ወሳኙ ነገር ምግብ ነው ተብሎ በመታመኑ ከክፍያ ነጻ የጣመ የላመ ምግብ የሚበሉበት ሁኔታ ተመቻቸ።ማደሪያውም እዛው ተመቻችቶላቸው ሰፊ ጊዜ ወስደው መለማመድ ቀጠሉ።በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአዲስ ዓመት መድረክ ላይ የሚቀርብ አፍሪካ የዓለም ዘውድ የሚሰኝ በተስፋዬ አበበ የተደረሰ ግጥምና ዜማ ተሰጥቷቸው ጥናቱን ተያያዙት፡፡

የፖሊስ ቤት ሁሉ ነገር ተመችቷቸዋል።ምግቡ ማረፊያ መገኘቱ ደሞዝተኛ መሆናቸው እንዲሁም የሚወዱትን ሙዚቃ የመሥራት እድሉ አስደስቷቸዋል።ግን እሳቸው ጋር ባይደርስም ያጠፉ የፖሊስ አባሎች ሲቀጡ በጭቃ ላይ ተንከባለሉ ተብለው ሲንከባለሉ እንዲሁም ጭቃ ሲያቦኩ ሲያዩ ሆዳቸው ባር ባር እያለው ይሄ ቅጣት እሳቸው ጋር እንዳይደርስ በጸሎት ፈጣሪያቸውን ይማፀኑታል።

ከዕለታት አንድ ቀን የልምምድ ቀን ቢሆንም ከሳቸው ከፍ ያለ ሰው የእረፍት ቀን ነው ስላላቸው በማረፊያቸው ከጓደኞቻቸው ጋር እያወጉ ተኝቶ ማርፈድን ምርጫ አድርገዋል።እሳቸው ደግሞ ከሃምሳ ብር ደሞዛቸው ቀንሰው በገዟት ቄንጠኛ ነጭ ሱሪ አልጋቸው ላይ ጋደም ብለው ያወጋሉ።ሆኖም ትልቅ ዱላ ይዞ የፖሊስ ዩኒፎርሙን ለብሶ በቁጣ ማረፊያቸው የደረሰው መኮንን ጓደኛቸውን በያዘው በትር መቶ ነጭ እንደለበሱ በሥራ ቀን ተኝታችሁ አረፈዳችሁ ብሎ የፈሩት ጭቃ ላይ እንዲንከባለሉ ፈረደባቸው።

እንደፈሩት አልቀረም በሰው የፈሩትና አታጋጥመኝ ብለው ለፈጣሪያቸው የነገሩት ጭቃ ላይ ተንከባለሉ። በእሱም አልበቃም ቅጣቱ ግጫ ሲነቅሉ አመሹ።ያኔውኑ ሙዚቃ እንዲህ ካመጣ ብለው ልባቸው ዋለለ።ግን የተሰጣቸውን ሙዚቃ

የአፍሪካ የዓለም ዘውድ መሆንሽን አውቃለሁ

እኔን መስክር ቢሉኝ ከልቤ እምላለሁ

መለማመዱ ላይ በረቱ።ሙዚቃውን ለአዲስ ዓመት ብሔራዊ ትያትር በነበረው ዝግጅት ላይ በተገቢው መልኩ አቀረቡ።በቀጣይ በክፍለ ሀገር የመዞር ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ቢሆንም ከካምፕ እግሬ አውጭኝ ሲሉ ወደ ሰፈራቸው ገሰገሱ።የነጭ ሱሪያቸው መበላሸት ይበልጥ ልባቸውን አጨክኖት ሳይሆን አይቀርም ከካምፑ እንደወጡ ሳይመለሱ ቀሩ፡፡

ከቆይታ በኋላ የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር ቤት የአሁኑ ብሔራዊ ትያትር ሙዚቀኞችን ለመቅጠር ማስታወቂያ ማውጣቱን ይሰማሉ።ውድድሩ ላይ የጥላሁን ገሰሰን ለወሬም አይመች ዜማን በግሩም ሁኔታ በማቀንቀናቸው ትያትር ቤቱን ሊቀላቀሉ ችለዋል።

ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ

እንቁጣጣሽ እያልን ሳናጌጥ በአበባ

በትያትር ቤቱ በነበራቸው አጭር ቆይታ ከሠሯቸው ግሩም ሥራዎች መካከል ይገኝበታል።ዘፈኑ ከግጥም፣ ከዜማው እና ከቅንብሩ የተሳካ መሆን እኩል መሀል ላይ የተካተተው ፉጨት የተለየ ውበት ሰጥቶታል።በወቅቱ ፉጨቱ ከመድረክ ተለቆ እንጂ እሳቸው የሚያፏጩ የማይመስላቸው በርካታ ታዳሚዎች እንደነበሩና ለማረጋገጥ መድረክ ላይ ፊት ለፊት የሚቀመጡ ታዳሚዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።በወቅቱ እንኳን የዘፈኑ አካል ሆኖ ቀርቶ እንዲሁም ማፏጨት ይወዱ ነበርና በግሩም ሁኔታ ያፏጩ ነበር።በግሩም ሁኔታ የማፏጨታቸውን ሚስጥር “የጉርምስና ትንፋሽ” ይሉታል።

ትያትር ቤቱ በ1954 ዓ.ም የእንቁጣጣሽ በዓልን አስመልክቶ ባደረገው የአዳዲስ ዜማዎች ውድድር ጋሽ ግርማ ያቀረቡት የኔ ሃሳብ አሸናፊ ነበር።በወቅቱ ከ70 በላይ አዳዲስ ዜማዎች ለውድድር ቢቀርቡም በአዘጋጆቹ ታምኖባቸው ለውድድሩ የቀረቡት 21 ነበሩ።በወቅቱ ከቀረቡት 21 አዳዲስ ዜማዎች መካከል በአሁኑ አንጋፋ በያኔው ወጣት ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ የተቀነቀነው ግጥሙ በደራሲ ጌታቸው ደባልቄ ዜማው በካሳ ወልዴ የተደረሰውና በነርሲስ ናልባንዲያን የሙዚቃ አቀናባሪነት በትያትር ቤቱ የኦርኬስትራ አባላት የታጀበው የኔ ሃሳብ ለአሸናፊነቱ የ300 መቶ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

ጋሽ ግርማ ከ300 ብር ውስጥ ድርሻዬ ብለው ያሰቡትን 50 ብር ወስደው ከተቀረው 250 ብር የራሱን ድርሻ እንዲወስድና ለሌሎች ባለድርሻዎች እንዲያከፋፍል ለዜማ ደራሲው ካሳ ወልዴ አስረክበው ጉዞ ወደ ፊት በር።መለስ ብለው ሲያስቡት ከሽልማት ድርሻቸው 50 ብር ላይ ያልተጋበዘ የሰፈር ጓደኛ አልነበረም፡፡

የኔ ሃሳብ ባንች ፍቅር ተመርዞ

ቢያስቸግረኝ እጅግ ልቤን አስተክዞ

ተረታሁኝ ባንቺ ፍቅር ተይዤ

አሀሀሀሀ ሀሀሀሀሀሀ

ቁጭ ብዬ ቀረሁልሽ ተክዤ

የተሰኘችው ድንቅ ዜማ የጋሽ ግርማ መታወቂያ የተለየች ምልክት ነች።በአጭር ጊዜ የትያትር ቤት ቆይታቸው ከየኔ ሃሳብ በተጨማሪ ምነው ተለየሽኝ፣ አልበቃኝም ገና ጨርሶ፣ የሸማኔ ፍቅር፣ አዝናለሁ ስላንቺ የተሰኙ ሙዚቃዎችን አቀንቅነዋል።በድምጹ ውበት በርካቶችን መማረክ ቢችልም ቤተሰቦቹ ግን የሱን ድምጻዊነት አምነው መቀበል አልቻሉም።በወቅቱ በአብዛኛው ማሕበረሰብ ዘንድ ዘፋኝነት አዝማሪ ተብሎ የተናቀ ሙያ ነበርና ቤተሰቦቹ በሱ ዘፋኝ መሆን አልተደሰቱም።በዚህ የተነሳም ጋሽ ግርማ በዘፈን ያገኘው ብር ከቤተሰብ ብር ጋር እንዳይቀላቀል ሁሉ ይባል ነበር።በተለይም የታላቅ ወንድማቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሦስተኛ አብዮታዊ ሠራዊት አዛዥ ጀነራል ሙላቱ ነጋሽ ዛቻ ቢበረታባቸው ጋሽ ግርማ በ1955 ዓ.ም ከሚወዷት ሙዚቃ ተሰናበቱ።

በመቀጠልም የኮካ ኮላ የለስላሳ መጠጦች ድርጅትን በሽያጭ ሠራተኝነት ማገልገል።በ1959 ዓ.ም በኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የትራንስፖርት ኃላፊ በመሆን ሥራ ጀመሩ።በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሬዲዮ አንድ ተቋም በመሆኑ የቢሮው ኃላፊዎች ጋዜጠኛ ሆነው መሥራት እንደሚችሉ በማመናቸው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የስፖርት ክፍል ባልደረባ በመሆን ጋዜጠኝነትን ሀ ብለው ጀመሩ።በዚህ ጉዟቸውም በጣቢያው ከሳቸው ቀድመው የስፖርት ክፍል ጋዜጠኞች የነበሩት ይንበርበሩ ምትኬ፣ ደምሴ ዳምጤና፣ ጎርፍነህ ይመር ሙያውን በማስለመድ እንደረዷቸው ያስታውሳሉ።ለዚህም በዘፈን የተገራው ድምጹ የአድማጮችን ትኩረት ሰቅዞ በመያዝ አስተዋጽኦው የጎላ ነበር፡፡

ከሙዚቃ ጋር ካለው ቅርበት የተነሳም በጣቢያው አርብ ምሽት ይቀርብ የነበረው የባህል ሙዚቃ አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን ሰርቷል።ድምጹ በተፈጥሮ የታደለ መረዋ ነበርና በሬዲዮ የጋዜጠኝነት ዘመኑ አድማጭን ሰቅዞ የሚይዝ ግሩም ጋዜጠኛ ነበር።ጡረታ እስኪወጣ ድረስ ከ30 ዓመት በላይ በማስታወቂያ ሚኒስቴር አገልግሏል፡፡

በ1985 ዓ.ም ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹን በካሰቴት አሳትሞ ለአድማጭ አቅርቧል።የእሱ ሥራዎች የታዳሚውን ቀልብ ብቻ ሳይሆን የድምጻውያንንም ልብ ያሸፍታሉ። ለዚህም ይመስላል በርካታ ሥራዎቹ በሌሎች ድምጻውያን በድጋሚ ተዚመዋል።62 ዓመት የሞላት የኔ ሃሳብ አብነት አጎናፍር፣ እንደሻው ተስፋዬና ሞገስ መብራቱ በተለያየ ጊዜ በድጋሚ ዘፍነውታል።

እንገናኛለን አልቆረጥኩም ተስፋ

ብደነዝዝ እንኳን ቆሜ ባንቀላፋ

በ1955 ዓ.ም የወጣውን እንገናኛለን የተሰኘ ተወዳጅ ሥራቸውን ወደ አምስት የሚጠጉ ድምጻውያን ተጫውተውታል።ከእነዚህ ውስጥ ሰላማዊት ነጋ፣ ብጽአት ስዩም፣ እያዩ በሌና ማርታ አሻጋሪ ይገኙበታል።በአንድ ወቅት ዘፈኑን በርካታ ሰው በድጋሚ መጫወቱን ተጠይቀው ሲመልሱ “እንገናኛለንን ያልሞከረው የለም፤ መለኩሴ ወይም ቄስ ካልሆነ በቀር ብዙ ሰው ሰርቶታል” ብለዋል።አልበቃኝም ገና ጨርሶ የተሰኘው ዘፈናቸውን ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ደግሞ ተጫውቶታል፡፡

ጡረታ ከወጡ በኋላ የጋሽ ግርማ የሙዚቃ ብቃት አብሮአቸው ስለቆየ በአድናቂዎቻቸው አማካኝነት የተለያዩ መድረኮች ላይ በሦስት ዓመት የሙዚቃ ቆታቸው የሰሯቸውን ሥራዎች እያቀረቡ ቆይተዋል።ከዚህ በተጨማሪም በራሳቸው መኪና ለተማሪዎች የሰርቪስ አገልግሎት በመስጠት ሕይወታቸውን ሲመሩ የቆዩ ቢሆንም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ይሄን ሥራቸውን አቋርጠዋል።እድሜያቸው ሰማንያን ቢሻገርም አሁንም የድሮ ሥራቸውን የሚያዳምጥ እሳቸውን መድረክ ላይ ሲያይ የሚደሰት በርካታ ታዳሚ አላቸው፡፡

የኢትዮጵያውያን በቁም የማመስገን ባህል አነስተኛ ነው በማለት በርካቶች ሲወቅሱ ቢታይም፤ ነሀሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም በአሜሪካ የሚኖሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በአሜሪካ ቨርጂንያ ጋሽ ግርማን ‹‹ስለአገልግሎትህ እናመሰግናለን›› ያሉበትን የምስጋና መረሀ ግብር አሰናድተዋል።በፕሮግራሙ ላይ የጋሽ ግርማ የልብ ወዳጅ ድምጻዊ መሀሙድ አሕመድን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች ተገኝተው ድምጸ መረዋውን አመስግነዋል።

 ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን መስከረም 13/2016

Recommended For You