
ከሰባት ዓመታት ድካም በኋላ፤ በ8ኛው ወር ላይ ስምንተኛውን አልበሟን አስደመጠች። ከጥበብ አድማስ ባሻገር፣ ከጥበብ ሰማይ በታች እልፍ ክዋክብትን አስከትላ ደጃዝማችነቷን አሳይታለች። ‹ደጅ ለጥበብ፣ አዝማች በሙዚቃ› ደርሰው ሰሞነኛውን ውብ አድርገውታል። ዛሬም ድረስ ከሙዚቃዎቿ ጋር አጣጥመው ያልጨረሷት ኩኩ ሰብስቤ፣ አሁን ደግሞ “ደጃዝማች” ብላ መጥታለች። ቴዲ አፍሮ የአልበሟን ስምንት ሙዚቃዎች ግጥምና ዜማ ተሸክሞ ስጦታውን ለእርሷም ለእኛም አድርጎታል። ሽታው የሚያውድ የአዲስ ሙዚቃ ጣዕም ከሰሞኑ ነፋስ ጋር አብሮ መንፈስ ጀምሯል። ከዚህ ነፋስ አየር ምገን ወደ ውስጥ የሳብንም ብንሆን ወደ ውጭ ተንፍሰን በእፎይታ የተጠባበቅን፣ ከሁላችንም ዘንድ የኩኩ ሰብስቤ ስምና ዝና አይጠፋም። ዛሬ ሳይሆን ያኔም ጀምረን ሙዚቃዎቿ ከትንፋሻችን ተዋህደዋልና ይህንኑ እያጣጣምን ከዝና ማህደሯ ጥቂት ገጾችን እንግለጥ።
1953ዓ.ም ኩኩ ሰብስቤ ወሊሶ ላይ ተወለደች። የተወለደችውም ከአውራጃው ገዢ ከደጃዝማች ሰብስቤ ሽብሩ እና ከወይዘሮ አሰገደች ወልዴ ነው። ወሊሶ ላይ ብትወለድም፣ ወሊሶ ላይ ግን ብዙም አልከረመችም። ትንሽ ልጅ ሆና፣ ልጅነቷን ይዛ አዲስ አበባ ገባች። በራስ መኮንን ድልድይ ስትሻገር፣ በሰባ ደረጃ ስትወጣና ስትወርድ ብዙ ተመላልሳበታለች። የምትማረውም እዚያው ሰፈር ውስጥ ነውና። በኋላ ላይ፤ ወደ አሜሪካን ሚሽን ት/ቤት አቅንታ፣ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜዋን በዚያው አሳለፈች። እዚህም ብትሆን እዚያ ግን፤ ውስጧ የሚላወስና የሚያላውሳት አንድ ነገር ሙዚቃ ነበር። ኩኩ ሰብስቤና የልጅነት ህይወት፣ ሙዚቃና የሙዚቃ ፍቅር ብቻ። ልክ እንደ አብዛኛዎቹ ድምጻውያን ልጅነት ብቻ ሳይሆን፤ ዝም ብሎ የማንጎራጎር አባዜ ተጸናውቷት እንደነበር በቅርብ የሚያውቋትም ይናገሩታል። ስትሄድ እየተከተለ፣ ስትቆም እንደ ጥላ አብሯት ይቆማል። ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ሳሎን መኝታ ቤት ሳይል አፏን እያላወሰ፣ በእንጉርጉሮ ያንበለብላታል። ሀገርኛ ፈረንጅኛ ብሎ ነገር አታውቅም፤ ሁሉንም ዓይነት ታንጎራጉረዋለች። ብቻ ከድምጽዋ ጋር ይጣጣም እንጂ፤ የሴት የወንድ፣ ሶጵራና አልቶ ብሎ ምርጫ አታውቅም። ከወፍራሙ ጋር አወፍራ፣ ከቀጭኑ አቅጥና፣ ከከፍታው ከፍ እያለች ከዝግታው ትወርዳለች፡፡
ከየትኛውም በላይ ግን ለእርሷ ሙሉቀን መለሰን የሚያህል የለም። እንደርሱ ሙዚቃዎች አብዝታ የምታንጎረጉራቸውም የሉም። ስትወዳቸውና ስታደንቀው የእውነት በሆነው ሙዚቃዊ ስሜት ነው። ምናልባት ልቧ ወደ ሙሉቀን መለሰ እንዲያደላ ያደረጋት ከአድናቆት ባሻገር በአባቷ ደጃዝማች ሰብስቤ በኩል በቅርበት ትመለከተው ስለነበረም ይሆናል። ለእርሱ የነበራት ቦታ በልቧ አድናቆት ብቻ ሳይገታም የኋላ ላይ ፍሬን አፍርቷል። በሌላ በኩል ጌታቸው ካሳ፣ ሽሽግ ቸኮል፣ እታገኘሁ ኃይሌ እና ብዙነሽ በቀለ ሌላኛዎቹ የልጅነት ሙዚቃ አፍ መፍቻዎቿ ናቸው።
1960ዎቹ መጨረሻ ታዳጊዋ ኩኩ ሰብስቤ ልቧ በሙዚቃ ፍቅር ጨርቁን የጣለበት ጊዜ ነበር። አሁንም አሁንም ማንጎራጎር። አሁንም መዝፈን። ሙዚቃ…ሙዚቃ…ብቻ ነው የሚታያት። ባሰባት እንጂ የጀማመራትስ ገና ከልጅነት ነበር። ከሙዚቃዎች ሁሉ ሙዚቃዎቹን፣ ከሙዚቀኛ ሁሉም ሙዚቀኛውን ሙሉቀን መለሰን የሚገዳደርባት ማንም የለም። ሴት ሆና ከሴት ድምጻውያን ሥራዎች የምታዘወትረው በወንዱ ሙዚቃ ነው። ዕለት ተዕለት በሙዚቃ ሀሴት እያደረገች የምትገራው ድምጽና ጉሮሮዋ ለእርሷም ሆነ ለሚሰማት ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። የልጅነት ምኞቷን የምታሳካበትን አጋጣሚ ‹ይመጣል› እያለች አንድ ቀን፣ አንድ አጋጣሚ ትጠብቃለች። ራሷን ከአድማስ ባሻገር እየተመለከተች፣ በጉጉት የምትጠብቃት ሌላኛዋን የተስፋ ማንነቷን ነበር።
አንድ ቀን ከመድረክ ላይ ቆማ ስታንጎራጉር፣ ሁልጊዜም ስትናፍቃት የነበረችው የተስፋ ማንነቷ ድንገት ተከሰተች። አብራት ከፊቷ ስትቆም ተመለከተቻት። ታዳጊዋ ኩኩ ሰብስቤ፣ ከቆመችበት የሂልተን ሆቴል መድረክ ሆና ያቺን ማንነቷን ስትገልጥ ታወቃት። አዳራሹን ከሞላው አብሯት ከሚማረው ተማሪ ፉጨትና ጭብጨባ ጋር፤ የዘመኑ የሙዚቃ ዱንኳን የነበሩት የአይቤክስና ዋልያ ባንድ አባላት አጅበዋት ጎኗ ቆመዋል። ያቺ ዕለት ለተማሪው ሁሉ ልዩ የመመረቂያ ቀን ናት። ለዚህች ወጣት ተስፈኛ ግን ከዚያም በላይ ነው። ምክንያቱም፤ ሁለቱ ዝነኛ ባንዶች ከተማሪዎቹ ጋር ተጣምረው ባዘጋጁት በዚህ ዝግጅት መድረክ ቆሞ መዝፈን በራሱ አንድ ትልቅ የስኬት ጅምር ነውና። ከተማሪዎቹ ወገን ሆና ምንም ዓይነት የመድረክ ልምድና ከእውቅ ባለሙያዎች ጋር የመሥራት ዕድል ገጥሟት አያውቅም ነበር። የዚያን ዕለት መጀመሪያዋ ግን ልዩ ነበር። እናም ህልም በሚመስለው የልጅነት ህልሟ ውስጥ ያቺን አዲስ መልኳን በዓይን በብረቷ ከፊትለፊቷ እንድታያት ያደረጋት፣ ከመዝፈኗ ጀርባ በተከተላት አዲስ ነገር ውስጥ ነበር። አንጎራጉራ ስትወርድ የራስ ሆቴል ድምጻዊት እንድትሆን ታጨች።
ወጣትዋ ባለተሰጥኦ፣ የጥበብ ተስፋዋን አንግታ ከመድረክ በወጣችበት ቅጽበት ከትክክለኛው ቦታና ጊዜ ጋር ተገጣጠመች። የውስጧን ኃይል ገልጣ ሙዚቃን አንጎራጎረች። ከዚያ ስርቅርቅታና ከሆዷ ከሚወጣው ድምጽ ጋር አብራ ዝነኛዋ ኩኩ ሰብስቤ ብቅ አለች። ለትምህርት ቤት ጓደኞቿ ሌላ ሆና ታየች። በአይቤክስና በዋልያ ባንዶች አድናቆትን ተቸረች። ሁሉንም ነገሮች እውነት ባደረገው በራስ ሆቴል ዓይን ውስጥ ገባች። በልቡ ውስጥ ተጻፈች። ከዚያ በኋላ በራስ ሆቴል ድምጻዊነት በ3 መቶ ብር አንድ ብላ ጀመረች። ውስጧ ያለው የሙዚቃ ኃይል ግን በዚያ ብቻ የሚቆም አነበረም። ብዙም ሳትቆይ ከመነሻዋ ምክንያት ከሆኗት ሁለት ባንዶች መካከል አንዱ ወደሆነው አይቤክስ ባንድም አቀናች። የሄደችው የትዝታው ንጉሥ ማህሙድ አህመድ ከሚሠራበት ባንድ ነበር። በሳምንት ለሁለት ቀናት በአጃቢነት መሥራቷንም ቀጠለች። ችሎታው በይበልጥ እየተቀጣጠለ መውጣት የጀመረበት ጊዜም ነበር። ቀጥሎም ሁለተኛው መነሻዋ ወደሆነው ዋልያ ባንድ ተቀላቀለች። ከባንዱ ጋር ወደ ሂልተን ሆቴል አምርታ፣ በሦስት መቶ ብር ደሞዟ የጀመረችው ድምጻዊነት እጥፍ አድጎ በ6 መቶ ብር ተቀጠረች።
ወጣቷ ድምጻዊት እየተከፈላት መድረኮች ላይ ለመታየት ከመብቃቷም፣ አብራቸው የምትሠራው በሀገራችን አሉ ከተባሉ አንጋፋ ድምጻውያንና የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር መሆኑ ትልቁን በር በቀላሉ ከፍታ እንድትገባ ጉልበት ሆኗታል። ከተለያዩ ባንዶች ጋር ከምታደርጋቸው የውስጥ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ከውጭ ታደርጋቸው የነበሩ ርምጃዎቿንም አልገታቻቸውም። ገና መድረክ ላይ ከመታየቷ በፊት የሙሉቀን መለሰን ልብ ለመርታት ትጣጣር ነበር። የምትሰጠው አድናቆት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የግጥምና ዜማ ሥራዎችንም ጭምር ነበር። ከአባቷ ዘንድ የምትገኛቸውን ሥራዎች ጭምር ታቀብለዋለች። ሙሉቀን መለሰ “ናኑ ናኑ ነይ” የሚለውን ካሴቱን ካወጣ በኋላ አንድ ነገር ተናገረ፤ “የግጥም ደራሲዬ ኩኩ ሰብስቤ ናት” የሚል ነበር። እኚያ ትንንሽ ጥረቶቿ ተጠረቃቅመው፣ በዚህ ሥራው ውስጥ ለመጠራትና ምሰሶ ለመሆን በቅተዋል።
ኩኩ ሰብስቤ አሁንም በዕድሜዋ ገና ሀያ እንኳን አልደፈነችም። የሙዚቃ ህይወቷ ግን ዕድሜዋን ጥሎ የገሰገሰ ይመስላል። ሌላ አዲስ ታሪክ፣ ሌላ መጀመሪያ ያጻፈችበትን ሮሃ ባንድን ተገናኘች። ከሮሃ ባንድ ውስጥ የጊዜውን ዝነኛ ድምጻዊ አገኘችው። አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ከዚያ ነበር። ኩኩ ሰብስቤም ብትሆን በእርሱ መኖር ከዓይኖቹ የተስፋ ብርሃን ሳይበራ አልቀረም፤ አጅባ ጎኑ በቆመች ቁጥር ሁሉ የሚታያት ትልቅ ነገር ነበር። እንግዳ ሆና እንደመጣችውም፣ እንግዳ ነገር ታስብና ታልም ነበር። አለማየሁም ህልሟን ፈቶ “እንግዳዬ ነሽ” አላት። እርሷም መልሳ “እንግዳዬ ነህ” አለችው። “እንግዳዬ ነሽ…እንግዳዬ ነህ…” ይህቺው አንዲት ነጠላ ዜማ ሀገር ምድሩን በእንግዳ አጥለቀለቀችው። ራሱ ሙዚቃውም እንግዳ ነገር የሆነ መሰለ። በአንዲት ነጠላ ዜማ ያውም እያጀቡ ተቀባብለው ዝነኛ መሆኑም በሙዚቃ መንደር ውስጥ እንግዳ ነበር። ይሄው እንግዳ ዜማ ለስለስ ብሎ ከካሴት ክር ውስጥ ተንቆረቆረ።
ከላይ ከተጠቀሱት ባንዶች በተጨማሪ ከኢትዮ ስታርና ኤክስፕረስ ባንዶች ጋርም ሠርታለች። መድረክ ላይ ከማንጎራጎር አልፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአለማየሁ እሸቴ ጋር በካሴት ከተደመጠችበት ሮሃ ባንድ ጋር በመሆን፣ ከነጠላ ዜማ ተነስታ ሦስት አልበሞቿን እስከመሥራት ደርሳለች። ጥቂት ከማይባሉ አንጋፋ ድምጻውያን ጋር በቅብብሎሽ የተደመጠችባቸው አብዛኛዎቹ ሥራዎችም እዚሁ ሮሃ ውስጥ የተቀነባበሩ ናቸው። ከዚህ ባንድ ጋር ሆና በ1974ዓ.ም “ፍቅርህ በረታብኝ” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሟን ስታወጣ፣ ገና በ20 ዓመቷ ነበር፡፡
እርሷም በሙዚቃ ፈረሷ ላይ ተቀምጣ፣ እያዜመች በኤርትራ ስነዓ ላይ ቆማ፣ በዝግታ ከሚገማሸረው የቀይ ባህር ሞገድ ጋር አብራ በትዝታ ፈሳለች። በጅቡቲና አቡዳቢ መድረኮች ላይ ቆማ ወንበር አዳራሹን ሳልሳ አስደንሳዋለች። ከዱባይ ፎቆች ጋር ሙዚቃዊ ሰላምታን ተለዋውጣለች። በየመንና በአሜሪካን፣ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ እየሄደች የሀገሯን ውብ ሙዚቃ አስደምጣቸዋለች። እኚህን ሁሉ ዓለም አቀፍ ጉዞዎቿ ያደረገችው ከተለያዩ ባንዶች ጋር እየዞረች ነበር። ከማህሙድ አህመድ፣ አሊ ቢራ፣ ከተክሌ ተስፋዝጊና መንገሻ ጌታሁን ጋር በተለያዩ ሀገራት መድረኮች ላይ አብራቸው ቆማለች።
ከኢትዮ ስታር ባንድ ጋር ተጉዛ በየመን ሸራተን ሆቴል ውስጥ የነበራት ትዝታ ግን ከሁሉም የሚለይ ይመስላል። በወቅቱ በአቀራረብና በድምጽ ውበቷ የተማረከው ታዳሚ ከመቀመጫው ብድግ እያለ የሽልማት መዓት ያዥጎደጉድላት ጀመረ። በወርቅ ሰዓትና በገንዘብ ጌጣጌጥ አንቆጠቆጣት። ያኔ ተስፋ የተጣለባት ወጣት ጀማሪ የነበረችበት ጊዜ ነበርና ሽልማቶቹ ከስጦታነት ያለፉ ብሩህ የተስፋ ስንቆች ሆነዋታል።
የኩኩ ድምጸ ቅላጼ የተቀረጸበትና የሚታወቅበት ዘውግ ያለው ነው። የሙዚቃ ሥራዎቿ አብዛኛው ክፍል ለስለስ ብለው ወደ ትዝታ እልፍኝ የሚያስገቡ ናቸው። ተወዳጅነትና ዝናን በልዩነት ያጎናጸፏት ዜማዎችም ከትዝታ ደጅ ተቀምጣ ያንጎራጎረቻቸው ናቸው። የእርሷ ሙዚቃዎች በግጥምና ዜማ የበሰሉና ጠንከር ያለ ይዘትና መልዕክት ያላቸውም እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ጭምር ይናገሩላታል። ሙዚቃ አፍቃሪ አድናቂዎቿ ደግሞ ጆሮና ስሜታቸውን ለሙዚቃዎቿ ሲሰጡ ያለስስት ነው። ቀስቃሽ በማይሰማ ተመስጦ ውስጥ ይነጉዳሉ፡፡
1980ዓ.ም ኩኩ ሰብስቤ በ20ዎቹ መጨረሻ የምትገኝ ወጣት ድምጻዊት ነበረች። ዝናዋ ከፍታው ላይ እየተደላደለ የነበረበትም ጭምር ነው። በዚሁ ጊዜ ግን ኩኩ በሥራ ወደ አሜሪካን አቀናች። ከዚህ ቀደም እንደሄደችባቸው ሀገራት ደርሶ የመመለስ አነበረም። የቆየችው ለ17 ዓመታት እንደሆነ ስናስበው፤ ስምና ዝናዋ ከዚሁ ቀርተው ነበር? ያስብለናል። ምክንያቱም የሄደችውና ሄዳም የቀረችው ገና ብቅ ከማለቷ ነው። እንኳንስ ወጣት ጀማሪዋን፣ የዘመሩለት ስንቱ አንጋፋ እንደወጣ ተረስቶ የለም እንዴ? እንደዛሬ ‹ዓለም አንዲት መንደር ናት› እያለ የሚፎክር ቴክኖሎጂ እንኳን በማይታወቅበት ጊዜም ነውና መገረም አይቀርም። በእርግጥ ኩኩ ከዚያ ሆና ሥራዎቿን ስታበረክትም ነበር። በአሜሪካ ግዛቶች እየተዘዋወረች፣ ከሀገሯ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር ሆና በበርካታ ኮንሰርቶችና በልዩ ልዩ የመድረክ ዝግጅቶች ላይ ሥራዎቿን ታቀርብ ነበር። ወዲህ ደግሞ አልበሞቿን ትልክ ነበር። “ጊዜ” የተሰኘውን አልበሟን ከአበጋዝ ክብረወርቅ፣ እንዲሁም “ኢትዮጵያ” የሚለውን ደግሞ ከቴውድሮስ መኮንን(ቴዲ ማክ) ጋር ሆና የሠራቻቸው እዚያው በአሜሪካ ሳለች ነበር።
ከብዙ ዓመታት በኋላ…ኩኩ ሰብስቤ ስምንት አልበምና በርካታ ነጠላ ዜማዎችን አፍርታ ለወግ ማእረግ አብቅታለች። ዓመታት ነጉደው፣ ብዙ ሄደው ተለዋውጠዋል። በግሌ አንድ ነገሯ ያስገርመኛል፤ በማውቃት ዕድሜ ዘመን ሁሉ ስሟ ከፍ ዝቅ የማያውቅ መሆኑ ነው። ዝናዋ ሁሌም አንድ ዓይነት ከፍታ ላይ ረግቶ የተቀመጠ ነው። ዛሬ የደረሰችበትን የዝና እርካብ የጨበጠች ሰሞን ሲወዷትና ሲያደንቋት የነበሩ አሁንም እንደዚያው ናቸው። የሙዚቃ አፍቃሪውም ሆነ የአድናቂዎቿ የልብ ግለት የማይበርድ ነው። ‹ምስጢሩ ምን ይሆን?› እላለሁ። ስለ ሁለተኛው ‹እጅ አልሰጥም…› ስላለችበት ማንነቷ ግን ብዙ ጊዜ በቀልድም ይሁን በቁም ነገር ሲያነሱት እንሰማለን። አንዳንዴም ከማህበራዊ ሚዲያው የምትቆረጠም የሀሜት ሽንብራ። በቀጥታም ይሁን ስር በስር ወሬው ከጆሮዋ ይደርሳልና ራሷም ስትቀልድበት ብዙ ጊዜ ሰምተናት ይሆናል። በቅርቡ እንኳን ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረገችው ቆይታ ይህንኑ አንስተው ሲጨዋወቱ ነበር፡፡
“በፌስቡክ አንቺ አርጅተሻል፤ ለምንድነው ዘፈን አቁመሽ ቤተ ክርስቲያን የማትሄጂው? ይላሉ። እንደዚህ የሚሉት እኮ ወጣቶች አይደሉም፤ እርግጠኛ ነኝ የዕድሜ እኩዮቼ ናቸው። እውነቱን ልንገርህ ወጣቱ ትውልድ በጭራሽ ይሄን አያስብም” በማለት ‹ስለምን አብረን አናረጅም› የሚል ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ስለሚመስሉ ጠያቂዎቿ ቀልዳ ወይንም አውርታ ነበር። እርሷም እንደ ጥበብ፣ የጥበብ ጸጋና ቅባት ፈሶባት ይሆናል ዕድሜን አስንቃ ዛሬም ኩልል ማለቷ፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2017ዓ.ም ለስምንተኛ ጊዜ ኩኩ በአልበሟ ተሞሽራለች። “ደጃዝማች” የተሰኘውን ሥራዋን ይዛ ‹ቤቶች!” ከማለቷ ‹ደጆች!› ተብላ ከጥበብ እልፍኝ፣ ከውብ የሙዚቃ አዳራሽ ውስጥ መጋረጃው ተገልጧል። የሙዚቃ ክዋክብት የተጣመሩበትን በሳል አልበሟ ሰሞነኛውን ማጣጣሚያ ሆኖ ቀጥሏል። ሰባት ዓመታት ሙሉ የተደከመበት ሥራ መሆኑንም ቀደም ሲል ገልጻው ነበር። እኚህን ሁሉ ዓመታት ሲበስል ሲገላበጥ፣ ሲገጣጠም ሲከረከም የቆየ አልበም እንዴት ያለው ጣፋጭ የማር ወለላ፣ ናና ከረሜላ ሊወጣው እንደሚችል እያሰቡ፣ በጉጉት የተጠባበቁ ብዙዎች ነበሩ፡፡
አልበሙ 13 የሙዚቃ ስብስቦችን የያዘ ነው። ከአሥራ ሦስቱ መካከል አንደኛው “ወለላዬ” ሲሆን፤ ከቀደሙት ሥራዎቿ መካከል ዳግም የተሠራ ነው። ከቀሪዎቹ 12 አዳዲስ ሥራዎች ውስጥ የስምንቱን ግጥምና ዜማ ቀምሞ ያበጀው ቴውድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) ነው። ድሮውንም ቢሆን ለእርሷ ያለው ክብርና ፍቅር የተለየ ነበር፤ እርሷም እንደዚያው። ይልማ ገብረአብ፣ መሰለ አስማማው እና ናትናኤል ግርማ በግጥም በዜማ የባተሉበት ሌላኛዎቹ ባለ አሻራዎች ናቸው። አቤል ጳውሎስ ዘጠኙን በማቀናበር፣ አሥራ አንዱን ደግሞ ሚክስ አድርጓል። ቀሪ ሁለቱን አሬንጅ በማድረጉ ማሩ ዓለማየሁ አለበት። የሙሉ አልበሙን የድምጽ ማስተር የሠራው ደግሞ ኪሩቤል ተስፋዬ ነው። በጊታር፣ በቤዝ ጊታር፣ በሳክስፎን፣ በድራሙ…በርከት ያሉ የሙዚቃ መሣሪያ ነበልባሎች ተጠበውበታል። የአልበሟን ስያሜ “ደጃዝማች” ማለቷ ምናልባትም ከአባቷ ደጃዝማች ሰብስቤ ጋር ተቆራኝቶ ይሆናል፡፡
“ሹም አዛዥ ነህ ዘዋሪ
የፍቅር ፊት አውራሪ
ሹም አዛዥ ጤና አዳይ
ግባ በል እንግዳዬ
እንግዳ ነው
ለእኔ እንግዳ ነው”
እያሉ ቴዲና ኩኩ ይቀባበሉታል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም