በሕጻናት ማቆያ ክፍል በተደበቀ አደገኛ ዕጽ ምክንያት የአንድ ዓመት ልጅ ሕይወት አለፈ

 አሜሪካዋ ኒው ዮርክ ግዛት በሕጻናት ማቆያ ክፍል ውስጥ ሕጻናት የሚተኙበት ምንጣፍ ስር ‘ፌንታሊን’ የተሰኘ አደገኛ ዕጽ በመደበቁ የአንድ ዓመት ልጅ ሕይወቱ አለፈ።

ፖሊስ ኒኮላስ ዶሚኒኪ የተባለው የአንድ ዓመት ልጅ በተኛበት የሕጻናት ማቆያ ክፍል በሽታ ብቻ የደረሰው ከመጠን በላይ ላይ የሆነ አደንዛዥ ዕጽ ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን ቢቢሲ ከባለሙያዎች አረጋግጦ ዘግቧል።

ሕይወቱ ካለፈው ሕጻን በተጨማሪ ሌሎች በሕጻናት ማቆያው የነበሩ ሦስት ልጆች ወደ ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።

ፖሊስ ዕድሜያቸው ከስምንት ወር እስከ ሁለት ዓመት የሚሆኑት ልጆች በሕጻናት ማቆያው ፌንታሊን የተባለውን እጅግ አደገኛ አደንዛዥ ዕጽ በአፍንጫቸው ስበዋል ብሎ ያምናል።

ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ በግድያና አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ወንጀል ክሶች በሁለት ግለሰቦች ላይ መስርቷል።

ፖሊስ በሕጻናት ማቆያ ስፍራ ባደረገው ብርበራ ሕጻናት ከሚተኙበት ምንጣፍ ስር የተደበቀ አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን ፌንታሊን አግኝቷል።

የሕጻናት ማቆያ ባለቤት ዲቪኖ ኒኖና የሕንጻው አከራይ ካርሊስቶ ብሪቶ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የማንሃተን ዐቃቤ ሕግ ዳሚየን ዊሊያምስ “ተከሳሾቹ የሕጻናት ማቆያን የአደንዛዥ ዕጽ ማከማቻ በማድረጋቸው አራት ልጆችን መርዘው አንዱን ገድለዋል” ብለዋል።

የሕጻናት ማቆያ ስፍራ ሕጻናት ደህንነታቸው የሚጠበቅበት ስፍራ እንጂ ለአደንዛዥ ዕጽ የሚጋለጡበት ቦታ መሆን የለበትም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ፖሊስ እንደሚለው ከማቆያ ቦታ የተገኘው አንድ ኪሎ ግራም ፌንታሊን 500 ሺህ ሰዎችን የመግደል አቅም አለው።

ይህ በክኒን መልክ ለሕመም ማስታገሻነት ተብሎ የሚዘጋጅ መድሃኒት 50 እጥፍ ከሄሮይን በላይ አደገኛ ሲሆን በአሜሪካ ከአደንዛዥ ዕጽ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እየጨመረ ላለው ሞት ምክንያት ተደርጎ ይቀርባል።

እ.አ.አ. በ2010 በአሜሪካ ከመጠን በላይ የሆነ አደንዛዥ ዕጽ ወስደው ከሞቱ 40 ሺህ ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ፌንታሊን ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ ነበር።

በ2021 ደግሞ በአደንዛዥ ዕጽ ምክንያት 100 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 66 በመቶ ፌንታሊን ከመጠን በላይ የወሰዱ ናቸው።

በኒውዮርኩ የሕጻናት ማቆያ ለታዳጊው ሞትና ለሦስት ልጆች መመረዝ ክስ የቀረበባቸው ሁለቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ቀሪ ዘመናቸውን በእስር ሊያሳልፉ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ቢቢሲ አስታውቋል።

 በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You