እኛ እኮ ለዘመን ክንፎቹ አይደለንም
ሰንኮፍ ነን ለገላው
በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው!
ይቺ የበዕውቀቱ ሥዩም ሁለት ስንኝ ግጥም ብዙ ነገር ትነግረናለች፡፡ በአጭሩ ግን ስንፍናችንን ነው የምትነግረን። ዘመን ሲቀየር እኛ አንቀየርም፡፡ እኛ ለዘመን ክንፎቹ ሳንሆን ሰንኮፍ ነን፡፡ ሰንኮፍ የእባብ ልብስ ነው። ‹‹እባብ ደግሞ ልብስ አለው እንዴ?›› ይባል ይሆናል። አዎ! አለው፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች እባብ የነዋሪዎች ፀር ነው፡፡ ታዲያ በክረምት ወራት ይጠፋል፡፡ መስከረም ወር ላይ ፀሐይ ሲወጣ ብቅ ማለት ይጀምራል፡፡ ታዲያ በዚህ በመስከረም ወር አካባቢ በእባብ ቅርጽ ልክ የሆነ (የድሮውን ረጅሙን የጃንጥላ ልብስ የመሰለ ማለት ነው) በየጥሻው ይገኛል፤ ይህ በተለምዶ የእባብ ልብስ (ሰንኮፍ) ይባላል፡፡ ገበሬዎች በክረምት ወራት ይህን ሰንኮፍ ለብሶ ነው የሚቆይ ብለው ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በክረምት የበሰበሰ ሰውነቱ፤ ፀሐይ ሲወጣ ይደርቅና ከላይ ቅርፊቱ በልብስ መልክ ሹልክ ብሎ ይወድቃል፡፡ ይህን ልብሱን የሆነ ቦታ ላይ ጥሎት ይሄዳል፡፡
በበዕውቀቱ ስዩም ግጥም እኛ ለዘመን እንዲህ ነን፡፡ አብረነው የምንበር ክንፎቹ ሳንሆን ጥሎን የሚሄድ ሰንኮፉ ነን፡፡ እባብ ሰንኮፉን ጥሎ እንደሚሄደው ሁሉ እኛም ለዘመን ከኋላው የምንቀር ሰንኮፍ ነን፡፡
እነሆ መስከረም አዲስ ዓመትን ይዞ መጣ፡፡ መስከረም ሰዎች ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ ራሱ ዕቅድ የምታወጣበት ይመስላል፡፡ በመስከረም ወር ምድር ትደምቃለች፤ ትታደሳለች፡፡ ሰዎችም አዳዲስ ዕቅዶችን ያወጣሉ፡፡ ይህ ተፈጥሮም ሰውም የሚታደሱበት የመስከረም ወር ስመ ገናና ወር ነው፡፡
ከወራት ሁሉ እንደ መስከረም ስሙ ተደጋግሞ የሚጠራ ወር ይኖር ይሆን ? የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ሌሎች ወራት የሚጠሩት በራሳቸው ወር ውስጥ ነው፤ የሚጠሩት ምናልባትም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ነው፡፡
መስከረምን የምንጠራው ግን በመስከረም ወር ብቻ አይደለም፤ ዓመቱን ሙሉ የምንጠራበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በእርግጥ የሰኔ ወር ትንሽ ሳይፎካከረው አይቀርም፡፡ ምናልባት ሁለቱን ስመ ጥር እንዲሆኑ ያደረጋቸው የክረምት ወር መግቢያና መውጫ ስለሆኑ ሳይሆን አቀይቀርም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለተማሪ እና ለአንዳንድ ተቋማት ሠራተኞች ሁለቱም ወሮች ልዩ ስሜት አላቸው፡፡ የሰኔ ወር ተማሪ የሚለያይበት፤ የመስከረም ወር ደግሞ ተማሪ የሚገናኝበት ነው፡፡
በተለይ ጎበዝ ተማሪ መስከረምን በጣም የሚወደው ሲሆን ሰነፍ ተማሪ ደግሞ ሰኔ ወርን ይወደዋል፤ ለሰነፍም ይሁን ለጎበዝ ተማሪ መስከረም በተማሪ አፍ ተደጋግሞ ይጠራል፡፡ ትምህርት የሚጀመርበትና ከጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበት ነው፡፡
ይሄ ነገር በተማሪ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ለመንግሥት ሠራተኛውም ሆነ ለግል ሠራተኛው የሰኔ እና የመስከረም ወር የተለየ ቦታ አላቸው፤ ለመንግሥትም እንደዚያው ነው፡፡ ለገበሬውም የተለየ ቦታ አላቸው፡፡ ስለዚህ ሰኔ እና መስከረም ስመ ጥር ናቸው ማለት ነው። ስመ ጥር ማለት ግን ዝነኛ ማለት ነው አይደል? (ዝና ለአርቲስት ብቻ ነው ያለው ማነው?)
መስከረም ግን ለምን ስመ ጥር ሆነ?
በበጋም በክረምትም ስሙን እንጠራዋለን፡፡ ለምሳሌ በአባባል እንኳን ብንሄድ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፣ ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ፣ መስከረም በአበባው ሰርግ በጭብጨባው፣ የመስከረም ዝናብ ከላም ቀንድ ይለያል…›› ከቃል ግጥሞችም ይሄን እንጥቀስ፤
ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፤
ወፍጮውም ሲያጋምር መስከረም ዘለቀ፡፡
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ
እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ።
አባባ እገሌ የሰጠኝ ሙክት
ከግንባሩ ላይ አለው ምልክት
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት።
የሚሉ ሥነ ቃሎች አሉ፡፡ በሰው ስም ከሄድንም ብዙ መስከረም የሚባሉ ሰዎች አሉ፡፡ ሴቶች ቢበዙም መስከረም የሚባሉ ወንዶችም አሉ፡፡
መስከረም ግን የጥበብ ምንጭም ነው ልበል? ለነገሩ ባይሆን ነበር የሚገርመው፤ የልቦለድ ጽሑፎች መጀመሪያ ከተራራ፣ ከሰማይና ከወንዝ ርቆ አይርቅም፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ መስከረም ላይ ያምራሉ፡፡ መስከረም በስሙ ራሱ ብዙ ግጥም አለ፤ የገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹ደስ ይላል መስከረም››ን ልብ ይሏል፡፡ ዘፈንማ ስንቱ ይቆጠራል? እንዲያውም የበዓል ሰሞንም ስለሆነ ከዘፈን ግጥሞች እንጠቃቅስ፡፡ መጀመሪያ የጥላሁን ገሠሠን፤
ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ
የኔ ቆንጆ ተጊጣ ተውባ
አምራ ደምቃ በአበቦች ታጅባ
ያቻትና መጣች ውብ አበባ።
ይህኛው ደግሞ የሀመልማል አባተ ነው፡፡
የክረምቱ ወር አልፎ ለበጋው ለቋል
ሜዳው፣ ሸንተረር ጋራው በአበቦች ደምቋል
ሸሞንሟናዬ ውብ ሽቅርቅሩ
ድረስ በዓውዳመት በአገር መንደሩ
በወራት መጀመሪያ በአዲስ ዓመቱ መግቢያ
በል ፈጥነህ ድረስልኝ በዘመድ መሰበሰቢያ….።
በነገራችን ላይ መስከረም እንዲህ ስሙን እንድንደጋግመው ያደረገን በምክንያት ነው፡፡ አባባሎች እንኳን ራሳቸው ምክንያት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› ይባላል፡፡ መስከረም የአዲስ ዓመት መግቢያ ነው፡፡ እናም በዓመቱ ውስጥ የሆነ አስገራሚ ነገር መኖሩ ስለማይቀር ነው እንዲህ የተባለው። ልብ ብላችሁ ከሆነ ከነሐሴ ወር ወር መጨረሻ ጨምሮ ጳጉሜን ውስጥ ‹‹የ…. ዓመት ክስተቶች›› እየተባለ ያለፈው ዓመት አበይት ክንውኖች ሽፋን ይሰጣቸዋል፡፡ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› መሆኑ ነው፡፡
‹‹ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ›› የተባለው ደግሞ ለሰነፍ ገበሬ ነው፡፡ በሰኔ ገበሬ ትጉ መሆን አለበት። ሞኝ ከሆነ ግን ዝም ብሎ ይቀመጣል፤ ክረምቱ ካለፈ በኋላ መስከረም ላይ ቢነቃ ዋጋ የለውም፤ መስከረም ሰብል አምሮ የሚታይበትና እረፍት የሚገኝበት እንጂ ለዘር የሚሯሯጡበት አይደለም፡፡
‹‹የመስከረም ዝናብ ከላም ቀንድ ይለያል›› የምትለዋ አባባል የዋዛ እንዳትመስላችሁ፡፡ ይሄ ደግሞ ለመስከረም ወር ዝናብ የተባለ ነው፡፡ የመስከረም ወር ዝናብ አንድ አካባቢ እየዘነበ ከሆነ ሌላ አካባቢ አይዘንብም፤ ለምሳሌ አራት ኪሎ እየዘነበ ፒያሳ ላይዘንብ ይችላል፤ ያው የላም ቀንድ የተጠጋጋ ነውና ለግነት የተጠቀሙት ነው፡፡
‹‹ያረሰማ ጎበዝ…›› የተባለውም በምክንያት ነው። ያላረሰ ገበሬ ብዙ ጊዜ ክረምት ላይ ይቸገራል፡፡ ምክንያቱም ቀለቡ ከበጋ ወቅት አያልፍም፤ ክረምት ደግሞ ሥራ የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡ ጎበዝ ገበሬ ግን በጋ ክረምት አይቸገርም፤ እናም ዓመቱን ሙሉ ከቤቱ ይጋገራል፣ ይቦካል፣ ይፈጫል፤ ለዚህ ነው ‹‹ወፍጮውም ሲያጋምር መስከረም ዘለቀ›› የሚባለው፡፡
መስከረም በእነዚህ ምክንያቶች ስሙ የሚጠራበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ መስከረም ይደጋገማል አልኩ እንጂ ሁሉም ይጠራሉ፡፡ ሁሉም የሚታወቁበት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ጥቅምት ብርዳማ ነው፤ ጥር የሰርግ ወቅት ነው (ስንደርስበት እናወራበታለን)፡፡
መስከረም ስመ ገናና የሆነው እነዚህን አስገራሚ ነገሮች ስለያዘ ነው፡፡ እንኳን ሰው ተፈጥሮ ራሱ የሚታደስበት ስለሆነ ነው፡፡ በመስከረም ብቻ የሚታዩ የወፍ ዝርያዎችም አሉ፤ ሳይንሳዊ ምክንያት አላቸው፡፡ በአጠቃላይ የተፈጥሮም ሆነ የሰው መንፈስ የሚታደስበት ነው፡፡ ለዛሬው በእነዚህ የመስከረም ዘፈን ስንኞች እንሰናበት፡፡
እሰይ አበባው እሸቱ ደርሷል
ሰፈር መንደሩ አረንጓዴ ለብሷል
ገደል ሸለቆው ታጥሮ በአበባ
አደይ አበባ እንበል መስከረም ጠባ
የሰላም የፍቅር የፍስሃ አዝመራ
ሸጋ ሸጋ ታብቅል እሰይ ምድር ታፍራ
የመከራ ዘመን ያዘን ስቃይ ያብቃ
ሀብት በመስከረም ይሄው ትታይ ደምቃ
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ
ቤት ለእንቦሳ በሏት የልቤን እንግዳ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም