78ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በኒውዮርክ ይጀመራል

78ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በኒውዮርክ ይጀመራል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በ78ኛው ጉባኤ የ150 ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ለዓለም ሀገራት የጋራ መጻኢ ይመከርበታል ብለዋል።

የዓለም መሪዎች በቀጣዩ ዓመት በሚያተኩሩባቸው የጋራ ጉዳዮች እና አንገብጋቢ ጉዳዮች የሚመክሩበት ጉባኤ የተመድ ትልቁ ዓመታዊ ስብሰባ ነው። በ78ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ ዓለምን እየፈተነ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ እና የዩክሬን ጦርነት ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ይሆናሉ ተብሏል።

የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በጉባኤው የመጀመሪያውን ንግግር ሲያደርጉ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ሀገራቸው እየሰራች ያለውን ስራ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ሉላ ዳ ሲልቫን ተከትለው ንግግር እንደሚያደርጉ ነው ሬውተርስ የዘገበው።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም በጉባኤው ንግግር እንደሚያደርጉና ከአሜሪካው ፕሬዝዚዳንት ጆ ባይደን ጋር ከጉባኤው ጎን ለጎን እንደሚመክሩ ተዘግቧል።

በመንግስታቱ ድርጅት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ካላቸው አምስት ሀገራት ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ በ78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በመሪዎቻቸው አይወከሉም።

በዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሰርጌ ላቭሮቭ ወደ ኒውዮርክ እንደሚልኩ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። የብሪታንያ እና ፈረንሳይ መሪዎች ግን በሌላ ስራ መጠመዳቸውን በመግለጽ በጉባኤው እንደማይሳተፉ ነው የገለጹት።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግም ነገ በሚጀምረው ጉባኤ ይሳተፋሉ ተብሎ አይጠበቅም። በዚህ ጉባኤ ሀገራት በዩክሬን ላይ ጦርነት በከፈተችው ሩሲያ ላይ ጫናቸውን እንዲያበረክቱ ምክክር ይደረጋል።

በምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ የተደረጉ የመንግስት ግልበጣዎች፣ የሱዳን እና ኢትዮጵያ ግጭቶችም የጉባኤው አጀንዳዎች ይሆናሉ ተብሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You