ጉዳፍ ፀጋይ የዓለም ቻፒዮና ቁጭቷን በዓለም ክብረወሰን ተወጥታለች

በ10ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒን መሆናን ካረጋገጠች ገና ወር አልሞላትም። በ5ሺ ሜትርም አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለወራት ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጅ ወጥቶ የቆየውን የ5ሺ ሜትርም ቡዳፔስት ላይ ወርቅ ለመድገም ያደረገችው ጥረት በገጠማት ጉዳት አልተሳካም ነበር። በዚህም እንቁዋ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ቁጭት ውስጥ ነበረች። ‹‹ጉዳት ባይገጥመኝ ሁለት ወርቅ የማጥለቅ አቅሙ ነበረኝ›› በማለት ከቡዳቤስት መልስ አስተያየት የሰጠችው ኮከብ አትሌት እውነትም በ5ሺ ሜትር አንዳች እክል ካገጠማት አቅሙና ብቃቱ እንዳላት የተናገረችውን በተግባር ለማሳየት ሁለት ሳምንት ብቻ በቂዋ ሆኗል።

ከሶስት ወር በፊት ከኢትዮጵያውያን እጅ ወጥቶ የነበረውን የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኑን እሁድ ምሽት በውድድር ዓመቱ የመጨረሻ የዳይመንድሊግ ፍልሚያ ዩጂን ላይ ወደቤቱ መልሳለች። ከወር በፊት ከሌላኛዋ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ለተሰንበት ግደይ እጅ ወጥቶ በኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን እጅ የገባውን የርቀቱን ክብረወሰን ብዙም ሳይቆይ በአምስት ሰከንዶች ተሻሽሎ ጉዳፍ እጅ ገብቷል።

በውድር ዓመቱ ምርጥ አቋም እያሳየች የምትገኘው ጉዳፍ፤ በ5ሺ ሜትር የሴቶች ሩጫ ታሪክ ለ17 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያለተቀናቃኝ ክብረወሰኑን እየተቀባበሉ ሲያሻሽሉ የኖሩበትን ታሪክ አስቀጥላለች። በእነዚህ ዓመታት የርቀቱ ክብረወሰን በሌላ ሀገር አትሌት የተሰበረው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ቆይታውም ለሶስት ወራት ዕድሜ ነው። እአአ በ2006 አትሌት መሠረት ደፋር በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የቱርክ አትሌት ኤልቫን አቢይ ለገሰ ለሁለት ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማይክሮ ሰከንዶች ብቻ በማሻሻል ነበር ክብሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣችው። ጀግናዋ አትሌት በዓመቱ ደግሞ ኦስሎ ላይ በ8 ሰከንዶች የራሷን ሰዓት በማሻሻል አስደናቂ ታሪክን ስታስመዘግብ፤ በርቀቱ ታሪክ በተከታታይ ክብረወሰን የሰበረች ብቸኛዋ አትሌት በመሆን ነው።

በቀጣዩ ዓመት ደግሞ እዛው ኦስሎ ላይ ሌላኛዋ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በሀገሯ ልጅ የተያዘውን ፈጣን ሰዓት በድጋሚ በማሻሻል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በርቀቱ ያላቸውን የበላይነት ማጠናከር ችላለች። በ14፡11፡15 የተመዘገበው የጥሩነሽ ክብረወሰን ለ12 ዓመታት በአንድም አትሌት ሳደፈር ቆይቷል። ከዓመታት በኋላ የርቀቱን ቁጥር አንድ አትሌትነት የያዘችው ደግሞ ሌላኛዋ ድንቅ እና ብርቱ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ስትሆን፤ እአአ በ2020 ቫሌንሺያ ላይ 14:06.62 በሆነ ሰዓት በመሮጥ ሶስተኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት በመሆን ታሪክ ልታስመዘግብ ችላለች።

ይህ ሰዓት ከሶስት ወራት በፊት በኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን በአንድ ሰከንድ ተሻሽሎ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጅ ወጥቷል። ወጥቶ ግን አልቀረም፣ ከወራት የዘለለ ዕድሜን ሳያስቆጥር ኬንያዊቷም ክብሩን አጣጥማ ሳታበቃ በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ወደነበረበት ሊመለስ ችሏል። ከወራት አስቀድሞ ይህንን ክብር ለመቀዳጀት ጥረት ስታደርግ የቆየችው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለጥቂት ክብረወሰኑን መስበር ባትችልም ሁለተኛው የፈጣን ሰዓት ባለቤት ለመሆን ችላ ነበር። በአስደናቂ አቋም ላይ የምትገኘው ጉዳፍ በ3ሺ ሜትርም በተመሳሳይ ሙከራ አድርጋ ሳይሳካላት ነበር ወደ ቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ያመራችው።

ጉዳፍ የዓለም ቻምፒዮና ቁጭቷን በዓለም ክብረወሰን ተወጥታለች። ኦሪጎን የብቃቷን ልክ ማሳየት የቻለችው ኮከብ አትሌት የመጨረሻውን ዙር የሸፈነችው እጅግ አስደናቂና ተመልካችን ቁጭ ብድግ ባደረገ ብቃት ነው። የመጨረሻውን መስመር ስታቋርጥም 14:00.21 በሆነ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ ነው። ለጉዳፍ ፈተና ትሆናለች ተብላ ቅድመ ግምት ያገኘችው ባትሪስ ቺቤት በአንጻሩ 5 ሰከንዶችን ዘግይታ ውድድሩን በሁለተኛነት ማጠናቀቅ ችላለች። የዳይመንድሊጉን አጠቃላይ አሸናፊነት ክብር ከክብረወሰን ጋር የደረበችው ጉዳፍ ከውድድሩ በኋላም ጉዳፍ በሰጠችው አስተያየት ‹‹በዓለም ቻምፒዮናው ሁለት ሜዳሊያዎችን አለማግኘቴ አስቆጭቶኝ ነበር። ከዝግጅቴ አንጻር ጥሩ ብቃት ላይ እንዳለሁና አዲስ ነገር ማስመዝገብ እንደምችል አስብ ነበር፤ በኦሪጎን የነበረው ሁኔታ ምቹ ባይሆንም ማድረግ እንደምችል ግን እርግጠኛ ነበርኩ›› ማለቷን የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገፁ አስነብቧል።

ለሁለት ዓመታት የርቀቱ ክብረወሰን ባለቤት የነበረችውና በቡዳፔስት ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከእጇ የወጣውን ሰዓት ለማስመለስ በርሊን ላይ ከቀናት በፊት ሮጣ ነበር። ይሁንና 14:08.79 በሆነ ሰዓት ርቀቱን መሸፈኗ ያሰበችው ክብረወሰን ባይሳካም አራተኛውን ፈጣን ሰዓት ጨብጣ ነበር።

በሌላ በኩል በኦሪጎኑ የፍጻሜ ውድድር ከተሳተፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የኢትዮጵያን ሰዓት ማሻሻል ችሏል። እጅግ አስደናቂ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር በቡዳፔስት በ5ሺ ሜትር የወርቅና በ1ሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያዎችን ያጠለቀው ኖርዌያዊው አትሌት ጃኮብ ኢንብሪግሰን አሸናፊ በመሆን ሌላኛውን ታሪክ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በቴክኖሎጂ ፍጻሜው በተለየበት ድንቅ ትንቅንቅ ኢትዮጵያዊው አትሌት በ7:23.63 የርቀቱን የኢትዮጵያ ክብረወሰን የግሉ መሆኑን አረጋግጧል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You