በመዲናዋ ከ900 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታና ጥገና ይከናወናል

አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ በ2016 በጀት ዓመት 902 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች ለማከናወን እቅድ መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ባለሥልጣኑ በአጠቃላይ በ2016 በጀት ዓመት 902 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታ እና ጥገና እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃ መሥመሮች ጥገና እና ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን በዕቅድ ይዟል፡፡

በበጀት ዓመቱ 31 ነጥብ 62 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 22 ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንገድ፣ 49 ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ 48 ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገዶች መልሶ ግንባታ ለማከናወን ታቅዷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ 95 ኪሎ ሜትር የኮብል ንጣፍ መንገዶች ግንባታ እና አንድ ነጥብ 88 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ግንባታ የሚከናወን ሲሆን በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 248 ነጥብ 44 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል ባለሥልጣኑ በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት የተዳረጉ 102 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 35 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ 80 ኪሎ ሜትር የኮብል መንገዶች ጥገና ለማካሄድ ታቅዷል። የመንገድ ዳር የውሃ መፋሰሻ መስመሮች በመፈተሽ 349 ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ፅዳትና ጥገና እንዲሁም 13 ነጥብ አምሥት ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ጥገና ይከናወናል ነው ያሉት አቶ ኢያሱ፡፡

የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አኳያ 65 ነጥብ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የነባርና የአዳዲስ መንገዶች የትራፊክ ቀለም ቅብ ሥራ እና ስምንት ኪሎ ሜትር የእግረኛ መከላከያ አጥር ሥራ፤ በድምሩ 654 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራ በበጀት ዓመቱ ለማከናወንም ታቅዷል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በቁጥር 22 ድልድዮች እና 16 ሺህ የመንገድ ዳር መብራቶች ጥገና በዕቅዱ ከተካተቱ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You