ከክረምት ጥገኝነት መላቀቅ ያለበትየበጎፈቃድ አገልግሎት

 አንዱ ሲቸገር አንዱ ለሌላው መድረስ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ በመተሳሰብና በፍቅር አብሮ የመኖራችን ሚስጥር ነው። ከተረጂው ምንም አይነት ምላሽ ሳይጠብቁ ለችግሩ መድረስ አለሁልህ ማለት፤ በጭንቀት የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጥቶ ሲብሰለሰል የከረመን ሰው ለችግሩ ደርሶ ነብሱን ከጭንቅ መገላገልን የመሰለ ውስጣዊ ሰላም የሚሠጥ መልካም ሥራ በምድር ላይ አለ ለማለት አያስደፍርም።

ይህ የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህላችን ከፍ ሲልና በአደባባይ ወጥቶ ብዙሃንን ተደራሽ ማድረግ ሲችል ደግሞ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚል ስያሜ በርካቶችን የሚያሳትፍ እና ብዙ የማህበረሰብ ችግሮችን የሚፈታ ሆኖ በተለያዩ ቦታዎች ሲተገበር እንመለከታለን።

የበጎ ፍቃድ በጎነትን መሠረት ያደረገ ፤ ያለማንም አስገዳጅነት ከልብ በመነጨ ቅንነት እና በራስ መነሳሳት የሚሳተፉበት አገልግሎት ነው። ይህ አገልግሎት ምንም አይነት የአይነትም ሆነ የገንዘብ ክፍያ የማይገኝበት ለውስጣዊ እርካታ በነፃ ማህበረሰብን የማገልገል ተግባር ነው።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለያዩ የዓለም ሀገራት በስፋት ተግባራዊ ይደረጋል። በአገልግሎቱም የደም ልገሳን ጨምሮ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ግልጋሎቶች ይሰጡበታል። በሀገራችንም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።

ከዚህ ቀደም በሀገራችን በስፋት በሚተገበረው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የደም ልገሳና የትራፊክ አገልግሎቶች ቢሆንም፤ አርሶ አደሩን ማገዝ፣ ለአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት አገልግሎት መስጠትና ለተማሪዎች የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትም በዚሁ አገልግሎት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በብዛት የሚሳተፉት ወጣቶች ናቸው። የበጋውን ጊዜ በትምህርት የሚያሳልፈው አብዛኛው የወጣት ክፍል፤ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ወጣቶች፤ የትምህርት ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስ የክረምት ጊዜያቸውን ደግሞ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ያሳልፋሉ።

ይህ በክረምት የሚተገበር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መኖሩ ታዲያ በርካታ ወጣቶችን ከአልባሌ ቦታዎች አድኗል። ቤት በመቀመጥ የድብርት ስሜት ውስጥ እንዳይገቡ ከማገዙም በላይ ለተለያዩ ሱሶች የመጋለጥ አድላቸውን ይቀንሰዋል። ከዚህ ባሻገር በፅንሰ ሃሳብ (theory) የተማሩትን በተግባር ላይ የሚያውሉበትን ሰፊ እድልም ይሰጣቸዋል።

ከአምስት ዓመት ወዲህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከወትሮው በተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። በተለይም በበጎ ፍቃድ የሚሳተፈው ወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል እንደመሆኑ መጠን የወጣቶች ምክር ቤት መቋቋሙና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በስፋት መሠራቱ ትልቅና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።

አገልግሎቱ እንደሀገር በርካታ ጠቀሜታዎች እያስገኘ መምጣቱን ማየት ከጀመርን ዋል አደር ብለናል። ከነዚህም መካከል በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት የመጣውን ለውጥ ማንሳት ይቻላል። በተለያዩ ቦታዎች በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ በተካሄደ የችግኝ መትከል ተግባር አማካኝነት በአንድ ጀንበር ከ500 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን እስከመትከል የደረስንበት ሁኔታ የማይዘነጋ ነው።

የሰው ልጅ ችግሩ ወቅትን መርጦ ጊዜና ቦታ ለይቶ የሚመጣ አይደለም። የትኛውም የማህበረሰብ ክፍል በወቅት በተገደበ አገልግሎት ችግሩ ከስር መሠረቱ ተነቅሎ ይወገድለታል ማለት አይቻልም። በሁሉም ዘርፍ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ያስፈልጋል።

በእለት ተእለት ኑሮ ውስጥ የበርካታ በጎ ፍቃደኞችን የደግነት እና የድጋፍ እጆች እንዲሁም የቅንነት ጉልበት ለእገዛ የሚናፍቁ የማህበረሰብ ክፍሎች በርካቶች ናቸው። ታዲያ በሀገራችን የሚደረገው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ክረምትን መሠረት አድርጎ ተግባራዊ መሆኑ በቂ አይደለም።

ለምሳሌ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አማካኝነት ሲሰጡ ከነበሩ አገልግሎቶች መካከል የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ አንዱ ነው። በእርግጥ የክረምት ወቅት ላይ የአየሩ መቀየርና የዝናብ ወቅት መሆኑ የቤት እድሳት መደረጉ አስፈላጊ መሆኑ ባያጠራጥርም የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት የሚያስፈልገው በክረምት ወቅት ብቻ ነው ማለት ግን አይደለም።

በክረምቱ መርሀ ግብር እድሉም ማግኘት ያልቻሉ ነገር ግን በአቅም ማጣት ቤታቸውን ማደስ ያቃታቸው በርካቶች አሉ። በግብርናው ዘርፍም ቢሆን ከክረምቱ እርሻ ባሻገር በበጋው ወቅት ምርት ለማሰባሰብ ብዙ የሰው ሃይል የሚያስፈልግባቸው ሥራዎች ይገኛሉ። በመሆኑም የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በበጋውም ወቅት አጠናክሮ መቀጠል ቢቻልና ልክ እንደክረምቱ ሁሉ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራበት የተሻለ ለውጥ ማየት ይቻላል።

ማህበረሰቡም ቢሆን ችግሩ ከመፈታቱ ባሻገር ክረምት ከበጋ ሳይለይ አለውልህ የሚለው ወገን እንዳለው የሚረዳበት ትልቅ አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል። ከዚህም ባለፈ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የተጀመሩ በርካታ ሥራዎች በበጋው ጊዜ ትኩረት አጥተው እንዳይበላሹ ማድረግ ያስችላል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል ሆኖ ከዓመት ዓመት የሚከናወንበትን አስቻይ ሁኔታም መፍጠር ያስችላል።

ቲሻ ልዑል

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You