
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሁለት በዩክሬን የሚገኙ ታሪካዊ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና ገዳም አደጋ ላይ መውደቃቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ እና የባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) አስታወቀ።
ዩኔስኮ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት የተነሳ የመውደም አደጋ ተጋርጦባቸዋል ያላቸው ታሪካዊ ቅርሶች ጥንታዊ እንደሆኑ ዩኔስኮ ይፋ አድርጓል።
በኪየቭ ፔሰርስክ የምትገኘው እና በመካከለኛው ዘመን የተገነባው ላቭራ ገዳም እና በመዲናዋ የምትገኘው የቅድስት ሶፊያ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የመፍረስ አደጋ ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
በሊቪቭ ከተማ የሚገኝ ታሪካዊ ማዕከልም በዩኔስኮ አደጋ ከተጋረጠባቸው የዓለም ቅርሶች መዝገብ ተካትቷል።
እነዚህን ታሪካዊ ስፍራዎች ለመጠበቅ ሁኔታዎችን ማሟላት ፈተና እንደሆነበትም ነው ዩኔስኮ የገለጸው።
በሁለቱ ከተሞች ላይ እየደረሰ ባለው የቦምብ ጥቃት ታሪካዊ ቅርሶች በቀጥታ የመመታት ስጋት ተጋላጭ መሆናቸውንም ነው ዩኔስኮ በማጠቃለያው ያመላከተው።
ዩኔስኮ እነዚህን ታሪካዊ ቅርሶቹ በአደጋ ላይ መሆናቸውን በድረ-ገጹ ዝርዝር ውስጥ ለማካተት የመረጠበት ዋነኛ ምክንያትም የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ለቅርሶቹ ጥበቃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መሆኑንም አመላክቷል።
በተጨማሪም ለቅርሶቹ ጥበቃ እንዲሆን የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ በር ይከፍታል ሲል ዩኔስኮ ገልጿል።
ሩሲያ በነዚህ ቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የታጠቁ ኃይሎቿ «አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን» እየወሰዱ መሆኑን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አረጋግጣለች። ይህንን ማረጋገጫ ግን ዩክሬን አልተቀበለችውም።
ዩኔስኮ በቅርሶቹ አካባቢ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ የተለያዩ ወቀሳዎችን ሲያሰማ ቆይቷል።
ተቋሙ ከወራት በፊት ታሪካዊ ከሆነችው ሊቪቭ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሕንፃ ላይ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት አውግዟል።
ከተማዋ የተቆረቆረችው በመካከለኛው ዘመን ሲሆን ከ13ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ አስተዳደራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የንግድ ማዕከልነቷንም ጠብቃ ቆይታለች።
በኪነ ሕንፃዎቿ እና በቅርሶቿ የምትታወቀው ይህች ጥንታዊ ከተማ በአውሮፓውያኑ 1998 በዓለም ቅርስነት ተመዝግባለች።
የቅድስት ሶፍያ ካቴድራል በበኩሏ የተገነባችው በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በወቅቱ የቁስጥንጥንያ አካል ከነበረችው ሃጊያ ሶፍያ ጋር እንድትወዳደርም በማሰብ ነበር።
በዚያ ዘመን ከተገነቡት እና ካልወደሙት ሕንፃዎች ውስጥ አንዷ ናት። የኪዬቭ ፔቨርስክ ላቭራ ወይም የኪየቭ የዋሻዎች ገዳምም ከካቴድራሏ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ነው የተገነባው።
ዩክሬን በበኩሏ በሩሲያ ከተሞች ላይ በምትፈጽመው የድሮን ጥቃት ቅርሶችና ታሪካዊ ሀብቶች እንዳይወድሙ ኃላፊነት ልትወስድ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካ በበኩሏ ከሦስት ሳምንታት በፊት ዩክሬን ወደ ሰላም እንድትመጣ ግፊት ልታደርግ እንደምትችል ገልጻለች።
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት 570 ቀናት አልፎታል።
ይህ ጦርነት በፍጥነት እንዲቋጭ በሚል በሞስኮ ላይ ከ12 ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥለዋል።
ይሁንና ለዩክሬን የጦር መሣሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ ቀስ በቀስ ድጋፏን ልትቀንስ እንደምትችል ተጠቁሟል።
ብሉምበርግ እንደዘገበው ከሆነ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን ዓይነተ ብዙ ድጋፍ ቀስ በቀስ ልትቀንስ እንደምትችል አስታውቃለች።
በተለይም በአሜሪካ በቀጣይ አመት የሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዩክሬን ጉዳይ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ እንደሚችል ተገልጿል።
ለዩክሬን የሚሰጠው ርዳታ እንዲቆም የሚፈልጉ አሜሪካውያን ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለኬቭ የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲቀንሱ ሊያደርጋቸው ይችላልም ነው የተባለው።
አሜሪካ ባለፉት 18 ወራት ውስጥ ብቻ 43 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን በመስጠት ቀዳሚ ሀገር መሆኗን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት የታሰበውን ያህል ድል ማስመዝገብ አለመቻሏና አሁንም ምዕራባውያን ተጨማሪ የጦር መሣሪያ እንዲልኩላት እየወተወተች መሆኑ አሜሪካ ዩክሬንን ወደ ሰላም ስምምነት እንድትገባ ጫና እንድታደርግ ሊያስገድዳት ይችላል በሚል ተሰግቷል።
ከአንድ ወር በፊት ዩክሬን የተወሰኑ ግዛቶቿን ለሩሲያ በመስጠት ወደ ስምምነት እንድትመጣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የሥራ ኃላፊ ምክረሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ዩክሬን የኔቶ ኃላፊውን ሃሳብ ሉዓላዊነትን ያላከበረ በሚል ውድቅ ማድረጓ አይዘነጋም።
በ2024 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ዕጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ እንደማይሰጡ እና ጉዳዩን በድርድር እንዲፈታ ግፊት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ይሁንና በቀጠለው ጦርነት ከሰዎች ሕይወት ህልፈት ባለፈ ታሪካዊ ሕንፃዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም