ባሳለፍነውና እየተጠናቀቀ ባለው የክረምት ወር ወንዞች በውሃ ሞልተው፤ ሰማዩ በደመና ተጋርዶ፣ መልክዓ ምድሩ በጉም ተሸፍኖ ከርሟል። ይሄ በመብረቅና በነጎድጓድ የታጀበው ክረምት ታዲያ የጊዜ ዑደቱን ጠብቆ አላፊ ሊባል፤ ጊዜውን ለአበባ፣ ለፍሬና ለልምላሜ ሊያስረክብ እነሆ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ሁሌም በሀገራችን በክረምቱ ወራት መጠናቀቂያ፤ መስከረም ወር ከመግባቱ አስቀድሞ አልያም በወሩ የመጀመሪያዎቹ ቀናትና ሳምንታት በርካታ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው በዓላት ይከበራሉ። ከነዚህ ውስጥ በሕፃናት ጭፈራና ፈንጠዝያ የሚከበሩትን የቡሄ፣ የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንቁጣጣሽ አበባየሆሽና የመስቀል በዓል ጭፈራን (ሆያ ሆዬን) ማንሳት እንችላለን።
እነዚህ በዓላት በየአካባቢው የተለያየ ስም ይሰጣቸው እንጂ፤ ከብዶ የቆየውን የክረምቱን ወራት ማለፍ የሚያበስሩን ባህሎቻችን ናቸው። ለምሳሌ፣ በነሐሴ 13 የሚከበረው የቡሄ ወይም የደብረ ታቦር በዓል፤ በሀገራችን የክረምቱ ጭጋግ ተወግዶ የብርሃን ወገግታ መታየቱን ለማሳወቅ ዕለቱ ‘ቡሄ’ የሚለውን ስያሜ አግኝቷል። እናም ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ እንደ ማለት ነው። አባባሉስ ቢሆን ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት አይደል የሚባለው?
ከዚህ ባሻገር የክረምቱን መጠናቀቅ የሚያበስሩን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በስፋት የሚከበሩት የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት ናቸው። በዓላቱ በየአካባቢው በተለያየ ስያሜ ይከበሩ እንጂ፤ በሁነታቸው ሴቶች በበዓል ልብሶቻቸው አምረው በየአካባቢው በመዞር በ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› መልዕክትና ከፍ ባለ የደስታ ስሜት ነፃነታቸውን የሚገልጹባቸው
ወርሃ ነሐሴ አልቆ መስከረም አንድ ተብሎ መቆጠር ሲጀምርም በየአካባቢው የሚኖሩ ሴቶች ‹‹አበባየሆሽ›› እያሉ ይጨፍራሉ። በዚያው ዕለትም ወንዶች ልጆች የተለያዩ የአደይ አበባና መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ስእሎችን በየቤቱ እየዞሩ «እንኳን አደረሳችሁ» ሲሉ ይሰጣሉ። አዲስ አመትን አስከትሎ በሚመጣው የመስቀል በዓልም ወንዶች በየአካባቢው እየዞሩ ሲጨፍሩ ማየት የኖርንበት ባህላችን ነው።
እነዚህ ሥርዓቶች በዋናነት በሕፃናት፤ በወጣቶች፤ እንዲሁም በአዋቂዎች ጭምር እምብዛም የእድሜ ገደብ ሳይስተዋልባቸው የሚከወኑ ናቸው። እሴቶቹ ያደግንባቸው ብቻ ሳይሆን አብሮነትን ፤ መተማመንና ጓደኝነትን የሚያጠናክሩ የአንድነታችን ገመድ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
እነዚህ ከሃይማኖታዊ ገጽታ በላይ ባህላዊነት ጎልቶ የሚታይባቸው እሴቶች ታዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ንግድ በሚመስል መልኩ ዳራቸውን ለቀው ሌላ መልክ ሲይዙ እያስተዋልን ነው። አሁን ላይ በአብዛኛው በዓላቱን ለማክበር የሚወጡት ልጆች አላማ ከአብሮነት ይልቅ ገንዘብ ማግኘቱ ላይ ያተኮረ መሆኑን ማስተዋል ቀላል ነው።
በቀድሞ ጊዜ በቡሄ በዓል በገጠርም ሆነ በየከተማው የሚኖሩ ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ያጮሃሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ። ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር። እረኞችም ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር። የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ለፍለጋ ወጡ። ይህን እውነታ ለማስታወስ ነበር በዕለተ ቡሄ ለሚጨፍሩ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠው፣ ችቦም የሚበራው።
አሁን ባለንበት ጊዜ ግን ልጆች ታሪካዊ መነሻውን ካለማወቅ ሊሆን ይችላል ለቡሄና መሰል በዓላት የሚጨፍሩት ቤት እየመረጡ ሆኗል። ይህ አልበቃ ብሎ ከገንዘብ ውጪ ሌላ ነገር የመቀበል ፍላጎት የላቸውም። እንዲህ መሆኑ በዓሉ የተለያየ ምልከታ እንዲኖረው አስገድዷል።
ከእነዚህ ከተዛቡ አመለካከቶች መካከል በበዓላቱ የሚደረጉት ጭፈራዎች ዘመናዊ ልመና የመመስል ይዘት እንዳላቸው መታዘብ ይቻላል። ይህ ዓይነቱ የተዛባ አመለካከትም በዓሉን ለሚተካካው ትውልድ እንደነበረ ከማስተላለፍ ይልቅ እሴቱ እንዲሸረሸርና እንዲደበዝዝ የሚያደርግ ነው።
በዓላቱን ንግድ በሚመስል መልኩ መከወን ብቻ አይደለም። ከዚሁ ተያይዞ የጭፈራ ስልቱ ጭምር ሊቃኝ ይገባል። በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚሰሙ ግጥሞች የራስን አጥላልቶ የምዕራባውያንን የሚያዳንቁ ከሆኑ ሰነባብቷል። ይህ ዓይነቱ ሀቅ በዓሉ እንዲፋዘዝ ብቻ ሳይሆን በቱሪዝም ዘርፍ ሀገር ልታገኝበት የሚቻላትን ጠቀሜታ እንዳያደናቅፍ ጭምር የሚያሰጋ ነው፡
ከዚህ ቀደም ልጆች ከየቤቱ የሚሰጣቸውን ሙልሙልና ሌላ ምግብ ብሔርና ሃይማኖት ሳይገድባቸው በአብሮነት ተሰባስበው፣ በመጎራረስ ይካፈሉ ነበር። የአሁኑ ልማድ ግን ከቀድሞው በእጅጉ ይለያል። ነበሩ ሥርዓት እየጠፋ፣ እየደበዘዘ ነው። አንድነታቸውና ኅብረታቸው ከእነሱ አይደለም። አሁን በርካቶቹ ገንዘብና ጥቅም ጉዳይ ላይ ብቻ እያተኮሩ ነው። በግጥሞቻቸው የሚተላለፉት መልዕክቶችም እኛን የማይመስሉ፤ የባዕዳንን ኑሮና ባህል የሚያደንቁና የሚደግፉ ናቸው።
ችግሩን በቡሄ ጭፈራ ላይ እንደ ማሳያ ልጠቅሰው ሞከርኩ እንጂ፤ ይህ እውነታ በእንቁጣጣሽና በሌሎቹም ላይ እየተስተዋለ ይገኛል። ዛሬ በዘመን መለወጫ የሚከወነው የሴቶቹ የአበባየሆሽ ጭፈራ እንደ ቡሄው ጭፈራ ሁሉ መልኩን እየቀየረ ነው። ይሄን ዓይነት አካሄድ ደግሞ ከወዲሁ መስመር እንዲይዝ ካልተደረገ ነገ ሙሉ ለሙሉ ላለመቀየሩ ዋስትና የለም።
እንደመፍትሔ ሁሉም በየቤቱ ኃላፊነትን ሊወጣ ይገባል። ከዚህ ባለፈም በትምህርት ካሬኩለም በማካተት ጭምር ልጆችን ማስተማር ያስፈልጋል። ሕፃናቱ በቤታቸውም ቢሆን ወላጆች የበዓሉን ዳራና ታሪካዊ አመጣጡን ጨምረው ስለ በዓሉ ትክክለኛ የአከባበር እሴት ሊያስተምሯቸው ግድ ነው። ከዚህ ባለፈ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በበዓላቱ አከባበር ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች እንዲዘጋጁ ከማድረግ ባሻገር ባህሉ የነበረውን መልካም የአከባበር ቅርጽ ይዞ እንዲቀጥል ሙያዊ ድርሻውን ሊያበረክት ይገባል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም