በ2015 ዓ.ም. የተፈጸሙ ዐበይት ሀገራዊ ክንውኖች

 በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም. ከተከናወኑ ዐበይት ሀገራዊ ክንዋኔዎች መካከል አንኳር የሆኑት ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል።

 ዲፕሎማሲያዊ ድሎች

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ ከተደረገው የሰላም ስምምነት በመከተል ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ተቀዛቅዞ የነበረው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ መቀጠል መጀመሩ በዓመቱ ከተከናወኑ ዓበይት የዲፕሎማሲ ድሎች መካከል የሚዘከር ነው። ከዲፕሎማሲያዊ ድሎቹ መካከል ተጠቃሽ የሆነው አንዱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊነትን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት አንቶኒ ብሊንከን፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ስለሀገራቱ ቀጣይ ግንኙነት መወያየታቸው ነው። ሌላው ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጣሊያን ሮም በተካሄዱ የተባበሩት መንግሥታት የልማትና ፍልሰት ጉባዔ እንዲሁም የዓለም ምግብ ድርጅት የምግብ ሥርዓት ስብሰባ ላይ ተሳትፈው ኢትዮጵያ በምግብ ራስን በመቻልና ሕገ ወጥ ስደትን በመከላከል በኩል ያላትን ልምድ ማካፈላቸው ነው። ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይትም አድርገዋል።

ከጣሊያን ስብሰባ በኋላ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረዋል። ዶክተር ዐቢይ እንዳሉት የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የትብብር አድማስ በማስፋት ለኢኮኖሚ እድገታችን በኮንሴሽናል ፋይናንስ፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኩል ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መጥተው 17 ስምምነቶችን የተፈራረሙትም በዚሁ ዓመት ነው። ከዚህ በመቀጠልም ኢትዮጵያ ብሪክስ በመባል የሚታወቀውን የአምስት ሀገራት ጥምረት ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ጆሃንስበርግ በተደረገው 15ኛው ጉባዔ ላይ ተቀባይነት አግኝቶ አባል ሆናለች። ኢትዮጵያ አባል እንድትሆን የተደረገው በተከታታይ በተሠሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ነው። በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ሲደረግ የነበረው ውይይት ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ እንደገና በግብጽ መዲና ካይሮ መምከር የተጀመረውም በዚሁ ዓመት የመጨረሻ ወር ላይ ነው። ከእነዚህ በተጨማሪ በባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች በመደረጋቸው በዓመቱ ውስጥ የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ተወካዮች በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።

 የሰላም ስምምነት መፈራረም

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መሪዎች መካከል በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ተጠናቆ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ከስምምነት ላይ ተደርሷል። «ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች» በሚለው የአፍሪካ ኅብረት መርህ በመመራት ለአስር ቀናት ያህል ሲካሄድ በቆየው ድርድር ማብቂያ ላይ የተፈረመው ባለ 12 ነጥብ ስምምነት ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ይዟል። እነዚህም በዘላቂነት ግጭት ማቆም፣ የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ናቸው። ስምምነቱን የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በሕወሓት በኩል ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳ ፈርመውታል። ቀደም ሲል ሽብርተኛ ተብሎ የነበረው ሕወሓት ስምምነቱን ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሽብርተኛ ድርጅት እንዲሠረዝ ውሳኔ ተላልፏል።

 ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን የስንዴ ምርት ወደ ውጭ የመላክ መርሃግብር በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. አስጀምረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ባሌ ላይ ያየነው ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ሂደት ለኢትዮጵያ ማድረግ ከሚገባን ትንሹ ስኬት ነው ብለዋል። የምናደርገውንና የምናቅደውን በተግባር በአረንጓዴ ዐሻራና በሕዳሴ ግድብ እያሳየን መጥተናል፤ አሁን ደግሞ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ከማቆም ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ ያሰብነውን በተግባር ፈጽመን ለኢትዮጵያውያንና ለዓለም አሳይተናል:: በዚህም ኢትዮጵያ ከስንዴ እርዳታ መላቀቅና ወደ ውጭ መላክ አትችሉም ያሉንን ችለን በማሳየታችን ኩራት ተሰምቶናል በማለት በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውን በመጥቀስ «ኢትዮጵያን ኤይድ» በሚል ስንዴ ለመለገስ ተግተን እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል።

በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፤ የስንዴ ምርት እና የምግብ ፍጆታ ሚዛን ታይቶ ከሀገሪቱ ፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ እንደሚኖር በመረጋገጡ በዚህ ዓመት ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ሥራ በይፋ መጀመሩን፣ ለዚህም ዘንድሮ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ስድስት ሀገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈርሟል ብለዋል።

 ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ኤክስፖ

በደብረ ብርሃን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ፋይናንስ ኤክስፖ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ተከፍቷል። በዚህ ኤክስፖ ላይ ከ200 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል። በዓመቱ ከተከናወኑት ውስጥ ሌላው ተጠቃሽ የሆነው ኤክስፖ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በአዲስ አበባ መከናወኑ ሲሆን በኤክስፖው የማዕድን አቅራቢዎች፣ አምራቾች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የያዙ ተቋማትና የዘርፉ አማካሪዎች ምርቶቻቸውን አስተዋውቀዋል። የሕንድ አፍሪካ የአይሲቲ ኤክስፖ በአዲስ አበባ ከተካሄዱ ዓለም አቀፍ ኤክስፖዎች አንዱ ነው። ሀገር አቀፍ ከሆኑት ውስጥ ደግሞ «የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2015» በአዲስ አበባ መከናወኑ ተጠቃሽ ሲሆን በኤክስፖው በአምራቹና በፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት መካከል የነበረውን የቅንጅት ክፍተት በመፍታት ተቋማቱ ለዘርፉ እድገት ተቀራርበው እንዲሠሩ በማስቻል ረገድ የፈጠረው ሚና ከፍተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በዓይነቱ ለየት ያለው የባህላዊና ዘመናዊ ህክምናዎችን ያካተተው የጤና ኤክስፖ በሀገር አቀፍ ደረጃ መካሄዱ ተጠቃሽ ነው። ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎች ኤክስፖዎችም በብዛት ተካሂደዋል።

 ሐላላ ኬላ- ምድራዊ ገነት

በኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክልል በዳውሮ ዞን በኮንታ ልዩ ወረዳ የሚገኘው ሐላላ ኬላ ሪዞርት በጠቅላይ ሚስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ተመርቋል። በወቅቱ ሐላላ ኬላ ሪዞርት ከመዝናኛ ስፍራነቱ በተጨማሪ ታሪካዊና ባህላዊ ሙዚየሞችና የምርምር ማዕከላትን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሐላላ ኬላ ሪዞርት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማጎልበትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መዳረሻ ለማድረግ በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት በ2013 ዓ.ም. ይፋ በሆነው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ስር የሚገኘው የኮይሻ ቅርንጫፍ አንዱ ክፍል ነው። ሪዞርቱ ከአዲስ አበባ 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በ16ተኛው ክፍለ ዘመን በዳውሮ ነገሥታት ስር ከነበሩት ጠንካራ ዓለቶች ስያሜውን አግኝቷል። ከባህር ጠለል በላይ በ900 እና በ1000 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ እንዲሁም ከ25 እስከ 36 ዲግሪ ሴንትግሬድ ሙቀት ያለው ሥፍራ ነው። ቀዝቀዝ ያለው ከሰዓት በኋላውና ነፋሻ ምሽቱ ለቆይታ የሚመች ሲሆን ፀሐይ ስትጠልቅም ከእነ ሙሉ ውበቷ ለማየት ያስችላል። ይህ ምድራዊ ገነት የሆነ ሥፍራ በርካታ የተፈጥሮ ገፀ በረከቶች በአንድ ቦታ ስለሚገኙበት ለተጓዦችና ለጎብኚዎች የሚመኙት ዓይነት ነው።

 በአንድ ጀንበር ከ569 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተከላ

በሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዘንድሮ ለመትከል ከታቀደው ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በአንድ ጀንበር አምስት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ 566 ሚሊዮን 971 ሺህ 600 ችግኞች ተተክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደተናገሩት፣ ችግኞቹ በ302 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተተከሉ ሲሆን የተጠቀሰው ቁጥር በጂኦስፓሻል መረጃ መሠረት የተጠናቀረ ሲሆን በጂኦስፓሻል ባልተካተቱ አካባቢዎች የተተከሉ ችግኞች ስላሉ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ይሆናል። ኢትዮጵያ በአለፉት አራት ዓመታት በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በስኬት አጠናቃለች።

 የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀት

በኢትዮጵያ የሚገኙ ክልሎች በመደበኛ ሠራዊት ደረጃ ሰልጥነው የተደራጁ ልዩ ኃይልን ማደራጀት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ተጠሪነታቸው ለየክልሎቻቸው የሆኑት እነዚህን ልዩ ኃይሎች የማደራጀቱ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በትጥቅም ሆነ በቁጥር ሲጨምሩ ይስተዋል ነበር። ክልሎች ከፖሊስ ባሻገር የታጠቀ የፀጥታ ኃይል ለማደራጀት የሚያስችላቸው የሕግ መሠረት ስለሌላቸው የፌዴራል መንግሥት በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የተደራጁትን ልዩ ኃይሎች መልሶ ለማደራጀት ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔው የሕዝቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባና ሕገመንግሥታዊ ስለሆነ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት የሚያስችል ነው። በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸውና እንደ ፍላጎታቸው በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት እንደሚችሉ አቅጣጫ በማስቀመጥ ከልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ በመድረስ ተግባራዊ ተደርጓል።

 የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ

በአማራ ብሔራዊ ክልል እየተባባሰ የመጣውን የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ ስለመጣ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጣልቃ እንዲገባ የክልሉ መንግሥት ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠይቋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በሕገመንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 እንዲታወጅ ወስኗል። በዚህም መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሞ ተግባራዊ ሥራ ማከናወን ጀምሯል። አስቸኳይ አዋጁ በዋናነት በአማራ ብሔራዊ ክልል ተፈጻሚ ቢሆንም እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚነት አለው። ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረትም የተወካዮች ምክርቤት ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የሚኒስትሮች ምክርቤት የውሳኔ ሀሳብን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

 የሸገር ከተማ ምስረታ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አምስት ከተሞችን ማለትም ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ገላን እና ሰበታን በአንድ አጣምሮ የሚያስተዳድር የሸገር ከተማ አስተዳደር እንዲመሰረት በመወሰን ከጥር ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል። ሸገር ከተማ በ160 ሺህ ሔክታር ላይ የተመሠረተ ሲሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን በማጣመር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 የወረዳ አስተዳደሮችን በአንድ ላይ አዋቅሯል። ጽዱና የተሻለ መሠረተ ልማት መገንባት፣ ከሕገወጥነት የፀዳ ሳቢ ከተማ መገንባት፣ ብሎም ኢንቨስትመንትን መሳብ ከአዲሱ ሸገር ከተማ አስተዳደር ምስረታ ዋነኞቹ ግቦች መሆናቸውና በቀጣይ 7 ዓመታት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዟል። ከተሞቹን በአንድ ላይ የሚያስተዳድረው ከንቲባ ዋና መቀመጫም አዲስ አበባ ነው።

የሸገር ከተማ የመጀመሪያው ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ የቀድሞ ልዩ ዞን መፍረስ እና የአዲሱ ከተማ ምስረታ አስፈላጊነት ቀደም ሲል በልዩ ዞን ስር ገብተው የነበሩ ከተሞች ሰፊ የማልማት እቅድ ቢያዝላቸውም በታሰበው ልክ ከመሄድ ይልቅ ለሕገወጥ ግንባታ እና መሠረታዊ የአገልግሎት ቅልጥፍና ችግር በመጋለጥ ሌላ አማራጭ በማስፈለጉ ነው ብለዋል።

 የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና በተሟላ መልኩ መጀመር

ትምህርት ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ በማዕከል ደረጃ በተሟላ መልኩ ለሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዕጩ ተመራቂዎች (የመጀመሪያ ዲግሪ) የመውጫ ፈተና በማዘጋጀት ከሰኔ 30 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀናት 150 ሺህ 184 ተፈታኞችን ፈትኗል። የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የመውጫ ፈተናውን ከወሰዱት አጠቃላይ ተፈታኝ ዕጩ ተመራቂዎች መካከል የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 40.65 በመቶ ማለትም 61 ሺህ 54 ብቻ መሆናቸውን አሳውቀዋል። ከነዚህም ውስጥ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለፈተና ካስቀመጧቸው 77,981 ተፈታኞች ውስጥ 62.37 በመቶ ተፈታኞቻቸው እንዲሁም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለፈተና ካስቀመጧቸው 72,203 ተማሪዎች ውስጥ 17.2 በመቶ የማለፊያውን 50 በመቶና ከዚያ በላይ የሆነውን ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል። በወቅቱ የመውጫ ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኖራቸውም ተጠቅሷል። በመውጫ ፈተናው የማለፊያ ውጤት ያላስመዘገቡ ቅድመ ምሩቃን ተማሪዎች ፈተናውን በየስድስት ወሩ በሚሰጠው የመውጫ ፈተና ደጋግመው መውሰድ እንደሚችሉም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

 የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መመስረት

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ «ደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች» በሚል ስያሜ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህ ክልል ውስጥ የሚካተቱት ከዚህ ቀደም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ተካተው የነበሩ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ናቸው። ምክር ቤቱ እንዳስታወቀው የጌዴኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የዲራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚል ስያሜ እንዲደራጅ የተወሰነው። በአርባምንጭ ከተማ መሥራች ጉባዔውን ያደረገው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥቶ ራሱን የቻለ ሦስተኛው ክልል ሆኖ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ተመስርቷል። በጉባዔው የቀድሞው የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ የአዲሱ ክልል ምክር ቤት ሹመት ሰጥቷል። ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከዚህ ቀደም ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች(ማዕከላዊ ኢትዮጵያ) ክልል በመውጣት ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች መሆናቸው ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ ዘጠኝ የነበሩት የሀገሪቱ ፌዴራል ክልሎች ቁጥራቸው ወደ 12 ከፍ ብሏል።

 የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ምረቃ

በአዲስ አበባ በተለምዶ ሸጎሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የተገነባውን አዲሱን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ሚዲያ ኮምፕሌክስን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. መርቀው ከፍተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን ችግር የሚያንጸባርቁ አጀንዳዎችን መፍጠር አለባቸው ብለዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን ልዕልና ከፍ የሚያደርጉ ሃሳቦችን የሚያነሱ እና መንግሥት ሲያበላሽ የሚጠይቁ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል። መገናኛ ብዙኃን የሚነገርን ድምጽ የሚያጎሉ ሳይሆኑ ድምጽ የሚፈጥሩ መሆን እንደሚገባቸውም በአጽንኦት ተናግረዋል። በሚዲያው ዘርፍ የሚሠሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ከሰፈር ሽኩቻ በመውጣት በቀዳሚነት የሕዝብ ድምጽ መሆን አንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። አዲሱ የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ዓለም በደረሰበት የሚዲያ ቴክኖሎጂ የተደራጁ ስቱዲዮዎች ያሉት ሲሆን፣ ኢቢሲ ‹‹ለኢትዮጵያ ልዕልና›› በሚል መሪ ቃል በሁሉም አማራጮቹ አዳዲስ ይዘቶችን እና አቀራረቦችን አካቶ ወደ አድማጭ ተመልካች እንደሚደርስም ተመላክቷል።

 ጦርነት አስቀሪና ጨራሽ ኃይል ምረቃ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በብላቴ የኮማንዶና የአየርወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የ41ኛ ዙር የዞብል ኮርስ አባላቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ነሐሴ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. አስመርቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በዚህ መጠን ኮማንዶና አየር ወለድ በአንድ ጊዜ አስመርቃ እንደማታውቅ ተናግረው፤ ይህን ማድረግ ያስፈለገው ኢትዮጵያን የሚመጥን ተለቅ ያለ ኃይል በመገንባት ውጊያን በማስቀረት፣ ሰላምን ማጽናት ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል። የተመራቂው ኃይል አንደኛ ዓላማ ውጊያን ማስቀረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውጊያን በመጨረስ የተከበረውን የክቡር ሕዝቦች አደራ የሆነውን ባንዲራ ሰቅሎ በማውለብለብ ድል ማብሰር እንደሆነም ገልጸዋል።

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You