የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን የማርገብ ቁርጠኛ አቋም መገለጫ!

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ሕዝብ እየተባባሰ ከመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት፣ ከሕገወጥ ግብይትና ከደላሎች የሚታደጉ ተግባሮችን ማከናወኑን ቀጥሏል። የኢንዱስትሪ ምርቶችን በድጎማ እያቀረበ ይገኛል፤ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ፋይናንስ በማቅረብ ጭምር እየሠራ ነው። ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ከገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በማስተሳሰር በግብርና ምርቶች ላይ የሚታይ የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነቱን ለማረገብ ሲሠራ ቆይቷል።

አስተዳደሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደነበረው አሁን ደግሞ የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከላትን በመገንባትና ወደ ሥራ በማስገባት ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት እየሆኑ ያሉ ችግሮችን መፍታት ጀምሯል። ቀደም ሲል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የአትክልትና ፍራፍሬ የግብይት ማዕከል ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል። በዚህም መሀል ከተማዋ ላይ ዘመናትን ያስቆጠረውን የአትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ስፍራ የሚተካ ማዕከል በማቋቋም በአትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ላይ ይታይ የነበረውን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ተንቀሳቅሷል።

ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ መግቢያ በሮች የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከላትን ለመገንባት ይዞት በነበረው አቅድ መሠረት ቀደም ሲል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አንድ የግብይት ማእክል አስገንብቶ ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን፤ ሰሞኑን ደግሞ አንድ ተመሳሳይ የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከል በለሚኩራ ከፍለ ከተማ አስገንብቶ አስመርቋል። የተመሳሳይ ማዕከላት ግንባታ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተካሄደም ይገኛል።

የግብይት ማዕከላቱ ፋይዳ ብዙ ነው። የማዕከላቱ መገንባት አስተዳደሩ የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት የያዘው ቁርጠኝነት አንድ ሌላ መገለጫ ነው። በግብይት ማዕከላት ርቀትና በብዛት አለመኖር ሳቢያ ኅብረተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን የዋጋ መናር፣ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪና እንግልትም ያስቀራል።

የከተማዋ የንግዱ ማኅበረሰብም ሆነ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች የግብርና ምርቶችን በዋናነት የሰብል ምርቶችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከአማኑኤል እህል በረንዳ ብቻ ነበር የሚሸምቱት። ይህ ሁኔታ እየሰፋች ለመጣችው የአዲስ አበባ ከተማና ነዋሪዎቿ በፍጹም አይመጥንም። የገበያ ማዕከላቱ ግንባታ ይህን ግዙፍ ችግርም መፍታት ያስችላል።

የማእከላቱ በየአካባቢው መገንባት ሕዝቡ የግብርና ምርቶቹን በአካባቢው ማግኘት እንዲችል ያደርጋል። አርሶ አደሩ በቀጥታ ምርቱን የሚያቀርብበት የንግዱ ማኅበረሰብም ሆነ ሕዝቡ ያለምንም ውጣውረድና ደለላ የሚሸምትብን እድል ይፈጥራል፤ በተለይ በመሀል ላይ ሆነው ምንም አይነት እሴት ሳይጨምሩ የግብርና ምርቶችን በመደበቅና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ዋጋ የሚያንሩትንና በመሳሰሉት ሕገወጥ ተግባሮች የተሰማሩትን ቆርጦ መጣልና ኅብረተሰቡና አርሶ አደሩ ጤነኛ ግብይት የሚያደርጉበትን እድል መፍጠር የሚያስችል አንድ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።

ማእከላቱን መገንባት አንድ ትልቅ ነገር ነው። በቀጣይ ደግሞ ማዕከላቱ ለአምራቹም ሆነ ለሸማቹ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆናቸው በየጊዜው መፈተሸ ይገባል። ለእዚህም ማዕከላቱን በማስተዳደርና ግብይቱን በመከታተልና በመቆጣጠር ላይ ለመሥራት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። በቦታው ላይ ተገቢዎቹ አካላት ምርት የሚያቀርቡበትንና የሚሸምቱበትን ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም ሥርዓቱ እንዳይፋለስ ማድረግም ይገባል።

ማዕከላቱ ዘመናዊና አገልግሎቶች የተካተቱባቸው ናቸው፤ የከተማዋን ቀጣይ ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገነቡ ናቸው። በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ማዕከልን ለአብነት ወስደን ብንመለከት ማዕከሉ በርካታ የችርቻሮና የጅምላ መሸጫ መደብሮችና መጋዘኖች የተካተቱበት ሲሆን፣ በቂ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ አንድ ላይ ተገንብቶለታል፤ የደኅንነት ካሜራና የመሳሰሉት ቴክኖሎጂዎችም እንዲኖሩት ተደርጓል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ሸማቾችም ሆኑ አምራቾች ያለምንም ስጋት ግብይታቸውን እንዲፈጸሙ ያስችላል፤ ከኋላ ቀር የግብይት ስፍራዎች ግብይት ወጥተው በዘመናዊ የግብይት ማእከል እንዲገበያዩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ማቀዝቀዣና ማሞቂያ ክፍሎች እንዲሁም የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ጭምር የተካተቱባቸው በመሆናቸው፣ ሊባላሹ የሚችሉ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ምርቶችን ከብክነት በመታደግ ብልሽትን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ያደርጋሉ።

ይህ አይነቱ ማዕከል ከተማ አስተዳደሩ ለሚገነባት ዘመናዊት አዲስ አበባ በእጅጉ ያስፈልጋል፤ መሰል ማዕከላት የከተማዋን ገጽታም ለመቀየር የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ እንደመሆኑም ግንባታው ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባውም ነው።

ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ግንባታዎች በከተማዋ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ውስጥ በማካተት በፍጥነት ተገንብተው ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ያለበት ሁኔታም ሊደነቅ ይገባዋል። በተለይ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላቱ ግንባታ ፈጥኖ መጠናቀቅና ወደ ሥራ መግባት ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪ በእጅጉ እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት በወሳኝ መልኩ ለማርገብ ለያዘው አቋም ቁርጠኛ መሆኑ የተመላከተበት ነው!

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You