የታሪክ ማርሽ ቀያሪው መስከረም 2

በየትኛውም ጎራ ያለ የፖለቲካ ቡድን ይህን ቀን ይጠቅሰዋል። ይህን ታሪክ የሚያስታውሰው የፖለቲካ ሰው ወይም የታሪክ ባለሙያ ብቻ አይደለም። ማንኛውም ዜጋ ያስታውሰዋል። ቀኑ መስከረም ሁለት መሆኑን ባያስታውሱ እንኳን ኢትዮጵያ ንጉሣዊ ሥርዓት የነበራት አገር መሆኗን ከ40 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ሁሉ ያውቁታል። ከ40 ዓመት በላይ የሆኑት ደግሞ የታሪኩ አካል ናቸው።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ49 ዓመታት በፊት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ገርስሶ የኢትዮጵያ መንግሥት የሆነበትን ክስተት እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው በዚህ ሳምንት ውስጥ የተከሰቱ ሌሎች ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውሳለን።

ከ110 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 1 ቀን 1906 ዓ.ም የታሪክ ፀሐፊው ተክለፃድቅ መኩሪያ ተወለዱ።

ከ102 ዓመታት በፊት በዚሁ ሳምንት መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ብሎም በዓለም የስፖርት (በተለይም የእግር ኳስ) ታሪክ ውስጥ የከበረ ስም ከነበራቸው ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ (የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ልጅ) ተወለዱ።

ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 2 ቀን 1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሬዲዮ ጣቢያ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተጀመረ። በአሁኑ ወቅት ‹‹የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ብሔራዊ ሬዲዮ አገልግሎት›› የሚል ስያሜ ያለውና፣ ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ‹‹የኢትዮጵያ ሬዲዮ›› በሚባለው ስሙ የሚያውቁት የሬዲዮ ጣቢያ ተቋቋመ። ሬዲዮ ጣቢያውን መርቀው የከፈቱት የወቅቱ ንጉሥ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሲሆኑ ልክ በ39ኛ ዓመቱ በዚያው ቀን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ከዙፋናቸው መውረዳቸው ታውጆበታል።

በዚሁ ሳምንት ከ102 ዓመታት በፊት መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም አንጋፋው ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት›› ተቋቋመ። የዛሬው ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት›› የመጀመሪያ (የቀድሞ) ስሙ ‹‹ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት›› ነበር። ማተሚያ ቤቱ መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም ስራውን በይፋ የጀመረው በንጉስ ተፈሪ መኮንን መኖሪያ ግቢ በምትገኝ ‹‹ጨው ቤት›› በምትባል ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ሲሆን፣ የበኩር ስራው ደግሞ ‹‹ዮሐንስ አፈወርቅ›› የተሰኘው ቅዱስ መጽሐፍ ነበር። የድርጅቱ የመጀመሪያው ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረክርስቶስ ተክለሃይማኖት ነበሩ።

በዝርዝር ወደምናየው ታሪክ እንመለስ።

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ የመጣበት ታሪካዊ ክስተት ነው። በዚህ ክስተት የተከናወነው የተለመደው የአገር መሪ በሌላ መሪ መቀየር አይደለም። አንድን ሥርዓት በሌላ ሥርዓት መቀየር ብቻም አይደለም። ለሺህ ዘመናት የኖረ ንጉሣዊ ሥርዓት፣ ከግማሽ ሚሊኒየም በላይ የዘለቀ የአንድ ሥርዎ መንግሥት (ሰለሞናዊ) ሥርዓት የተቀየረበት ነው።

የመስከረም ሁለቱን ክስተት የታሪክ ባለሙያው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹አዝጋሚ መፈንቅለ መንግሥት›› ይሉታል። እንደሚታወቀው መፈንቅለ መንግሥት የሚደረገው ሲቪሉ ወገን ሳያውቅ ነው፤ ድንገተኛ ነው። የመስከረም ሁለቱ ግን ሳይታሰብ በድንገት የተደረገ መፈንቅለ መንግሥት አይደለም። ሥርዓቱን ሲገዘግዝ የቆየ የሲቪል እና ወታደራዊ ተቃውሞና አድማ ተደርጓል። ከሰኔ ወር 1966 ዓ.ም ጀምሮ ደርግ በይፋ ተመስርቶ ማስተዳደር ጀምሯል። ከመስከረም ሁለት በፊት ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ብዙ ተቋማትን ተቆጣጥሯል። በእነዚህ ሁኔታዎች ‹‹አዝጋሚ መፈንቅለ መንግሥት›› ለመባል በቅቷል።

መፈንቅለ መንግሥት የሚያሰኘው ደግሞ እንቅስቃሴው ወታደራዊ መሆኑ ነው። ሥልጣን የተቆጣጠረውም የወታደሩ ክፍል ነው። የመጀመሪያውን እምቢታ የጀመረውም ወታደሩ ነው። የ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተደረገ በኋላ ንጉሡ ብዙ የማርገቢያ ሙከራ ቢያደርጉም ሊሳካ አልቻለም። በመጨረሻም ወታደሩ የንጉሡን ሥርዓት ገርስሶ ለ17 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ አስተዳድሯል። ለመሆኑ የደርግ አነሳስና አመሰራረት እንዴት ነበር?

በኢትዮጵያ ሲያዘግም የቆየው የአብዮት ፍንዳታ፤ የወታደሩ አመጽ ተስፋፍቶ፣ የየካቲት አብዮት ፈንድቶ፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚሉት፤ የካቲት 20 ቀን 1966 ዓ.ም አዲስ አበባ የሚገኙ የአራተኛ ክፍለ ጦር፣ የጦር ሠራዊት፣ አየር ኃይል እና የዋና መሥሪያ ቤት ወታደሮች በከተማው ቁልፍ ቦታዎችን በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ። የአክሊሉ ሀብተወልድ ሚኒስትሮችን አስረው ያዙ። ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አቶ እንዳልካቸው መኮንንን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ጄኔራል አቢይ አበበን የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው ሾሙ። በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ ሊካሄድ ተዘጋጅቶ የነበረው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ስብሰባ በረብሻው ምክንያት ተሰረዘ።

በዚህ ሁኔታ የተቀጣጠለው አብዮት እየተፋፋመ ሄደ። አመጹም ወደ ሕዝቡ ወረደ። የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፋቸው ‹‹ሕዝባዊ አመፅ›› በሚለው ርዕስ በወቅቱ የነበረውን ሁነት እንዲህ ይገልጹታል።

‹‹በየካቲት 1966 ገንፍሎ የወጣው ሕዝባዊ አመፅ በመሰረቱ የከተሜ ንቅናቄ ነበር። አልፎ አልፎ አንዳንድ ጉምጉምታ ቢሰማም ገጠሬው ባብዛኛው ድምጹን አጥፍቶ ቁጭ ብሎ ነበር። በከተሞች ግን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች (ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወታደሮች እና ሥራ አጥ ወጣቶች) ሥርዓቱን አሻፈረኝ ብለው ተነሱ። ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ይህ ሕዝባዊ አመጽ የተለኮሰው በነገሌ ቦረና የሰፈሩት የ4ኛ ክፍለ ጦር ወታደሮች በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ባነሱት አድማ ነው።››

እንዲህ እንዲህ እያለ ነው እንግዲህ የየካቲት አብዮት የተቀጣጠለው። በነገሌ ቦረና የነበረው የአራተኛ ክፍለ ጦር ወታደሮች ጥያቄ የደሞዝና ሌሎች የኑሮ ሁኔታዎችን የተመለከተ ቢሆንም በውስጡ ግን ፖለቲካዊ ብሶቶች ነበሩበት። በመኮንኖችና በወታደሮች መካከል የነበረው የጌታና ሎሌ ግንኙነት ሁኔታውን አባብሶታል። በሕዝቡ ዘንድ ደግሞ የባላባትና የገባር ግንኙነትም ሕዝቡን ያመረረ ሥርዓት ነበር።

ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየው የወታደሩ እንቅስቃሴ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አገኘ፤ ይህም የሕዝቡን ትኩረት በመሳብ አመጽ እንዲቀጣጠል አደረገ። የሥራ ማቆም አድማዎች ተደረጉ። የታሪክ ተመራማሪው የፕሮፌሰር ባህሩ መጽሐፍም ይህን ይለናል። ‹‹በመጀመሪያ የካቲት 11 ቀን 1966 ዓ.ም የሀገሪቱ መምህራን ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ መቱ›› ይላል።

ይህ አድማ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችንና የወላጆችንም ድጋፍ እያገኘ መጣ። ባለታክሲዎች ደግሞ በወቅቱ የነበረውን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተከትሎ በነዳጅ ዋጋ ላይ የተደረገውን የ50 በመቶ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ተመጣጣኝ የታሪፍ ጭማሪ እንዲደረግ የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ። ይህ አድማ ደግሞ የተማሪዎችንና ሥራ አጥ ወጣቶችን ድጋፍ በማግኘቱ ወደ አመጽነት ተቀየረ። የታክሲዎች ጠላት ናቸው የሚባሉት አውቶብሶችንና ሌሎች ባለቤትነታቸው የመንግሥት ነው የሚባሉ ተሽከርካሪዎችን መሰባበር ተጀመረ። ገንፍሎ የወጣው ሕዝባዊ ቁጣም ሥርዓቱን አስደነገጠው። በመሆኑም በጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የሚመራው ካቢኔ የካቲት 21 ቀን ከሥራ ተሰናበተ።

ንጉሡ ሥራውን በለቀቀው ካቢኔ መተካት የግድ ሆነባቸው። የመገናኛ ሚኒስትር የነበሩትን ልጅ እንዳልካቸው መኮንንን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ሾሙ። የተደናገጠው የንጉሡ መንግሥት መላ መስሎት የካቲት 23 ቀን የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ።

የየካቲት አብዮት ግን በዚህ ሊረጋጋ አልቻለም ነበር። የየካቲት አብዮት ገናና የሆነበትና ‹‹አብዮት›› የተባለበት ምክንያትም፤ የታሪክ ማርሽ የቀየረ በመሆኑ ነው። የታሪክ ደማቅነቱ ብቻም ሳይሆን የፈጠረው ሹም ሽር የኢትዮጵያን መንግስት መሪውን ከተመሪው፣ ሰራተኛን ከአሰሪው፣ ሹሙን ከምንዝሩ ሳይለይ የገለባበጠ በመሆኑ ነበር።

ንጉሣዊ ሥርዓቱን የሚቃወመው የየካቲት አብዮት የክስተት አብዮት ብቻ አልነበረም። ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት ሁኔታ ፈር ቀዳጅ የሆኑ ሀሳቦች አብዮት የፈነዳበት ነው። የመሬት ሥሪት ጥያቄ፣ የዴሞክራሲ መብት ጥያቄ፣ የሰራተኛ የመደራጀት መብት ጥያቄ፣ የብሔርና የብሔረሰብ መብት ጥያቄ እና ሌሎችም ጥያቄዎች የዩኒቨርሲቲውን መድረክ ያዙት።

ከዚህ ጋር ተያይዞም፤ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የለውጥ አቀንቃኝ ተዋንያን በአብዛኛው በጊዜው ለተነሱት ጥያቄዎች የ‹‹ግራ ዘመም ርዕዮት›› ነው ባዩ እየበዛ፤ በአማራጩ የ‹‹ቀኝ ዘመም›› አስተሳሰብ በአድሃሪነት ተፈርጆ ማረፊያ ቤት ተቀመጠ። ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት የኖረችበትን ንጉሣዊ ሥርዓት እስከወዲያኛው የሚያሰናብት አብዮት እየሆነ መጣ።

በዚህ ሁኔታ ዘውዳዊ ሥርዓቱን እያፈራረሰ የሄደው ወታደራዊ ኃይል ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በይፋ ‹‹ደርግ›› ተብሎ ተመሰረተ። ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። ይህን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ለስርዓቱ መገለጫነት የተጠቀሙት ግለሰብ የኮሚቴው የማስታወቂያ ጉዳይ ሠራተኛ የነበሩት ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ እንደሆኑ ይነገራል። ደርግ በዚህ ሁኔታ በዝቅተኛ መኮንኖች (ከኮሎኔል ማዕረግ በታች) ከተመሰረተ በኋላ በዚያው ቀን ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያምን የደርግ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል።

ከዚህ በኋላ ደርግ መንግሥት መሆን እየጀመረ ነው። ዋና ዋና የሚባሉ ቦታዎችን ይዟል። አዋጆችንና ውሳኔዎችንም ማሳለፍ ጀምሯል። በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ሁለተኛው ቀን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሡን ከዙፋናቸው አውርዶ ቤተ መንግሥቱን በመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን አዋጀ። እነሆ በታሪክ ድርሳናታም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የንጉሣዊ ሥርዓት ፍጻሜ ተደርጎ ተወሰደ።

ፕሮፌሰር ባህሩ የአብዮቱን ዱብ ዕዳነት ሲገልጹ ደግሞ፤ ለአሥር ዓመታት ያህል የታገሉለትን ተማሪዎችንም እንደ ማዕበል ነው የበላቸው ይላሉ። ‹‹አብዮት የሚለውን ቃል ብዙዎች ያጤኑት ከአብዮት ፍንዳታ በኋላ ነው›› ይሉታል ፕሮፌሰሩ። የክስተቱን ድንገተኝነት ለመግለጽም ‹‹አብዮት ፈነዳ›› ተባለ። ልክ እንደማንኛውም ፍንዳታ አብዮቱ በመንግሥትም ሆነ በጠላቶቹ ላይ መደነባበርና መደናገርን አስከትሏል። በዚህም ምክንያት ነው አገሪቱን ለፍፁም ወታደራዊ አገዛዝ አሳልፎ የሰጣት። ከሌሎች አገራት አብዮቶች የሚለየውም አብዮቱን ያቀጣጠለው አካል አብዮቱን መቆጣጠር አለመቻሉ ነው ተብሏል። ከፈረንሳይና ከሩሲያ አብዮቶች ጋር እንደሚመሳሰል ነው የታሪክ ምሁሩ የሚገልጹት። በሦስቱም አገሮች ንጉሣዊ ሥርዓትን አስወግዶ ዳሩ ግን ዳግም ለሽብር አመጽ ተዳርጓል።

አብዮታዊው የደርግ መንግሥትም ያላቋረጠ የአገር ውስጥ ጦርነት እያደረገ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት ያህል ሲመራ ቆይቶ በ1983 ዓ.ም ፍጻሜው ሆኗል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You