የአፋር መልክ የሚታይበት የባህል ማዕከል

በአፋር ባህላዊ መገለጫዎች ላይ በርካታ ጥናታዊ መዛግብት አሉ፤ በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል። ብዙ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ተሰርተዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ፕሮግራሞቻቸውን በአፋር ባህላዊና ተፈጥሯዊ ስሞች ሰይመዋል። ጋዜጦችና መጽሔቶች ብዙ ጽፈዋል። ይህ ሁሉ የሆነው የአፋር ባህል ብዙ አስደናቂ ነገሮች ስላሉት ነው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንዱ ዳጉ ነው። ዳጉ ረጅም እና ብዙ ራሱን ችሎ የሚዘረዘር ስለሆነ በሌላ ጽሑፍ ካልሆነ ተቀንጭቦ የሚተው አይደለም።

ስለአፋር ሲነሳ አንድ ተደጋግሞ የሚገለጸው ነገር ‹‹አፋር እንኳን ሰዎቹ ግመሎች የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቁታል›› የሚለው ነው። አፋር ውስጥ የኢትዮጵያ መልክ ይገኛል። አፋር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለም ናት፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ዝርያ መገኛ አፋር ነው። የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ ሁሴን ኦባማ ሉሲን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ለካ ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን›› ያሉት አይዘነጋም። ይህቺ የሰው ልጅ መገኛ የሆነች ሉሲ የተገኘችው አፋር ነው፤ አፋር የድንቅ ተፈጥሮ ባለቤት ነው።

አፋር የድንቅ ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን የድንቅ ሰው ሰራሽ ባህሎችና ጽኑ ስነ ልቦና ባለቤትም ነው። አፋር በሀቀኝነት ይታወቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ገጠመኞችን አንብቤ አውቃለሁ። አፋር ውስጥ ዕቃ የጣለ ሰው በየትኛውም ጊዜ ቢሄድ ያገኘዋል እየተባለ ይነገራል። ይሄ መገለጫቸው ነው።

በአጠቃላይ አፋር ውስጥ ለመላው ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ምሳሌ ሊሆኑ የሚገባ፣ ለዓለም ባህል ሊሆኑ የሚገባቸው ባህሎች አሉ። የዛሬዎቹ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ከመፈጠራቸው በፊት የመረጃ ማግኛ መንገድን ያስተዋወቀ ባህል ያለው ሕዝብ ነው።

እነዚህ ሁሉ የአፋር ባህሎች በተለያየ መንገድ ሲጠኑ እና ውይይት ሲደረግባቸው ቆይቷል። አሁን ግን በአንድ ማዕከል ሥር ሆነው ራሳቸውን ችለው የባህልና አገር በቀል ዕውቀት የምርምር ማዕከል ሊሆኑ ነው። በእነዚያ አገር በቀል ዕውቀቶች ውስጥ ለሥልጣኔ መነሻ የሆኑ ነገሮች ይገኛሉ።

ባለፈው ዓመት መጨረሻ (ባሳለፍነው ሳምንት ማለት ነው) ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው እና በዚያው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኘው የባህል ማዕከል ተመርቋል። የማዕከሉ ስያሜ ‹‹ሬዶ የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች የምርምር ማዕከል›› የሚል ነው። ማዕከሉ የተሰየመው የአፋርኛ ቋንቋ እና የአፋር ባህል አጥኚ እና አስተዋዋቂ በነበሩት የክብር ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር ሬዶ መታሰቢያ ነው። የአፋርኛ ቋንቋን ያጠኑ፣ በአፋርኛ ቋንቋ መጻሕፍትን የጻፉ፣ በተለያየ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍትን ወደ አፋርኛ ቋንቋ የተረጎሙ፤ በአጠቃላይ በአፋር ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ላይ ምርምር ሲያደርጉ በነበሩት የአፋር ባለውለታ የምርምር ማዕከሉ ተሰይሟል።

በማዕከሉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተገኝተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የአፋር ክልል ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያስተሳስር ነው። የአፋር ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህልና አገር በቀል ዕውቀት የሚጠናበት ይህ የምርምር ማዕከል ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር በሰላምና በፍቅር ይበልጥ እንድትተሳሰር የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም በመድረኩ ላይ የተገኙት የጎረቤት አገራት የባህል ልዑካን ቡድን አባላት የሚጋሩት ባህል ስላለ ነው። ለጎረቤት አገራት የልዑካን ቡድኖች ‹‹የባህል ማዕከሉ ተጠናቆ መመረቅ የእናንተም ደስታ ነው›› ያሉት አቶ አወል አርባ፤ በባህልና ምርምር ማዕከሉ ውስጥ የጎረቤት አገራት ባህሎችም እንደሚጠኑበት ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የጅቡቲ እና ኤርትራ ልዑካን ቡድኖች ተገኝተዋል። የተለያዩ ባህላዊ ትርዒቶችም ቀርበዋል፤ የተለያዩ ምሁራን አፋርና አካባቢውን የተመለከቱ ታሪካዊና ባህላዊ የጥናት ውጤቶችን አቅርበዋል። የታሪክ ባለሙያው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በአፋርና አካባቢው ላይ ያተኮረ ጽሑፍ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ በአፋር ባህልና ታሪክ ላይ ያተኮረ ጽሑፍ አቅርበው ውይይቶች ተደርገዋል። ምሁራኑ እና አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፤ የባህል ምርምር ማዕከሉ መቋቋም ለአፋር ባህል መበልጸግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መሀመድ ዑስማን እንደገለጹት፤ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ጋር በመሆን ማዕከሉን ለምርምር ያውለዋል። የባህልና አገር በቀል እውቀቶች ጥናት ማዕከሉ በውስጡ በርካታ ቅርሶችን የያዘ ሙዚየም፣ ባህላዊ ትውፊቶች የሚቀርቡበት አዳራሽ እና ለጥናት ማጣቀሻ የሚሆኑ መጻሕፍትን የያዘ ቤተ መጻሕፍ ያለው ነው። ባህልን ጠብቆ ከማቆየት ባሻገር፣ ዩኒቨርሲቲው ለሚሰራቸው ዘርፈ ብዙ የባህል፣ ቱሪዝም እና ሀገር በቀል እውቀቶች ጥናት የልዕቀት አካል በመሆን እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የተለያዩ ቅርሶችን ወደ ማዕከሉ የማስገባት ሥራ በመገባደድ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዝግጅት ክፍል በቦታው ተገኝቶ እንዳስተዋለው የአፋርን ባህልና ትውፊት የሚያሳዩ መገለጫዎች በማዕከሉ በር ላይ፣ ግቢ ውስጥ እና በአጠቃላይ በማዕከሉ ዙሪያ ይታያሉ። የአፋር ባህላዊ ጎጆ፣ የአፋር መገለጫ የሆነው ጊሌ፣ የአፋር መገለጫ የሆነችው ግመል በሩ ላይ እና በግቢው ውስጥ ለእይታ ቀርበዋል። ጊሌ የማዕከሉ በር አናት ላይ በትልቁ ተሰርቶ ይታያል። ወደ ስብሰባ አዳራሹ መግቢያ በር ላይ ያለችው የግመል ምስል በአካል የቆመች እንጂ በምሥል የተሰራች አይመስልም። ጎጆዎቹ በትክክልም በአካል የተሰሩ ናቸው። ከውስጣቸው የአፋር መገለጫ የሆኑ ምልክቶች ይታያሉ። የምርምር ማዕከሉ የስብሰባ አዳራሽ የአፋርን አየር ንብረት ያማከለ የአየር ማቀዝቀዣዎች (ቬንትሌተር) ያሉት ነው። በአዳራሹ ውስጥ በስክሪን እና በወረቀት ምስሎች የአፋርን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ገጽታዎች የሚያሳዩ ምስሎች ይታያሉ።

ወደ ዩኒቨርሲቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መረጃ ስንመለስ፤ ሠመራ ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም የልዕቀት መስክ ላይ እየሰራ ይገኛል። ለሚሰራው የቱሪዝም የልዕቀት ሥራ ይህን የምርምር ማዕከል ያቋቋመ ሲሆን በአፋር ሕዝብ ታሪክና ባህል ላይ ምርምር ለሚያደርጉ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

‹‹ማህበረሰቡን እናገለግላለን›› የሚል መሪ ቃል ያለው የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ሦስት የልዕቀት ማዕከላት አሉት። አርብቶ አደር ግብርና፣ የሥነ ምድር ሳይንስ እና ቱሪዝም ናቸው። ዩኒቨርሲቲው ቱሪዝምን እንደ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የልዕቀት ማዕከል አድርጎ የያዘ ሲሆን ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የአፋር ክልል የሚታወቅባቸውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስሕቦች ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ፣ በዚህም ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል።

ማዕከሉ የባህላዊ ተውኔቶችና ቴአትር ክፍሎችን ጨምሮ በርካታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ክፍሎች ሰፊ የሚባለው የሚዳሰሱ ቅርሶች የሚገኙበት ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ ከጎረቤት አገራት ኤርትራ እና ጅቡቲ፣ እንዲሁም ከግብጽና ቱርክ የአፋር ታሪክና ቅርስ የሆኑ ቅርሶች ተሰብስበው የሚገኙበት ነው። እነዚህም የባህል አልባሳት፣ ከእንጨት፣ ከቆዳ እና ከብረት የተሰሩ ባህላዊ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ባህላዊ የመዋቢያ ቁሶች፣ ባህላዊ የጦር መሳሪያዎች የመሳሰሉት ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው የባህል ምርምር ማዕከሉን ከማስገንባትም በተጨማሪ በቱሪዝም ልዕቀት ላይ ከአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም፣ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እና ከብሔራዊ ሙዚየም ጋር በመተባበር የቱሪዝም መድረኮችን በማዘጋጀት ይሰራል ተብሏል።

ሬዶ የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች ማዕከል በተመረቀ ዕለት 12 መጻሕፍት ተመርቀው ለንባብ ቀርበዋል። መጻሕፍቱ በአፋር ታሪክ፣ ባህልና ባለውለታ ሰዎች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። መጻሕፍቱ የተጻፉት ለጊዜው በአፋርኛ እና ጥቂቶች ደግሞ በአረብኛ ቋንቋዎች ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎች ይተረጎማሉ ተብሏል። እያንዳንዱ የአፋር ባህል የየራሱ መጽሐፍ ይወጣዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ ለዚያውም በአንድ መጽሐፍ መግለጽ ከተቻለ ነው። ታሪክ እና ባህሎቻችን በዓመት ወይም በወራት አንድ ጊዜ በሚዘጋጁ መድረኮች ሊገለጹና ሊታዩ ስለማይችሉ በመጽሐፍ መልክ ማዘጋጀቱ የተሻለ ያደርገዋል። ጸሐፊዎቹ የአካባቢውን ቋንቋ፣ ባህልና ስነ ልቦና ስለሚያውቁት ተገቢ ማብራሪያ ያደርገዋል። ጊዜ ወስደው፣ አጥንተው ስለሚጽፉት ‹‹ይህን ያህል ደቂቃ አለህ›› ተብሎ መድረክ ላይ ከሚያብራራ ሰው የተሻለ የመግለጽ አቅም ይኖራቸዋል።

የአፋር ታሪክ፣ ባህልና ወግ የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ከዳሎል እስከ ዳሽን›› የሚባል ፕሮግራም አለ። የፕሮግራሙ ይዘት ሁልጊዜም ስለዳሎል እና ሰሜን ተራሮች ማውራት አይደለም። ሁለቱ ቦታዎች የተወሰዱት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ብዝሃነት ጥግ ለማሳየት ነው። ኢትዮጵያ በማህበረሰባዊ ባህል ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም አስደናቂ ብዝሃነት ያላት ናት። በአንድ ወቅት፣ በአንድ ወር እና በአንድ ቀን ውስጥ እንደ ሰሜን ተራሮች ያለ በረዶ ያዘለ ብርድ እና እንደ ዳሎል ያለ እሳት የሚተፋ ሙቀት ያለባት አገር ናት። ይህን የአፋር ዳሎል ኢትዮጵያን ለመግለጽ እንጠቀመዋለን ማለት ነው።

በዳጉ ስም የተሰየሙ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች አሉ፤ የሚተነተንባቸው ስለአፋር ዳጉ ብቻ አይደለም። በዳጉ የተሰየመው መነሻ ስለሆነ እና የመታሰቢያነት ክብር ስለሚገባው ነው። ኢትዮጵያን ስንገልጽ የአፋርን ታሪክና ባህል መጠቀም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ያስፈልገናል ማለት ነው። ስለዚህ ይህ የአፋር የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች የምርምር ማዕከል የኢትዮጵያ ማዕከል ነው ማለት ይቻላል። ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም አገር በቀል ዕውቀቶችን እንዲህ ወደ ምርምር ሊያመጡ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You