የአየር መንገዱ ሽልማት ለሕዝባችን የከበረ የ‹እንኳን አደረሳችሁ› ስጦታ ነው!

 ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ባለ ክብር እያስጠሩ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። አየር መንገዱ ታኅሣሥ 21 ቀን 1938 ዓ.ም ከአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል በተገዙ እና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ባገለገሉ አምስት ዲ.ሲ. 3-ሲ47 (DC 3-C47) አውሮፕላኖች ሥራ እንደጀመረ የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ።

ከቀድሞው ትራንስ ወርልድ ኤይርዌይስ/ /Transworld Airways/ ጋር በጋራ ወደ ሥራ የገባው አየር መንገዱ፤ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ በረራውን መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ካይሮ በተሳካ ሁኔታ በማካሄድ ሥራውን አንድ ብሎ ጀም ሯል።

በዓመታት ሂደት ውስጥ ራሱን ዘመኑን በሚመጥን የአየር ትራንስፖርት እና የአመራር ክህሎት እያበቃ ረጅሙን ዘመን በስኬት እየተጓዘ ያለው ተቋሙ ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥሩ ከሆኑ ጥቂት አየር መንገዶች መካከል አንዱ ነው።

የራሱ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያለው፤ ለግል እና ለንግድ አውሮፕላን አብራሪዎች ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ፈቃድ መስጠት የሚያስችል ደረጃ ላይ የደረሰ እንዲሁም በዘርፉ የሀገር ልጆችንም ሆነ የውጭ ዜጎችን በማሰልጠን እስከ አርባ ዓመታት ልምድ ያካበተ አንጋፋና ስኬታማ ተቋም ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ ያተረፈ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል ያለው፤ ከራሱ አልፎ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ አየር መንገዶችና የግል አውሮፕላኖች የጥገና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ አየር መንገድ ነው። በቅርቡም የአውሮፕላን አካላትን ማምረት የሚያስችል ስምምነት ከአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ጋር መ ፈራረሙ ይታወሳል።

አየር መንገዱ ለመንገደኞች አገልግሎት አዳዲስና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ወደ ሥራ በማስገባት ግንባር ቀደም ነው። የቦይንግ 787 (Boeing 787) ድሪምላይነር አውሮፕላን በማዘዝና ጥቅም ላይ በማዋል ከአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ መሆኑ የሚታወስ ነው። ትርፋማነቱን አስጠብቆ በመጓዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ከበሬታንና ዝናን የተጎናፀፈ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት እጅግ ፈጣን በሆነ እድገት ላይ የሚገኝ፤ በአፍሪካም ትልቁ አየር መንገድ ነው። በ77 ዓመታት የስኬት ጉዞው የአፍሪካ ምርጡና ተመራጩ አየር መንገድ በመሆን በስኬት ላይ ስኬት እየተጎናፀፈ በመጓዝ ላይ ነው። ለሀገር ገጽታ ግንባታም የማይተካ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።

የአፍሪካን የመንገደኞችና የካርጎ አገልግሎቶች በመስጠት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ፤ በአምስት አኅጉራት ከ150 የሚበልጡ አካባቢያዊና ዓለምአቀፍ የመንገደኞችና የካርጎ መዳረሻዎች ያሉት ነው።

ተቋሙ እየተገበረ ባለው የ15 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በ2035 በዓለማችን ከሚገኙ 20 ምርጥ ተወዳዳሪ እና አስተማማኝ አየር መንገዶች አንዱ ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል። ለዚህም ሠራተኛውና አመራሩ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ ነው። በመንግሥት በኩል እየተሰጠው ያለው ትኩረትም ለስኬቱ ትልቁ አቅም እንደሆነ ይታመናል።

አየር መንገዱ ሰሞኑን መቀመጫውን ለንደን (ብሪታኒያ) ካደረገውና አየር መንገዶችን በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በየዓመቱ አወዳድሮ ከሚሸልመው “ቢዝነስ ትራቭለር አዋርድስ” ተቋም (Business Traveller Awards) የ2023 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሆኖ በመመረጥ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ክብርና ሞገስ ተጎናጽፏል።

ከ2020 ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የሽልማቱ ባለቤት የሆነው አየር መንገዱ ፤ በ2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ተጨማሪ ሽልማቶችን ማግባቱ ይታወሳል።ይህም የ15 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ትርጉም ባለው መልኩ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ እየሆነ ስለመምጣቱ የሚያመላክት፤ ትልቅ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ስኬት ነው።

የሰሞኑን ሽልማት በኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት 2016 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ማግኘቱ ደግሞ ሠራተኛውንና አመራሩን ለተጨማሪ ስኬት ማነሳሳት የሚያስችል ትልቅ አቅም ፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የከበረ የ‹እንኳን አደረሳችሁ› ስጦታው እንደሚሆን ይታመናል!

አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You