የጽናትና የአንድነት ቃል ኪዳናችንን ማደስ ይጠበቅብናል

 አልበርት አነስታይን ፤ “ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ፤ ችግር መፍታት አይቻልም። “ እንዳለው ፤ አበው ነገር በነገር ይጠቀሳል፣ እሾህ በእሾህ ይነቀሳል፤ ይላሉ፤ አባባሉ በዕለት ተዕለት ኑሮ ችግርን በፈጠረው ነገር መልሰን በራሱ ችግሩን መፍታት እንችላልን የሚል አንድምታ አለው። እሾህ ቢወጋን በእሾህ እናውጣው ወይም እንንቀሰው የሚል ምክር አዘል ፈሊጣዊ አነጋገር ነው። በተለይ ሀገራዊና ፖለቲካዊ ለሆኑ ጉዳዮች ግን አነስታይን እንደሚለው ችግር ባመጣ አስተሳሰብ በራሱ ችግሩን መፍታት ወይም እሾህን በእሾህ መንቀስ አያዋጣም። አይሰራም። ዛሬ ሀገራችን ከገባችበት እረፍት ነሽ ቀውስ መውጣት የተሳናት፤ ቀውስ ውስጥ በዘፈቃት አስተሳሰብ በራሱ ከቀውስ ለመውጣት ስለምትሞክር ነው። የልቦና ውቅሯን ባዘመሙ ተቋማትና መዋቅሮች መልሳ የልቦና ውቅሯን ለማቃናት ስለምትታትር ነው ነገሯ ሁሉ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሆነባት።

ያው ሁላችንም እንደምንረዳው ለውጡ እስከ ባዕተበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ያልዘመመ እና ውሃ ልኩን ያልሳተ የልቦና ውቅር አልነበረም። የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ ወዘተረፈ የልቦና ውቅራችን ዘሞ ነበር ማለት ይቻላል። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተቀነቀነው የማንነትና የዘውግ ፖለቲካ የዘመመ የልቦና ውቅር አዋቅሯል። በዚህ የተነሳም በዜጎቿ መካከል ጥላቻ፣ ልዩነትና መጠራጠር በመጎንቆሉ ላለፉት አምስት ዓመታት ሁላችንም ያሸማቀቁ፣ አንገታችንን ያስደፉና ያሳፈሩ፤ ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጥቃቶችና ግፎች ተፈፅመዋል።

እስካሁን ድረስ በአማራ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች ግጭቶችና ጦርነቶች እየተካሄዱ ወንድማማቾች እየተገዳደሉ፣ ንጹሐን እየተፈናቀሉና እየሞቱ፣ የሀገር ሀብት እየወደመ፣ ኢኮኖሚው እየደማ፣ ሰላምና መረጋጋት እየተሳነን ይገኛል። ዛሬም ሀገራችን ሕልውና ላይ አደጋ እንደተደቀነ ነው። ዜጎች ይህ አልበቃ ብሎአቸው በዋጋ ግሽበትና በኑሮ ውድነት አለንጋ እየተገረፉ ይገኛል። አንዱ ግጭትና ጦርነት ሲቋጭ ሌላ ያገረሻል። በአጠቃላይ ሀገራችንና ዜጋው እረፍት እያጡ ነው። የስጋት ዳመናዎች እያንዣበቡባቸው፣ ተስፋ እየራቃቸው ይገኛል።

ከዚህ አዙሪት ለመውጣት መንግሥትም ሆነ ዜጎች በአዲስ ዘመን አዲስ የልቦና ውቅር ሊኖራቸው ግድ ይላቸዋል። እሾህን በእሾህ መንቀስ ሊተው ይገባል። መንግሥት ልዩነትንና ጥላቻን ተቋማዊና መዋቅራዊ ያደረጉ አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን ከፍ ሲልም የመንግሥትነት የልቦና ውቅሩን ፈትሾ ሊያድስ ይገባል። ሕዝብ ይሄን የመንግሥት ዳና ለመከተልና የልቦና ውቅሩን ከዚህ አንጻር ለመቃኘት አይቸገርምና። የኢትዮጵያ ሕዝብ አርዓያና ምሳሌ የሆኑ መሪዎችን የመከተል ችግር የለበትምና ።

አዎ ! በሀገራችን ዛሬ የምናስተውለውን ቀውስ በቀፈቀፈ መዋቅርና ተቋም መልሰን በራሱ ሰላም መረጋጋት መደማመጥ መግባባት መቀባበል መታረቅና አንድ መሆን አንችልምና ጨርቄን ማቄን ሳንል በሕግ አግባብ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ፤ ዜጎች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን የሚያበለጽጉበት መብት ባስጠበቀ መንገድ በማንነትና በጎሳ የተመሠረተውንና የተዋቀረው የፌደራል ሥርዓት በቅንነት መፈተሽ

 አለብን። ካለበለዚያ ከዚህ አዙሪት ሰብረን መውጣት አንችልም። የፈጠራ ትርክቶችን ከወል እውነቶቻችን ለመለየትና ለማረቅ ካልተነሳን የተሰበረው የልቦና ውቅራችን አይታጀልም።

98 በመቶ የሚሆን ዜጋ የተለያዩ ዕምነቶች ተከታይ በሆነባት ሀገር የቻርለስ ዳርዊን ዝግመት ለውጥ አማንያን፤ ፈጣሪ የለም በሚሉ ጉግ ማንጉጎች ማለትም በእነ ማርክስ ፣ ኤንግልስ ፣ ሌኒን ፣ ስታሊን፣ ማኦ ፣ ፓል ፓት ፣ ወዘተረፈ የተተወረ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም (አይዶሎጂ) ተከታይ የሆነ ጊዜ የልቦና ውቅራችን ዘሟል። ከኢትዮጵያውያን የሥነ ልቦና ውቅር የተናጠበ የግማሽ ክፍለ ዘመን ማህበራዊ ወረታችንን፣ እሴታችንንና ትውልዶች ከማሳጣቱ ባሻገር የከሸፉ ሁለት አብዮቶችን አስታቅፎን፤ ዛሬ ድረስ የራስ ምታት ታማሚ ላደረገን ፖለቲካዊ ሀንጎቨር አሳልፎ ሰጥቶናል።

ሀገራችን ለ50ና ከዚያ በላይ ዓመታት በድቅድቅ ጨለማ እንድትደናበር አድርጓል። ይህ ብቻ አይደለም ህልመኛና ሀገር ወዳድ የሆነ ትውልድ አሳጥቶናል። የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳንገነባ ፤ ተቋማትን እንዳንተከል አድርጎናል። ተጠያቂነት ባለመኖሩ ሀገር በጠራራ ስትዘረፍ፤ የዜጎች መብት በአደባባይ ሲጣስ በመኖሩ ዛሬ ለምንገኝበት ፈተና ዳርጎናል። ዳፋው ገና ለዓመታት እንደ ጥላ ይከተለናል።

ከ50 ዓመታት በላይ እየተፈራረቀ ተጭኖብን የኖረው የሶሻሊስትና የማንነት ፖለቲካ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም የልቦና ወቅራችንን ከመሠረቱ አናግቶታል። አዛብቶታል። በተለይ የሶሻሊዝም አይዶሎጂ የኃይማኖት ተቋማትን አዳክሟል። የኃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን ሆን ብሎ ማህበራዊ ቦታቸውን እንዲያጡ አድርጓል። ከፈጣሪያቸው ይልቅ እነ ማርክስን እንዲያመልኩ እስከ ማስገደድ ደርሶ ነበር። እንደ ባህላዊ ሽምግል ያሉ እሴቶች እንዲደበዝዙ፤ ለዘመናት አጋምደው በአብሮነት ያኖሩን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ ትስስሮችን አንድ በአንድ እንዲበጠሱ አድርጓል።

በዚህም ለባህሉ ለእሴቱ ግድ የማይለው ትውልድ ተፈጥሯል። ታላላቆቹን የሚያንጓጥጥ፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶቹን ቁልቁል የሚያይ ትውልድ መጥቷል። በአናቱ ለአመታት ሲነዛና ሲቀነቀን የነበረው የተዛባ የማንነት ፖለቲካ ሲጨመር ፤ “ ኢትዮጵያ ትውደም ! “ የሚል፤ በየቀዬው የተፈጥሮ ሀብት ብሔርተኝነትን በመፍጠር ዜጋን በማንነቱ የሚነቅል የሚያፈናቅል ጽንፈኛ ትውልድ ተፈጥሯል። በሀገሪቱ እዚህም እዚያም ጥላቻና ቂም ተንሰራፍቷል። የጋራ ታሪክና ጀግና ከመቀዳጀት ይልቅ በፈጠራ ትርክት እየተጓተተ ይገኛል።

በሶሻሊዝምና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲንጠራወዝ የኖረው የኢኮኖሚ መዋቅር ድህነትን፣ ኋላቀርነትን፣ ሥራ አጥነትን ፣ የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን አስታቅፎ ጥቂት ባለጊዜዎችን ደግሞ ባለጠጋ አድርጎ እንደ ደራሽ ጎርፍ አልፏል። ይህም ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ፈጥሯል። በዚህ የተነሳ ወጣቱ በትንሹም በትልቁም ሆድ እንዲብሰው ከማድረግ አልፎ ለተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ ሆኗል። ሀገርም ሕዝብም ለጉስቁልና

 ተዳርጓል። በዚህ አጭር መጣጥፍ የዘመሙ የልቦና ውቅሮች ያስከተሉትን ዳፋ ፤ እያስከፈሉን ያለውን ውድ ዋጋ ሁሉ ማውሳት አይቻልም።

የሀገሪቱን የዜጋውን የተቋማቱን የተዛመሙ የልቦና ውቅሮች ቀና ለማድረግ የተቋማት ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረተ ልማት ወይም ተቋማት ማለትም ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ ብዙኃን መገናኛ፣ የሰብዓዊ መብት እና የእንባ ጠባቂ ኮሚሽን ፤ የፍትሕ ፣ የዳኝነት ፣ የጸጥታ ፣ የደህንነት ፣ የትምህርትና ሌሎች ተቋማት ሊገነቡ ይገባል። የዳኝነት አካሉን ፣ ምርጫ ቦርድን፣ ሚዲያውንና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግም በአሰራርና በአደረጃጀት የታገዙ ለውጦች ሊተገበሩ ግድ ይለናል።

ከለውጡ በፊት የነበረው አገዛዝ ለጭቆና ለአፈና ይጠቀምባቸው የነበሩ አዋጆች ተሻሽለዋል። አዳዲስ አዋጆችና ሕጎችም ወጥተዋል። ተቋማዊ የግንባታ ሂደቱን የሚያግዙ በርካታ አዋጆችና ውሳኔዎች ፀድቀው ሥራ ላይ ውለዋል። ከፀደቁት መካከል የምርጫ ቦርድ የማቋቋሚያ እና የሲቪል ማህበራት አዋጆች ይገኝበታል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተስፋ የተጣለባቸው ለውጦች ወደኋላ እየተንሸራተቱ ነው። ይህ ለሀገርም ሆነ ለመንግሥት እንደማይበጅ ታሪካችን እማኝ ነውና ሳይረፍድ ሊታረም ይገባል።

ከአምስት ዓመታት በፊት በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርጀው እና የፖለቲካ ምህዳሩ በመከርቸሙ በእስር፣ በስደትና በትጥቅ ትግል ለነበሩ ዜጎች፣ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ይቅርታና ምህረት የተደረገው የዘመመውን የልቦና ውቅር ቀና ለማድረግ ነበር። እንደ ኢሳት ያሉ ከ200 በላይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ድረ ገጾች ፣ ጦማሮች ፣ ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደገና ወደ ሥራ ተመልሰውም ነበር። ፍትሕን ፣ ኢትዮጲስን ፣ ዘሀበሻን ፣ ሳተናውን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። የዘመመው የሀገር የሕዝብና የመንግሥት የልቦና ውቅር ቀና የሚለው በአንድ ጀምበር ባይሆንም አበረታች ለውጦች መታየት ጀምረው ነበር።

አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመከላከያና በሌሎች የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ፤ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፤ በብዙኃን መገናኛ ፤ በሶስቱ የመንግሥት አካላት ማለትም በሕግ አውጭው ተርጓሚውና አስፈጻሚው ለዓመታት ይስተዋል የነበረውን መደበላለቅ በአሰራርና በአደረጃጀት ለመለየት የተጀመሩ ጥረቶች የዘመመውን የልቦና ውቅር ለማቃናት ተስፋ አሰንቀው ነበር።

የገጠመንና የሚገጥመን ፈተና ትውልድ የሚሻገር ነውና። የትኛውም ዓይነት ፈተና የማይበግረን ጽኑ መሆን ስለሚገባን ፤ በሀገራችን ሕልውና የማያወላውል የጸና አቋም እንዳለን ለወዳጅም ለጠላትም ለማረጋገጥ በ2016 ዓ.ም ለውጡ ሲብት የጀመርናቸው ማሻሻያዎች ላይ መልሕቃችንን በመጣል የጽናትና የአንድነት ቃል ኪዳናችንን ማደስ ግድ ይለናል።

ከጀመርነው መንሸራተትና እንደ ገበቴ ውሃ መዋለል ፤ መልሕቋን እንዳልጣለች መናወጥና መዋዠቅ ማቆም ይጠበቅብናል። በቅሎ ፣ ፈረስ፣ ሰረገላ በልጓም ከመስገር ፣ ሽምጥ ከመጋለብ እንደሚገታ እንደሚቆም ሁሉ የመኪና ፣ የባቡርና

 እና የአውሮፕላን ልጓም ቴክኒኩ ይለያይ እንጂ ያው ፍሬን ነው። ፍጥነቱ ይገታል። ይቆማል። መርከብ ደግሞ በመልሕቅ ይቆማል።

በሮማን አገዛዝ ዘመን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ይሳደዱ ፣ ይዋከቡ ፣ ይጋዙ ፣ ይገረፉ ፣ ይሰቀሉ ስለነበር ዕምነታቸውን በሚስጥር ለመያዝ ይገደዱ ነበር። በአደባባይ ማምለክ ፣ መመስከር ፣ በዕምነት መመላለስ ስለማይችሉ ህቡዕ ገብተው ነበር። እርስ በእርሳቸው የሚተዋወቁትም በያዙት ፣ አንገታቸው ላይ ባሰሩት የመልሕቅ ምልክት ነበር። ይህ ምልክት ያለበት ቤትም መማፀኛ ለሚፈልጉ ክርስቲያኖች አስተማማኝ መሸሸጊያ ሆኖ ያገለግል ነበር። መልሕቁን በመለያነት የመረጡት መርከቡ በኃይለኛ ማዕበል ሲናወጥ ፀንቶ ለመቆም እንደሚያስችል ሁሉ በዕምነታቸው የተነሳ የሚደርስባቸውን ግፍ፣ መከራ ፣ መሳደድ በፅናት ፣ በተስፋና በጥንካሬ እንደሚያልፉት ለማሳየት ነው።

የክርስትናስ አስተምህሮ ይሄው ተስፋ እና ፅናት አይደል !? መልሕቅ ሚዛናዊ እና በመስቀል ላይ የተቀመጠ ነው። በመስቀሉ ወደ ጎን የተጋደመው መስመር መንፈስን ከላይ ወደ ታች የተሰመረው ደግሞ አካልን ይወክላል። መስቀሉ በአንድነት የመንፈስና የአካልን አንድነት ያሳያል። የሰውን ሥጋ ለባሽነትንም ያመለክታል። ከፍ ሲልም በመልሕቁ ያለው መስቀል ተባዕታይ ጾታን ግማሿ ጨረቃ ደግሞ አነስታይ ጾታን ፣ ማህጸንን ይመሰጥራል። መርከቡ ከቆመበት ወደብ ተነስቶ አዲሱን ጉዞውን ፣ ጀብድ adventure የሚጀምረው የጣለውን መልሕቅ በማንሳት ስለሆነ ተስፋን ይወክላል። ለዓመታት ሕይወት በአንድም በሌላ መልክ ከረጋበት ፣ ከቆመበት በአዲስ ወኔ መንፈስ መልሕቃችንን አንስተን አዲስ መንገድ ስንጀምር ሰንቀነው የምንነሳ ተስፋንም ይገልጻል።

መርከብ መቅዘፍ ሲጀምር ወደ አዳዲስ ውኆች ሲንቀሳቀስ መልሕቁን እንደሚያነሳ ሁሉ እኛም በሕይወት መርከብ መቅዘፍ ስንጀምር ሊመጣ ያለውን በተነቃቃ ስሜት ፣ ተስፋና ጉጉት እንጠብቃለን። አዲሱን ህልም ከሩቅ እየተመለከትን ለመድረስ በድፍረት ፣ በፅናት እንቀዝፋለን። ፅናታችን ውሳኔ የመስጠት ብቃታችን ተምሳሌታዊ ወኪል ከመሆኑ ባሻገር የምንወስደውን አቋምም ሆነ የምንመራበትን መርህ ያሳያል። መርከብ መልሕቁን ከጣላ በኋላ እንደማይንቀሳቀስ ሁሉ እኛም ስለ እውነት ፣ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር በመተማመን ስለ መጠበቅ አቋም ከወሰድን ከወሰን በኋላ ዳር እስኪደርስ እውን እስኪሆን መጽናት እንጂ ማወላወልና ማመንታት አያስፈልግም።

ምንም አይነት ቀውስ ፣ ምስቅልቅል ፣ ትርምስ፣ ፍርሀት ፣ ችግር ፣ መከራ ፣ ፈተና ዙሪያችንን ቢከበን ብርክ ቢይዘን ሁኔታዎች ሁሉ ምንም ያህል ቢያጠራጥሩን የሕይወትን መልሕቅ መጣል በፅናት መቆም እንጂ መናወጥ አይገባም። ይህ የተረጋጋ ሰብዕና መገለጫም ነው። መንግሥትም ወደ ሥልጣን ሲመጣ ይዟቸው ከመጣቸው ማሻሻያዎች ላይ ዓይኑን ሊያነሳ አይገባም። በሚያምኑበት ነገር ፅኑ አቋም ያላቸው ሰዎች ለማህበረሰባዊም ሆነ ለግል እሴቶች ከፍ ያለ ዋጋ እንዳላቸው ሁሉ መንግሥትም እንደዚያ ሊሆን ይገባል።

ሻሎም !

አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You