‹‹ግብጾች የሚከራከሩት ባፈጀና በዚህ ዘመን በማይሰራ መሰረት ላይ ቆመው ነው››- ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በአ.አ.ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ በተለይ በዘርፉ በመመራመርም ሆነ የድርድሩ አካል በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ፊተኛው መስመር ላይ ይገኛሉ፡፡ የዛሬው የዘመን እንግዳችን የተወለዱት በቀድሞ ከምባታ አውራጃ በያያማ አካባቢ፣ ዘግሾ መንደር ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በከምባታ እንዲሁም በወላይታ ተምረዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ደግሞ በአዲስ አበባ እና በአምቦ ጉደር ነው። እኚህ እንግዳችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

ዶክተር ያዕቆብ፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተምረዋል፡፡ በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ጉዳይና በፖለቲካል ሳይንስ መስክ አሜሪካ ከሚገኘው ኦሀዩ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የማስተርስ ዲግሪ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በስዊዘርላንድ ከሚገኘው ከታዋቂው ዙሪክ ዩኒቨርሲቲ በናይል ውሃ ጉዳይ በፖለቲካል ሳይንስ መስክ አጠናቅቀው የፊሎሶፈል ዶክተርነት ተቀብለዋል። ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መስክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር፣ በምርምርና በማማከር ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡

የዛሬው እንግዳችን የአፍሪካ፣ የእስያና የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች የውሃና ማህበረሰብ ምርምር አባልና የኢትዮጵያ አስተባባሪም ናቸው፡፡ እንዲሁም የሰሜንና የደቡብ አህጉራዊ ምርምር የምስራቅ አፍሪካ ዘርፍ አማካሪ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነውም አገልግለዋል፡፡

ዶክተር ያዕቆብ፣ በርከት ያሉ ሙያ ነክ የምርምርና የስርጸት ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡ እንዲሁም በርካታ የሙያ ማጠናከሪያና ማስፋፊያ መጻሕፍትን ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን አበርክተዋል። ‹‹ናይልና ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ደግሞ መጽሐፍ ማሳተም ችለዋል፡፡ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ተዘዋውረው ትምህርታዊ ሌክቸር ሰጥተዋል።

እርሳቸው በርከት ያሉ ተግባራትን ያከናወኑ ናቸው፡፡ ላበረከቱትም አስተዋፅኦ የተለያዩ ሽልማቶችን ተሸልመዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የ2012 ዓ.ም የዓመቱ በጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ መሆናቸው ተጠቃሽ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰርተፍኬቶች፣ የምስጋና ደብዳቤዎች እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የፈረሙበትን ጨምሮ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ሲመሩ ከነበሩ ከተለያዩ ሚኒስትሮች የምስጋና እና የምስክር ወረቀትን ተበርክቶላቸዋል፡፡ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ዳይሬክተርም የሰጧቸው ሽልማቶችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለይ በህዳሴ ግድብና በአባይ ውሃ ጉዳይ የካበተ የምርምር ስራ ካላቸው ከዛሬው እንግዳችን ከዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት ያካሔደችውን 4ኛው ዙር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ተከትሎ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሌቱ የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፤ እውን ኢትዮጵያ ከውሃ ሙሌቱ ጋር ተያይዞ የጣሰችው ዓለም አቀፍ ሕግ አለ?

ዶክተር ያዕቆብ፡– ለግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብቻ የሚሰራ የዓለም አቀፍ ሕግ አይኖርም፡፡ የሚኖረው ሕግ ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለሌሎች  የተፋሰሱ አገሮች ጭምር የሚሰራ ጭምር ነው፡፡ እናም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚጠቅሱት ስምምነት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጭምር ከራሷ ከግብጽ ጋር በመሆን እኤአ በ2015 የተፈራረሙት የመርህ መግለጫ (Declaration of Principle) የሚባል ሰነድ አለ፤ ከዚህ ሰነድ ውስጥ እርሳቸው የሚጠቅሱት የሚመቻቸውን አንቀጽ ነው፡፡ ይሁንና እሱ ሰነድ በጣም ጠቃሚ የሆኑ አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡

ከዚህ ውስጥ አንዱ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከግንባታው ጋር ጎን ለጎን ይሄዳል የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ እያለ ተጉዞ አሁን አራተኛ ሙሌት ላይ መድረስ የቻልነው፡፡ ስለዚህም የግድቡ ውሃ ሙሌት ከግንባታው ስራ ጎን ለጎን እየሔደ ያለ ነው፡፡

ሌላው ነጥብ የሕዳሴ ግድብ የውሃ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እና ሌላውን ወገን በከፋ ደረጃ እንዳይጎዳ በመጠንቀቅ ይሞላ የሚል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውሃውን እያለማች ነው፡፡ ይህ ደግሞ መብት ነው፡፡ ምክንያቱም ውሃውን ማልማት ለልማት ስራዬ ዋጋ ያለው ነው ብላ በኃላፊነት ዲዛይን አውጥታና በጀት በጅታ በእቅድ የምታሰራው ስራ ነው። ይህን ስታደርግ ሌሎቹን እንዳይጎዳ በከፍተኛ ሁኔታ በመጠንቀቅ ነው፡፡ ዲዛይኑም ሆነ አሰራሩ የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡

ለዚህ ማረጋገጫው ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ አንደኛ ሙሌት ግብጽን ሲጎዳ አልታየም፡፡ በተመሳሳይ ሁለተኛውም ሆነ ሶስተኛው የውሃ ሙሌት አልጎዳቸውም። ጎዳን የሚሉ አካላት ቢኖሩም ስለመጎዳታቸው ያቀረቡት አሊያም ደግሞ ሊያቀርቡት የሚችሉ ማስረጃ የለም፡፡ ይልቁኑ የጠቀማቸው ብዙ ነገር አለ፡፡ ከዚህም መካከል ጎርፍ በመቀነስ ደረጃ እና ውሃን ዓመቱን ሙሉ በትክክል እንዲፈስ በማድረጉ ረገድ አግዟቸዋል፡፡ እነርሱ አቅደው፣ ዓልመው እና ዲዛይን አድርገው ሊሰሩ ያልቻሉትን እንዲህ አይነቱን ጥቅም እያገኙ ያሉት ያለምንም ክፍያ በነጻ ነው፡፡ ስለሆነም የግድቡ መሞላት እነርሱን አልጎዳቸውም።፡ ግድቡ ስምምነትን የጣሰ ሳይሆን በጥሩ ሁኔታ እየተካሔደ ያለ እና የእነርሱን መብት ያልተጋፋ ነው ብሎ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ስለዚህ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው የሚሉት እርሳቸው አውቀው ሌላ ሰው የማያውቅ ሕግ ካለ ይናገሩ እንጂ በስምምነቱ መሰረት ከሆነ የሚከለክል ነገር የለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እኤአ በ2015 በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሶስቱ መሪዎች የተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት ያጠነጠነው ምን ላይ ነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- በአገራቱ መካከል በተደረገው የመርህ ስምምነት ውስጥ ያለውን ነጥብ ስናጤን አስር ያህል አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡ በእነዚህ አስር አንቀጾች ላይ የስምምነት ፊርማው በመሪ ደረጃ የተካሔደበት ነው፡፡ ለምሳሌ አንደኛውን ነጥብ መጠቀስ ካስፈለገ የኢትዮጵያ የውሃ ልማት አጠቃቀም (ግድቡን ጨምሮ) በፍትሃዊ እና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲሆን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ የሆነና ይህም ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ስምምነት ውስጥ የተጠቀሰ ነው። ስለዚህም ብዙ አገሮችም የሚስማሙበት አጠቃላይ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እሳቤም ስለሆነ ነጥቡ እዛ ውስጥ የተካተተ ነው፡፡

the most popular brands of today like click here in our store.

ኢትዮጵያ ልማቷን ስታካሂድ ሌላው አገርም እንደሚያደርገው ሁሉ የውሃ ተጋሪ አገር ጉልህ ጉዳት ከማድረስ መጠንቀቅ የሚለው አለ፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ግድብ ለመገንባት ስታቅድ እና ዲዛይኑን ስታወጣ እንዲሁም ባወጣችው ዲዛይን መሰረት ግድቡን ስትገነባ የራሱ የሆነ አካሄድን በመከተል ነው፡፡ በዚህ አግባብም እየተገነባ እንዳለም የሚታወቅ ነው፡፡

በተለይም ውሃ የሚሞላው ከፍተኛ የዝናብ ጊዜ ነው በተባለበት የክረምት ወቅት ስለሆነ ደረጃ በደረጃ በየዓመቱ ያለምንም ችግር ሲከናወን ቆይቷል፡፡ በዚህም አግባብ በሌሎቹ ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳትም ሳይደርስ ውሃ ሲሞላ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ግብጾችም ሆኑ ሌሎች የተጎዱበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህ የግድቡን አሰራር እና የውሃ አሞላል ጤነኛ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይህ አይነቱ አካሔድ ደግሞ እንደተባለው የዓለም አቀፉን ሕግ እና መርህ የጣሰ ሳይሆን በሕግ መሰረት እየተሰራ ያለ ስራ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የሕዳሴ ግድብ የሚሞላው ግንባታው እየተካሔደ እያለ ጎን ለጎን ነው፡፡ ይህ አካሄዱ ደግሞ በመርህ ስምምነቱ ውስጥ ያለ አንቀጽ ውስጥ የተካተተ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት የሞላችው የግድቡን ግንባታ ከፍ ያለ ቦታ አድርሳ ነው፡፡ ሁለተኛውም በተመሳሳይ ግንባታውን ከፋ አድርጋ ሰርታ ነው፡፡ ሶስተኛውንም ዙር የውሃ ሙሌት እንዲሁ ግንባታው ከፍ ባለ ጊዜ የሞላችው ነው። ግንባታው በየዓመቱ ከፍ ሲል የውሃ ሙሌቱ ደግሞ እንዲሁ ስለሚሞላ አራተኛውም ዙር የተከናወነው በዚህ መልኩ ነው፡፡

ይህ አካሄዷ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ግድቧን በአንድ ጊዜ ውሃ ልሙላ አለማለቷን ነው፡፡ ይልቁኑ በክረምቱ ወራት ውሃ በብዛት የሚገኝበትን ጊዜ ጠብቃ እነርሱን በማይጎዳ መልኩ ያከናወነችው ተግባር ነው፡፡ ይህ አሰራሯ የትኛውንም አካል የጎዳ እና የሚጎዳ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ሊፈጠር የሚችለውን የጎርፍ ጉዳትን ጭምር የሚያስቀር አካሄድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውሃውን በመሙላቷ በእነርሱ ላይ የጎላ ጉዳት አልደረሰም፡፡ ስለዚህ የተፈረመው የመርህ መግለጫ (Declaration of Principle) በኢትዮጵያ በኩል ምንም የተጣሰ ነገር የለም፡፡

እንዲያውም ሲፈረምም የግድቡ ስራ የውሃ አሞላሉ በሚቀጥልበት መንገድ እና በማይከለክል መንገድ በጥንቃቄ ድርድር ተደርጎ የተፈረመ ነው፤ ስለሆነም እነርሱ ሕገ ወጥ የሚሉት ጉዳይ የራሳቸው አባባል ነው እንጂ ስምምነቱ ያንንም የሚወክል አይደለም፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቀጣይ የምታካሂደው የውሃ ሙሌት የሚከተለው አቅጣጫ ምን የሚመስል ነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ለወደፊቱም ቢሆን የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ አልቆ የተያዘለትን እቅድ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እስከሚያዝ ድረስ ኢትዮጵያ የምትቀጥለው በዚህ አይነት ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑም ግድቡን ውሃ መሙላት የሚከለክል ምንም አይነት አካሄድ የለም፡፡ አንደኛ ኢትዮጵያ እየሰራች ያለው ነገር ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የውሃ አሞላሉ ከግንባታው ጋር ጎን ለጎን እየሄደ ነው፡፡ በመሆኑም ግንባታውም ሆነ አሞላሉም ደረጃ በደረጃ እየሄደ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። እነርሱ ግን ውሃ አነሰን ያሉት ነገር ሲጤን እስከ አሁን ድረስ አራት ጊዜ ግድቡ ተሞልቷን፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም አይነት ማረጋገጫ ማምጣት አልቻሉም። ደግሞም ሊኖርም አይችልም፤ ምክንያቱም ግድቡ በጥንቃቄ እየተሰራ እዚህ የደረሰ ነው፡፡ የግድቡ ስራ እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚህ አይነት ሁኔታ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ቀጥሎ ባሉትም ጊዜያት ውሃ የሚያዘው በዚሁ አይነት አካሄድ ነው፡፡ ግድቡ የታለመለትን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እስኪይዝ ድረስ በዚህ አግባብ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የጣሰችው ዓለም አቀፍ ሕግ ሳይኖር ሕግ ጥሳለች መባሉ ራሱ ሕግ ጥሰት አይሆንም?

ዶክተር ያዕቆብ፡– ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሳለች መባሉ በመጀመሪያ ደረጃ በራሱ ሙሉ ለሙሉ ሐሰት ነው። የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብቻ የሚያውቁት የዓለም ሕግ ከሆነና ሌላ ሰው የማያውቀው የዓለም ሕግ ከሆነ ነው እንጂ እኛ በተፈራርምነው እና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ በሚደረገው ልማት ስምምነት እና ልምድ አንጻር እርሳቸው ያሉት በምንም መልኩ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ልክ ናቸው ወይስ አይደሉም በሚል ማረጋገጫም ሆነ ክርክርም የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግብጽ በኩል እንዲህ መባሉ በኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖር ይሆን?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ይህ ለራሳቸው የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ያሉት እንጂ በኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው አንዳች ነገር የለውም፡፡ ምናልባትም የፖለቲካ መልዕክቱ ለግብጽ ሕዝብ ሲሆን፣ ለእነርሱም ‹‹ይኸው እኛ ዝም አላልንም፤ ኢትዮጵያ ግድቧን ውሃ እንዳትሞላ እየተከላከልን ነው፤ የግብጻውያንን ውሃ እየጠበቅን ነው›› በሚል በተለመደው መልኩ ለሕዝባቸው መልዕክት ለማስተላለፍ የተጠቀሙበት አካሄድ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ ሕዝባቸውን ያሳምናል የሚል ቃላት መርጠው መጠቀማቸው ነው እንጂ ጉዳዩ ትክክል ሆኖ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አይነቱ አባባል የተለመደ እና ሁሌም ሲሉት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬም እየደገሙት ያለው ያንኑ አባባል ሲሆን፣ መደጋገም ደግሞ አይሰለቻቸውም፡፡

አዲስ ዘመን፡- አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌትን ተከትሎ እስካሁን ድረስ ሱዳን ያለችው ነገር የለም፤ ይህን እንዴት ያዩታል? የሱዳን ዝምታ የኢትዮጵያ ትክክለኛነትን ያረጋግጣል ይላሉ?

ዶክተር ያዕቆብ፡– በአሁኑ ወቅት እንደሚታወቀው የሱዳን የሰላም ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ነው። በአሁኑ ወቅት ግጭት ላይ ስላለች የሱዳን ትኩረት በአገሯ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ላይ ነው፡፡ ሱዳን በአሁን ወቅት ያጋጠማት ግጭት አጣብቂኝ ውስጥ ባይካተት ኖሮ ግብጽ የምትለውን የሰሞኑን አባባል ተከትላ ታንጎራጉር ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ የሱዳን ዝምታ ኢትዮጵያን በመደገፍ ነው ማለት አያስደፍርም፡፡ ወይም ደግሞ ግብጽ የምትለውን ነገር ባለመቀበል ነው ማለት አይቻልም፡፡ ጉዳዩ ገብቷት ነውም ማለት አያስችልም፡፡

በጥቅሉ ግን አንደኛ የስምምነቱን ፍሬም ቀደም ሲል ያልፈረመች ናት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያ ከእነርሱ ጋር የግድቡን አሞላል በተመለከተ ድርድር በሚያደርጉበት ጊዜ ከግብጽ ጋር ተለጥፋ የነበረች በመሆኗ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ግጭት ባይኖርባት ኖሮ ከግብጽ ትለያለች ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌቱ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት እንደሚወስድ ሲነገር ነበር፤ ከሰሞኑ የተከናወነው አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ግን የመጨረሻው እንደሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲገለጽ ተደምጧል፤ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶክተር ያዕቆብ፡– ይህን የሚያውቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ጉዳዩን ፍሬም ያደረጉ አካላት ናቸው። ለማንኛውም እንደሚታወቀው የግድቡ ስራም ሆነ የውሃ ሙሌቱ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ የሲቪል ስራ 93 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የኮርቻ ግድቡ ደግሞ ከተጠናቀቀ ቆየት ብሏል፡፡ ሌሎች ቀሪ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው። የግድቡን ቁመት የሚወስነው ስራ ወሳኝ ነው። እሱ ደግሞ ገና አላለቀም፤ በቀጣዩም ዓመት ቁመቱ ከፍ ሲል ሌላ ዙር የውሃ ሙሌት የሚካሄድ ይመስለኛል፡፡ ከዚያም ከፍ እያለ ሲሄድና መቶ በመቶ ሲጠናቀቅም የመጨረሻው ውሃ እየሞላ ይሄዳል፡፡

ምናልባትም የተባለው ከእንግዲህ በኋላ ውሃ ሲሞላ ከላይ እየፈሰሰ አይታይም የሚለውን ለመግለጽ ይሆናል። እንዲህም ሲባል የውሃ ሙሌቱ እየፈሰሰ የማየቱ ጉዳይ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡ ሰው ደግሞ ውሃ ሞላ ማለት ከላይ ሲፈስ መታየቱ ነው ብሎ ካሰበ ለየት ያለ ነገር ለማሳየት ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ግድቡ እየተገነባ እና እየተሞላ የሚሰራ ሆኖ እዚህ ደርሷል፡፡ ከዚህም በኋላ የውሃ ሙሌቱ የሚጠናቀቀው በእንዲህ አይነት ሁኔታ እየሄደ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ በመሆኑም እዚህ ላይ ቆሟል፤ አሊያም ተጠናቋል የሚሉ አይመስለኝም፤ የሚሉበትም ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡

እንደሚታወቀው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባታውን ሒደት በየዕለቱ የሚከታተሉት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም የመጨረሻው ነው ማለት ከእንግዲህ ወዲያ ግድቡ አይሞላም የሚል አይነት ትርጓሜ ያለው አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ አስተሳሰቡም ይህ አይመስለኝም፡፡ አገላለጹን በተመለከተ ግን ጉዳዩን ፍሬም ያደረጉትና አማካሪዎቻቸው በጥልቀት ስለሚያውቁ ሊያስረዱ ይችላሉ የሚል አተያይ አለኝ፡፡

እስካሁን ግድቡ ውሃ ይዞል ተብሎ የተነገረው ወደ 42 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በአንድ ዙር ሳይሆን በየጊዜው በተከናወነው የውሃ አሞላል ስርዓት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው በዚህ መልኩ በቀጣይ እየሞላ እና እየጨመረ መሄዱን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከሕዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ በቀጣዩ ድርድሩ የሚደረገው አዲስ አበባ ውስጥ እንደሆነ ተጠቅሷል፤ ባለፈው ግብጽ ውስጥ የተካሄደው የድርድር መድረክ ላይ ግን ከፍ ያለ ክርክር ተስተናግዶበታል ይባላልና ምን መልክ ነበረው?

ዶክተር ያዕቆብ፡– በግብጽ በተካሔደው መድረክ ላይ እኔ አልነበርኩም፡፡ በቦታው ስላልነበርኩ ምን አይነት ውይይት እንደሆነ ልጠቅስ አልችልም፡፡

ይሁንና በኢትዮጵያ ወገን እስካሁን እኔ እስከማውቀው ድረስ በግብጽ በኩል የሚመጣን አስገዳጅ የስምምነት ፊርማ አታውቅም፤ አትፈርምም። የኢትዮጵያ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ግብጽን እያስፈቀዱ ለመስራት በሚመስል መንገድ ፈርሙልን የሚባለውን ነገር ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት ተቀብላ አታውቅም፤ ዛሬም የማትቀበለው ነገር ነው፡፡

ግብጾች ከዚህ አኳያ ከመጡ በማንኛውም መድረክ ላይ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ እሱን ከወዲሁ መገመት እችላለሁ፡፡ ምናልባትም ግብጽ በነበረው መድረክ ክርክር ከነበረም የሚሆነው በዚሁ አቅጣጫ ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ሁሌም ቢሆን መብት የማስከበር ተግባር ይኖራል፤ ግብጽ ደግሞ ይህንን እንደ ጭቅጭቅ ልትወስደው ትችል ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ በእንዲህ አይነት መልኩ እየተሟገቱ መጓዙ ያስኬዳታል? ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው ምንድን ነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡– ግብጽ እስካሁን ድረስ የምትሰራው ነገር ቢኖር የማያስፈልጋትንም ነገር ሁሉ በድርቅና ስትናገር መቆየት ነው፡፡ መሰል ነገሮችን በመሟገትና ለሶስተኛ ወገን አቤት ከማለት እንዲሁም የኢትዮጵያን ስም ከማጠልሸት እና ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሳለች ከማለት የምትመለስ አገር አይደለችም። ይህን አካሄዷን ልክ እንደ ዋና የዲፕሎማሲ ስራ አድርጋ ስለምትሰራበት ቢያዋጣትም ባያዋጣትም በዚሁ በለመደችው አቅጣጫ እየሄደች ስለሆነ የምትቆም አይደለችም፡፡

እኛ ግን የሚጠበቅብን የራሳችንን ስራ ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መስራት ነው፡፡ በሚያግባባን ነገር መግባባት እችላለሁ ብላ ከመጣች መግባባት ነው፤ ካለበለዚያ ግን ኢትዮጵያ ጥቅሟንም፣ ስራዋንም ሆነ መብቷንም በግብጽ ፈቃድ ቆልፋ የምትተው አገር አይደለች፡፡ ደግሞም ይህንን ማንም አያደርገውም፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ እንደ አንድመደራድርዎ እና በዘርፉም ለረጅም ጊዜ እንደመመራመርዎ ለግብጻውያን ፖለቲከኞች ምን ማለት ይሻሉ?

ዶክተር ያዕቆብ፡– የዓባይ ውሃ እና ወደ ናይል የሚፈሱ የውሃ አካላት የሆኑ ሀብቶች በተፈጥሮ የኢትዮጵያም፣ የግብጽም ሆነ የሱዳንም በመሆናቸው ለጋራ ጥቅም መዋል ያለበት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያ ስትቀበል ኖራለች፡፡ ነገር ግን ይህ የጋራ ሀብት አገራቱ በመተሳሰብ፣ በመተጋገዝ እና በመተባበር ሊሰሩበት የሚገባ ነው፡፡ የቱ አገር የትኛው አይነት የውሃ ልማት ይመቸዋል? ያዋጣዋል? የትኛው አገር በየትኛው የውሃ ሀብት ልማት ቢያተኩር ይሻላል? የሚለው ላይ መግባባት መቻል መልካም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጋራ ጥቅማቸው እና ለኢኮኖሚያዊ ልማታቸው እንዲሁም ለየሕዝባቸው እድገት ይጠቅማልና የሚያስፈልገውም ሆነ የሚያዋጣው በትብብር መስራት ነው፡፡

እኛም ይህንን ሐሳብ ስንመኘውና ስንከራከርበት ኖረናል፡፡ ይህ ደግሞ ለግብጾችም ለሱዳኖችም ጥሩ ሐሳብ ነው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ትብብር እስካለ ድረስ ጉዳት ነው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ግብጾች የሚደራደሩትና የሚከራከሩት ባፈጀ እና በዚህ ዘመን በማይሰራ መሰረት ላይ ቆመው ነው፡፡

ከእንግሊዞች ጋር ሲስማሙ እኤአ በ1929 ላይ የተፈጥሮ እና የታሪክ መብት አላችሁ ተብለው በወርቅ ሳህን የቀረበላቸው ያ መብት ሊሆን የማይገባውና ማንም የማይቀበለውን ሰነድ መብታችን ነው ብለው ይዘዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከሱዳኖች ጋር ተሸሽገው እኤአ በ1959 የተፈራረሙት የአባይ ውሃ ሙሉ መብት የግብጽ እና የሱዳን ነው በሚል ነው፡፡

ይህን አይነቱ ሐሳብ ግን በተፋሰሱ ውስጥ ባሉ አገሮች ተቀባይነት የሌለው አመለካከት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ስምምነቶቹም ስምምነት ናቸው መባል እንዳይችሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ ውሃ አመንጪ አገራት ያልተሳተፉበት እና ያልመከሩበት ስምምነቶች ስለሆኑ በእነዚህ አገራት በፍጹም ሕጋዊ መሰረት የሌለውና ተቀባይነትን ያጣ ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህ ግብጾች በሌለ መሰረት ላይ ቆመው ስለሚደራደሩ ጽናታቸው የሚዘልቅ አይደለም፡፡ ውሃ አመንጪ በሆኑ አገሮች አስተሳሰብ አኳያ ሲታይ በዘመኑም በአስተሳሰቡም የተራራቀ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በማይሰራበት ሐሳብ ላይ ስለቆሙ ከዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ፖለቲከኞቻቸው፣ ተደራዳሪዎቻቸውም ሆኑ ጸሓፍቱና ጋዜጠኞቻቸው ይህንን አጢነው በመጠኑም ቢሆን ወደጋራ አቅጣጫ ሐሳባቸውን ቢያቃኑ የተሻለ ይሆናል የሚል አተያይ አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቆራጥነትና በጽናት ግድቡን ከመንግስት ጎን ሆኖ እየገነባ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን?

ዶክተር ያዕቆብ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም እንኳ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም በኑሮው ለውጥ እያመጣ ያለ ሕዝብ ነው፡፡ በእርግጥ አሁንም ቢሆን የልማት ጥማት ያለበት ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ድህነትም ያለበት ሕዝብ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የውሃም ሆነ በከርሰ ምድሯ ውስጥ ያለ የተፈጥሮ ሀብቷን በሚገባ አልምታ የሕዝቧ ኑሮ የተስተካከለ እንዲሆን የግድ ይላታል፡፡ ሕዝቧም የሚፈልገው ይህንኑ ነው፡፡ ሕዝቡ ወደፊት የተሟላ የኑሮ ደረጃ እንዲኖረው ኢትዮጵያ ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠቀም መቻል አለባት፡፡ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በልማት ስራ ላይ እንድታውል ደግሞ የሕዝቡ መተባበር የግድ ነው። ሕዝብ ልክ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያሳየውን ትብብርና ርብርብ ሌሎች የልማት ስራዎች ላይም መድገም ይኖርበታል፡፡

በመተባበር፣ በመተጋገዝ እንዲሁም በብሔራዊ ስሜትና በብሔራዊ አስተሳሰብ የጋራ ሀብቶቻችንን ማልማት ለኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ያለውም የልማት ስራ ጥሩና የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ አመላካች ነው፡፡ የበለጠ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ቆሞ በዚህ አቅጣጫ ወለም ዘለም ሳይባል መስራት ጠቃሚም ወሳኝም አካሄድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሁልጊዜ ትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር ያዕቆብ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

 አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You