የዓባይ ግድብ ለአፍሪካውያን ተጨማሪ የይቻላል መንፈስ ምንጭ ነው!

 የዓባይ ግድብ ዳግም ዓድዋ ተደርጎ የሚቆጠር፤ የይቻላልን መንፈስ ዳግም በአህጉሪቱ ሕዝቦች መንፈስ ውስጥ ማስረጽ የሚያስችል ተጨማሪ ታሪካዊ ክስተት ነው። መጪው ጊዜ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ብሩህ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ስለመሆኑም በብዙዎች ዘንድ ይታመናል::

በጨለማው የቅኝ ግዛት ዘመን አፍሪካውያን በዓድዋ ድል በፈነጠቀ ብርሃን፤ ዓይናቸውን ከፍተውና ተነቃቅተው፤ ከፍ ባለ መራራ ትግል፣ በብዙ መስዋእትነት ከባርነትና ባርነት ከፈጠረው ሁለንተናዊ ጉስቁልና ነፃነታቸውን መጎናጸፍ እንደቻሉ የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።

ዛሬ ላይ አሁን ባለው ትውልድ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እየተገነባ ያለው የዓባይ ግድብ፤ በዚህ ዘመን ለአህጉሪቱ ሕዝቦች ፈተና የሆነባቸውን ድህነትና ኋላቀርነት፤ አሸንፈው ለመውጣት ለሚያደርጉት ትግል ስኬት አዲስ የይቻላል መንፈስ ምንጭ እንደሚሆናቸው ይታመናል።

ግንባታው፤ በብዙ ተደራራቢ የውጭ ጫና ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ባላቸው አቅም፤ ሕዝባቸውን አስተባብረው የተፈጥሮ ሀብታቸውን በመጠቀም የመልማት ህልማቸውን እውን ማድረግ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን በተጨባጭ ማሳየት የሚያስችል፤ ለዚህም ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የሚያነሳሳ እና የሚያነቃቃ ነው።

በተለይም የአህጉሪቱ ሕዝቦች ዘመናት ካስቆጠረው፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች አንገታቸውን ከሚያስደፋቸው የድህነት አረንቋ ወጥተው የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን የሚያስችላቸውን ሁለንተናዊ አቅም ለመገንባት የሕዝብ አቅም የቱን ያህል አልፋ እና ኦሜጋ እንደሆነ ያመላከተ ነው።

ለዚህም በድህነታቸው የዓለም መሳለቂያ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሆኖ ለማየት ሲናፍቁት የነበረውን የዓባይ ግድብ፤ ዛሬ ላይ ሆኖ ያዩበት መንገድ በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላ፤ በብዙ ማስፈራሪያዎች፤ ዓለም አቀፍ ጫናዎችና ያልተገቡ እንቢታዎች የተሞሉ እንደነበሩ ማስተዋሉም ተገቢ ነው።

ኢትዮጵያውያን ከጉድለታቸው ቆጥበው የገነቡት ይህ ግድብ፤ ተስፋ ፣ ከተስፋ የሚቀዳ መደማመጥና መተባበር የቱን ያህል ሀገራዊ አቅም ሆኖ ታሪክ መሥራት እንደሚያስችል በተግባር ያሳየ ነው።

ባለንበት ዘመን ገዥ ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሳቤ ማንኛውም ሀገር በሌሎች መልካም ፈቃድ/በጎነት ወደሚፈልገው ልማት መጓዝ አይችልም። ከሁሉም በላይ ለመልማት ያሉ ሀገራዊ አቅሞችን መለየት፤ አቅሞቹን አቀናጅቶ መንቀሳቀስ፤ በሂደት ለሚያጋጥሙ ፈተናዎች /ተግዳሮቶች ራስን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት የሚጠይቅ ነው።

በተለይም አፍሪካውያን ከእርስ በርስ አለመተማመንና መገፋፋት ወጥተው፤ በብዙ የኑሮ ፈተናዎች ውስጥ ያሉ ሕዝቦቻችውን፤ ካሉባቸው ፈተናዎች ለመታደግ በመተባበርና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ የጋራ ራዕይ ፈጥረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። በጸረ-ቅኝ ግዛት ወቅት የነበረው የትብብር መንፈሳቸው ዳግም ሊታደስና ድህነትን አሸንፎ ለመሻገር ለሚያደርጉት ትግል ጉልበት ሊሆናቸው ይገባል።

ከራስ ወዳድነት ያለፈው በሰብአዊነት፤ በፍትሐዊነት እና በሕጋዊነት ላይ የተመሠረተው የቀደመው ዘመን የጋራ እሳቤያቸው፤ የነፃነት ትግሉን ፍሬያማ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ፤ እስከ ዛሬ ለዘለቀው የአህጉሪቱ ሕዝቦች የወንድማማችነት መንፈስ መሠረት እንደጣለ ይታመናል።

ዛሬ ላይ የዓባይ ግድብ እንደ ዓድዋው ድል፤ አፍሪካውያን የፖለቲካ ነፃነታቸውን ሙሉ ለማድረግ፣ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው ለመቆም ለጀመሩት ትግል ፍሬያማነት የይቻላል መንፈስ መፍጠር የሚያስችል፤ የዘመኑ የአፍሪካውያን ሆኖ የመገኘት ስኬት ምልክት ነው።

ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ራስን የመቻል፣ ከልመና የመገላገል፣ የልማት ምልክት እንደሆነ ሁሉ፤ ነገ ላይ ለብዙ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በተመሳሳይ መልኩ፤ ራስን የመቻል፣ ከልመና የመገላገል፣ የልማት ምልክት ሆኖ የሚያገለግል የጽናት ተምሳሌት ሆኖ የሚያገለግል ነው።

በተለይም ለሱዳን እና ለግብጽ ወንድሞቻችን የዓባይ ግድብ ግንባታ፤ በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሐዊነትን በማስፈን ለዘመናት የቆየውን አለመተማመን ለዘለቄታው በማስወገድ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር የሚረዳ፤ በሀገራቱ ሕዝቦች መካከልም አዲስ የትብብር የታሪክ ምዕራፍ መክፈት የሚያስችል ነው!

 አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You