የኢትዮጵያ ቦክስ ቡድን በሴኔጋል የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር እየተሳተፈ ነው

የኢትዮጵያ ቦክስ ብሔራዊ ቡድን በ2024 ፓሪስ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችለውን የማጣሪያ ውድድር በሴኔጋል ዳካር በማከናወን ላይ ይገኛል። ቡድኑ በሆቴል ተሰባስቦ የረጅም ጊዜ ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥፍራው ማቅናቱም ታውቋል።

የአፍሪካ ዞን የኦሊምፒክ የቦክስ ማጣሪያ ውድድር ከጳጉሜን 04/2015 ዓ.ም እስከ ነገ መስከረም 04/2016 ዓ.ም በሴኔጋል ዳካር እየተካሄደ ሲሆን፤ ለአፍሪካ የተሰጣት የተሳትፎ ኮታ 18 ነው። ኢትዮጵያም አፍሪካን ከሚወክሉ ሀገራት መካከል አንዷ ለመሆን የማጣሪያ ውድድሩ ላይ እየተካፈለች ትገኛለች። በዚህ የማጣሪያ ውድድር በወንዶች በ7 የተለያዩ ኪሎ ግራሞች ለፓሪሱ ውድድር ሀገራቸውን እና አፍሪካን ወክለው ለመሳተፍ የሚመረጡ ሲሆን ከእያንዳንዳቸውም አንድ አንድ አሸናፊዎች ለኦሊምፒኩ ብቁ ይሆናሉ። በሴቶችም በ6 የተለያዩ ክብደቶች 11 ሴት ቦክሰኞች ይፋለማሉ። በወንዶች 51 ኪሎ ግራም፣ 57 ኪሎ ግራም፣ 63ነጥብ5 ኪሎ ግራም፣ 71ኪሎ ግራም፣ 80ኪሎ ግራም፣ 92 ኪሎ ግራም እና ከ92 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያላቸውን ቦክሰኞች በማፋለም ለፓሪሱ ውድድር አፍሪካን የሚወክሉ ቦክሰኞች እንደሚለዩበት ይጠበቃል። በሴቶች ደግሞ በስድስቱ የተለያዩ ኪሎ ግራሞች 51ኪሎ ግራም፣ 54ኪሎ ግራም፣ 57ኪሎ ግራም፣ 60 ኪሎ ግራም 66 ኪሎ ግራም እና በ75 ኪሎ ግራም ውድድራቸውን በማድረግ የኦሊምፒክ ተሳታፊ የሚሆኑት የሚለዩ ይሆናል።

በማጣሪያ ውድድሩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞች በተለያዩ ኪሎ ግራም ከአራት ክለቦች ስድስት ቦክሰኞች ተመርጠው ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተው ወደ ውድድሩ ሥፍራ ማቅናታቸውን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ቡድኑ በፌዴሬሽኑ የውድድርና ስልጠና ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ብርሃኔ መሪነት ወደ ዳካር እንዳቀና ታውቋል። በሁለት አሰልጣኞች እየተመራ የማጣሪያ ውድድሩን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡድን የኦሊምፒክ ተሳትፎውን ሊያረጋግጥ የሚችል ዝግጅት ማደረጉም ታውቋል።

ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት ያላትን የኦሊምፒክ ተሳትፎ ለማስቀጠል የማጣሪያውን ውድድር በከፍተኛ ብቃት ማጠናቀቅ ይኖርባታል። በመሆኑም በሁለቱም ጾታዎች በስድስት ቦክሰኞች ተወክላ ማጣሪያዋን እያደረገች ነው። በወንዶች አራት ቦክሰኞች እና በሴቶች 2 ቦክሰኞች ተወክሎ ለፓሪሱ ኦሊምፒክ ማጣሪያቸውን እያከናወኑም ይገኛሉ። በ51 ኪሎ ግራም ፍትሐዊ ጥዑማይ፣ በ57 ኪሎ ግራም ፍቅረማርያም ያደሳ፣ በ63 ኪሎ ግራም አብርሃም ዓለም እና በ71 ኪሎ ግራም አቤኔዘር ዳንኤል ኢትዮጵያን በመወከል ማጣሪያቸውን እያደረጉ ነው። በሴቶች 51 ኪሎ ግራም ቤተልሄም ገዛኸኝ እና በ54 ኪሎ ግራም ሀገሬ እማኙ ኢትዮጵያን በመወከል የማጣሪያ ውድድራቸውን እያካሄዱ የሚገኙ የቡጢ ተወዳዳሪዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ፣ የቡድኑን ምርጫና ዝግጅት አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት ለብሄራዊ ቡድኑ የተመረጡት ቦክስኞች በዓመቱ እና በአራተኛው ዙር የቦክስ ክለቦች የማጠቃለያ ውድድር በነበራቸው ብቃትና ውጤት መመረጣቸውን አስረድተዋል። ከሌላ ጊዜ የተለየ እና ለአንድ ወር ከ15 ቀን የቆየ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልፀዋል። ቡድኑ በአንድ ላይ ተሰባስቦ ለ23 ቀናት በሆቴል የቡድን ስልጠናን እንዳከናወነ የጠቆሙት አቶ ስንታየሁ፣ ይህም ስፖርተኞቹ የተሻለ ጊዜና እረፍትን በመውሰድ ልምምዳቸውን በበቂ ሁኔታ በማድረግ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚረዳቸው አስረድተዋል።

የተመረጡት ቦክሰኞች የውድድር ልምድን ያካበቱና በርካታ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የቻሉ ናቸው። ብሔራዊ ቡድኑን በኡዝቤኪስታን በተካሄደው የዓለም ቦክስ ቻምፒዮና ወክለው በተሳተፉ ቦክሰኞች በመካተታቸው ለቡድኑ ውጤታማነት አስተዋጽኦ እንዳለውም ተጠቁማል። በተደረገው ዝግጅትም ቡድኑ ጥሩ የሥነ ልቦና እና የራስ መተማመን ደረጃ ላይ ይገኛል።

ለቡድኑ ከሆቴል መያዝ እስከ የጉዞ ሁኔታን ማመቻቸት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚጠበቅበትን ድጋፍና ትብብር እንዳደረገም ተጠቅሷል። ከዚህም በተጨማሪ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ቡድኑን ከማበረታታትና የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በማድረግ የድርሻቸውን እንደተወጡም ተገልጿል። ብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆንና የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የተጠቆመ ሲሆን፣ ለዚህም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚደረገውን ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ትኩረት በመሰጠት ከሌሎች ስፖርቶች እኩል መደገፍ ይኖርበታል ተብሏል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You