‹‹አንድ እፍኝ ፤ ለአንድ ልጅ››

እቴቱ ከበደ የአንድ ልጅ እናት ናት። የዘጠኝ ዓመት ልጇ ታማሚ እንደሆነ ትናገራለች። በዚህም ምክንያት በምትንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ ልጇን አዝላ መንከራተት ግድ ይላታል። በገጠማት ችግር እንደ እኩዮቸ በአቅሟ ሠርታ ኑሮዋን ለመምራት አልሆነላትም። ቀለቧንም ‹‹ቶራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በየወሩ ይሰፍርላታል። ብቸኛዋ እናት፤ ድርጅቱ ባይኖር የበለጠ የከፋ ሕይወት ለመምራት ትገደድ እንደነበር ትገልጻለች።

ወይዘሮ ብርሃኔ ቱራ፤ የሁለት ልጆች እናት ናት። የካንሰር ታማሚ ስትሆን፤ ባለቤቷም አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ኑሮን ለማሸነፍ ቸግሯቸዋል። በየወሩ አስቤዛ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሁም በዓል ሲመጣ ለአውድ ዓመት ማክበሪያ የሚሆን ድጋፍ ይደረግላቸዋል። እቴቱ እና ወይዘሮ ብርሃኔ፤ ድርጅቱ ባይደግፋቸው ኖሮ ሕይወት የበለጠ ፈታኝ እንደሚሆንባቸው በመግለጽ፤ ለሚደረግላቸው ሁሉ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ።

ጥቂት ስለ ቶራ

‹‹ቶራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በተለያዩ ምክንያት ለችግር የተጋለጡና ወላጅ ያጡ ሕጻናትን ተቀብሎ ፤ ግብረገብ፣ በትምህርት እና በሥነ ምግባር የታነፀ እንዲሁም ከራሱ አልፎ ለሀገሩ የሚጠቅም ዜጋ ማፍራትን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። በተጨማሪም ለችግር የተጋለጡ ሴቶች (እናቶች) የሙያ ስልጠና እና የገንዝብ ድጋፍ በማድረግ ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲችሉ ለማድረግ በማለም በወርሃ መጋቢት 2012 ዓ.ም በይፋ ሥራውን ጀመረ።

አቶ ሳምሶን ገብረእግዚአብሔር በድርጅቱ የፕሮጀክት ማናጀር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በማዕከሉ ውስጥ ያሉት ልጆች እንደ አንድ እህት እና ወንድም እንዲያድጉ ነው የሚፈለገው። ምንም እንኳን ይህን ማድረግ ከፍተኛ ወጪ ቢጠይቅም ከማህበረሰቡ ሳይነጠሉ ፤ ማንኛውም ወላጅ ለልጆቹ እንደሚያደርገው ለእነርሱም ነገሮች ተሟልቶላቸው እንዲያድጉ ይደረጋል። ‹‹ማሳደግ የፈጣሪ ድርሻ ነው። የእኛ የሰዎች ድርሻ ደግሞ ድጋፍ የማድረግ እና የማብቃት ሥራ ነው። ›› ይላሉ።

ሄቨን ጃዳ የፋይናንስ ማናጀር ሆና በድርጅቱ ትሠራለች። ቶራ ዘር ቀለም ሳይለይ ለሁሉም የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን በመግለጽ፤ ድርጅቱ በይፋ ከመመስረቱ በፊት አብሮ አደጎች በሆኑ በጎ ፍቃደኛ አባላት ለአስር ዓመታት ያህል የረድኤት ሥራችን ሰርተል። በነዚህ ዓመታት ለዘጠኝ ቤተሰብ የተቸገሩትን ልጆች በገንዘብና በቁሳቁስ እየደገፈ የመጣ የበጎ ፍቃደኞች ስብስብ መሆኑን ታስወሳለች። በወቅቱ እርዳታ ይደረግላቸው የነበሩ ልጆች ወላጆቻቸውን ጨምሮ እራሳቸውን እንዲችሉ ከተደረገ በኋላ ፤ በትምህርት በተሻለ ሥነ ልቦና እና በሥነ ምግባር ያደገ ዜጋ ለማፍራት ‹‹በቤት ውስጥ›› ለምን ልጆችን አናሳድግም በማለት ወደ ሥራ ተገብቶ ስብስቡ ወደ ድርጅትነት ማደግ ችሏል።

ቶራ ዛሬ ላይ

ድርጅቱ በአሁን ወቅት 15 ሕጻናትን ከመንግሥት በመረከብ እያሳደገ ይገኛል። ልጆቹን ለማስተማር የተለያዩ የድጋፍ አሰባሰብ መንገዶችን የሚከተል ሲሆን ፤ 64 ቋሚ አባላት አሉት። ከሁለት መቶ ብር ጀምሮ እስከ አምስት ሺህ ብር በየወሩ ከአባላቶቹ ይሰበስባል። እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች በጎ ፈቃደኛ ሆነው የተለያዩ አገልግሎት በመስጠት ድርጅቱን በማገዝ ላይ ናቸው። በተጨማሪም ማዕከሉን ጎብኝተው እና አይተው በተለያየ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ እንዳሉ የፕሮጀክት ማናጀሩ አቶ ሳምሶን ይናገራሉ።

ቶራ ለ30 እናቶች በየወሩ በቋሚነት የሚደግፍ ሲሆን፤ ከአስቤዛ በተጨማሪም የሕክምና ወጪያቸውን እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ድጋፍ ያደርግላቸዋል። እነዚህ 30 እናቶች 46 ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ልጆች ያሏቸው በመሆኑ፤ ለእነርሱም በየወሩ በቋሚነት ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ሌላው ለ15 እናቶች ከተረጂነት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ በየዓመቱ የሙያ ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ለሥራ ማስጀመሪያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እና ግብዓቶችን በማሟላት ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን አቶ ሳምሶን ያስረዳሉ።

‹‹በያዝነው ዓመት ከሁለት ልጆች በስተቀር ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ገቢ ናቸው። ልጆችን እንደራሳችን ልጆች ማሳደግ አለብን። ለልጆቻችን ማንኛውም ጥሩ ነገር እንደምንመኘው ሁሉ፤ እነዚህም ልጆች ተመርቀው ነገ ላይ የተሻለ ቦታ ተገኝተው ለሀገር የሚጠቅሙ እንዲሆኑ በማለም አቅማችንን አሟጠን የተሻለ ምግባር የተሻለ ትምህርት ፣ የተሻለ ሥነ ልቦና ይዘው እና በልጽገው እንዲያድጉ ስለምንፈልግ ነው የግል ትምህርት ቤት የምናስተምራቸው›› በማለት ሄቨን የድርጅቱን አላማና ራዕይ ታብራራለች።

የነገው ቶራ

ድርጅቱ ወላጅ ያጡ ጨቅላ ሕጻናትን ለመታደግ እንዲሁም በገንዘብ እጥረት ልጆቻቸውን ለመጣል የሚገደዱ እናቶች ቁጥርን ለመቀነስ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። ከነዚህ መካከል ቋሚ የገቢ ማስገኛ የዳቦ ቤት ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማዋል 20 ሚሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል። ብሩንም ቲኬት በመሸጥ እና በተለያየ መንገድ ለመሰብሰብ እየሠራ ይገኛል። በመሆኑም የሚጣሉ ሕጻናትን እንዲሁም በችግር ውስጥ ያሉ እናቶችን ከችግር ለማውጣት ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርጉ እና ‹‹አንድ እፍኝ ፤ ለአንድ ልጅ›› ብለው ያላቸውን ቢያመጡ በደስታ እንደሚቀበሏቸው ሄቨን ትናገራለች።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You