ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ሀገር ነች። ይሁን እንጂ በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሆኑት የዘርፉ ችግሮች የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል። በተጨማሪ ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲነገርለት የቆየው መዋቅራዊ የምጣኔ ሃብት ሽግግር እስካሁን ድረስ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆኗል። ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች ተተብትቦ የተያዘ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
በዘርፉ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የአጠቃቀም ፍትሃዊነት መጓደል፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት፣ የሥራ ባህል ደካማነት ጋሬጣ መሆናቸው ይነሳል። በዚህ ሳያበቃ ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበሩ ባለሀብቶች ከሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ችግሮች መካከል ውስጥ ዋንኞቹ መሆናቸውን በተለያየ ሲናገሩ ይደመጣል።
ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት ከአቅማቸው በታች እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከሰባት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ያለው ሲሆን በቀጣይ 10 ዓመታት ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ መያዙን እነዚሁ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል በሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል ነው። በተጨማሪም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻል፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ የገቢ ምርቶችን የመተካት አቅምን ማጎልበት ናቸው።
ንቅናቄው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር እንደሆነ ታምኖበታል። ሀገሪቷ ያላትን ትልቅ የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር የተጀመረው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ፤ ምሰሶዎች ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ ናቸው።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችና በመፍጠር ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን መጨመርና እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ወጪን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ዋና ዋና ውጤቶች ናቸው።
ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአንድ ዓመት ጉዞ አስመልክቶ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በተጀመረበት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ50ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በማሳተፍ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ባለሀብቱንና አመራሩን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህም ዘርፉ እንዲነቃቃ አግዟል። ሥራ አቁመው የነበሩ ከ352 በላይ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል። 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል። አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል።
ክልሎች በኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ላይ ተመስርተው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄን ተግብረዋል፤ ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ውጤታማ ሥራ መሥራት እንዳስቻላቸውና በንቅናቄው ትግበራም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚኖረው ውጤታማነት ትልቅ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትና ቀልጣፋ አሠራርን ለማስፈን የሚረዱት የአንድ መስኮት አገልግሎት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። የማምረቻ ማዕከላት (ሼድ) ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል።
ንቅናቄው አምራቾች በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ያመርቱ እንደነበርና ለሌሎች ፋብሪካዎች ምን ያህል ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት መረጃ አልነበረም። ንቅናቄው ይህ መረጃ እንዲታወቅ በማስቻሉ በአምራቾችና በገዢዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪዎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አግዟል። በተጨማሪም ቀደም ሲል የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝና በትግበራውም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ እንደሆነ አምራቾች ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2015 የበጀት ዓመት አፈፃፀሙን በተመለከተ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በበጀት ዓመቱ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በተከናወኑ ሥራዎች ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት ተተክተዋል። የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምም 55 በመቶ መድረስ ችሏል። በንቅናቄው ትግበራ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በምርት አቅርቦትና በተኪ ምርቶች ምርት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ከመመዝገባቸው በተጨማሪ የአምራች ዘርፉ ተዋንያን የገበያና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትስስር እንዲኖራቸው፣ ግንዛቤያቸው እንዲጎለብትና በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በመደገፍ ረገድ የተሻለ ሥራ ተከናውኗል።
የ‹‹ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር›› ኩባንያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ቡልቻ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በአምራቾች መካከል ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት በአምራቾች መካከል የሚኖር ትስስር የግብዓትና የምርትና ግብይት እንዲሁም የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል። ይህም ለዘርፉ አዲስ አሰራርና አቅም ይፈጥራል። ተጨማሪ አምራቾች በአምራች ዘርፉ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ንቅናቄውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አቶ ቢኒያም ይናገራሉ።
በኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን የ‹‹ዋንኮ ቡና›› ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ታደለ ንቅናቄው ምርትን ለመጨመር፣ አዳዲስ ምርቶችን ለማቅረብ፣ የምርት ደረጃዎችን ለማሳደግ እንዲሁም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሥራ ትስስር ለመፍጠር እድል እንደፈጠረላቸው ያስረዳሉ። ‹‹ንቅናቄ የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ፣ በችግሮች ላይ በጋራ ለመወያየት እና ምርቶችን ለማስተዋወቅ እና ድጋፍ ለማግኘት የሚያግዝ በመሆኑ ንቅናቄው ያስገኛቸውን ውጤቶች የበለጠ በማጠናከር የአምራች ዘርፉን ችግሮች ለማቃለል የሕዝብና የሀገር ጥቅምን በማስቀደም ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል። በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በምርቶች ላይ እሴት ጨምረው እንዲያቀርቡ ሊበረታቱ ይገባል። ለዚህም አምራቾች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው በዘርፉ ችግሮች ዙሪያ መምከርና፣ መንግሥትም የዘርፉ ችግሮች የሚቃለሉበትን አሰራሮች ማመቻቸት ይጠበቅበታል›› ይላሉ።
የ‹‹ሀብቴ ጋርመንት›› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብተሥላሴ ገብረክርስቶስ በበኩላቸው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ቀላል ግምት የሚሰጠው ርምጃ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ንቅናቄው በተለይም ለዘርፉ ያለውን የተዛባ አመለካከት በማስተካከል ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ንቅናቄው መተግበር ከጀመረ ወዲህ አዎንታዊ የግንዛቤ ለውጦች ታይተዋል። ብዙ የዘርፉ ተዋንያን ስለንቅናቄው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ንቅናቄው የአምራቾችን ምርታማነት ለመጨመር የሚያስችሉ አሠራሮችን ያካተተ በመሆኑ ክፍተት የሚታይባቸውን ክፍሎች በመደገፍ የተሻለ ምርታማ እንዲሆኑ ያግዛል። እነዚህ ሁሉ ርምጃዎች የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ትግል ጥሩ ግብዓቶች ሆነው ያገለግላሉ። በአጠቃላይ ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንደተቀመጡበት የንቅናቄው የአንድ ዓመት ጉዞ አሳይቷል።
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን በእጅጉ እየፈተኗት ያሉት ዐበይት ምጣኔ ሀብታዊ ተግዳሮቶች የሥራ አጥነት እና የምርቶች ዋጋ ንረት ችግሮች መሆናቸውን የሚጠቁሙት አቶ ሀብተሥላሴ፣ ችግሮቹ የሚፈቱት በአምራች ዘርፉ ስኬት እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹አንድ ባለሙያ ወይም የሥራ ኃላፊ አምራች ኢንዱስትሪውን ሲደግፍ ሕይወቱን እንደሚያስተካክል አድርጎ ማሰብ መቻል አለበት። የሥራ አጥነትም ሆነ የኑሮ ውድነት ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍና ችግሮቹን መፍታት ሲቻል ነው። ለዚህ ደግሞ ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ንቅናቄን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል›› በማለት ይገልፃሉ።
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና በኢባዳን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ዘመቻው ምን ለውጥ እንዳስገኘ በየጊዜው ክትትል እያደረጉ መገምገም እንደሚያስፈልግና የዘርፉ ችግሮች መዋቅራዊ የሆኑ መፍትሔዎችን የሚፈልጉ በመሆናቸው ከአጭር ጊዜ ይልቅ ዘላቂ ለውጥ ለሚያመጡ የመፍትሔ አማራጮች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ አንድ ሀገር ባላት እምቅ ሀብት ላይ ተመስርታ ማምረት እንደሚገባት የሚጠቁም መርሃ ግብር እንደሆነ ያስረዳሉ።
‹‹በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው፣ ባለሀብቶቻቸውና የሌሎች ሀገራት ባለሀብቶችም በሀገራቸው እንዲያመርቱ ጥረት ያደርጋሉ። የኢትዮጵያም ጥረት ከዚህ የተለየ አይሆንም። ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ሲባል ሀገራዊ የማምረት አቅሟን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ተግባሯን ከማጠናከር ጋር ትስስር አለው›› ይላሉ።
እንደርሳቸው ገለፃ፣ ‹ለማምረት ምን ያስፈልጋል?› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። የግብዓት እጥረት የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ከግማሽ በታች በሚሆነው አቅማቸው እንዲያመርቱ ስላስገደዳቸው የማምረት አቅምን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን ማመቻቸት ይገባል። ንቅናቄው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ በተሻለ አቅም እንዲሰማሩ ያስችላቸዋል። በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ እና በተቀናጀ ጥረት ከታገዘ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትንም ለማቃለል አማራጭ መፍትሔ መሆን ይችላል።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማሳካት የያዘችውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ሚና እንደሚኖረው የታመነበት ይህ ንቅናቄ ዓላማውን እንዲያሳካ የተቀናጀ ተግባር እንደሚያስፈልግ ዶክተር ሞላ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ለመርሃ ግብሩ ስኬት የመንግሥት፣ የባለሀብቱና የሕዝቡ ድርሻ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል። ንቅናቄው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብና ለዘላቂ መፍትሔ አጋዥ እንዲሆን በተገቢ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መደገፍ ይኖርበታል።
መንግሥት ንቅናቄውን እንዲሁም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ምቹ የኢንዱስትሪ ከባቢን መፍጠር ይጠበቅበታል። የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመደገፍ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል። መንግሥት ማበረታቻዎችን ሲያደርግም ማበረታቻዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ማረጋገጥ አለበት። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የመርሃ ግብሩን አፈፃፀም እየተከታተለና እየገመገመ ማስተካከያዎችን በማድረግ የአመቻችነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል። ባለሀብቶችም አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር አቅማቸውን ማሳደግና ከመንግሥት የሚደረጉላቸውን ማበረታቻዎች በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚኖርባቸውም ዶክተር ሞላ ይናገራሉ።
ኅብረተሰቡ ስለሚኖረው ሚና ደግሞ ‹‹ከሀገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ ለውጭ ምርቶች የተሻለ ትኩረትና ፍላጎት የመስጠት አመለካከትን መቀየር ይገባል። የሀገር ውስጥ ምርቶችን በተጠቀምን ቁጥር የአምራቾቹን አቅም እያጎለበትን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል›› ይላሉ።
‹‹መንግሥት የጀመረው ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ንቅናቄ ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ተግባርን ከማጠናከር ርምጃ ጋር ትስስር አለው›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፣ ‹‹ለማምረት ምን ያስፈልጋል?›› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት ከተሰጠና ንቅናቄው በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ እና በተቀናጀ ጥረት ከታገዘ የአምራቾችን ችግሮች ለማቃለል አማራጭ መፍትሔ መሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ።
ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማጎልበት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለልና ተወዳዳሪ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ብሎም የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት ያስችላል ተብሎ የታመነበት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በእስካሁን ትግበራው ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ያሳየ በመሆኑ በቀጣይም በከፍተኛ ትኩረት ሊከናወን የሚገባው አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሆነ የአምራች ዘርፉ ተዋንያን አሳስበዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም