የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሀገር ምጣኔ እድገት ውስጥ የላቀ ድርሻ እንዲኖረው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ከተለዩት አምስት የኢኮኖሚ ምንጭ ምሶሶዎች(ፒላሮች) አንዱ ነው። ዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለመጨመር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል።
ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ሥራ ሲሠራ ቢቆይም ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ ተከስተው የነበሩ ሁከቶች፣ግርግሮችና ጦርነት እንዲሁም የዓለም ስጋት ሆኖ ያለፈው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ለዘርፉ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ማነቆዎች እንደነበሩ አይዘነጋም። የነበሩትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሲከናወኑ ስለነበሩ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን እንዲሁም የቀጣይ ተግባራትን በተመለከተ ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፦ ወደሌሎች ጥያቄዎች ከመግባታችን በፊት ስለኢንዱስትሪ ስናወሳ መገለጫዎቹ ምን እንደሆኑ ቢገልጹልን?
አቶ ታረቀኝ፦ ኢንዱስትሪን አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ትላልቅ የሆኑ ተቋማት ማለት ብቻ አይደለም። ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ሆነው ሊሰሯቸው የሚችሉ ሥራዎችን መሠረት ያደርጋል። እንጀራ አዘጋጅቶ ለገበያ ማቅረብ፣የብረትና የእንጨት ውጤቶች፣እንደ ባህል ሽመና እና እደጥበብ ያሉ ሥራዎች ሁሉ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። ከግንዛቤ ማነስ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን አሳንሶ የማየት ሁኔታ ይስተዋላል። ነገር ግን እሴት ጨምረው ማንኛውንም ምርት የሚያመርቱ ሁሉ ለሀገር ምጣኔ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው። ትልቅ ነው የሚባለው ኢንዱስትሪ የትናንሾቹ ኢንዱስትሪዎች ስብሰብ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። ለአብነት አንድ መኪና አምራች ኢንዱስትሪ የመኪናውን ክፍል ከሚያመርቱ የተለያዩ አነስኛ አምራቾች በሚያገኘው ግብዓት ነው መኪና አምርቶ ለገበያ የሚያቀርበው።
አዲስ ዘመን፦በአጠቃላይ ኢንዱስትሪዎችን በስንት መክፈል እንችላለን?
አቶ ታረቀኝ፦ኢንዱስትሪዎች በአራት ይከፈላሉ። አንደኛው አዲስ ሥራ የሚፈጥሩ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች አሉ። እነዚህ በመጠናቸው አነስ ብለው የሥራ ፈጠራ የታከለበትና ለፈጠራቸው እውቅና ወይንም ፓተንት ያላቸው ናቸው። ሥራውም በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ውስጥ ነው የሚካተተው። ቀጥሎ ያለው ደግሞ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ነው። ይሄም አነስ ያለ፣የሥራ እድል የሚፈጥር፣ ምርት ያለውና ለገበያ የሚያቀርብ ነው። ሦስተኛው መካከለኛ ተብሎ ነው የሚጠራው። ከፍተኛው ወይንም ትልቁ አራተኛ ደረጃ የሚይዘው ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ የአምራች ሀገር አይደለችም የሸማች ሀገር ናት። በመሆኑም ማንኛውም ሰው በቤቱ ውስጥ በማምረት ሊንቀሳቀስ ይገባል። መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን አምራች የመደገፍ ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ውስጥ ዘርፉ በምን ሁኔታ እያለፈ እንደመጣ ቢያስታውሱን፤
አቶ ታረቀኝ፦ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ታሪክ በተለይ በንጉሱ ሥርዓት የጎጆ አንዱስትሪን የሚያበረታታ ነበር። በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ደግሞ የምርት ሂደትን ሊያቀጭጩ የሚችሉ በተለይም ከሶሻሊስት አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ አምራችነት እንዳይኖር፣ኢንዱስትሪው እንዳይሰፋ የሚያደርግ፣በጀትንና ፋይናንስን የሚወስን ሁኔታ ነው የነበረው። በዚህ ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪው አላደገም። በኢህአዴግ አገዛዝ ደግሞ እራሱን የቻለ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ነበር። ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ጋር በተያያዘ ሥራዎች ተሰርተዋል። ጥሩ የሆነ መነቃቃትም ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ አገዛዙ የተለያየ የፖለቲካ ተቃውሞ በገጠመው ጊዜ ኢንቨስትመትን የማውደም ሁኔታ በስፋት ተስተውሏል። በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮች ወይንም ባለሀብቶች ደህንነት እንዳይሰማቸው አድርጓል። አጠቃላይ የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ አምራችነትን የሚያወድምና የሚያጠፋ ነው የነበረው። ይህም አምራች ኢንዱስትሪው እንዲቀዛቀዝ አድርጓል። ከሀገራዊ ለውጥ በኋላም ዘርፉን የሚጎዱ ነገሮች ተከስተዋል። በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የአገዋ ገበያን ለመጠቀም የነበረውን እንቅስቃሴ አስቀርቷል። አገዋን ተስፋ በማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በጦርነቱ የገበያ መዳረሻቸው ተስተጓጉሏል። ይህም በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ያለው ሽግግር ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ታረቀኝ፦ አሁን ላይ የሀገራችን ስልተ ምርቷ መሠረት ያደረገው ግብርና ነው። የሀገሪቱን ጂዲፒ ድርሻ የያዘው ግብርና ነው። አገልግሎት ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል። ኢንዱስትሪ በጂዲፒ ከሰባት በመቶ ያለበለጠ ድርሻ ነው ያለው። ይሄ በጣም ዝቅተኛ ነው። አሁን ላይ ዝቅተኛ ቢሆንም ዘርፉ ለማደግ ምቹ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ለዚህም እንደምቹ ሁኔታ ከሚወሰዱት አንዱ በኢትዮጵያ ሰፊ መሬት መኖሩ ሲሆን፤ ይሄም ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያስችላል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሰፊ ቁጥር ያለው አምራች ኃይል መኖሩ ነው። የመንግሥት ፖሊሲ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ይገለጻል። ለዚህም መገለጫው በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተወሰደው እርምጃ ነው። በመጀመሪያው ዙርም ሆነ በሁለተኛው ዙር የማሻሻያ እርምጃ አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሥራውም ተግባራዊ እየሆነ ነው። ይሄ ሁሉ እንቅስቃሴ ወደፊት አምራች ሀገር ለመሆን የሚያስችል ነው። እንደሀገር በተቀረፀው የአስር አመት መሪ እቅድ ኢንዱስትሪ በጂዲፒ 17 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ነው። ይህንን ከስኬት ለማድረስም መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። በዚሁ መሠረትም መንግሥት በተመረጡ አምስት ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። ዘርፎቹም ግብርና፣ኢንዱስትሪ፣ቱሪዝም፣ማዕድንና አይ ሲቲ ናቸው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በነዚህ ላይ በትኩረት እየተሰራ ቢሆንም በሂደት ግን ኢንዱስትሪው የመሪነት ሚና እንዲኖረው ይፈለጋል። መዋቅራዊ ሽግግሩ ኢንዱስትሪ መር እንዲሆን የመንግሥት ፍላጎት ነው።
አዲስ ዘመን፦ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የመሥሪያ ቦታና ሌሎችም ድጋፎች እንደማያገኙ ቅሬታ ሲያነሱ ይሰማል። እዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ታረቀኝ፦ የድጋፍ ማዕቀፍን በተመለከተ፤የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ለኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ ተደርገው የሚወሰዱት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም፣ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነ እነዚህን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚመራ ተቋም አለ። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተባለው ተቋም ነው ድጋፍ የሚያደርግላቸው። የድጋፍ ማዕቀፎቹም ከመደራጀት ጀምሮ የምርት ሂደት፣ስለሚጠቀሙበት የማምረቻ መሣሪያ፣ያላቸውን የክህሎት ክፍተት የሚሞላ ስልጠና በመስጠት ሲሆን፣ስልጠናው አዲስ ወደ ሥራው የሚገቡና በሥራ ላይ የሚገኙትን ያካትታል። ሁለተኛው ድጋፍ የሥራ መሣሪያ አቅርቦት ነው። ይሄም በሊዝ ፋይናንስ ተቋም አማካኝነት ነው ድጋፍ የሚደረገው። አምራቾቹ በሊዝ ፋይናንስ ያገኙትን የሥራ መሣሪያ እየተጠቀሙ ለመሣሪያው ክፍያ የሚፈጽሙበት አሠራር ነው። ሌላው የፋይናንስ አቅርቦት ድጋፍ ነው። በዚህ ረገድም በ2015 በጀት ዓመት ከልማት ባንክ ወደ አራት ቢሊዮን ብር ነው ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ቀርቧል። ከዚህ ውስጥ ወደ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለማምረቻ መሣሪያ የዋለ ሲሆን፣አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ደግሞ ለሥራ ማስኬጃ ጥቅም ላይ እንዲውል የቀረበ ነው። በዚህ መልኩ በመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በሚደረግ ስምምነትም ድጋፍ የማድረጉ ተግባር የተጠናከረ ነው። ለምሳሌ ከዓለም ባንክ ጋር 25 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተገኝቷል። ድጋፉ በተለያየ መንገድ እየተደረገላቸው ቢሆንም በቂ ነው ተብሎ አይታመንም። አምራች ኢንዱስትሪዎቹ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ የማያገኙበት ሁኔታ አለ። ቅሬታም ይነሳል። በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል። አለበለዚያ አነስተኛ መካከለኛውን ኢንዱስትሪ በሚፈለገው ደረጃ አምራች እንዲሆን ማድረግ አይቻልም። ይህ ካልሆነ ደግሞ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን እንደሀገር ማፍራት እንችልም።
አዲስ ዘመን፦ ኢንዱስትሪዎች አምራች እንዲሆኑ ምን ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ?
አቶ ታረቀኝ፦ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ትስስር መፍጠር ነው። የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሥራ አንዱ አምራቾች ለማምረት የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። ትስስሩ በአራት መንገድ ነው የሚገለጸው። አንዱ ግብርና ነው። ምግብን በተመለከተ የግብርና ምርትን ተጠቅሞ የተለያዩ የታሸጉ ምግቦችን ማዘጋጀት ነው። ግብአቱንም ከኅብረት ሥራ ማህበራት ወይንም ከገበያ ላይ እንዲያገኙ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ። የቆዳ ውጤቶችን የሚያዘጋጁትም እንዲሁ በተመሳሳይ ትስስር ይፈጠርላቸዋል። የጎንዮሽ በሚባለው የትስስር ዘዴም እርስ በርሳቸውም አንዱ ለሌላው የሚፈልገውን እንዲያቀርብ በማድረግ ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ይደረጋል። የገበያ ትስስር ላይም እንዲሁ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ክትትሉና ድጋፉ አለ።
አዲስ ዘመን፦ በሀገራዊ ምጣኔ እድገት ላይ አምራች ኢንዱስትሪው እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ታረቀኝ፦ አምራች ኢንዱስትሪው እንዲጠናከር መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ኢንዱስትሪው በጂዲፒ ውስጥ ያለው ድርሻው አነስተኛ ነው። ሌላው ደግሞ የገበያ ድርሻ ማሳደግ ነው። አሁን ባለው መረጃ የሀገራችንን ምርት በመጠቀም ረገድ የገበያው ድርሻ 38 በመቶ ነው። ይሄ የሚያሳየው 62 በመቶ እየተጠቀምን ያለው ከሌሎች ሀገሮች ተመርቶ የሚገባውን ነው። ይሄ ደግሞ ቀጥታና ቀጥታ ባልሆነ ንግድ ውስጥ አልፎ የመጣ ሊሆን ይችላል። ከሸማችነት ወደ አምራችነት መሸጋገር ግድ ይላል። ራሳችንን ያልቻልንባቸው ብዙ ነገሮች ይቀሩናል። የምንጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎች ሳይቀሩ ከውጭ የሚገቡ ናቸው። ስለዚህ ተኪ ምርቶች ያስፈልጉናል። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ታምርት ወደ ሚል ንቅናቄ ውስጥ የገባነው። ሌላው የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ ነው። የአምራች ኢንዱስትሪው ዋና ግብም ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማስቻል ነው። በአሁኑ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ፣ከቴክኒክና ሙያ በተለያየ ዘርፍ የሰለጠኑ ግን ሥራ የሌላቸው ዜጎች በርካታ ናቸው። ለነዚህ ዜጎች ሥራ ፈጣሪ መሆን የሚችለው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው። በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ወደ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲመቻችት ታቅዷል። በ2015 በጀት ዓመት በዘርፉ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው 225ሺ ዜጎች ናቸው። በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ለ327ሺ ዜጎች በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ነው የታቀደው። ምርታማነትን በተመለከተም፤ምርታማ አይደለንም። አንድ ሰው በቀን ስንት ያመርታል? አንድ ኢንዱስትሪ በቀን ስንት ያመርታል?ብለን ስናይ የማምረት አቅማችን ከግማሽ የበለጠ አይደለም። ይሄንን ማሻሻል ያስፈልጋል። እንዲህ ያሉ የማሻሻያ ሥራዎች ለመሥራት የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ስለሚያስፈልግ አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አዘጋጅተናል። የኢንዱስትሪ ፖሊሲውን ማሻሻል ያስፈለገው በዘርፉ ላይ ለሚሰማራው ምቹ ከባባዊ ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ሌላው ደግሞ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ነው። በ2014 እና 2015 ብቻ ወደ 18 የሚሆኑ የአሰራር ሥርዓቶች ተለይተዋል። የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር ተገብቷል። አንዱ የተኪ ምርት ስትራተጂ ነው። በዚህም ወደ 96 የምርት አይነቶች ተለይተዋል። በመቶኛ ስንት ላይ እንደምንገኝ፣እነዚህን በስንት ዓመት ልንለያቸው እንደምንችል፣ከመንግሥት የሚያስፈልጉ የድጋፍ ማዕቀፎችን ያካተተ አንድ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነው። ይሄ ትልቅ መነሳሳት ነው። በዚህ የተኪ ምርት ሥራ እንቅስቃሴ ሥራው አምና ነው የተጀመረው። አንድ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። ለሠራዊቱ የሚሆን አልባሳት ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ማቅረብ ተችሏል። በዚህም ለግዥ ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር ይወጣ የነበረውን ወጪ ማዳን ተችሏል። ትልቅ ልምድ የተገኘበትን ይሄን ተሞክሮ ለማስፋት ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። በሁለተኛ ደረጃ በተኪ ምርት ጥሩ ውጤት እየታየበት ያለው ለቤትና ለቢሮ የሚሆኑ ቁሳቁሶች(ፈርኒቸር) ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ነው። በተለይ በ2016 በጀት ዓመት በከፍተኛ ደረጃ በርብርብ የሚሰራበት ዘርፍ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም የእንጨትና ሌሎች ግብአቶችን በሀገር ውስጥ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። የሰው ኃይልም ቢሆን በስፋት ስላለ ምርቱን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል አቅም አለ። ሌላው ከምግብ ጋር የተገናኘ ሲሆን፤ ይሄም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። ከግብርናው ጋር ስለሚተሳሰር ምቹ ነው። ከዚህ ቀደም በስፋት ከውጭ በግዥ ይገባ የነበረ ፓስታ፣ማካሮኒና ሌሎችም የታሸጉ ምግቦች በሀገር ውስጥ እየተተኩ ነው። አልሚ ምግቦችን የማቅረብ አቅምም ተፈጥሯል። ለዓለም ምግብ ድርጅት (ዎርልድ ፉድ ፕሮግራም) እያቀረብን ነው። ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ምግብ በሀገር ውስጥ ማቅረብ እየተቻለ ነው። ወደፊት በልዩ ትኩረት አጠናክረን ከሠራን የገበያ ድርሻችንን ማሳደግ እንችላለን። አሁን ላይ ያለውን 38 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማድረስ ነው እቅድ ተይዞ እየተሠራ ያለው። በጣም መሥራት ይገባል። ለውጭ ገበያ የምናቀርበው የውጭ ምንዛሪ ስለሚያስፈልገን ነው እንጂ ትርፍ አምራች ስለሆንን አይደለም። እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪም በቂ ነው የሚባል አይደለም። በብዛት ለውጭ ገበያ እየላክን ቢሆንም ነገር ግን እያገኘን ያለው ገቢ ከአራት ቢሊዮን ዶላር የበለጠ አይደለም። ከዘርፉ የተገኘው ከጂዲፒ አኳያ እንዲሁ በቂ አይደለም። ኢኮኖሚያችንን እየደገፈ አይደለም። ዘላቂ ተወዳዳሪ የሚያደርገን ኢንዱስትሪው በመሆኑ በግብርናው የሚመራው ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪው መሸጋገር ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ በ2015 ለዜጎች የተፈጠረው የሥራ ዕድልና በ2016 የተያዘው እቅድ ዘርፉ ከሚጠበቅበት የሥራ እድልን ከመፍጠርና ካለው ሥራ ፈላጊ አኳያ በቂ ነው?
አቶ ታረቀኝ፦ በእቅድ የተያዘው ለሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ነው። በአነስተኛውና በመካከለኛው ኢንዱስትሪ ላይ ወደ 327ሺ መፍጠር ከቻልን አምና ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ላይ ነው የሚደመረው። በዓመት በመቶሺ የሥራ ዕድል መፍጠር ከቻልን በሂደት ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እናዳብራለን።
አዲስ ዘመን፦ በሀገር ውስጥ ተመርተው የሚቀርቡ ምርቶች ውድ ከመሆናቸውም ሌላ የጥራት መጓደል ጉዳይም ይነሳል። ግብአቱም ፣ምርቱም፣ የሰው ጉልበቱም በሀገር ውስጥ በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ ሲገባው ለምን የቅሬታ ምንጭ ሆነ?
አቶ ታረቀኝ፦ አንድ ምርት ሊያድግ የሚችለው በጥራት መቅረብ ሲችል እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ከጥራት አንጻር የተነሳው ጥያቄ አግባብ ነው። እኛም የምንቀበለው ነው። ምክንያቱም የኢንዱስትሪ ምርቶች በጥራት ማረጋገጫ ቤተሙከራ ውስጥ በፍተሻ እንዲያልፉ ይደረጋል። ሆኖም በሚባለው ደረጃ የኢትዮጵያ ምርቶች ጥራታቸው የተጓደለ ነው ለማመን እቸገራለሁ። አይሶ(ISO) የሚባለው የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸው ነው ለተጠቃሚው እንዲቀርቡ የሚደረገው። በጥራት ማረጋገጫ ፍተሻ ውስጥ የምርቶች ማከማቻ ክፍሎች ሳይቀር ነው በመፈተሽ፣የተለያዩ ሂደቶች እንዲያልፍ ነው የሚደረገው። በዚህ ሂደትም ቢያንስ የመጨረሻውን አስገዳጅ ሂደት ያለፈ ምርት ነው ለገበያ የሚቀርበው። በእርግጥ ክፍተት የለም ማለት አይደለም። በቱርክና በቻይና የተሰሩ ለማስመሰል የሚደረግ ጥረት አለ። የሌላ ሀገር ታግ የሚደረግባቸው በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርቶች ናቸው። ይሄ በህብረተሰብ ላይ ያለውን አመለካከት ያሳያል። የኛ ምርት ጥራት የለውም የሚለው ከሰው አእምሮ ውስጥ ባለመውጣቱ የተፈጠረ ችግር ነው። የግንዛቤ ማስጨበት ሥራ ያስፈልጋል። ሆኖም ከጥራት ጋር በተያያዘ ችግር የለም ብሎ ሙሉ ለሙሉ መናገር አይቻለም። ጥራት ከክህሎት የሚመነጭና በሂደት የሚታይ በመሆኑ የበለጠ ጥራትን እያረጋገጡ መሄድ ይጠይቃል። ስለጥራት ስናነሳ ምርቱ ብቻ ሳይሆን ግብአቱም በጥራት መቅረቡን ማረጋገጥ ይገባል። ተወዳዳሪነትን መጨመር የሚቻለው በጥራት በማምረት በመሆኑ የጥራት ንቅናቄ ሥራ ያስፈልጋል። ሚኒስቴር መሥሪያቤቱም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል። ከዋጋ ጋር ተያይዞ ለተነሳው፤በሀገራችን ትልቁ ችግር የዋጋ ጭማሪ ጉዳይ ነው።
አንዳንዴ ከማምረቻ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ይደረጋል። ነገር ግን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በስፋት ይስተዋላል። ይሄ አይነቱ የዋጋ ጭማሪ ፍትሐዊ አይደለም። ስለዚህ ሊታረም ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ከተቋማዊ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ በየጊዜው መቀያየር መኖሩ የዘርፉን እድገት ጎድቶት ይሆን ?
አቶ ታረቀኝ፦ እውነት ነው አደረጃጀት እንደ ችግር ይነሳል። መዋቅር ሲቀያየር መረጋጋት አይፈጠርም። ይሄ ደግሞ ሠራተኞችም ሆኑ ኢንዱስትሪዎች ተረጋግተው እንዳይሰሩ ያደርጋል። አደረጃጀት ሲታጠፍና ሲዘረጋ የሚወስደው ጊዜ አለ። የሚበላው በጀት አለ። ነገር ግን በ2014ዓም በአዋጅ 2012/63 ላይ ተመስርቶ የተደራጀው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አደረጃጀት ሊያሰራ የሚችል ነው። በተለይም ሚኒስቴር ከንግድ ጋር በነበረበት ወቅት በአብዛኛውን ጊዜውን ያውል የነበረው ከንግድ ጋር በተያያዘ ነው። የንግድ ሥራ ደግሞ በባህሪው የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ያለው በመሆኑ ቁጥጥርና ክትትል ይፈልጋል። በዚህ ምክንያት ለኢንደዱትሪው ዘርፍ ይሰጥ የነበረው ትኩረት አናሳ ነው። 2014ዓም ላይ መልሶ ከተደራጀ በኋላ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትኩረቱ ለኢንዱስትሪ ሆኗል። በዚሁ መሠረትም የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ክለሳ፣19 ስትራተጂዎችን የማዘጋጀት፣የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሥራዎችን መሥራት ተችሏል። ለምሳሌ የኢትጵያ ታምርት ንቅናቄ ብንወስድ ንቅናቄውን ስንጀምር እንደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተወያይተናል። የንቅናቄው ዋና ዓላማ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ችግር በቅንጅት መፍታት መሆን አለበት በሚል የጋራ መግባባት ላይ ደርሰን ነው ወደ ትግበራ የገባነው። ዘርፉ ተያያዥ ነገሮችን ይፈልጋል። መሬት አቅርቦት ላይ ከክልሎች፣ፋይናንስ አቅርቦት ከፋይናንስ ተቋማት ፣ ከግብአት አኳያ ከግብአት አቅራቢ ድርጅቶች፣ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር መሥራት ያስፈልጋል። የዘርፉን ማነቆዎች በቅንጅታዊ አሰራር መፍታት ብለን የጀመርነው ከዚህ መዋቅር ጋር የተያያዘ ነው። ይሄን በመሥራታችን ምን አገኘን ስንል ደግሞ፤ቅንጅቱ ተሻሻለ፣ ከመሠረተ ልማትና ከፋይናንስ አቅራቢዎች፣ከትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ ሥራ እየተሻሻለ መጣ። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በፋይናንስ፣በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና በተለያየ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ 352 ተከፍተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። በተጨማሪም አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያስፈልገናል የሚል የእይታ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክን ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በራሳቸው መምራት ችለዋል። ስለዚህ ከባለሀብቱ ጋር መገናኘትና የሚቆጠሩ ችግሮችን መፍታት ጀምረናል። ይሄ ሁሉ ውጤት ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ የተገኘ ፋይዳ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ የመሬት አቅርቦት ጨምሯል። በዚህ ሁለት ዓመት ክልሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት እያቀረቡ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም በዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት ማነቆ በሰፊው ይነሳ ነበር። አሁን አሰራሩ ተሻሽሏል። በ2015 በጀት ዓመት ብቻ 60ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ነው ለዘርፉ የቀረበው። ይሄ ከአጠቃላይ የፋይናንስ አቅርቦት 12 በመቶው ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀርቧል ማለት ነው። ይሄ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ነው። የፋይናንስ አቀራረብ ዘዴውም አንዱ የፕሮጀክት ፋይናንስ ሲሆን፣ይሄም ለኢንዱስትሪዎች ለፕሮጀከት ሥራ የሚውል ነው። ሌላው ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ተያይዞ የሚከናወነው የሥራ ማስኬጃ የብድር አቀርቦት ነው። ከአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በተያያዘ ደግሞ የሊዝ ፋይናንስ የሚባለው የማሽን ግዥ አቅርቦት ነው። አጠቃላይ ለጥቃቅን፣አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የቀረበ ፋይናንስ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ውስጥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ታረቀኝ፡-የአምራች ኢንዱስተሪው ትልቁ ተግዳሮት የአምራችነት ባህል አለመዳበር ነው። በቅንጅት ሆኖ ድጋፍ የማድረግና የዘርፉን ችግር ለመፍታት ያለው ዝግጁነት ላይ አሁንም ውስኑነት መኖሩ ሌላው ተግዳሮት ነው። ከትምህርትና ስልጠና ጋር በተያያዘም አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል አቅርቦት ላይም እንዲሁ ውስንነት ይስተዋላል። ሌላው አብዛኞቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጭ በግዥ በሚገቡ ጥሬ እቃዎች ጥገኞች ናቸው። ለግብአቱ ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ላይ ደግሞ ከፍተኛ እጥረት አለ። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሰሞኑን ያሻሻለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከ20/80 ወደ አኩል 50/50 እንዲሆን መደረጉ በተሻለ ግብአት ለማግኘት የሚያስችል ቢሆንም አሁንም ግን የተጠናከረ ሥራ ይጠይቃል። በመሠረተ ልማት አቅርቦት ላይም ከፍተኛ ተግዳሮት አለ። ለአንድ ኢንዱስትሪ መብራት አልቀረበም ማለት ሥራ ቆሟል ማለት ነው። ምርት ይቀንሳል። የሰው ኃይሉም ከሥራ ይስተጓጎላል። በሌላ በኩል የፀጥታ መደፍረስ አንዱ ተግዳሮት ነው። በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት ኢንዱስትሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ያለው የፀጥታ ችግር ዘርፉን እየጎዳው ይገኛል። የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የተቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ፤የቅንጅት ክላስተር መመስረት ነው። በዚሁ መሠረትም ስድስት ክላስተሮች ተመስርተዋል። ከዚህም አንዱ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ወደ ተቋማዊ አደረጃጀት የመቀየር ስራ ነው ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ይባል የነበረው ኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ቢሮ ሆኗል። ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የክልል አስተዳደሮች የተካተቱበት ብሄራዊ የኢትዮጵያ ታምርት ኮሚቴም ተቋቁሟል። ይህ ኮሚቴ በየስድስት ወሩ እየተገናኘ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በምን ሁኔታ እየተደገፈ እንደሆነና የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ይገመግማል። በተጨማሪም ስድስት ክላስተሮች ተደራጅተዋል። በሥራቸውም ቴክኒካል ኮሚቴዎች ይገኛሉ። አንደኛው የፋይናንስና ክላስተር ሲሆን፤ በገንዘብ ሚኒስቴር ነው የሚመራው። ቀሪዎቹ የግብአት፣የመሠረተልማት፣የኢንቨስትመት፣ የግሉና የአቅም ግንባታ እንዲሁም የክልሎችና የከተማ አስተዳደር ክላስተር ናቸው። ይህን አደራጃጀት መፍጠር ያስፈለገው የአምራች ኢንዱስትሪ ሥራ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥራ ብቻ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው። በተቀመጠው አቅጣጫ ሥራዎችን መሥራት ከተቻለና ተፈጥሮ የሰጠችንንም ፀጋ ተጠቅመን በእርግጠኝነት ከሸማችነት ወደ አምራችነት መሸጋገር እንችላለን።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ፕሮጀክት አሠራር መቀየሩ ቀደም ሲል በነበረው አካሄድ አይቀጥልም ማለት ነው?
አቶ ታረቀኝ፦ ይቀጥላል እንጂ፣ተቋማዊ አደረጃጀት ኖሮት የበለጠ ኃላፊነትና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ እንዲቀጥል ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። ተቋማዊ መሆኑ ዘርፉን የሚደግፉት ሁሉ በኃላፊነት እንዲሰሩ ያስችላል። ቴክኒካል ኮሚቴ በጋራ የሚያወጣው እቅድ ወደ ተግባር እንዲለወጥና ሥራው ባለቤት እና ተጠያቂነት ኖሮት ይሰራል። ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓመታዊ ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜም መሆን ይኖርበታል የሚል እሳቤ ነው ያለው። በየጊዜው የተከናወነው ሥራ ደግሞ በዓመታዊ የንቅናቄ ሥራ ሊጠናከር ይገባል። እንዲህ ያለው መርሀ ግብር በሌሎች ሀገሮችም የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ሦስተኛ ዓመቱ ነው። ባለፈው ዓመት 126 ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት ንቅናቄ ተካሂዷል። በዚህ ንቅናቄ ትስስር የተፈጠረበት፣አመራር በመፍጠር ልምድ የተገኘበት ነው። ሥራ ከተሰራ ችግርም መፍታት እንደሚቻል ትምህርት ተገኝቶበታል። 350 ኢንዱስትሪዎችን ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ለባለቤቶቹ፣ለሠራተኛው፣ለሀገር ጠቃሚ በመሆኑ ይሄም እንደተሞክሮ የሚቀመር ነው። የንቅናቄ ሥራ በመሰራቱ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች መጥተዋል። ዘርፉ ከዚህ ቀደም ድጋፍ የለውም፣ትኩረት አልተሰጠውም በሚል ተስፋ ቆርጦ የነበረ ባለሀብት ተመልሶ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው እንዲገባ ያደረግንበት በመሆኑ እንደ አንድ መልካም ተሞክሮ እንወስደዋለን።
የፋይናንስ አቅርቦት መሻሻል፣የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ ያደረገው ማሻሻያ የንቅናቄው ውጤት ነው። ንቅናቄው በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልሎችም ጭምር ይጠናከራል። ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ግብርናውን ነው ወይንስ ኢንዱስትሪውን ነው የምናስረክበው የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት። የማንሰራት ኢትዮጵያ ከሆነች ግብርናውን ነው የምናስቀጥለው። ከግብርና ጋር የተጣበቁ ስል ትምርታቸው የማይቀየር፣የእሴት ሰንሰለት የማይጨምሩ ከሆነ ወደ ኋላ ያስቀራል። አሁን የምናየው ሀገራዊ ቀውስ ካለመሥራትና ካለማምረት ጋር ይያያዛል። ነገር ግን ያደገች፣የምትበለጽግ፣ተወዳዳሪ የምትሆን፣ቀጣይ ተስፋ ያላት ሀገር እንድትሆን ከፈለግን አምራችነትን መደገፍ ይኖርብናል። የመንግሥትም ፍላጎት በተለይም ከሁለተኛው ዙር ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም አራቱም ነጥቦች ከአምራችነት ጋር የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር ነው አንዱ፤የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲሁም የተረጋጋች ሀገር ካለችን የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ግኝት፣የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ካለ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን መፍጠር ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
ምቹ የቢዝነስ ከባቢያዊ ሁኔታ ማለት ለምርት ትኩረት፣ለአምራቾች ቅድሚያ የሰጠና የሚደግፍ፣የገበያ እድል የሚሰጥ የአሰራር ሥርዓትን የሚያሻሽል ማለት ነው። ይሄ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ተስፋ ነው። ሦስተኛው ምርታማነትን ማሻሻል ነው። የግብርና ምርት ሲሻሻል የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ይሻሻላል። የአሰራር ሥርዓት ምርታማነት ሲሻሻል የአምራች ዘርፉ ይሻሻላል። አራተኛው አስተዳደራዊ ሁኔታዎችን ማሻሻል ነው። ይሄ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ማሻሻልን ይመለከታል። በዚህ መልኩ የታቀዱትን መሥራት ከተቻለ በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያን የአምራች ኢንዱስትሪው ማዕከል ማድረግ እንችላለን። ይሄን ካላሳካን ውድቀት ነው የሚጠብቀን።
አዲስ ዘመን፦ በዘርፉ የአጭር፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶች በምን መልኩ ነው የተቀመጡት?
አቶ ታረቀኝ፦ በረጅም ጊዜ እቅድ የዘርፉ የጂዲፒ ድርሻ ማሳደግ አንዱ ተቀዳሚ አላማ ነው። ከሰባት ዓመት በኋላ ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የዘርፉን የገበያ ድርሻ 60 በመቶ ማድረስ፣የማምረት አቅምን ማሻሻል፣አዳዲስ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ወደ ማምረት የሚገቡ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት በተለያዩ ድጋፎችን ማጠናከር፣የወጪ ምርቶችንም ማሳደግ የሚሉት ልናሳካቸው የምንፈልጋቸው ዕቅዶቻችን ናቸው። በተለይም በወጪ ንግድ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ማግኘት የዕቅዳችን አንዱ አካል ነው። ይህን እቅድ ለማሳካት ትልቅ ጥረት ይጠይቃል። ከአጭር ጊዜ አኳያ ደግሞ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ መከለስና ምቹ የሆነ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሥራ ላይ ማዋል ነው። በዚህ በኩልም ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው። ረቂቅ ፖሊሲውን ሚኒስትሮች ምክር ቤት እስኪያፀድቀው እየጠበቅን ነው።
ቀደም ሲል የተሰሩትን የተኪ ምርት፣የሰው ኃይል፣የማበረተቻ፣ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር፣የኢንዱስትሪ ምርቶችን በድረ ገጽ(ኦላይን) እንዲገበያይ የማድረግ ስትራቴጂዎችን ወደ ሥራ ማስገባት እንፈልጋለን። ይሄንን ለማሳለጥም በ2016 በጀት ዓመት ኢንዱስትሪዎቹ የሚጠቀሙበት ቴክኖሎጂ፣ካፒታላቸው፣የፈጠሩት የሥራ ዕድል እና የመሳሰሉት የኢንዱስትሪ ቆጠራ (ሰርቬይ) ይካሄዳል። ቆጠራውን መሠረት በማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በመለየት የማገዝ ሥራ ይሰራል። በተመሳሳይ የተፈጥሮ ሀብት ፀጋ ልየታ ሥራ ይሰራል። የዚህ ጥቅሙ ከውጭ ግብአት ጥገኛ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን ከጥገኝነት ለማውጣት አዳዲስ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያግዛል።
አዲስ ዘመን፦ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዙሪያ የሚሰራው ሥራ ካለ ቢገልጹልን?
አቶ ታረቀኝ፦ ወደ 22 የሚሆኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለምተዋል። ከነዚህ ውስጥ አራት ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ናቸው ቀጥታ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው። ከነዚህ ውስጥም ሰልቫዶ የሚባል ድርጅት ከአቮካዶ ዘይት በማምረት ዘይት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል። መሠረተ ልማትን ማጠናከር ከተቻለ ባለሀብቱ በእነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የመሥራት ፍላጎት መኖሩን ማረጋገጥ ተችሏል። አሁን ላይ በእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንዲሰሩ፣በፓርኮቹ ውስጥ የሚመረተው ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያም እንዲቀርብ አቅጣጫ ተቀምጧል። የገበያ ድርሻን ለማሳደግ ሲባል 50 በመቶ፣ሙሉ ለሙሉ እንደ ሁኔታው በሀገር ውስጥ እንዲያቀርቡ ተፈቅዷል። አገዋ ገበያን ተስፋ አድርገው መጥተው የነበሩ ነገር ግን በጦርነቱ ምክንያት የአገዋን እድል መጠቀም ባለመቻሉ ለቀው የወጡም አሉ።
አዲስ ዘመን፦ለአምራቾችም ለተጠቃሚዎችም መልእክት እንዲያስተላልፉ እድሉን ልስጥዎት
አቶ ታረቀኝ፦ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች በሀገራችን እድገት ውስጥ የማይተካ ሚና አላቸው። ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው ጥሬዬን የማስተላልፈው። ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እስካሁን ያመረቱት ምርት፣ለዜጎች የፈጠሩት የሥራ እድል ያስመሰግናቸዋል። ሠራተኞችም ድርሻቸው ከፍተኛ ስለሆነ ምስጋና ይገባቸዋል። ከባቢያዊው ሁኔታው ሰላማዊ እንዲሆን በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት፣ጥያቄም ካላቸው በተደራጀ ሁኔታ በሰላማዊ ሁኔታ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ተጠቃሚዎች በተመለከተ ሀገር መውደድ የሚገለጸው የራስን በመጠቀም ነው። ስለዚህ በሀገራቸው ምርት መኩራትና በመጠቀም ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል። የመንግሥት ተቋማትም ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ታረቀኝ፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም