ከቅሬታዎች በስተጀርባ ያለው ተጨባጭ እውነት

ለመነሻ

የዝግጅት ክፍላችን ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም በዚህ ገጽ ‹‹የተቋማት አለመናበብ፤ የመረጃም ድብብቆሽ የበረታበት-የመሬት ክፍፍል›› በሚል ርዕስ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ስለሚስተዋለው የመሬት ወረራ የደረሰንን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ሰፋ ያለ የምርመራ ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል። የዘገባውን ለሕትመት መብቃት ተከትሎ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና ግለሰቦች ወደ ዝግጅት ክፍላችን በአካል በመምጣት እና ደብዳቤ በመፃፍ በዘገባው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፤ እኛም በዛሬው እትማችን ለቅሬታዎቹ መልስ እንሰጣለን።

 የመረጃ ምንጮቻችን

በወቅቱ ለዝግጅት ክፍላችን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢ ነዋሪዎች የመረጃ ምንጭ ሆነውናል። ምንጮቻችን በወረዳቸው የተለያዩ አካባቢዎች ‹‹አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጆች ናቸው›› በሚል ለግለሰቦች የተመራ ቦታ አግባብነት በጎደለው መንገድ በአካባቢው ላልነበሩ ሰዎች በሙስና እየተከፋፈለ ስለመሆኑ ጥቆማ አድርሰውናል፣ እኛም ጥቆማውን መሰረት አድርገን ሙያው በሚጠይቀው መንገድ በአግባቡ የማጣራት ስራችንን ሰርተናል።

ከወረዳ 14 አስተዳደር የቀረበ ቅሬታ

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት በቀን 26/12/2015 ዓ.ም በቀጥር ፡- አ/ከ/ክ/ወ/4/ዋ/አስ/ፅ/ቤት /2015 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፤ በዘገባው ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች፤ ዘገባው የተቋማትን አሰራር ታሳቢ ያደረገ አይደለም።

ለአርሶ አደር መሬት የመስጠት ሂደት፤ ወረዳ ላይ ባሉ አርሶ አደሮች ወይም በአርሶ አደር ልጆች ከሚወጣጡ የብሎክ ኮሚቴ የወረዳ አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት፤ የወረዳ መሬት ልማት ጽሕፈት ቤት በመለየት እና መረጃን በማጥራት በመመሪያ ቁጥር 20/2013 መሰረት የተለዩትን ለወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ያቀርባል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው መረጃውንና ሂደቱን በማረጋገጥ ለክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ይልካል፤ በዚህ መልኩ ይወሰናል። በጋዜጣው ላይ የወጣው ዘገባ ግን ይህንን አሰራር ታሳቢ ያደረገ አይደለም።

በልዩ ሁኔታ በፅሁፍ የቀረበው የአቶ ፍቃዱ ዳባ ይዞታ በፕላን እና በአየር ካርታ ምንም ዓይነት የመንገድ ጥናት የሌለው፤ ጥያቄ በቀረበበት ወቅት የአየር ካርታውን መሰረት በማድረግ በቀን 7/1/2013 ዓ.ም ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ካርታ ተዘጋጅቶ የተሰጣቸው ፤በከንቲባ ጽሕፈት ቤት በተደረገው ኦዲት ካርታው እንዲመክን እና እንዲጣራ የተደረገ ነው።

በቀን 22/09/2014 ዓ.ም በቁጥር አአኮድ/35/09/535/ አቶ ፍቃዱ ዳባ የተባሉት ግለሰብ ካርታው መምከኑ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ካቢኔ ተገቢ አይደለም ተብሎ በተገለጸው መሰረት መረጃው ለጋዜጠኞች ቢሰጣቸውም ይህንን መረጃ ለመጠቀም ፈቃደኝ አልሆኑም።

በጋዜጣ ላይ የወጣው የአቶ ፍቃዱ ዳባ ካርታ ወይም የባለይዞታ የምስክር ወረቀት በካርታ ቁጥር 14/02/1/1703/32187/00 የተሰጠበት ቀን 7/1/2013 ዓ.ም የሚል ሲሆን፤ ሆን ተብሎ ካርታው አሁን አዲስ እንደተሰራ በማስመሰል የፊት ገጽ ላይ መቅረቡ ተገቢነት የሌለው ፤ መታረም አለበት የሚል እና ሌሎች ሀተታዎችን የያዘ ነው። የቅሬታውን ሙሉ ጽሁፍ በአባሪ መልክ አቅርበነዋል።

የዝግጅት ክፍሉ ምላሽ

የዝግጅት ክፍሉ ከነዋሪዎች የደረሰውን ጥቆማ ይዞ በጉዳዩ ዙሪያ ከወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ይታወሳል። የደረሰን ጥቆማ በወረዳው የተለያዩ ቦታዎች መሬት ያለአግባብ ለማይመለከታቸው አካላት እየተላለፈ ነው የሚል ስለነበር በቃለ መጠይቁ ወቅት የተወሰኑ ግለሰቦች መረጃ በተለየ ሁኔታ አልተጠየቀም። የዝግጀት ክፍላችን ያቀረበው ጥያቄ፤ አቶ ፍቃዱ ዳባ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን

 ከ10 ያላነሱ ግለሰቦችን ፋይል የማጣራት ነው።

በወቅቱ የዝግጅት ክፍላችን ያቀረባቸው ጥያቄዎች፤ ቦታውን የወሰዱት እና ቦታው ይገባቸዋል በሚል ውሳኔ የተላለፈላቸው አርሶ አደሮች ናቸው? የወረዳው ነዋሪ ናቸው? ሥራ አስፈጻሚውም የሰጠን ምላሽ ‹‹አዎ የዚህ ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው›› የሚል ነበር። ይህን ተከትሎ የአርሶ አደር ልጅ ስለመሆናቸው እና የቀጠና ኮሚቴዎችም አርሶ አደር እና የዚህ ወረዳ ነዋሪ ስለመሆናቸው ከወረዳ 14 ሲቪል ምገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ፋይላቸው ይጣራ? የሚል ጥያቄ ለአቶ ድሪባ አቅርበን ነበር።

ይሁንና አቶ ድሪባ የሲቪል ምገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ፋይል ለማየት ከፈለጋችሁ መስሪያ ቤታችሁ በሌላ ደብዳቤ ይጠይቀን የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። የዝግጅት ክፍሉ ጋዜጠኞችም አሁን መረጃ እየሰጡን ያለው ህጋዊ ደብዳቤ ስላመጣን ነው። በደብዳቤው መሰረት ሁሉን አቀፍ መረጃ ቢሰጡን ምን የአሰራር ችግር ይፈጥራል የሚል ተጨማሪ ጥያቄ አቅርበዋል።

ሥራ አስፈጻሚው ሌላ ደብዳቤ ጽፋችሁ ካልመጣችሁ መረጃውን አልሰጥም በማለታቸው ሌላ ደብዳቤ በማዘጋጀት ወደ ቦታው ተመልሰናል። ይህም ሆኖ ግን ደብዳቤውን ይዘን በቀጠሮ ቀን ስንሄድ አቶ ድሪባ አልነበሩም። የወረዳ 14 ሲቪል ምገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊም አልተገኙም። ይልቁንም ነዋሪዎች ብቻ ተሰብስበው ነበር።

ወረዳ 14 ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጽሕፈት ባለሙያዎች እነዚህ ነዋሪዎች ናቸው ወይስ አይደሉም? መረጃ ስጡን ብለን ጠይቀናል። ባለሙያዎቹም በግለሰቦቹ የመሬት ካርታቸው መሰረት ጥያቄያችንን ተቀብሎ መረጃ ለመስጠት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። ከሰዓታት ቆይታ በኋላ በመታወቂያቸው ካልሆነ በቀር በመሬት ካርታቸው መሰረት ነዋሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ሰነድ እንዳላገኙ አሳውቀውናል። በመሆኑም የዝግጅት ክፍላችን በወቅቱ ተገቢውን መረጃ አለማግኘቱን ለማሳወቅ ተገዷል። የአቶ ፍቃዱ ዳባ ካርታ ወይም የባለይዞታ የምስክር ወረቀት በተመለከተም በእጃችን ያለውና ለህትመት የበቃው መረጃ ከወረዳው ያገኘነው ነው።

የአቶ ፍቃዱ ዳባ ቅሬታ

አቶ ፍቃዱ ዳባ ለዝግጅት ክፍላችን ባቀረቡት ቅሬታ፤ አቅም ደካማ በመሆናቸው በሌሎች ድጋፍ እንደሚኖሩ ነግረውናል። በዚህ የመሬት ጉዳይ መፍትሄ ፍለጋ በየተቋማቱ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማሳለፋቸውን ጠቁመውናል። ለዘመናት ለግብርና ሥራ ሲጠቀሙበት የኖረውን መሬት ያለአግባብ በመወሰዱ በተደጋጋሚ ለካሳ ክፍያ እና መብታችን ለማስከበር ለፍትህ ሲጮሁ እንደነበር፤ አሁን ያገኙት አንገት ማስገቢያ ቢያንስ እንጂ የሚበዛባቸው እንዳልሆነ ገልጸውልናል።

ሌላው ቀርቶ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በመሬታችን ላይ ተገንብተው ሲከፋፈሉ እኛ ‹‹የበይ ተመልካች›› ሆነን ኖረናል። ይሁንና ለዘመናት ዋጋ የከፈልንበት ጉዳይ በእኛ ጥረትና በመንግሥት ይሁንታ ፍትህ ማግኘቱ የማይዋጥላቸው ግለሰቦች ዱካችንን እየተከተሉ የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ እንደሆነ ጠቁመውናል። ለዝግጅት ክፍላችን፤ የወረዳ ነዋሪ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጥ መታወቂያ እና የሚመለከተው የመንግሥት አካል የሰጠኝ ነው ያሉትን ካርታ አቅርበዋል።

ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ቅሬታ

ያለ አግባብ በጋዜጣ የወጣ ስም ማጥፋት እንዲስተካከል መጠየቅን ይመለከታል በሚል ርዕስ፤ ጽሕፈት ቤቱ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ለዝግጅት ክፍሉ በላከው ደብዳቤ፤ በአቶ ፍቃዱ ዳባ በዳዳ ጉዳይ በጽሁፍም በቃልም መረጃም ይሁን ማስረጃ የተጠየቅነው ነገር የለም፤ ባልተጠየቅንበት አግባብ መረጃ አልሰጡም ተብሎ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ስማችን መጠቀሱ ተገቢ አይደለም ብሏል።

በምላሹም፤ አቶ ፍቃዱ ዳባ በዳዳ በቤት ቁጥር 887/ሀ እና በቤተሰብ ቅጽ 01 ላይ ተመዝገበው የሚገኙ የወረዳቸው ነዋሪ መሆናቸውን፣ ከዚህም በላይ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መዝገብ ቁጥር 443/1993 ዓ.ም ውሳኔ ያገኘ የኑዛዜ መረጃ በጽሕፈት ቤቱ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የዝግጅት ክፍሉ ምላሽ

የዝግጅት ክፍላችን መረጃዎች ለማጥራት በተደጋጋሚ በወረዳው ተመላልሷል፤ ለህትመት የበቁ ዶክመንቶችን ጭምር ከወረዳው መውሰዱም ይታወቃል። በተጨማሪም የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ድሪባ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ቢጠየቁ፣ ሌላ ደብዳቤ ካልተፃፈ መረጃ አልሰጥም በማለታቸው ተቋማችን ሌላ ደብዳቤ ለመፃፍ የተገደደበት ሁኔታ እንደነበር ቀደም ብለን ለመግለጽ ሞክረናል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በጠየቁት መሰረት ተጨማሪ ደብዳቤ ጽፈን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት በሳቸው ፈቃደኝነት ማጣት ሳይሳካ ቀርቷል፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ለህትመት በበቃው ዘገባ ላይ ያሉ አንዳንድ መረጃዎች ከተቋሙ ባለሙያዎች የተወሰዱ መሆናቸውን መዘንጋት የለበትም ፣ ከዚህ የተነሳም በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ አልተጠየቅንም በሚለው የቀረበው ቅሬታ አግብብነት የጎደለው ነው።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘ ተጨማሪ መረጃ

ምንም እንኳን የወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምንም የፕላን ተቃርኖ የለውም ቢሉም፤ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ቁጥር 1 ሥራ አስኪያጂ ከፍተኛ ኃይል ቀርቶ አነስተኛ ኃይል ቢሆንም በግለሰቦች ጣሪያ ላይ ማለፍ እንደሌለበት ገልጸዋል።

በወቅቱ የዝግጅት ክፍላችን ምሰሶው በሚያልፍባቸው ቦታዎች ላይ ሕንፃዎችን መገንባት ይቻላል ወይ? ቤት የሚገነቡ ካሉስ ተቋማችሁ መብቱን እንዴት ያስጠብቃል? ተብለው የተጠየቁት የምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ቁጥር 1 ሥራ አስኪያጂ አቶ ወንድወሰን ፈዬራ እንደገለጹት፤ መሬት የሚሰጠው ሌላ አካል ነው። የመብራት ኃይል የሚሰራው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ብቻ ነው።

መስመር ከተዘረጋ በኋላ ቤቶች ቢገነቡ የቤት ግንባታ ጋር የሚያገናኘው አካል ነው መጠየቅ ያለበት እንጂ የእኛ ተቋም አይደለም። ሆኖም መስሪያ ቤቱ በሰዎች መኖሪያ ቤት ላይ ከባድ ኃይል ተሸካሚ ገመድ መዘርጋት ይቅርና በአጥር ላይ እንኳን ዝቅተኛ ኃይል ተሸካሚ ገመድ አይዘረጋም ብለዋል።

የኃይል ተሸካሚ መስመር ተዘርግቶ ከነበር እና በኃይል ተሸካሚው ገመድ ስር ግንባታ ማከናወን የሚፈልግ ሰው በመመሪያው መሰረት ማዘዋወሪያ ይጠይቃል። ለማዘዋወሪያው ክፍያ ይከፍላል። በመቀጠልም የኃይል ተሸካሚ መስመር ማዘዋወር ግዴታቸው መሆኑን ያስረዳሉ። በዚህ አግባብ ለሚመጡ ሰዎች የማዘዋወር ሥራ እየሠራን ነው ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁን ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ግን ማንም አካል ጥያቄ ለተቋማቸው እንዳላቀረበና ስለጉዳዩም ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዝግጅት የምርመራና መልካም አስተዳደር ክፍል መስማታቸውን አስረድተዋል።

በመሠረታዊነት ሊታረሙ የሚገባቸው ጉዳዮች

ከሁሉም ቀድሞ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለዝግጅት ክፍላችን የመጣው ደብዳቤ ቁጥር በአግባቡ አለመፃፉ፤ በቅሬታውም በተደጋጋሚ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊት ገፅ በወጣ ዘገባ የሚል ትችት አለበት። እውነታው ወረዳውን በተመለከተ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊት ገጽ የወጣ ዘገባ የለም። ይልቁንም በገጽ 6 እና 7 ፍረዱኝ በሚል ዓምድ የተስተናገደ ነው።

ሌላው ዝግጅት ክፍሉ ለክፍለ ከተማው ሆነ ለሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ስለአቶ ፍቃዱ ዳባ ጉዳይ በተለየ ሁኔታ መረጃ አልጠየቀም። የአቶ ፍቃዱ ዳባን ጉዳይም በተለየ ሁኔታ የማየት ፍላጎት የለውም። የዘገባው ዓላማ አጠቃላይ በሆነው የነዋሪዎች ቅሬታ ዙሪያ ነው።

ዘገባው የመልካም አስተዳደር /የመሬት ጉዳይ ሆኖ ሳለ፤ ለጉዳዩ ሃይማኖታዊ ይዘት ሰጥቶ ፤የተሰጠውያልተገባ አስተያየት ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው ተቋም የሚጠበቅ አይደለም። የዝግጅት ክፍሉ ለሃይማኖቶች መቻቻልና መከባበር አበክሮ የሚሠራ ስለመሆን የማንንም ምስክርነት የማይፈልግ፤ የዕለት ተዕለት ሥራዎቹ ተጨባጭ ማሳያ ሆነው የሚገልጹት ነው።

ቅሬታዎችን ማቅረብ በዝግጅት ክፍላችን አግባብነት ያለው መሆኑ ቢታመንበትም የዝግጅት ክፍሉ ከመልካም አስተዳደር ጋር ለሚነሱ ጥያቄዎች አስፈላጊ መረጃዎችን ለማግኘት ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በወቅቱ መረጃዎችን በመስጠት የሥራው ተባባሪ መሆን ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት ከሚንቀሳቀስ ተቋምና የተቋም አመራር የሚጠበቅ ነው፤ ከዚህ አንፃር ቅሬታ አቅራቢ ተቋማት የመረጃ አሰጣጥ ሥርዓታቸውን መልሰው ቢያጤኑት መልካም ነው።

ሙሉቀን ታደገ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You