እዮሃ አበባዬ………….መስከረም ጠባዬ
እዮሃ አበባዬ…………. መስከረም ጠባዬ
መስከረም ሲጠባ……..አደይ ሲፈነዳ
እንኳን ሰው ዘመዱን………ይጠይቃል ባዳ ይባላል። ይህ ዜማ አሮጌው ዘመን በአዲሱ የመቀየሩን ብሥራት አብሣሪው ነው።
የአዲስ ዓመት (እንቁጣጣሽ) በዓል፤ በእኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ልዩ ሥፍራ ከሚሰጣቸው በዓላት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። የጨለማ ተምሳሌት የሆነው ጭጋጋማው የክረምት ወቅት አልፎ፣ ቀን ከሌሊት ይዘንብ የነበረው ዝናብና አስገምጋሚው መብረቅ ጋብ የሚልበት፣ ምድር በአደይ አበባ ተጥለቅልቃ በልምላሜ የምትታይበት፣ አሮጌው ዘመን ወደኋላ ተትቶ አዲሱ ሊተካ “እዮሃ አበባዬ” የሚባልበት በዓል በመሆኑ በብዙዎቻችን ዘንድ የተለየ ትርጓሜ ይሰጠዋል።
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ተፈጥሮም ጭምር የሚለወጥበት ነው። በመስከረም ወር አዝመራው ያብባል፣ የደፈረሱ ወንዞች መጥራት ይጀምራሉ፣ አደይ አበባ ምድሪቱን ያለብሳታል ፣ የመስቀል ወፎች ከተደበቁበት ይወጣሉ። ለዚህም ነው አዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ መጀመሪያ ተደርጎ የሚታሰበው፡፡
ዓመቱ ለሀገራችን አዲስ ተስፋን የሰነቀ የሰላም፣ የፍቅር እና የዕድገት እንዲሆን ሁላችንም እንመኛለን። እርስ በእርሳችንም እንኳን አደረሳችሁ! ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የሐሴት ይሁንልህ/ሽ እንባባላለን፤ ይህ በራሱ አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ እንድንቀበለው የሚያስገድድ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል።
የ2016 ዓ.ም አዲስ ዓመትም ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ የብሩህ ተስፋ ዘመን እንዲሆንልን የምንመኘው በ2015 ዓ.ም ያሳለፍናቸውን ፈተናዎች ተወጥተን ሰላም የሚሰፍንበትና ልማታችን ላይ የምናተኩርበት ዘመን እንዲሆንልን ካለን ጽኑ ፍላጎት በመነጨ ነው፡፡
በመጪው አዲስ ግጭትና ያለመረጋጋት እንዲወገድ፣ ከቀያቸው በጦርነት ተፈናቅለው በየመጠለያው ያሉ ወገኖቻችን ወደየቤታቸው እንዲመለሱ፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶች እንዲጠገኑ በአጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታችን እንዲታደስ ጠንክረን የምንሰራበት ዘመን ሊሆንም ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም ሀገራት በተለየ የራሷ የዘመን ስሌትና ቀመር ያላት ሀገር ናት። ብቸኛዋ የአስራ ሦስት ወር ፀጋ ባለቤትም መሆኗ ይታወቃል። ታዲያ አስራ ሦስተኛው የጳጉሜን ወር አብቅታ የአዲሱ ዓመት መባቻ የሆነው የመስከረም ወር ሲዋጅ፣ ብዙዎቻችን አዳዲስ የሕይወት ዕቅዶችን ማውጣት ወይንም የጀመርነውን አጠናክረን በመቀጠል ውጤታማ ለመሆን እናስባለን። ዘመን ዕለቱን ጠብቆ ሲቀየር የእኛም የአስተሳሰብ፣ አመለካከትና አጠቃላይ የሕይወት ዘይቤና እሳቤ እንዲቀየርም እንተልማለን። መስከረም በራሱ ለሰዎች ተስፋን ይዞ የሚመጣ ወር ነው ተብሎ በብዙዎች የመታመኑ ምስጢር ይኸው ነው።
እቅድ ሥራዎችን በየደረጃቸው እና በጊዜ አስቀምጠን እንድንሰራ የሚረዳን ትልቅ መሳሪያ ነው፤ ብዙ ሰዎች አዲሱን ዓመት የሚጀምሩት እቅድ በማቀድ ነው፤ ለምሳሌ በዚህ ዓመት ይሄን ያህል ገንዘብ እቆጥባለሁ፣ በዚህ ዓመት ትምህርት እጀምራለሁ፣ ወይም ደግሞ የግል ሥራ የምጀመርበት ዓመት ነው፤ አልያም ወደ ሀገሬ በአዲሱ ዓመት እመለሳለሁ ብለው የተለያዩ የግል እቅዶችን ያቅዳሉ፡፡
ታዲያ ይህ እቅድ ዓመት ገብቶ ዓመት በወጣ ቁጥር የሚወጣ ሊሆን አይገባም። ቢያንስ የእቅዱ ከግማሽ በላይ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ መቻል ይኖርበታል። ነገር ግን በዚህ ልክ አዲስ ዓመት ሲመጣ የያዝናቸውን እቅዶች ምን ያህሎቻችን ከግብ አድርሰናል የሚለው ለሁላችንም የሚቀርብ ጥያቄና መልሳችንንም ለራሳችን የምናደርገው ነው። ዕቅድን አቅዶ ውጤታማ አለመሆን በሕይወታችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖዎችን ሊያመጣብን እንደሚችል ግን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው።
በሌላ በኩልም አሁን ላይ በሀገራችን እየታዩ ያሉት ችግሮች ጊዜያዊ እንደሆኑና እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያጋጥሙንን መከራና ችግሮች ማለፍ የምንችል ማኅበረሰቦች እንደሆንን በማመን ነገ የተሻለ ተስፋ እንዳለም መጠበቅ አንዱ የአዲስ ዓመት መገለጫው ሊሆን ይገባል።
ያሳለፍነው ክረምት በጣም ከባድና ተንቀሳቅሶ ለመሥራት በጣም አስቸጋሪ የሆነ ጊዜ ነበር። መስከረም ደግሞ በራሱ ከወራቶች ሁሉ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት ወር ነው፣ ነገሮች እንደምናስባቸው ላይሳኩ ይችላሉ ወይንም ሰርተን የምናገኘው ገንዘብ የምፈልገውን ነገር አሁን ላይበቃ ይችላል። ነገር ግን፣ ነገ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ለዚህም ደግሞ ተስፋ ባለመቁረጥ ከሕይወት ጋር መታገል ግድ ነው። መጪው አዲስ ዓመትም የተሻለ ሰላም ሰፍኖ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ላይ ጥሩ ሥራን ሰርቶ አቅዶ እቅዱንም ከግብ አድርሶ ሀገሩንም ራሱንም ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል።
ተስፋ አለመቁረጥና ነገ የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ በሙሉ ልብ ማመንን ያቀድናቸውን እቅዶቻችንን ከግብ ለማድረስ ትልቅ አቅም ይሆኑናል።
እንደሀገር በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ጫናዎች ውስጥ እንገኛለን። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት መንግሥትና ሕዝባችን ያለውን አንድነት እና ጽኑ አቋም ስንመለከት፣ ሁሉንም ጫናዎች መቋቋምና አሸናፊዎች መሆን እንደሚቻል ያመላክታል።
የምንሰማቸው ክፉ ዜናዎች በሙሉ ተወግደው ዕድገታችን የሚፋጠንበት ዘመን ይሆናል ። ነገ የተሻለ ነገር ለማምጣት ዛሬ ላይ እንደ ራሳችንም እንደ ሀገርም ትልልቅ እቅዶችን ማቀድ ለተፈጻሚነታቸውና ግባቸውን ለመምታታቸው ደግሞ ቆርጠን መነሳትን ይጠይቀናል። ነገሮች ወደ ሰላማዊ የመረጋጋት መስመር ውስጥ እንዲገቡ የሁላችንም ኃላፊነት ነውና ነገ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ እያደረግን ዛሬ ያለንን ነገር በአግባቡ እንጠቀም። በማለት እኛም አዲስ ዓመትና ተስፋው ብሎም ሰዎች አቅደው ስለመመራታቸው በተመለከተ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሥነልቦና መምህር ከሆኑት ከአቶ ጌታ ዋለልኝ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ አዲስ ዓመት ማለት ምን ማለት ነው?
አቶ ጌታ፦ አዲስ ዘመን ማለት የጊዜ መለወጥ ማለት ሲሆን ይህ ጊዜ ሲለወጥ ደግሞ ብዙ ሰዎች ከጊዜው ጋር የመለወጥ ፍላጎትና ተነሳሽነትንም የሚያሳዩበት ነው። ማንኛውም ጤነኛ የሆነ ሰው ደግሞ ሁሌም በለውጥ ሂደት ላይ የሚሆን ከመሆኑም በላይ በተለይም ዘመን ሲቀየር ራሱን ከዘመኑ ጋር ለመቀየር በርካታ ተግባራትን ስለማድረጉም የሚያጠያይቅ አይሆንም።
ሁሌም ቢሆን ደስታችንም ሆነ የሕይወት እንቅስቃሴያችን የሚወሰነው በእድገት ላይ ነው። ይህንን ነገር ደግሞ የሚያስታውሰን አዲስ ዓመት ነው።
አዲስ ዓመት ሲለወጥ ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን ከጊዜው መለወጥ ጋር ሕይወታቸውንም ለመለወጥ ተነሳሽነት የሚያድርባቸው ጊዜ ነውና ራሳቸውን የማደስና ሕይወታቸውን ለመለወጥ ተነሳሽነት ያድርባቸዋል። አዲስ አስተሳሰብም ይይዛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ አዲስ ዓመት የመታደስ የመለወጥ አዲስ ውጥንን የመያዣ ጊዜ ከመሆኑ አንጻር አቀባበላችንስ ምን መምሰል አለበት?
አቶ ጌታ፦ በነገራችን ላይ የነገሮች ወይም ደግሞ የዓመቱ መለወጥ ብቻውን ለእኛ መለወጥ ምክንያት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን እኛም ራሳችን እንደ ዘመኑ ለመለወጥ ከነበርንበት ወደተሻለ ሁኔታ ለመቀየር በጠቅላላው ራሳችን ላይ ለመሥራት ፍቃደኛ መሆን ያስፈልጋል። በመሆኑም ዓመቱ ስለተለወጠ ብቻ አዲስ ሕይወት አዲስ ሀገርና ሁኔታ ይመጣል ማለት ባለመሆኑ ያንን ለውጥ ራሳችን ቆራጥ ሆነን ለማምጣት ዝግጁ መሆንና የሚጠበቅብንንም ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፦ራሳችንን ለመለወጥ ፍቃደኝነታችንን ከምናሳይበት መንገድ አንዱ እቅድ ማቀድ ይመስለኛልና በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ጌታ፦ ከአዲስ ዓመት ጋር ተያይዞ ሕይወትን የተሻለ ሁኔታ ላይ ለማስቀመጥ ብዙ ሰው አቅዳለሁ ይላል ነገር ግን አብዛኞቻችን ያለን እቅድ ሳይሆን ፍላጎት ነው። ይህ ቢሆን ያንን ባሳካ ብለን ፍላጎት እናሳያለን እንጂ ጠንከር ያለ እቅድ ማውጣት ግብ መንደፍ ላይ ብዙዎቻችን አናስበውም ።
አዲስ ዓመት ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ እንዲህ ቢሆንልኝ፤ ይህንን ብሰራ፤ ወደዚህ ሀገር ብሄድ ወይንም ትምህርት ብጀምር ብቻ ብዙ ብዙ ነገሮችን እያስቀመጥን እንመኛለን ያ ምኞታችን የሚመስለን እቅድ ያቀድን ነው፤ ነገር ግን ይህ ሊሆንም ላይሆንም የሚችል ምኞት እንጂ እቅድ ሊባል አይችልም። እንደዚህ አስበን ብዙ ጊዜ ላይሳካልን ከቻለ ደግሞ ተስፋ ማድረግን ትተን ወደጨለምተኝነት የምንመጣበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ተስፋቢስነትን ተለማምደን ደግሞ ዓመት ቢቀየርም ምንም አዲስ ነገር አይኖርም፤ አይፈጠርም የምንልበት ሁኔታም ይመጣል። ከዚህ አንጻር ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተስፋቢስ ሆነው አልያም በተስፋ ተሞልተው ዓመቱን ሊጀምሩት ይችላሉ።
እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ነገር ለእኛ እቅድ የመሰሉን ምኞቶቻችንን ለማሳካትም ቢሆን ግብ መንደፍ በጣም አስፈላጊ ነው። በተለይም እቅድና ግብ እንዲኖረን ብዙ መማር ማንበብና ሁኔታውን በአግባቡ መረዳት የግድ የሚያስፈልግ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ምኞትን ወይም ፍላጎትን እንዴት ነው ወደ ዕቅድ መቀየር የምንችለው ?
አቶ ጌታ፦ ከላይ እንዳልኩት ብዙዎቻችንን እቅድና ግብ የለንም ከዛ ይልቅ ፍላጎትና ተስፋ ነው ያለን፤ ነገር ግን ግብ ነድፎ ተንቀሳቅሶ ውጤታማ መሆን በደንብ ይቻላል። ለዚህም ሃሳብን ሕልምን በጽሑፍ መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው። እንደ አባባልም “በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል” እንደሚባለው ሁላችንም ዘመን ሲቀየር ማድረግ የምንፈልገውን መሆን የምንሻውን መድረስ ያለብንን ቦታ በሃሳብ ከመያዝ ወይም በቃል ከማውራት በጽሑፍ ግብ አድርጎ ማስቀመጡ ወደፊት ለመፈንጠር ዓይነተኛ መንገድ ነው።
መጀመሪያም ቢሆን እቅድን እቅድ የሚያሰኘው በጽሑፍ መስፈሩ ሲሆን ሌላው ውስን ግልጽና የሚለካ መሆኑ ይኖርበታል። ለምሳሌ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ምንድን ነው አሳክቼ ማየት የምፈልገው? የሚለው ነገር በግልጽ መቀመጥ ያለበት ከመሆኑም በላይ በጊዜም የተወሰነ ሊሆን ይገባል፤ ተሳክቷል፤ አልተሳካም የሚለው ነገር ደግሞ ሊለካ የሚችል ሊሆን ይገባል። እንዲሁም ተጨባጭነት ያለውም ሊሆን ይገባል። የሚሳካ ሊሆንም ይገባል በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ተቀምጦ ነው እንግዲህ መሄድ ያለበት።
በመቀጠልም ምን አቅጄ የትኛውን ግብ አስቀምጬ እየተንቀሳቀስኩ ነው የትኛውንስ ማሳካት እችላለሁ የሚለው ነገር ደግሞ በየጊዜው መገምገምና መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የድርጅት እቅድና ግብ ለማስቀመጥ እሱንም ለማሳካት ብዙ ላይቸገሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የራሳቸው የሆነን ግብ ለማሳካት በጣም ይቸገራሉ። በመሆኑም ራስን በደንብ ማየት መገምገም ያስፈልጋል። በዚህም ለግቡ አለመሳካት ትልቁ ችግር ምንድን ነው? በምንስ ነው ሊፈታ የሚችለው? የሚለውን ከራሳችን ጋር በየጊዜው መገማገሙ በጣም አስፈላጊ ነው።
በዚህ መልኩ ምን አቅደን የትኛውን ግብ አስቀምጠን የት ደረስን? የሚለውን በለካንና ራሳችንን በገመገምን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የባህርይ ለውጥ እንድናመጣም ያግዘናል። እኛ ተለወጥን ማለት ግባችንን አሳካን ነውና ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ግብ ብቻውን ውጤት አያመጣም። ስለዚህ ለእቅዳችን መሳካት ወይ ማቆም ያለብን አጉል ባህርይ አለ፤ አለበለዚያም መላመድ ያለበን አስፈላጊ ነገር አለ ማለት በመሆኑ ይህንን በአግባቡ ተረድቶ መሥራት በጣም አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ሰዎች እንግዲህ ፍላጎትም እንበለው አቅድ አስቀምጠው እርስዎ እንዳሉትም ግብ ለማስቀመጥ ጥረት አድርገው ግን ደግሞ ስኬትን አይጎናጽፉም የዚህ ዋናው ምክንያት ምንድነው ይላሉ?
አቶ ጌታ ፦ አዎ ሰዎች ግብ አስቀምጠው ውጤት ሊርቃቸው ይችላል ምክንያቱ ደግሞ መጀመሪያም ቢሆን ያስቀመጡት ግብ የሚገዳደራቸው አልነበረም ማለት ነው። ስለዚህ ምን ጊዜም የምናስቀምጠው ግብ ሊገዳደረን የሚችል ሊሆን ይገባል።
የማይሳካ ከባድ ወይም ደግሞ በጣም ቀላል ግብ ካስቀመጥን ለማሳካት አነሳሽ ነገር አይኖረውም። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው የሚገዳደረን (የእኛን ጥረትና ትግል) የሚጠይቅ ሲሆን ግን ውጤታማነቱም የተሻለ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ግባችን ላለመሳካቱ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ኃይል ስላለም መሆኑን መርሳት አይገባም። ለምሳሌ አንድ ሰው ይህንን ይህንን አደርጋለሁ በማለት ግብ አስቀምጦ ነገር ግን የሀገራችን የማህበረሰቡ ሁኔታ ግቡን እንዳይመታ ተግዳሮት የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ በመሆኑ እነዚህን ነገሮች በሙሉ አስቦ ግብ ማስቀመጥ በጣም አስፈላጊ ነው።
እዚህ ላይ በጣም በትኩረት መታየት ያለበት ነገር እኛ ራሳችን ግባችንን ከዳር ለማድረስ ምን ያህል ቆራጦች ነን ? የሚለውን መፈተሽ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ለሁሉም ችግሮቻችን ውጫዊ ምክንያቶችን እየፈለግን በሄድን መጠን የእኛን ኃላፊነትም መርሳት ያመጣልና ቆም ብሎ እኔ ምን እየሰራሁ ነው? የሚጠበቅብኝን አድርጌያለሁ ወይ ለምንድን ነው ግቤ ያልተሳካው የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል።
የዘንድሮው ግብ ካልተሳካ በሚቀጥለው ዓመት እንዴት ግብ ማስቀመጥ እንዳለበን߹ ምን ዓይነት ትምህርት መቅሰም እንዳለብን ሁሉ መማሪያ ይሆነናል። ሕይወት አንዴ አልተሳካም ማለት ሁሉም ነገር አበቃ አለቀ ማለት ካለመሆኑም በላይ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሌላ እድል ስለሚሰጥ የአሁኑን ባለበት አቁሞ ትምህርት ወስዶ ለቀጣዩ መዘጋጀት ብልህነት መሆኑን መረዳትም አስፈላጊ ነው።
ግን ሰዎች አቅደው ግብ አስቀምጠው ነገር ግን ሕይወታቸው ለምን ስኬትን ያጣል ካልን መልሶቹ የራስ ቁርጠኝነትና ተገዳዳሪ ግብን ያለማስቀመጥ ጉዳይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ግብ ወደ ሀገር ብንቀይረው እንደው ሀገር አዲስ ዓመት ሲመጣ ምን ዓይነት ግብ ይዛ መነሳት አለባት ይላሉ?
አቶ ጌታ፦ ሀገር እንደ ግለሰብ ሁሉ ተስፋ ያስፈልጋታል፤ አሁን ላይ ግን ሰዎች ተስፋ ቢስነትን እየተለማመዱት ያለ ይመስላልና መጀመሪያ ሕዝቡ ውስጥ ያለውን “በዚህም ዓመት ምንም ለውጥ አይመጣም” የሚለውን ተስፋ ቢስነት መስበር ያስፈልጋል። በመሆኑም መጪውን አዲስ ዓመት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚለውን መፈተሽ በጣም አስፈላጊ ነው። አዲሱን ዓመት ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ ካልን ደግሞ በተጨባጭ ምን እንደሆነ ማስቀመጥም ተገቢና አስፈላጊ ነው።
ሰው ተስፋ ሲኖረው ኃይል ይኖረዋል፤ ኃይል ካለው ደግሞ ራቅ አድርጎ ያቅዳል። ነገር ግን በዚህ ዓመትም ምንም አዲስ ነገር የለም ከተባለ ሲጀመርም እቅድ ላይ አይገባም። በመሆኑም ሀገሬ ተስፋ አላት ብለን ከተነሳን ማቀድ እንጀምራለን። በመሆኑም መንግሥት ሕዝቡ ተስፋ እንዲኖረው አዲሱ ዓመት ከአሮጌው ዓመት የተለየና ተስፋ ሰጪ እንዲሆን ሊወስዳቸው ያሰባቸውን ርምጃዎች በቆራጥነት ማሳወቅ ይገባዋል። እንደ ሀገር በተቻለ መጠን ሕዝብ እምነትንና ተስፋን እንዲሰንቅ ማድረግ ያስፈልጋል።
ማህበረሰቡም ቢሆን ሁሌም ቢሆን ለውጥ ከውጭ ሳይሆን ከራሳችን የምናመነጨውና ብዙ ለውጦችን ማምጣት የምንችል መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ስለዚህም የግለሰብ ዕቅድ እንዲሳካ የሀገር ዕቅድ መሳካት ይገባዋል። አዲስ ዓመት ሲመጣም ሰዎችም ስለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ስለሀገራቸውም ማቀድ ይጠበቅባቸዋል። ሀገር ሰላም እንድትሆን፤ ልማቷ እንዲፋጠን፤ አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲዳብር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ሀገራችን ላይ እያጋጠሙን ያሉ የሰላም መደፍረስና ሌሎችም ችግሮች አሉብንና ህብረተሰቡ አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ምን ዓይነት የአእምሮ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል?
አቶ ጌታ፦ ችግሩ እያለ ችግሩን እንርሳው ወይም እንተወው ማለት አይቻልም፤ በተለይም እኛ ያሉብንን ችግሮች ሁሉ ረስተን አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ መቀበል የምንችልበት ቁመና ላይ እንገኛለን ብዬ አላስብም። ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት እንደ ሕዝብ ያለን ቆራጥነት ምን ይመስላል? የሚለውን ማየት ግን ይቻላል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እንደ ማህበረሰብ ተስፋ ያስፈልግናል። በተለይም እኔ እንደግለሰብ የማደርገው ነገር ሀገሬ ላይ ለውጥ ያመጣል ብሎ ማሰብ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
እንደ ሕዝብ ብዙ ጫናና ችግሮች የተደራረቡብን ጊዜ ላይ ብንሆንም ዘመን ሲለወጥ ግን ማሰብ ያለብን ቀናውንና እስኪ በአዲሱ ዓመት ነገሮችን ላስተካክል ልፍታ ብለን ተነሳሽነት የሚያድርብን ሊሆን ይገባል፤ እኔ የምወረውራት አንዲት ጠጠር ወይም የምሰራት ትንሿ ሥራ ሀገሬ ላይ ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽኦ አላት ብሎ ማመን ያስፈልጋል።
ይህንን ብለን ከተነሳን ደግሞ ማየት የምንፈልገው ለውጥ ይመጣል የሚል ሀሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ባለሙያ ሀገርና ሕዝብ አዲሱን ዓመት እንዴት መቀበል አለባቸው ብለው ይመክራሉ?
አቶ ጌታ ፦ ሕዝቡ እኔ የማደርገው ነገር ከእኔ አልፎ ሀገሬ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብሎ የሚያስብበት፤ መንግሥት ኃላፊነቶቹን ለመወጣት ፍቃደኛ የሚሆንበት ዘመን ሊሆን ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ጌታ ፦እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም