ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ግብር የመክፈል ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ኢኮኖሚዋ ከሚያመነጨው አንጻር ተመጣጣኝ የሆነ ገቢ መሰብሰብ ተስኗት የቆየ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ተሰበሰበ በተባለባቸው ወቅቶች ሁሉ ተያይዞ የሚነሳውም ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት አኳያ ሲታይ የሚሰበሰበው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን ነው። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ቆይተዋል፤ ከእነዚህም መካከል የግብር ከፋዩና የገቢ ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት በመግባባት፣ በታማኝነትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የግብር አከፋፈል ሥርዓት ማስፈን አለመቻላቸውን በቀዳሚነት መረጃዎቹ ይጠቀሳሉ።
ለሀገራዊ ገቢ ዕድገቱ ዓይነተኛ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ሁለት አካላት በተለየ ቅርበትና በባለቤትነት ስሜት ካልተንቀሳቀሱ በስተቀር ሀገራዊ ገቢውን ማሳደግ እንደማይቻል ይገለጻል። ለዚህም የገቢ ግብር ሰብሳቢ ተቋም ሀገራዊ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን በመገንባት፤ ምቹ፤ ቀላልና ፍትሕዊ አገልግሎት በመስጠት፤ ግብርን በፍቃደኝነት የመክፈል ባህል እንዲዳብር የማድረግ ኃላፊነት ይኖርበታል። በተመሳሳይ የገቢ ዕድገቱን ለመጨመር ግብር ከፋዩ ግብር የመክፈል የውዴታ ግዴታ መሆኑን አምኖ በታማኝነትና በፈቃደኝነት የመክፈል ባህሉን ማሳደግ ለገቢ ዕድገት አይነተኛ ድርሻ እንዳለው ይታመናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገሪቷ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር የገቢ ዕድገቱ ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም፣ የገቢ መጠን ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ከገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በዋናነት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ቀዳሚ ሥራው የላቀ ገቢ መሰብሰብ ሲሆን፤ ቢሮው የሚሰበስበው የገቢ መጠን ከዓመት ዓመት መሻሻል እየታየበት ስለመምጣቱ አስታወቋል። አያይዞም ከተማዋ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር ሲታይ ገቢ የመሰብሰብ አቅሙ ገና እንደሚቀረውም ጠቁሟል።
በገቢ ግብር አሰባሰብ ረገድ ቀሪ የቤት ሥራዎች ስለመኖራቸው የሚያምነው ቢሮው በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት የተሻለ ገቢ ሰብስቧል። ቢሮው እንዳስታወቀው፤ በበጀት ዓመቱ 100 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከዕቅድ በላይ 109 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ችሏል። ይህም ባለፉት ዓመታት ከነበረው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ለውጥና መሻሻል የታየበት ሆኗል።
የግብር ሥርዓት ውስጥ ያልገቡትን በሕጉ መሠረት ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ በማድረግና ወቅቱን ያላገናዘብ ግብር የሚከፍሉትንም ወቅታዊ እንዲሆኑ በማድረግ የገቢ መጠኑ በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 37 ቢሊዮን ብር ገቢ ተነስቶ በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት 109 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። ከተደረገው ማሻሻያ በተጨማሪ የግብር ከፋዩ ቁጥር መጨመርም ለገቢው ማደግ ዓይነተኛ ድርሻ አለው ነው።
ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከወጪ ንግድ የቀረጥና ታክስ ገቢን የሚሰበስበው የገቢዎች ሚኒስቴር በበኩሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት እንደቻለ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢ በበጀት ዓመቱ 266 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 264 ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፤ በዚህም የዕቅዱን 99 በመቶ ማሳካት ችሏል።
ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ እንዲሁ 183 ነጥብ 34 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 177 ነጥብ 68 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ ነው የዕቅዱን 96 ነጥብ ዘጠኝ ማሳካት የቻለው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የላቀ ገቢ ለመሰብሰብ ባደረገው ጥረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ አጠቃላይ 450 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 442 ነጥብ 03 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ 31 ነጥብ 28 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ገቢ የሀገር ሕልውናን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ፤ በበጀት ዓመቱ የተሻለ ገቢ መሰብሰብ የተቻለ ቢሆንም ከተማዋ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር ገና ብዙ መሥራት ይጠይቃል ይላሉ።
የዜጎችን የመልማት ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም ማህበረሰቡ በየጊዜው ለሚያነሳቸው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ መስጠት የሚቻለው ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ሲቻል ነው የሚሉት አቶ አደም፤ ለዚህም ግብር ከፋዩ ግብሩን በታማኝነትና በራስ ተነሳሽነት መክፈል እንዳለበትና ገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤትም ከግብር ከፋዩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንዳለበት ነው የሚያስረዱት።
እሳቸው እንዳሉት፤ ግብርን በፈቃደኝነትና በታማኝነት ከመክፈል አንጻር በማህበረሰቡ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመጡ ለውጦች ቢኖሩም ለውጡ የሚፈለገውን ያህል ነው ማለት አይቻልም። ይሁንና ዛሬም ሀገሪቱ ያልተሻገረቻቸው በርካታ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ግብር መክፈል እየተሻሻለ መጥቷል። ግብርን በታማኝነትና በራስ ተነሳሽነት የሚከፍሉ እንዳሉ ሁሉ ከግብር የሚሸሹ ሰዎች በርካቶች ናቸው። ይሁንና ግብር መክፈል ‹‹የውዴታ ግዴታዬ ነው›› ብለው የሚያምኑ ግብር ከፋዮች በመኖራቸው ምክንያት ቢሮው የሚሰበስበው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
ገቢው በተለያዩ ምክንያቶች እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ አደም፤ ከምክንያቶቹ የግብር ከፋዩ ቁጥር መጨመር አንዱ መሆኑን አመልክተዋል፤ ጠንካራ ክትትልና ቅንጅታዊ አሰራርን ጨምሮ የቤት ግብርን ዋጋ ወቅታዊ ማድረግና የማይከፍሉ ሰዎችን ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉ ለገቢው መጨመር ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ሕጉ እያለ የፍትሕዊነት ችግር ያለባቸውን ጉዳዮች ማሻሻያ ማድረግ ተችሏል። የቤት ባለይዞታዎች ለመሥሪያም ሆነ ለመኖሪያ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ቦታ ከያዙ በሕጉ መሠረት ግብር እንዲገብሩ ተደርጓል።
በቀጣይም ገቢ እንዲጨምር የፍትሐዊነት ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም ማሻሻያ የሚፈልጉና የገቢ መጠንን መጨመር የሚያስችሉ ጉዳዮችን በጥናት በመለየት ከተማዋ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚሠራ አመላክተዋል።
ሀገራዊ የገቢ መጠንን ማሳደግ የሀገር ሕልውናን ለማጽናትና የማህበረሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ወሳኝ ስለመሆኑ በምጣኔ ሀብትና ተያያዥ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ለዚህም መንግሥት የታክስ ፖሊሲን ከማሻሻል ጀምሮ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ፣ ከንክኪ የጸዳ ማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር ግብር ከፋዩ አምኖበት በታማኝነት መክፈል የሚችልበትን ዕድል መፍጠር እንዳለበት ይናገራሉ።
የሕዝብ አስተዳደርና የፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ገመቹ አራርሳ በጨፌ ኦሮሚያ የመንግሥት በጀትና ንብረት ቁጥጥር የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ለአንድ ሀገር ልማት፣ ለአገልግሎት አሰጣጥና ማንኛውም ሰላማዊ ሁኔታን ለማረጋገጥ መንግሥት ገቢ ሊኖረው ይገባል። ለዚህም ገቢ የሚያመነጭ ዜጋ ሁሉ ለመንግሥት ታክስ መክፈል መቻል አለበት። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው ሀገሪቷ ያላትን አቅም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅሞ ሃብት የሚያፈራ በመሆኑና የታክስ ዋና መርሆም ያለው ለሌለው መስጠት በመሆኑ የአንድ ሀገር ሃብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል ይኖርበታል።
የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ ግብር አሰባስቦ የልማት ሥራዎችን መሥራትና የሀገሪቷን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ሲሆን ማንኛውም ገቢ ያለው ሰው ደግሞ እንደ ገቢ መጠኑ ግብር ለሀገሩ መክፈል የዜግነት ግዴታው ነው። በሀገሪቱ ያለው የገቢ አሰባሰብ ሂደት ኋላ ቀርና የሚሰበሰበው ገቢም ዝቅተኛ መሆኑን ዶክተር ገመቹ ጠቅሰው፣ ማህበረሰቡ ካለው የልማት ፍላጎትና የመገልገል ጥያቄ አንጻር መንግሥት ያለው ሃብት በቂ አይደለም ብለዋል። ይህም የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው አቅም አንጻር የሚሰበሰበው ገቢ በቂ አለመሆኑን እንደሚያመለክት ይገልጻሉ።
ገቢያችን ኢኮኖሚያችንን መምሰል አለበት የሚሉት ዶክተር ገመቹ፤ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የገቢ ግብር አሰባሰብ አይነቶች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፣ በሀገር ደረጃ በተለይም በክልል ደረጃ ቀጥተኛ የታክስ አሰባሰብ ትልቁን ድርሻ መያዙን ነው ያመለከቱት። ይህም ለገቢ ዕድገቱ ዝቅተኛ መሆን ዋናው ምክንያት ነው ይላሉ። ገቢው እሴት የማይጨምርና ከፔሮል ላይ በቀጥታ ያለምንም ድካም የሚሰበሰብ እንደሆነ ገልጸው፣ የመንግሥት ትኩረት መሆን ያለበት ቀጥተኛ ባልሆነ የገቢ ግብር አሰባሰብ ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል። ይህም ትላልቅ ከሆኑ ኢንቨስትመንትና የተለያዩ ቢዝነሶች ጋር የተያያዘ ታክስ መሆኑን ተናግረው፣ እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል።
ሌሎች ዜጎች በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታና ክብር መሆኑን አምኖ መክፈል አለበት የሚሉት ዶክተር ገመቹ፤ ለዚህም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በስፋት መሥራት እንዳለበት ነው የሚጠቅሱት። ከዚህ በተጨማሪም ታክስ የሚሰበሰብበት ሁኔታና የግብር ከፋዮች መረጃ የሚያዝበት አግባብ ዘመናዊ አለመሆኑ በራሱ ለገቢ ዕድገቱ መቀነስ ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑን አመልክተው፣ የተጀመረው የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የሕግ ክፍተቶች ያሉባቸው ጉዳዮች ስለመኖራቸውም ዶክተር ገመቹ ጠቅሰው፣ በዋናነት የቢዝነስ ታክስ አሰባሰብ ላይ ሰፊ ክፍተት ስለመኖሩና ከፍተኛ ገቢ የሚሰበሰበውም ከዚሁ በመሆኑ መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በቅድሚያ ግብር ከፋዮቹን መለየት፣ ማሳወቅና ማበረታታት እንደሚያስፈልግና አለፍ ሲልም አስፈላጊውን ርምጃ በመውሰድ ተገቢውን ግብር መክፈል እንዲችሉ ማድረግ እንዲሁም መቆጣጠር ከመንግሥት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉና በምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ሥራዎችን በመሥራት የሚታወቁ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ፤ የሀገሪቱን የገቢ አሰባሰብና የገቢ መጠን አስመልክተው በሰጡት ሃሳብ ኢትዮጵያ ከምታመርተው የምታገኘው ሀገራዊ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ዕድገት እያሳየ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ባለሙያው ከሀገሪቷ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ 20 በመቶው የመሰብሰብ አቅም ቢኖረውም ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ ያህሉ ብቻ እየተሰበሰበ እንደሆነ ነው ያስረዱት። ይህም ማለት ሀገሪቷ አመርታለሁ ከምትለው ዓመታዊ ሀገራዊ ምርት አንጻር አሁን ያለው ገቢ እየቀነሰ መሆኑን የዓለም ባንክ ዳታን ዋቢ በማድረግ ያስረዳሉ።
የገቢ ምጣኔ ዕድገት የሚለካው ከዓመት ዓመት በሚመዘገብ የቁጥር ለውጥ አለመሆኑን ያነሱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፤ የገቢ ምጣኔ ዕድገት መለካት ያለበት ከሀገሪቷ አጠቃላይ ገቢ አንጻር እየተሰበሰበ ያለው ገቢ እየጨመረ ሲመጣ ነው ይላሉ። በዚህ ረገድ ሲታይ ደግሞ ገቢው እየጨመረ አለመሆኑን ነው ያስረዱት።
ገቢው እንዲጨምር ምን መደረግ አለበት ችግሩ ምንድነው ስንል ላነሳነው ጥያቄም የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ሲመልሱ፤ በርካታ ቴክኒካል ጉዳዮች እንዳሉ ነው የገለጹት። እሳቸው እንዳሉት፤ በዋናነት የታክስ ፖሊሲውን በየጊዜው መፈተሽና ጠንካራና ደካማ ጎኑን በመለየት ጠንካራ ፖሊሲ ማውጣት አንደኛው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በፖሊሲ የተቀመጠውን በጠንካራ አስተዳደር ማስፈጸም ነው። እነዚህ ሁለቱ ቁልፍ ጉዳዮች ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት ገቢውን ለማሳደግ ወሳኝ ናቸው።
ለአብነትም የውጭ ኩባንያ በዓመት ውስጥ አምርቶ ለገበያ ያቀረበው ምርት ትርፍ አላስገኘልኝም፣ ኪሳራ ውስጥ ገብቻለሁ ካለ ኪሳራውን ለማካካስ በቀጣይ ዓመት ታክስ የማይከፍልበት ሕግ ስለመኖሩ ተናግረዋል። ይህም ለታክስ ገቢው መቀነስ አይነተኛ ድርሻ እንዳለው ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንቨስትመንት ማበረታቻ በማለት ከፍተኛ ታክስ እያጣ ስለመሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ይናገራሉ። በተጨማሪም ድርጅቶቹ ከውጭ ዕቃ ሲያስገቡ የጉምሩክ ቀረጥ አይከፍሉም። እነዚህንና ሌሎች ከታክስ ሕግ ጋር ተያይዘው ያሉ ጉዳዮችን ማጥናትና የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ የገቢ መጠንን ለማሳደግ መፍትሔ ነው ሲሉም ያብራራሉ። ይህን ማስተካከል ከተቻለ በትንሹ ከጠቅላላው ሀገራዊ ዓመታዊ ምርት አምስት በመቶ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ነው ያስረዱት።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመትን ለመሳብ በሚል ሀገሪቷ ከፍተኛ ገቢ እያጣች ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ታክስን ከማስቀረት ይልቅ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ቀልጣፋ ማድረግ መፍትሔ እንደሆነ ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የኢንቨስትመንት ካባቢን ጤናማ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት ማግኘት የኢንቨስተሮች ምርጫቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በጥናት የተረጋገጠ ነው ይላሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንዳሉት፤ የዜጎች የገቢ አለመመጣጠን ከገቢ ግብር አሰባሰብ ክፍተት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፤ መንግሥት በተለይም ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ ሰፊ ርብርብ በማድረግ እንዲሁም ታክስ በሚሰውሩና በሚያጭበረብሩት ላይ ደግሞ አስፈላጊውን ርምጃ በመውሰድ ገቢውን ማሳደግ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ግብር ከፋዩ ግብር ሲከፍል ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ያለበት ቢሆንም፣ እርካታው ዝቅተኛ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ የግብር ከፋዩን እርካታ ለማሳደግ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አስታውቀዋል። ሰዎች በፍላጎትና በታማኝነት ግብርና ታክስ መክፈል እንዲችሉ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሠራት እንዳለበትም አጽንኖኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም