ዘመን መለወጫ እና አደይ አበባ

ኢትዮጵያውያን ተከባብረንና ተፈቃቅረን እንጂ ተነጣጥለን የምናከብረው አንድም ክብረ በዓል የለንም። በቅድሚያ ሁሉም የሀገራችን ዜጎች በጋራ ለምናከብረው በዓል እንኳን በጤና አደረሳችሁ!! እንኳን አደረሰን!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸውና ከሚያዘክራቸው በዓላት አንዱና ተወዳጁ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። እንደ ዕፅዋት ሁሉ ሰውም በወርሃ መስከረም በተስፋ ስሜት ይለመልማል። ከዋዜማው ጀምሮ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጎዘጉዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል።

በተለይ ልጆች አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። የአዲሱ ዓመት መባቻ አንድ ብሎ ሲጀምር በውብ ቢጫማ ቀለማቸው ዙሪያ ገባውን የማፍካት ተፈጥሮአዊ ጸጋን ተጎናጽፈው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ወይም ዘመን መለወጫ በዓልን ይበልጥ ያደምቁታል።

በአረንጓዴ ቅጠሎቻቸው፣ በቢጫ ቀለም አበቦቻቸው ደምቀው ሲታዩም ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አላቸው። የተስፋ፣ የልምላሜ፣ የሰላም፣ የምኞት መግለጫ ተደርገውም ይታሰባሉ።

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር /የጊዜ ቀመር/ አንድ ዓመት በውስጡ አሥራ ሦስት ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፤ ከእነዚህ አራቱ ክፍላተ ዘመን (ወቅቶች) ከሚባሉት ጊዜያት አንዱ ክረምት ነው።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ክረምቱ ሰኔ 26 ቀን ጀምሮ መስከረም 25 ቀን ያበቃል። የዘንሮው ክረምት ግን ከተለመደው ጊዜ ቀደም ብሎ መዝነብ የጀመረ መሆኑም ብዙዎች ይጋሩታል።

መስከረም የኢትዮጵያውያን ዘመን መለወጫ (አዲስ ዓመት)፣ እንቁጣጣሽ፣ አደይ አበባ… ”ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም፤ በእርግጥ የየራሳቸው ልዩ መገለጫዎች ቢኖሯቸውም ሁሉም የወርሃ መስከረም ስጦታዎች ወይም ገጸ በረከቶች ናቸው።

እንዲያው ከኖርንበትና ከምናውቀው እውነታ ጨልፈን፣ ከማህበረሰቡ የልማድ ተሞክሮ፣ ከሃይማኖት ሊሂቃንና ከተለያዩ የምሁራን ጥናቶች ተነስተን እውነታውን በወፍ በረር ለመቃኘት እንሞክር።

የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል በቀድሞው የ3ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መጽሐፍ ላይ ስለ ሁሉም ወራቶች ባህራይትና ግብር በዘረዘሩበት”የዓመቱ ወራት የሚል ርዕስ በሰጡት ግጥማቸው ውስጥ፦

“ጨለማው ሲጠፋ ዝናቡ ሲያቆም፣

ያ የለውጥ ወራት መጣ መስከረም።

ሰዎች ይነሳሉ ሊሰሩ ታጥቀው፣ መስከረም ነውና ብርሃን ሰጪው። ” ማለታቸው አይዘነጋም።

ጋሼ መንግስቱ ለማ፦ “የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣ ምን ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ።” ማን ያውቃል? ብሎ ተቀኝቷል። ለመሆኑ አደይ አበባና የመስቀል ወፍ ዓመቱን ሙሉ ተሰውረው ሳይታዩ ከርመው የመገናኛ ጊዜያቸውን በጋራ ስምምነትና ውሳኔ በቀጠሮ አስቀምጠውት የሄዱ በሚመስል አኳኋን ወርሃ መስከረምን ጠብቀው አብረው የሚከሰቱበት ምስጢር ምንድነው ?።

እውነታው አጃኢብ አያስብልምን? አደይ አበባስ ለምን ይሆን በፀደይ ወራት ብቻ ታይቶ የሚጠፋው? መቼም ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለማግኘት ተፈጥሮ ረቂቅና እጅግ ጥልቅ ነውና ሠፊ ምርምር፣ ብዙ ጥናት ማድረግ ብቻውን አይበቃም፤ ይህንን እውነታ በተጨባጭ ለማስረገጥ መለኮታዊ መሰጠት(ተሰጥኦ) እንደሚሻ ይሰማኛል።

ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-እፅዋት መምህር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ፣ የአደይ አበባንና የመስከረም ቀጠሮ የሚመሳስሉት ከሰዓት ጋር ነው። “ማታ ተኝተን ጠዋት እንድንነቃ ሰዓት እንሞላለን፤ ልክ እንደዚያው እፅዋት የራሳቸው ጉዳዮች ከተሳካላቸው፣ የሚፈልጉትን መጠን ዝናብና ፀሐይ ካገኙ’አሁን ነው የምታብቡት’ የተባሉ ይመስል ሰዓቱን፣ ቀኑንና ወሩን ሳያዛንፉ በተፈጥሮ ውስጣዊ ግፊት ያብባሉ ይህም ‘ባዮሎጂካል ክሎክ’ በመባል ይታወቃል።

መስከረም 1 የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የሚጀመርበት አዲስ ዘመን ነው፤ ይህ ጊዜ ርእሰ ዐውደ ዓመት የሚባልበትና የርእሰ ዐውደ ዓመቱ መጠሪያ እንዲሆን አባቶች ደንግገዋል። ዕለታቶቹ በሙሉ የሚገለፁበትና የተሰየሙበት ምክንያታዊ መጠሪያ አላቸው። ለምሳሌ ከመስከረም 9 እስከ 15 ባሉት 7 ቀናት ወይም ዕለታት መካከል “ፍሬ”፣ “ተቀጸል ጽጌ”(አበባን ተቀዳጅ) ተቀጸል ጽጌ ልዩ የመዝሙርና የጸሎት ሥርዓት” የሚባሉ ሲሆን የተዘራው ዘር ደርሶ ለፍሬ መብቃት የሚጀምርበት ጊዜ ነው።

ገበሬው የተዘራው ዘር ሁሉ ለፍሬ ባይበቃም አብዛኛዎቹ ፍሬዎች አፍርተው እሸት መብላት የሚጀመርበት ወቅት ስለሆነና ገበሬው ያሳለፈው ውጣ ውረድና ድካም በከንቱ ሳይቀር ለፍሬ የሚበቃበት ወቅት ስለሆነ ዘሩንም ከተለያየ አደጋ አትርፎ ለፍሬ ያበቃው ፈጣሪ የሚመሰገንበት ጊዜ ነው።

የኃይማኖት ሊሂቃን አባቶች በበኩላቸው “ከመስከረም 17 እስከ 25 ድረስ ያሉ 9 ቀናት(ዕለታት) ደግሞ መስቀል የሚል ስያሜ መያዛቸውን ይገልጻሉ፤ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እያንዳንዱ ቀን (ዕለት)፣ ሳምንት፣ ወር፣ ወቅት(ዘመን) በታላላቅ ሐይማኖታዊ የመጠሪያ ምክንያቶች የተሰየመ ሆኖ የሰው ልጅ ሕይወት ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን የሚሸጋገርበት፣ ከእርኩሱ የዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ የሚወጣበትና ሠናይ የፀደይ ዜና የሚታወጅበት ነው”ይላሉ።

በተጨማሪም…ዶክተር ሃብተማርያም አሰፋ “የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች” በሚለው መጽሐፋቸው “መስከረም” መስ-ከረም” ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው። የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት፣ ፀሐይ የምትወጣበት፣ ወንዞች ንጹሕ ውሃ፣ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚቆጠቆጡበት ነው›› ይሉታል።

እንዲህም በመሆኑ የጨለማ የችግርና የአፀባ ጊዜ የሚያበቃበት የብርሃን፣ የደስታ የእሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው ብሎ ሕዝቡ ስለሚያምንበትም የዕንቁጣጣሽ በዓልን ከሁሉ አብልጦ ግምት ስለሚሰጠው በእሳት ብርሃንና በእሳት ቡራኬ በየቤቱ እንደ ሁኔታው ከብት አርዶ፣ደግሶ ይቀበለዋል።

በወርኃ መስከረም መሬቷ በአደይ አበባ አሸብርቃ ስለምትታይና በተለይም ዕንቁ የመሰለ አበባ ስለምታወጣ መሬቷን ዕንቁጣጣሽ፣ ዕንቁ የመሰለ አበባ አስገኘሽ ለማለት ‘ዕንቁጣጣሽ’ ተብላለች። አቧራ፣ ቡላ የነበረው መሬት በዝናቡ ኃይል ለምልሞ ተመልከቱኝ፣ ተመልከቱኝ የምትል ያሸበረቀች፣ አበባ የተንቆጠቆጠች ሆነች የሚል- ለዕንቁጣጣሽ ስያሜ መነሻ ሊሆን እንደሚችል መዛግብት ይጠቁማሉ።

አበው “መስከረም በአበባ፤ ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል”። አንድም መስከረም ርዕሰ-ዓውደ ዓመት፣ የዘመን መለወጫ በመሆኑ ወርሃ አደይ፣ ወርሃ ጽጌ እፁብ ጌጡ ነው ይባላል። ለዚህ አብነቱ “ኢትዮጵያውያን በርዕሰ-በዓልነት ታላቅ ማዕዘን ላይ ያስቀመጡት ወርሃ መስከረም፣ ትልቅ የሆነ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ፋይዳን የያዘ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል።” ብለው በመተንተን ገለፃውን አጠናክረውታል።

ታዲያ ከዕንቁጣጣሽ በዓል ቀጥለው በሰፊው ከሚታወቁት በዓላት መካከልም፤ ተቀጸል ጽጌ፣ ዳመራ፣ የመስቀል ሥነ-ሥርዓት በአጠቃላይ ወርሃ መስከረም በተለያዩ ዐውደ በዓሎች ድምቅምቅ የሚል ልዩ ወር ነው ማለት ይቻላል፤ በዚህ ወር ብቻ ታላላቅ የበዓል አከባበር ሥርዓቶች ይከናወናሉ።

የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችም የዘመን መለወጫ በዓሎቻቸውን ያከብራሉ፡፡ በእነዚህ ክብረ በዓላት ውስጥ በርካታ የዳበሩ እሴቶች ያሉ ሲሆን በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት ቂም እና ቂያሜን በይቅርታ ሽሮ በአዲሱ ዓመት፣ በአዲስ የሥነ-ልቦና ዝግጅት፣ በብሩህ ተስፋ ለአብሮነት መነሣት በየብሔረሰቡ ተወላጆች የሚከናወን ተግባር መሆኑ የተለመደ ነው።

እንደ ዕፅዋት ሁሉ ሰውም በወርሃ መስከረም ላይ በተስፋ ስሜት ይለመልማል። ከዋዜማው ጀምሮ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጎዘጉዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል፤ በተለይም ልጆች አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ።

በአመሻሽ ላይ ደግሞ ችቦ አቀጣጥለው “እዮሃ አበባዬ፣ መስከረም ጠባዬ፣ እዮሃ…የበርበሬ ውሃ” እያሉ ያዜማሉ። እናም!! አደይ አበቦች የምድር ገፀ በረከቶች፥ የውበት ምስጢራት፥ልዩ እና ብሩህ ካባዎች ናቸው።

አደይ አበባን ያለ ዘመን መለወጫ ዘመን መለወጫን ያለ አደይ አበባ ማሰብ ለኢትዮጵያውያን ማይታሰብ ነው። ለመሆኑ አደይ አበቦችን ከሌሎች የዕፅዋት ዝርያቸው የሚለያቸው ባህሪ ምንድን ነው? ከውበት ባለፈ የሚሠጡትስ ጥቅም ምን ይሆን? ።

ከዓመታት በፊት በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያደረጉት ዶክተር በላይነህ አየለ ሙያዊ የማብራሪያ ገለጻቸው ላይ “አደይ አበባ ከሳር ዝርያዎች ይመደባል። ስሩ አጭር በመሆኑ ከላይኛው የመሬት ክፍል የሚገኙ ማዕድናትን ለምግብነት ይጠቀማል። የበጋውን ደረቃማ የአየር ንብረት ተቋቁሞ የክረምቱ እርጥበታማ የዝናብ ወቅት መምጣቱን ሲያጤን ከተኛበት ተፈጥሮአዊ እንቅልፍ ይነቃል።

በወርሃ ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ ለምልሞ በወርሃ መስከረም መግቢያ መጀመሪያ ቀናት “የአማርኛው አደይ አበባ ወይም የመስቀል አበባ በኦሮምኛ ቋንቋ ‘ኬሎ’፣ በትግርኛ ደግሞ ‘ገልገለ መስቀል’ ተብሎ የሚጠራው እፅዋት…በጋራና ሸንተረሮች አናት ላይ፣ በወንዞች ዳርቻ ዙሪያ አልፎ፣ አልፎ መፍካት ይጀም ራል።

የአዲሱ ዓመት መባቻ አንድ ብሎ ሲጀምር ግን በውብ ቢጫማ ቀለማቸው ዙሪያ ገባውን የማፍካት ተፈጥሮአዊ ጸጋን ተጎናጽፈው አዲሱን ዘመን መለወጫ የኢትዮጵያን በዓል የበለጠ ያደምቁታል። በአረንጓዴ ቅጠሎቻቸው፣ በቢጫ ቀለም አበቦቻቸው ደምቀው ሲታዩም ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አላቸው። የተስፋ፣ የልምላሜ፣ የሰላም፣ የምኞት መግለጫ ተደርገውም ይታሰባሉ” ብለዋል ዶክተሩ።

በአደይ አበባ የተፈጥሮ ዑደትና ልዩ ባህሪያት ያደረጉትን ጥናታቸውን ዶክተሩ ሲተነትኑ “አደይ አበቦች የወቅቱን ሙቀት መጨመርና መቀነስ መረዳት የሚያስችል ልዩ ባህሪ እንዳላቸው፤ የሙቀት ሂደቱ ሲጨምር ከእንቡጥነት ወደ ማበብ፣ ከማበብ ወደ ዘርን ተክቶ መክሰምና ለቀጣይ ዓመት ብቅለት ራሳቸውን እንደሚያሸጋግሩ ይህ ባህሪያቸውም ከሌሎች የሳር ዝርያዎች በተለየ ተርታ እንዲመደቡ ያደርጋቸዋል” በማለት አስረድተዋል።

አደይ አበቦች ከሚሰጡት ተፈጥሮአዊ ድምቀት ባለፈም የአካባቢ ሥነ ምህዳር ሚዛንን ለመጠበቅ ቁልፍ ሚና አላቸው። ከፍተኛ ማር ለማምረት የሚውል ንጥረ ነገር በውስጣቸው አላቸው፤ በዚህም ምክንያት በማር ምንጭነቱ ይታወቃል። ታዲያ ንቦች ይህን ንጥረ ነገር በመቅሰም ማር ያዘጋጃሉ።

ሰዎች ደግሞ ከንቦች የሚያገኙትን ተፈላጊ የማር ምርት ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነት ይጠቀሙበታል። ለገበያ አቅርበውም ኢኮኖሚያቸውን ይደግፉበታል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚታየው ደግሞ በከተሞች አካባቢ አደይ አበባ በባህላዊ ቀሚስ እና በካናቴራ ላይ ታትሞ አሊያም ተጠልፎ የሚሸጥበት አጋጣሚ በርክቷል።

እናቶችና ወጣቶችም ኑሯቸውን ለመደገፍ ከቄጠማ ጋር ቀላቅለው ስለሚሸጡት የዕለት ጉርስም ለመሆን ችሏል። እንዲሁም በክረምት ወራት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። አደገኛ ጎርፍ ለም መሬትን እንዳይጎዳ በስሮቻቸው የመሸርሸር አደጋን ይከላከላሉ። በእርጅና ወቅታቸውም አገዳቸው፣ ስራቸው እና ቅጠላቸው ስለሚበሰብስ ለመሬት ለምነት መጠበቅ ያገለግላሉ።

በተጨማሪም ስለ አደይ አበባ የተፃፉ የሥነ ጽሁፍ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ ቅጠሎቻቸውና አበቦቻቸውም ሰዎችን ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ የሚያስችል ፍቱን መድሃኒት ለማዘጋጀት ይጠቅማሉ። የታሪከ ተመራማሪ ፕሮፌሰር መስፍን ታደሰ ከ35 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ባደረጉት ጥናት አደይ አበባዎች ጋራና ሸንተረሩን፣ ሜዳና ተራራውን ከማስጌጥ ባለፈ በተለያዩ አደጋዎች ለሚከሰቱ የደም መፍሰሶች፤ በተለይም እናት ሴቶች ወልደው ደም እየፈሰሰ አልቆም ካላቸው ጨቅጭቀው ጭማቂውን ከጠጡ የሚፈሰውን ደም እንደሚያስቆምላቸው፣ፀረ-ተዋህስ/Anti-infction/ በመሆን እንደሚያገለግለም ጠቁመዋል።

ሌሎች አንዳንድ የምርምር ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ደግሞ የአደይ አበባ ለስኳር በሽታ፣ ለጭንቅላት ካንሰር ህክምና እንደሚውል ፍንጭ ሰጥተዋል። ከአደይ አበባ ክሬም ተመርቶም ወንዶች ጺማቸውን ከተላጩ በኋላ ለማለስለሻነት፣ ሴቶች ደግሞ ለማዲያት መከላከያ(ማጥፊያነት)፣ ለውበት መጠበቂያነት፣ ጭማቂው ለልብስ ማቅለሚያነት የሚውል መሆኑም ታውቋል።

በአንዳንድ ሀገሮችም ቅጠሎቻቸው ለሻይ ቅጠል አገልግሎት እንደሚውልም ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች እንደሚውል ይታመናል። አደይ አበቦች ከተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ችግሮች ጋር በተያያዘ የብቅለት ሂደታቸውም ይሁን ለፍካት የሚወስድባቸው የጊዜ ዑደት ከቦታ ቦታ ይለያያል።

ዕድሜና ጤና ከሰጠን ስለአደይ አበባ በርካታ ያልተነገሩ አስገራሚ ጉዳዮችን እየቆነጠርን ተከታታይ መጣጥፎችን እስከ ፀደዩ ማሳረጊያ ለአንባብያን ለማድረስ እሞክራለሁ። አስከዛው ለሀገራችንና ለህዝባችን ፍቅርና ሰላም ያበዛልን። ሠናይ አዲስ ዓመት!!

የአሰላው ኃይረዲን ከዲር ነኝ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You