ኢትዮጵያዊ አብሮነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል!

አብሮነት ለሰው ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብር ወሳኝ ሚና ያለው መርህ ነው። አብሮነት የተለየ ማንነትን፣ ባህልን ወይም ሃሳብን የሚያከብርና የሚያስተናግድ በሰላም አብሮ የመኖር መሠረት ነው። ዩኔስኮ የአብሮነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ያደረገው በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በቋንቋ ልዩነቶች ምክንያት ያለውን ልዩነት በመቀበል የሰው ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ በማሰብ ነው።

በልዩነቶች ምክንያት በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብና አብሮነት ለሰው ልጆች ተሳስበው መኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው። አንዱ የሌላውን ሰብዓዊ መብት በማክበርና ከሌሎች ጋር በመቻቻል መኖር ለዓለማችን ሕዝቦች ወሳኝ መሆኑን ግንዛቤ ለማስረፅ ጭምርም ነው።

ሰዎች በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በማንነት ወዘተ የተለያዩ እንደመሆናቸው አብሮ የመኖር ህልውና የሚረጋገጠው በአብሮነት ብቻ ነው። ኢትዮጵያውያን ከሌላው ዓለም የምንለይበትን የጳጉሜን ወር ስናከብር የዛሬዋን ዕለት በአብሮነት መሰየም ብቻ ሳይሆን አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል።

ኢትዮጵያ የባህል፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የመልክአ ምድር ብዝሀነትን የተላበሰች ኅብረ ብሔራዊት ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ሕዝቦቿ በአንድነት የሚቆሙበትና የሚተባበሩበት በርካታ ሀገራዊ እሴቶች አሏት። በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሟትን የውጭ ወራሪዎች ለመመከት ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በባህልና በሃይማኖት ሳይለያዩ አብረው ተዋግተው ነፃነቷን አስጠብቀዋል። ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል የመተባበርና አብሮ የመፋለም እሴት ዛሬም ጎልቶ ይታያል።

ለዚህም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ገበታ ለሀገር በመሳሰሉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉም ዜጋ በጋራ መሳተፉ ጉልህ ማሳያ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሕዝቦችን የሰላምና የአብሮነት ፍላጎት የማይመጥኑ፣ ትብብርና ወንድማማችነታቸውን ከማጠናከር ይልቅ የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያሻክሩ፤ በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት ከማጉላት ይልቅ ልዩነት ላይ የሚያተኩሩ፤ አብሮነታችንን ወደ ገደል አፋፍ የሚገፈትሩ ክስተቶች አጋጥመዋል፣ ፈትነውናልም።

በተከሰቱ ግጭቶቹ የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እንዲሁም ዜጎች ለዓመታት ከኖሩባቸው ቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት ከተወለዱበት፣ ካደጉበት እና ለዓመታት ከኖሩበት ስፍራ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም። ቀደም ባሉ ዓመታት የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች ከማጎልበት ይልቅ ልዩነቶች ላይ የተሠራው ሥራ በዝቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

በተለይ በማንነት እና በሃይማኖቶች መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ በር በመክፈት አንደኛው ወገን ሌላኛውን እንዲጠራጠር ብሎም የበዳይና ተበዳይ ትርክት እንዲፈጠር ተደርጎ ቆይቷል። የፖለቲካ ልሂቃን፣ የአክቲቪስቶች እና የአንዳንድ ምሁራን ትርክቶች ጥላቻ እንዲነግስ በር ከፍቷል። ይህም በጠነከረ አለት የተገነባ አብሮነታችንን ለመሸንቆር እየታገለ ይገኛል፡፡ ይሁንና በለውጡ ዘመን የተፈጠረውና አብቦ በመሄድ ላይ ያለው የወንድማማችነትና እህትማማችነት የአንድነት ትርክት በአሁኑ ወቅት መሠረቱን እያሰፋ በመሄድ ላይ በመሆኑ ለአብሮነታችን ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር የምትሆነው ሕዝቦቿ በአብሮነት መቆም ሲችሉ ነው። እንደ ሀገር በመጣችበት መንገድ ክፍተቶች አልነበሩም ባይባልም፣ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም ለነገው ትውልድ የሚሻገር ሠላም፣ አብሮነትና አንድነትን ማረጋገጥ ከዛሬው ትውልድ የሚጠበቅ ነው።

የሀገራችን ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡት ትስስር፣ መስተጋብርና የአብሮነት እሴቶች ለመለያየት የማያስችሉና የተሳሰሩ መሆናቸውን ማንም የሚገነዘበው እውነታ ነው። የአብሮነት እሴቶች የጎለበቱባቸው ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ሥነልቦናዊ ሁነቶች ጠንካራ ናቸው። እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት የዓለማችን ልዕለ ኃያል ያደረጋቸው አብሮነታቸው ነው። በኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች እና ልማዶች ቢኖሩም በእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ የሚያመሳስላቸው ኢትዮጵያዊ ማንነት አላቸው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የእርስ በርስ የትብብርና የአብሮነት ታሪክ ያላቸው በመሆኑ ብዙዎቹ ማኅበራዊ ግንኙነቶችና ልማዶች ተወራርሰዋል። ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያቆዩትን እሴት ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፉት በአብሮነት ብቻ ነው።

አብሮነት ከሌለ ወይም ከተሸረሸረ ውስጥ ለእርስ በርስ ግጭት ከውጭ ደግሞ ለብሔራዊ ደህንነታችን ስጋት የሚሆኑ አደጋዎችን ያስከትላል። ስለሆነም ጠንካራ ሀገር እንዲኖረን የአብሮነት እሴቶቻችንን ልንንከባከብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር ናት፡፡ አብረን ኖረናል አሁንም አብረን እየኖርን ነው፣ ወደ ፊትም አብረን እንኖራለን!

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You