የመኸር ወቅት እርሻ ልዩ ትኩረቶች

ከአራቱ ወቅቶች መካከል አንዱ የሆነውና በበጋ እና በክረምት መካከል የሚገኘው የመኸር ወቅት፣ የቀኖቹ ቆይታ የሚቀንስበት እንዲሁም የሙቀቱ መጠን ዝቅ የሚልበትና ምድሪቱ በአረንጓዴ ጸጋዋ የምታሸበርቅበት የለውጥ ጊዜ ነው፡፡

በዚህ ወቅት እጽዋት አንዳንድ ባህሪዎቻቸውን ጭምር ይቀይራሉ፡፡ የሽግግር ወራቱ ጥቂት ቢሆኑም አካባቢያዊ ለውጦች የሚታዩበት በመሆኑ ተባብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የግብርና ሚኒስቴርም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር (በተለይ ከኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር) ይህንን የመኸር ወቅት ስኬታማ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ገልጿል፡፡

እናም ሚኒስቴሩ ይህንን ወቅት ሦስት የስትራቴጂክ ዓላማዎችን መሠረት በማድረግ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው በቤተሰብና በሀገር ደረጃ ያለውን የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለውጭ ገበያ ሊውሉ የሚችሉ በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት የተለዩ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረትና የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካትና ለአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ማቅረብን የተመለከተ ነው፡፡

ወቅታዊ የመኸር ወቅት እንቅስቃሴ

የ2015/16 የመኸር ወቅት እንቅስቃሴን በተመለከተ የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን ዶ/ር እንዳሉት፤ ይህ ወቅት በግብርናው ዘርፍ ሰፊ ቦታ የሚሰጠውና በጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን፤ 573 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ ለሥራው የሚያግዙ በርካታ ተግባራትም እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ አንዱ ከክልሎች ጋር በመሆን እቅዶችን ተስማምቶና ተግባብቶ ማቀድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ተጨማሪ መሬት ከማረስ ጀምሮ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የእርሻ መሬት ጭማሬው መንስኤ የተለያየ ሲሆን፤ አንዱ በሰሜን አካባቢ በነበረው ጦርነት ሳቢያ መሬት ጦም አድሮ የነበረውን ዛሬ ላይ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉ ነው፡፡ ለአብነት ከትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ሌላው ደግሞ እስከ ዛሬ የማይዘራባቸው የነበሩ ረግራጋማ ቦታዎችን ጭምር እንዲሰራባቸው መደላድሎች መፈጠራቸው ሲሆን፤ በተደጋጋሚ የማምረትን ጥቅም የተረዱ አርሶ አደሮች በቆሎን እስከ መጨረሻው ከመጠበቅ ይልቅ በእሸትነቱ ሸጦ መሬቱን ለሌላ ሥራ ማመቻቸት መቻላቸው እንዲሁ የሚታረስ መሬት እንዲጨምር የተደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መለስ፡፡

የእርሻ መሬት ጭማሪ በመታየቱ የተነሳም በዚህ ወቅት 17 ነጥብ 59 ሚሊዮን ሄክታር ለማረስ ታስቧል፡፡ እስካሁንም 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩን በዘር ለመሸፈን ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሽ ያህሉ ማለትም ከሰባት ነጥብ 866 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማሳ በኩታ ገጠም የታረሰ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

በኩታ ገጠም ማረስ ለእርሻ ሥራው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የሚናገሩት ዶክተር መለስ፤ አንዱ አጎራባች የሆኑ አርሶ አደሮችንና መሬቶችን አንድ ላይ በማምጣት ለግብዓት አጠቃቀም፤ ለእርሻ ማሽነሪ አጠቃቀምና ለሌሎች እንክብካቤዎች እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ ላለው ሥራ የተሻለና የተናበበ ተግባር ለመከወን ያስችላል፡፡ የኤክስቴንሽን አገልግሎትን የተሳለጠ ለማድረግም እድል ይሰጣል፡፡ የምርት ጭማሬ እንዲመጣም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ይላሉ፡፡

የመኸር ወቅት ምርት ልዩ ትኩረቶች

ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ በምርት ዘመኑ ምርታማነትን ለማሳደግ 13 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 400 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴም 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር እንዲዘጋጅ ሆኗል፡፡ ቀሪው ደግሞ በቀጣይ የሚዘሩ ስብሎች ዝግጁ በማድረግ የዘር ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 11ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ ስለዚህም በዋና ዋና ሰብሎች በመኸር ወቅት እየተሰራ ይገኛል፡፡

‹‹በዚህ ወቅት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ሰብሎች መካከል አንዱ ጤፍ ሲሆን፤ ወደ አንድ ነጥብ 59 ሚሊዮን ሄክታር ለማረስ ታቅዶ እስካሁን ድረስ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በዘር ተሸፍኗል። አንዳ ንድ ቦታዎች ላይ መረጃዎችን ማግኘት አዳጋች ስለሆነብን እንጂ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ስንዴ ንም እንዲሁ ልዩ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው ነው። በዚህም በ2014/15 የምርት ዘመን ከተደረሰበት 154 ነጥብ 82 ሚሊዮን ኩንታል በ26 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል›› ይላሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ያለው ደግሞ የሩዝ ምርት ሲሆን፤ የውጪ ግዥን ለማስቀረት ታስቦ በልዩ ትኩረት የሚሰራበት እንደሆነ ዶክተር መለስ ይናገራሉ፡፡ ሀገራችን ለዚህ የሚሆን ደግሞ ብዙ ምቹ ነገሮችና ልምድ አላት፡፡ ምርቱም በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች ላይ ለወደፊትም መስፋት የሚችል ትልቅ አቅም አለ፡፡ ስለዚህም በዚህ ዓመት ብቻ አንድ ነጥብ 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሩዝ ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ 990ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏልም ነው ያሉት ዶክተር መለስ፡፡

አራተኛው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የአኩሪ አተር ልማት ሲሆን፤ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች በተለይም ለዘይት ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ግብዓት የሚሆን፤ ለእንስሳት መኖ በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውል፤ በፕሮቲን ይዘቱ በሰዎች ዘንድም በከፍተኛ መጠን ተፈላጊ የሆነ እንዲሁም እንደ ሀገርም ለውጭ ገበያ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ እየሆነ እንደመጣ የሚጠቁሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት እንዲሰራበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ ዓመት 900 ሺህ ሄክታር ለመሸፈን የታሰበ ሲሆን፤ እስካሁንም 705 ሺህ ሄክታር በዘር መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዶክተር መለስ ማብራሪያ፤ በዚህ ዓመት ከሰብልም ወጣ ብሎ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው የሆልቲካልቸር ምርቶችም አሉ፡፡ እነዚህም አትክልትና ፍራፍሬዎች፤ ሥራ ሥርና አበባ ሲሆኑ፤ በመኸር ወቅት ብቻ በ556 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለማምረት ታቅዷል፡፡ እስካሁን ባለው ወደ 390 ሺህ ሄክታሩን በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ በተለይም የፍራፍሬ ሰብሎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፍራፍሬ ኩታ ገጠም ሥራ ተጀምሯል፡፡ ገበያ ተኮር የፍራፍሬ ምርትንም ለማምረት በየዓመቱ የማስፋፋት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በተለይም የቅርብ ጊዜ ተሞክሮ የነበረው የአቮካዶ ምርት በስፋት ተከናውኗል፡፡ ይህ ሥራ እስካሁን በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ በሲዳማና በደቡብ ክልሎች በስፋት ተከናውኗል፡፡ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ የዝርያ ዓይነቶች ሳይቀሩ ተለይተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት እድል ተፈጥሯል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚውል ወደ 163 ሚሊዮን ችግኝ በልዩ እንክብካቤ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 13 ሚሊዮን በልዩ ሁኔታ የተከተበና ተክል መትከል ተችሏል፡፡ ይህም በየዓመቱ እየሰፋ የሚሄድ ይሆናል፡፡

የማዳበሪያ አቅርቦት

በ2014/15 እና 2015/16 የመኸር ወቅቶች በማዳበሪያ አቅርቦት ረገድ እንደ ሀገር ከፍተኛ ፈተና አጋጥሞ ነበር፡፡ ይህ ግን የእኛ ሀገር ብቻ አልነበረም፡፡ በሀገር ውስጥ ያለው ግጭት እንዳለ ሆኖ የዩክሬንና የሩስያ ጦርነት መኖር ነው አቅርቦቱን ፈታኝ ያደረገው፡፡ ከዚያም ቀደም ብሎ የነበረው የኮሮና ወረርሽን የችግሩ መንስኤ ነበር፡፡ በዚህም በችግሩ ሳቢያ በመጠን ብቻ ሳይሆን በዋጋም እንደ ሀገር የተፈተንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ የተፈለገውን ያህል ባይሆንም በቂ ነው የሚባለውን መንግሥት ድጎማ ጭምር በማድረግ ገቢ ማድረግ መቻሉን ያነሳሉ፡፡

‹‹ባለፈው ዓመት 15 ቢሊዮን ብር ድጎማ ሲያደርግ በዚህኛው የምርት ዘመን ደግሞ 21 ቢሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ ነው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በአነስተኛ ዋጋ እንዲከፋፈል ያደረገው›› የሚሉት ዶክተር መለስ፤ ‹‹ከግል ድርጅቶች ጋር በመነጋገርም ድጋፎች የሚጠናከሩበት እድል ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ኦሲፒ የሚባል የማዳበሪያ አምራች ድርጅት ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ድጋፍ አድርገውልን ለአርሶ አደሩ ማድረስ ችለናል›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

የሜካናይዜሽን ሥራ

የመኸር ወቅቱ ሥራ እየተከናወነ ጎን ለጎን ግብርናውን ለማዘመን አርሶ አደሩ በተለምዶ ይጠቀመው የነበረውን ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ለመቀየር የተለያዩ ተግባራት እንደተከናወኑ እንደሆኑ የሚያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህ ተግባር ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ተቅዶ ሁለት ነጥብ44 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር ማረስ ተችሏል። በተመሳሳይ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግም የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም ተግባር ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ያስተራረስ ዘዴ ለማልማት ታቅዶ ስድስት ነጥብ35 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ዝግጁ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውስጥም አምስት ነጥብ37 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗልም ነው ያሉት፡፡

የሰብል ጥበቃ ሥራ

በተባይ መከላከልና አሰሳ ዙሪያ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያለውን ባለሙያ ባሳተፈ መልኩ የተለያዩ ስልጠናዎች ከመስጠት ባሻገር በተለያዩ ቁሳቁሶችን በማቅረብ አቅምን የመገንባት ሥራ በተቻለ መጠን እየሰሩ እንደሆነ የሚጠቅሱት ዶክተር መለስ፤ እስካሁን ድረስ በነበረው የአየር ሁኔታ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ወቅቱ ለተምች መከሰት ምቹ ነበርና ሁኔታው እንደሚፈጠር ቀድሞ የታወቀበት እድል ስለነበር ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህም በኬሚካልና በሰው ኃይል የመከላከል ሥራ መሥራት ተችሏል ይላሉ፡፡

የመከላከል ሥራው እንዳለ ሆኖ የበልግም ሆነ የክረምት ወቅቱ በጣም ርጥበት አዘል ስለነበር ተባዮቹ እንዲስፋፉ እድል ሰጥቶናልና የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የግሪሳ ወፍ በዚህ በመኸር ወቅት የመከሰቻ አጋጣሚው ብዙ ነው፡፡ እናም በግብርና ሚኒስቴር በኩል በየጊዜው ክትትልና አሰሳ ይደረጋል፡፡ ማደሪያዎች የመለየት ሥራ በባለሙያዎች በልዩ ሁኔታ ይሰራል፡፡ በባህላዊም በዘመናዊም የመከላከል ሥራ ይከናወናል፡፡ ለዚህም ዝግጁ የሆኑ አውሮፕላኖች አሉ፡፡ በተመሳሳይ የበረሃ አንበጣንም ለመከላከል ልዩ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ስለዚህም ምርቱ ችግር ሳያገጥመው ለማንሳት ያለን ኃይል በመጠቀም ምርትን በወቅቱ ለመሰብሰብ ይሞከራል፡፡ እንደግብርና ሚኒስቴርም የተለያዩ የምርት መሰብሰቢያ መሣሪያዎችን በማቅረብ እገዛ የምናደርግ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

‹‹በሰብል ጥበቃ ረገድ ለወረርሽኝ መከላከያ የሚውለውን ኬሚካል ግብርና ሚኒስቴር የሚያቀርብ ሲሆን ለዚህ ተግባር የሚውል በቂ የኬሚካል ክምችት አለ፡፡ የፀረ-አረም ኬሚካሎችን ከሀገር ውስጥ አልያም ከውጭ የሚያቀርቡት የኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽን እና የግል ድርጅቶች ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ራሱ ገዝቶ ነው የሚጠቀመው። በዓይነትም በመጠንም በቂ ኬሚካል መኖሩን ግን እንከታተላለን፡፡ እጥረት ካጋጠመ መንግሥት የውጭ ምንዛሬ እንዲያቀርብ የማድረግ ሥራ ይሰራል›› ይላሉ፡፡

 ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You