ብዙ ጊዜ የእናት አባት ቤት ጭር ለማለት አይዘገይም። የደመቀ ሁካታና ፌሽታ፣ የልጆች ጸብና ጨዋታው ሁሉም ጎጆ በያዘ ማግስት ‹‹ነበር›› ይሰኛል። ቤቱም ለዝምታ እጅ ይሰጣል፡፡ ይህ ዝምታ ግን ውሎ አድሮ በልጅ ልጆች ቡረቃ ድል ይነሳል። ይህ እውነታ አያቶችን ከብቸኝነት ያወጣል። የአያት ልጅ ‹‹ቅምጥል›› እንዲሉም ልጆች እንዳሻቸው በነጻነት ያድጋሉ፡፡
የሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህም የልጅነት አስተዳደግ ከዚህ ሀቅ የሚቀዳ ነው፡፡ እሸቱ የወላጆቹን መለያየት ተከትሎ የአያቶቹ ቤት አድማቂ የሆነው የልጅነት ዕድሜውን በሳለፈበት የሰባ ደረጃ አካባቢና የቀበና ሰፈር ነበር፡፡
ህፃኑ እሸቱ በአያቶቹ ቤት እያዜመ ሲያሻው እየጨፈረ የቤቱን ዝምታ ነብስ ዘራበት፡፡ ለዚህ ውለታው የአያቶቹ ምላሽ ልዩ ነበር፡፡ የእሸቱ ድስት ብለው ለብቻ ለይተው የጣፈጠ አብልተው በእንክብካቤ አሳደጉት፡፡ የአራት ዓመት ህጻን ሳለ የቄስ ትምህርት በመግባት ፊደል ቆጥሯል፣ ወንጌል ተምሯል፣ ዳዊት ደግሟል፡፡ በተለይ ሰዓሊው ከእውቀት ባለፈ ከኪነጥበቡ ያስተዋወቀውን የኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ውለታ አይዘነጋም፡፡
እሸቱ በትምህርት ቤቱ የጥበብ መሰረት ጥሎበታል። እንደአቅም ድርሰት ለመጻፍ ሞክሮበታል፤ ቲያትር ሰርቶበታል ለቲያትሮቹ ደግሞ በስዕል ፖስተር የማዘጋጀት አጋጣሚው ነበር፡፡ አሁን ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በሀገራችን ስማቸው ከሚጠራ ሰዓሊያን አንዱ ነው፡፡ ይህ ጉምቱ ባለሙያ በስራው አንጋፋ ነውና ‹‹አንቱ›› ልንለው ወደናል፡፡
የአሁኑ ሰዓሊና መምህር እሸቱ ያኔ ከስዕል ይልቅ ልባቸው ለሙዚቃ ቅርበት ነበራት፡፡ ሙዚቃ ይሰማሉ፤ አለፍ ሲልም ያንጎራጉራሉ፡፡ የዛኔ በተማሪነት ዘመናቸው የሙዚቃ ክበብን እንዲቀላቀሉ ቅስቀሳ ተደረገ፡፡ እሳቸው ፒያኖ ለመማር ልባቸው ፈቀደ፡፡
በወቅቱ ለነበሩት የክበቡ ኃላፊና የሙዚቃ መምህር ቡድኑን ተቀላቅለው ፒያኖ መማር እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡ ይህን የሰሙት መምህር እሸቱን እጅህን ዘርጋ አሏቸው፡፡
የያኔው ትንሹ እሸቱ እንደተባሉት እጆቻቸውን ዘረጉ። የሁለተኛ ክፍል ተማሪውን ጣት በትኩረት ያጤኑት መምህር “ኦክታቭ አይዝም አሉ፡፡” ተማሪው የኦክታቭ አለመያዝ ትርጉም አልገባውም፡፡ መምህሩ ቀጠል አድርገው እንደአማራጭ ታምቡር ምታ አሉት፡፡
ምኞታቸው ፒያኖ መማር ነበርና “ምን ሲደረግ ታምቡር እመታለሁ?” ሲሉ ከሙዚቃ ትምህርቱ ተኮራርፈው ቀሩ፡፡ እሳቸው ሲገምቱ ያኔ ፒያኖ የመማር ጥያቄያቸው ሰምሮ ቢሆን ከሰዓሊነት ይልቅ ወደ ሙዚቃው አድልተው ይቀሩ ነበር፡፡ ለእሸቱ በወቅቱ ድምጽህ ደህና ነው የሚል አስተያየት ይሰጣቸው ነበር ‹‹አኩራፊ ባልሆን ኖሮ ይሄኔ ሙዚቀኛ እሆን ነበር›› ይላሉ፡፡
ሰዓሊ እሸቱ ዛሬ በሀገራችን እውቅ ሰዓሊ ሆነዋል። ሥዕልን አውቀው ያስተማሩት ደግሞ በልምድ ብቻ አይደለም፡፡ ከሀገር ውስጥ እስከ ሩሲያ በዘለቀ ትምህርት ታንጸው እንጂ፡፡ ወደ ሥዕል ትምህርት አገባባቸው ጊዜ እንደማሳለፊያ ነበር፡፡
ትምህርቱን አጠናቆ ሥራ የጀመረው ታላቅ ወንድማቸው በወጉ ይቆጣጠራቸው ነበር፡፡ ለትምህርታቸው ሲባል ከአያት ቤት ወስዶ ከእሱና ከእናቱ ጋር ኑሮ ተጀምሯል፡፡
በ1960 ዓ.ም፡፡ እሸቱ የአስራ አንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን በትጋት በሚከታተሉበት ወቅት በሀገሪቱ ታላቅ ረብሻ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርት ለአንድ ዓመት ተዘጋ፤ ቤት ውሎ በሰፈር ያልተገባ ነገር ከሚያደርግ በሚል ታላቅ ወንድማቸው “የምትሞጫጭረው ስላለ በአርት ስኩል የክረምት ኮርስ ሥዕል ተለማመድ” የሚል ሃሳብ አመጣ፡፡
ወንድምየው አርት ስኩል ሲል የገለጸው የአሁኑ አለፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የያኔው የአዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤትን ነበር። የታላቅ ምክር እምቢ አይባልምና ተማሪው እሸቱ ልባቸው ባይከጅልም ከመቀመጥ በሚል የክረምት ትምህርቱን ተከታተሉ፡፡ ኮርሱ ሲጠናቀቅ በጥሩ ውጤት አጠናቀቁ፡፡
በቀጣይ ዓመት 11ኛ ክፍልን ተምረው ሳይጨርሱ ወደ 12ኛ ክፍል ግቡ ተባለ፡፡ 12ኛ ክፍል ደግሞ ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወሰድበት ነው፡፡ በወቅቱ ፈተና መውደቅ ማለት እንደ ነውር ይቆጠር ነበር፡፡ እሸቱ ‹‹ፈተናውን አልፈዋለሁ›› በሚል በሙሉ ልብ እንዳይፈተኑ 11ኛ ክፍልን አልተማሩም። ጨነቃቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ ‹‹ጥሩ ውጤት ባመጣሁበት ትምህርት ለምን አልቀጥልም›› አሉ፡፡ ጊዜ አልፈጁም፡፡ በቋሚነት የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤቱን ተቀላቀሉ፡፡
እሸቱ ውስጣቸው የተደበቀ የሥዕል ተሰጥኦ ነበርና በአምስት ዓመት ቆይታ በየዓመቱ አንደኛ በመውጣት ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡ እሳቸው ‹‹ትምህርቴን ሳልጨርስ ሥራ አልሰራም›› ቢሉም ሥራ የተገኘላቸው ገና የዲፕሎማ ትምህርታቸውን ሊያጠናቅቁ ወራት ሲቀራቸው ነበር፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፤ የወቅቱ የሀገር ፍቅር ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ገሰሰ ለሰዓሊ አብዱረህማን መሀመድ ሰዓሊ እንደሚፈልጉ ይነግሯቸዋል፡፡ እሳቸውም ከተማሪዎቻቸው መካከል የተማመኑበትን የያኔው ተማሪ እሸቱ ጥሩነህን ይዘው ሀገር ፍቅር ይሄዳሉ። ሥራ አስኪያጁ ተስፋዬ በሰዓሊ አብዱረህማን ጥቆማ በመተማመን ወዲያው ሥራ እንዲጀምሩ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡
እሸቱ ግን ከሥራ ይልቅ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ይሹ ነበርና ቆይተው ሥራውን ሊጀምሩ ወስነው በቀጠሮ ተለያዩ፡፡ ትምህርቱ አለቀ፡፡ እሸቱ ቃላቸውን አክብረው ሥራውን ጀመሩ፡፡ ለሦስት ዓመታት በቲያትር ቤቱ ለሚወጡ ቲያትሮች፣ ፖስተሮችና መድረክ በመስራት አገልግለዋል፡፡ ሰዓሊ እሸቱ ሀገር ፍቅርን ‹‹የሕይወት ዩኒቨርሲቲዬ፣ መኖር ምንድነው? የሚለውን እውነት ያወኩበት ቤቴ ነው›› ይሉታል፡፡
ሰዓሊው ባገኙት ስኮላርሽፕ ሞስኮ በሚገኘው ሲሪኮቭ አካዳሚ ለአምስት ዓመታት የኪነቅብ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ ከጳጉሜ 1969 እስከ 1976 ዓ.ም መጨረሻ። ለትምህርት የሄዱባትን ሀገረ ሩሲያ የሚገርም የጥበብ መገኛ በማለት ይገልጿታል፡፡
እሸቱ ጥሩ አንባቢ ናቸው፡፡ ሞስኮ ደግሞ የማይገኝ የሥነ-ጽሁፍ አይነት የለም፡፡ ይህ መሆኑ የማንበብ ልምዳቸውን ይበልጥ አሳድጎታል፡፡ ሞስኮ በሚገኙ የውጭ ቋንቋዎች ቤተመጽሀፍት ውስጥ የኢትዮጵያ መጽሀፍት ይገኛሉ፡፡ በቆይታቸው ‹‹ኦሮማይ››ን ስለ ማንበባቸው ያስታውሳሉ፡፡ ሁሌም ባገኙት አጋጣሚ ስለኢትዮጵያ የተጻፈን ሁሉ ያነባሉ፡፡
እሸቱ ናፍቆታቸውን የሚያስታግሱት ስለሀገራቸው በሀገር ልጆችና በሌላ ሀገር ሰዎች የተጻፉትን ፈልጎ በማንበብ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በዚሁ ልማድ ተመርተው ከመጽሀፍት ውስጥ የሀገራቸውን ሥም ማሰስ ይይዛሉ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የእውቁ ሩሲያዊ ደራሲ የቶልስቶይ የሥብስብ ጥራዝ ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያ›› የምትል በሩሲያኛ የተጻፈች ቃል አይናቸው ትገባለች፡፡
ጥራዙ የቶልስቶይ መጽሀፎችንና እሱ የተጻጻፋቸውን ደብዳቤዎች የያዘ ነበር፡፡ የአድዋ ጦርነትን አስመልክቶ ለጣልያኖች በጻፈው ጦማርም ‹‹ልጆቻችሁን ወስዳችሁ አስጨረሳችሁ›› በሚል ጦርነትን እንዲያስቀሩ የመከረበት ክፍል ይገኛል፡፡
እሸቱ ይህን ሲያዩ የኛስ ልጆች የሚል ጥያቄ ፈጠረባቸው። ‹‹ወዳልሰለጠኑት ሀገር ወስዳችሁ አስጨረሳችኋቸው›› የሚለው አገላለጽ ጎረበጣቸው። ባህር ተሻግረው የመጡት እነሱ እያሉ እንዴት እኛ ያልሰለጠኑ እንባላለን ሲሉ ተብከነከኑ፡፡ እነሱ ቢያልቁ ሊወሩን መጥተው፣ እኛ ያለቅነው ሀገራችንን ላለማስደፈር ነው፡፡ ‹‹እንዴት ስለእኛ ማለቅ ሳይገልጽ›› ብለው ተቆጩ፡፡ ይህ እንዳለ ተክለጻዲቅ መኩሪያ በፃፉት ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› ላይ ከጦርነቱ በኋላ ጣልያኖች ምህረት ተደርጎላቸው እንደተመለሱ አነበቡ፡፡
በዚህ እውነታ ለስዕላዊ ድርሰት ጥናት ጀመሩ። የአሸነፈው ሁሉ መሀሪ ካልሆነ የዛሬ ተሸናፊ ተመልሶ የነገ አሸናፊ ስለሚሆን ምህረት ያስፈልጋል፡፡ በሚል ውስጣቸው ለተነሳ ጥያቄ ምላሽ ሰጡበት፡፡ ሥዕሉ መጀመሩን የሰሙ የአድዋ መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የሥዕል ኤግዚቪሽን ስለምናሳይ ቶሎ ጨርሰውና እናሳይ አሏቸው፡፡
በ1988 ዓ.ም በአድዋ መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል በኤግዚቪሽን የታየው “የአሸናፊው ምህረት” ሲሉ የሰየሙት ድንቅ ሥራቸው ሆነ፡፡ “ረሀብ የፈታው” የተሰኘው ሥዕላቸውም ጥሩ ሥም የቸራቸው ነው። ይህ ሥራ በ1966 ዓ.ም በሀገራችን የነበረውን ረሀብ መነሻ አድርጓል፡፡
ሞስኮ ሳሉ ለትምህርታቸው ማጠናቀቂያ የሰሩት “መይሳው ካሳ” ሌላው ተጠቃሽ ሥራቸው ነው፡፡ ይሄንን ስዕል አንዳንዶች ለምን አጼ ቴዎድሮስ አላልከውም ይሏቸዋል። ለእሳቸው ግን የአጼ ቴዎድሮስ ጀግንነት የሚጀምረው ገና ሳይነግስ መይሳው ካሳ እያለ ነው፡፡
ሚስቱ ‹‹ታጠቅ›› ብላ የሰየመችው ታሪኩ ደስ ይለኛል፡፡” ይላሉ፡፡ ስዕሉ ቴዎድሮስ ከመንገሱ በፊት ሕዝብን አስተባብሮ የተንቀሳቀሰበትን ጊዜ የሚያሳይ ነው። ለመመረቂያ በ1976 ዓ.ም የተጠናቀቀው የመጀመሪያው “መይሳው ካሳ” ሥራ በሲሪኮቭ አካዳሚ ቀርቷል፡፡
ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ አንድ የሥዕል ሀያሲ ሞስኮ ዩኒቨርሲቲ የቀረውን ሥዕል ፎቶ ተመልክቶ ድጋሚ ይስራው ወይ ይምጣ የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ እሸቱ በአስተያየቱ መነሻ ሥዕሉን ድጋሚ ሰርተው በ1982 ዓ.ም አጠናቀውታል፡፡ “መይሳው ካሳ” በሽያጭ፣ እንዲሁም “ረሀብ የፈታው” በስጦታ ተበርክተው በብሔራዊ ሙዚየም ይገኛሉ።
ሰዓሊ ስዕሉን የሚስልበት እንዲሁም የሚያስቀምጥበት ሰፊ ቦታ እንደሚያስፈልገው የሚያነሱት ሰዓሊው ትልልቅ ስዕሎችን ለመሳል የት አስቀምጠዋለሁ የሚለው እያሳሰባቸው እንደማይሰሩ ይናገራሉ፡፡ ስዕል በብዙ ዋጋ ይሸጥ የለ እንዴ ቢባሉ “የዘመኑ ልጆች ይሸጣሉ እኔ ግን አልሸጥም” መልሳቸው ነው፡፡
እሸቱ ለምን? ከተባሉ “እኔ እንጃን” ያስቀድሙና “መቼም ገንዘብ ጠላሁ አልልም፡፡ ነገር ግን ቅኝቴ በመሸጥ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ የሚሸጥ ሥዕል ብዬም አልሰራም፤ ገንዘብ ለማግኘት ስዕልም አልስልም።” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
በአዲስ አበባ የሥዕል ትምህርት ቤት ሳሉ ከ13 ሰዓሊዎች ጋር በጋራ በመሆን ያሳዩት የሥዕል ኤግዚቪሽን የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ጎንደርም ከሁለት ሰዓሊ ጓደኞቻቸው ጋር ኤግዚቪሽን ማሳየታቸውን ይገልፃሉ። ለብቻቸው ደግሞ አንድ ሙሉ ኤግዚቪሽን በአዲስ አበባ አሳይተዋል፡፡
ሰዓሊው የበርካታ የቡድን ኤግዚቪሽኖች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ እሳቸው ባይሄዱም በአሜሪካ ሥዕላቸው ከሌሎች ሥዕሎች ጋር ታይቷል፡፡ በሩሲያ በጀርመን በናይጄሪያና ቼኮስሎቫኪያም ሥራዎቻቸው ተጎብኝተዋል፡፡
ከሩሲያ መልስ በተማሩበት አለፈለገሰላም የስዕል ትምህርት ቤት ለሦስት ዓመታት አስተምረዋል። ‹‹የማስተማር ፍቅር ነበረኝ ነገር ግን ሁኔታዎች አልተመቹኝም ወይም አልተመቸኋቸውምና የግድ መልቀቅ ነበረብኝ›› ሲሉ በማመናቸው ቦታውን ለቀቁ፡፡
እሸቱ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሥዕል ክፍል ኃላፊ ሆነው ጡረታ እስኪወጡ እስከ መምሪያ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ ሰዓሊው አስተማሪ ለመሆን የወሰኑበትን አንድ ምክንያት አይረሱትም፡፡
አንድ ቀን የቢሮ ሥራቸው ላይ ሳሉ ሳያስቡት ይወድቃሉ፡፡ ህመማቸው ስኳር ነበር፡፡ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ባሉበት ‹‹ያለኝን እውቀት ሳልሰጥ፣ ሳላስተምር የቢሮ ሰው ሆኜ ልቀር ነው›› የሚል ቁጭት ውስጣቸው ይመላለሳል፡፡ የስዕል ትምህርት ቤት ለመክፈት አሰቡ፡፡ ሞልቶላቸው ትምህርት ቤት እስኪከፍቱ በአቢሲንያ የሥነ-ጥብብ ትምህርት ቤት በትርፍ ጊዜያቸው አስተምረዋል፡፡
ከሥራቸው በጡረታ ለመውጣት ባሰቡበት ወቅት ከቀድሞ ተማሪያቸው ሰዓሊ አስናቀ ክፍሌ ጋር ለምን ትምህርት ቤት በጋራ ከፍተን አንሰራም የሚል ሀሳብ አንስተው ይወያያሉ፡፡ ይሄ እቅድ ሰምሮ ኢንላይትመንት አርት አካዳሚን በጋራ መስርተዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ ሰባት ተማሪዎችን ይዞ በኪሳራ ቢጀምርም በጊዜ ሂደት አድጓል፡፡ ከአጋራቸው ጋር ከአስር ዓመት ለማያንስ ጊዜ በጋራ ሰርተዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም በስምምነት ንብረት ተከፋፍለው ትምህርት ቤቱ ተዘግቶ ነበር፡፡ ሆኖም ሰዓሊውን በቅርበት በሚያውቁት ወዳጆችና መማር በፈለጉ ሰዎች ጥያቄ ሰዓሊ እሸቱ ‹‹ኢንላይትመንት አርት›› አካዳሚን ዳግም ተከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
‹‹በሕይወቴ እግዚአብሄር ሰጠኝ ብዬ ከማስበው አንድ ነገር ደጋግሜ ሞክሬ ካልተሳካ ‹‹ፈጣሪ አልፈቀደም ብሎ መተውን ነው ›› ሆኖም ሰው ስህተት ሲሰራ ካየሁ አላልፍም፣ እናገራለሁ፡፡ በዚህ የተነሳም ጸብ ይመጣብኛል። መዋሸት አልችልበትም›› ይላሉ፡፡ ጎበዞችንም ያደንቃሉ፡፡ እንዲህ ያለ ተማሪ ሲገጥማቸው በተቋማቸው ከክፍያ ነጻ ያስተምራሉ፡፡
ሰዓሊው ወጣት ሳሉም ሆነ አሁን ሙዚቃን መስማትና ማንጎራጎር ያዝናናቸዋል፡፡ በተለይ የጥላሁን ዘፈኖች ለእሳቸው ትርጉሙ ልዩ ነው፡፡ እያንዳንዱን ዘፈን ያውቁታል፤ ከዘፈኖቹ ጥብቅ ቁርኝት ስላላቸው በትውስታ ትላንትናቸውን ያቀርብላቸዋል። ሙዚቃውን ሁሌም ይሰሙታል፤ ያንጎራጉሩታል፤ ሲዘፍኑት ደግሞ ያምርባቸዋል፡፡
‹‹ግርማ ነጋሽ፣ ሚኒሊክ ወስናቸው አለማየሁ እሸቴ ደስ ይሉኛል›› ይላሉ፡፡ በአሁን ዘመንም ለይተው የሚያደንቋቸው ዘፋኞች አሉ፡፡ እሸቱ ወጣት ሳሉ ዳንስ ያዝናናቸው ነበር። ከመሰሎቻቸው ጋር ፓርቲ እያዘጋጁ ያስነኩት ነበር፡፡ ማንበብ አሁንም ያኔም ያልተለየ መዝናኛቸው ነው፡፡
በመጽሀፍትና በጥበብ ዙሪያ በሚደረጉ መድረኮች ላይ አይቀሩም፡፡ ከማንበብ ባሻገር በርካታ የመጽሀፍት ስብስብ አላቸው፡፡ ‹‹ወደፊት ለአንድ ቤተመጽሀፍት ላወርሰው እችላለሁ፡፡ ይላሉ፡፡ ልብወለድ፣ የታሪክ፣ የሀይማኖት መጽሀፍት ከስብስባቸው ውስጥ ይጎላል፡፡
ከምግብ የበሬ ቁርጥ፣ ኮስተር ያለ ቀይ ወጥ፣ ይወዳሉ። ሰሪውን ይመርጣሉ እንጂ ዶሮ ወጥም ምርጫቸው ነው። ቂቤና በርበሬ የተቀባ አነባበሮ ሌላው ተወዳጅ ምግባቸው ነው፡፡ እሳቸው እንደልብ አይገኙም ቢሏቸውም አሁንም ምርጫዎቻቸው ናቸው፡፡
በ1986 ዓ.ም ከወይዘሮ ሂሩት ይርጉ ጋር የመሰረቱት ትዳር ሰምሮ በሁለት ወንድ ልጆች ተባርከዋል፡፡ የመጀመሪያው ልጃቸው የሕክምና ዶክተር ሲሆን የአንድ ወንድ ልጅ አያት አድርጓቸዋል፡፡ ‹‹አንድም ቀን ለትምህርት ቤት ሳልከፍል በነጻ ነው የተማርኩት›› የሚሉት ሰዓሊው በተራቸው የሀገርን ብድር መመለስ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል፡፡
ለዚህም ሌሎችን ማስተማር ያስደስታቸዋል፡፡ “በነጻ የተማርኩ ሰው ነኝ፤ በነጻ የተማርኩትን ብችል በነጻ፤ ባልችል በትንሽ ክፍያ ማስተማር ይገባኛል፡፡” ይላሉ በመሆኑም በትምህርት ቤታቸው ለመንቀሳቀሻ ብቻ ጥቂት እያስከፈሉ ማስተማርን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡
ባለ ተሰጥኦ ተማሪዎችን ሲያገኙም በአቅማቸው የነጻ ዕድል እየሰጡ ያስተምራሉ፡፡ እሳቸው የሀገር ውለታን እየከፈሉ መጪውን ትውልድ ሊያስተማሩ፣ ሊቀርፁ ቃል አላቸውና፡፡ እውቁ የሀገራችን ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፡፡
ቤዛ እሸቱ
ቤዛ እሸቱ አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም