ኢትዮጵያዊነት የብዙ ትውልዶች ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማኅበራዊ ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ቅብብሎሽ ውጤት ነው። በጊዜ ሂደት ውስጥ እያንዳንዱ ትውልድ ሆኖ ያለፈው የማንነቱ እና ሆኖ የመገኘቱ ድምር ስሌት ነው።
እንደ ሀገር ዘመናት ባስቆጠረው የጊዜ ሄደት ውስጥ ያለፉ ትውልዶች አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ/ በመፍጠርና ጠብቆ በማቆየት ከፍ ያለ ባለውለታ ናቸው። ውለታቸው በየዘመኑ በነበሩና ኖረው ባለፉ ትውልዶች ሲዘከር የሚኖር ነው።
እያንዳንዱ ትውልድ የኖረበትን ዘመን በሚዋጅ መልኩ ከቀደመው ትውልድ የተቀበላትን የአሁኗን ኢትዮጵያ በአደገ አስተሳሰብ ላይ ቆሞ ከትናንት የተሻለች ልትሆን የምትችልበትን ፤ በርግጥም ሆና የተገኘችበትን ተግባራት ፈጽሟል ፤ በዚህም እንደ ትውልድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ችሏል።
በዘመናት መካከል ገናና ታላቅ ሀገር በመፍጠር፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የራሷ የሆነ የገናናነት የታሪክ ትርክት ባለቤት እንድትሆን አድርገዋታል። ይህም በቀጣይ ዘመናት ለመጡ ትውልዶች የገናናነት የመንፈስ መነቃቃት አቅም ምንጭ ሆነዋል አገልግለዋል። ዛሬም እያገለገሉ ነው።
አሁን ያለው ትውልድ ብሔራዊ ከብር የሆኑ እንደ አክሱም እና ላሊበላ የመሳሰሉ ከፍያሉ ኪነጥበባዊ ፋይዳ ያላቸው ቅርሶችን፤ በብዙ መስዋእትነት የተጠበቀ ለመላ ዓለም ህያው ተምሳሌት የሆነ በነፃነት የመኖር ኩራትን አውርሰውን ሄደዋል።
ከሰብአዊነት የሚመነጩና በተጨባጭ ተሞክሮ ያደጉ ፤ የማንነታችን ስሬት መሰረት የሆኑ ማኅበራዊ ፤ ባህላዊ እና መንፈሳዊ አሴቶች ባለቤት እንድንሆን አድርገውናል። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቻችሎና ተከባብሮ በፍቅር የመኖር ተምሳሌት መሆን ችለናል።
የአሁኑም ትውልድ በቀደሙት ትውልዶች የደምና የላብ መስዋእትነት አንገቱን አቅንቶ በኩራት መራመድ እንደቻለ ሁሉ፤ ለራሱም ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች ኩራትና ክብር የሚሆኑ ተግባራትን የማከናወን፤ በዚህም የራሱን ህያው ዐሻራ ጥሎ ማለፍ ይጠበቅበታል።
በተለይም ባለበት ዘመን አንገቱን አቅንቶ እንዳይሄድ ያደረገውን ድህነትና ኋላቀርነት በተባበረ ክንድ በጠንካራ ስራ እና የስራ ባህል በማስወገድ እራሱና መጪዎቹ ትውልዶች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት የሚራመድበትን አዲስ የታሪክ ትርክት መፍጠር ይኖርበታል ።
የኢኮኖሚ የበላይነት አልፋና ኦሜጋ እየሆነ ባለበት አሁነኛው ዓለም ድህነትና ኋላቀርነት የቱን ያህል ሀገራዊ ፈተናዎች እንደሚሆን ፣ ከዚህ ትውልድ በላይ በተጨባጭ የተረዳና ለዚህም ዋጋ የከፈለ አለ ብሎ ለማመን የሚከብድ አይደለም።
ትውልዱ በነዚህ ማኅበራዊ ፈተናዎች ምክንያት ለከፋ ሞትና ስደት ፣ ለርስ በርስ ግጭትና፤ ላልተገባ የማንነት ግንባታ ተዳርጓል ፤ ትናንት ከነበረው የማንነት ከፍታ ወርዶ ራሱን በሚያሳንሱ አለመደማመጥና ንትርኮች ተጠልፎ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገድዷል ።
ከነዚህ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሀገርን እንደሀገር የማሻገር፤ በተለይም ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው ሀገራዊ መነቃቃት ትርጉም ያለው ፍሬ አፍርቶ ሀገር እንደሀገር ቀና ብላ የምትሄድበትን ተጨባጭ እውነት መፍጠር የትውልዱ ኃላፊነት እንደሆነ ይታመናል ።
የቀደሙት ትውልዶች በደምና በላባቸው በጻፉት ሀገራዊ ድል፤ ብዙ ትውልድ በኩራት መመላለስ እንደቻለ ሁሉ፤ ይህ ትውልድ ዘመኑን በሚዋጅ ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ መሰረት ላይ ቆሞ ለራሱም ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች ሙሉ ኩራት የሚሆን አዲስ ድል ማስመዝገብ ይጠበቅበታል።
ችግሮችን ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ ሀገር እና ሕዝብን ፤ ከዚያም ባለፈ መጪዎቹን ትውልዶች ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ለመፍታት ከፍ ያለ ዝግጁነት መፍጠር፤ በዚህም ባለመደማመጥ ምክንያት የደበዘዘውን ሀገራዊ ሁኔታችንን ማደስ ይኖርብናል ።
የዛሬን ቀን ስናከብርም ከሁሉም በላይ ትውልዱ እንደ ትውልድ ያለበትን ትልቅ ኃላፊነት መወጣት የሚያስችለውን መነቃቃት በመፍጠር ፤ በተጀመረው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሂደት ውስጥ ባለው አቅም ሁሉ ተሳታፊ በመሆን የአዲስ ታሪክ ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል ነው!
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም