በጎነት – ብሔራዊ አንድነታችንንለማጠናከር

 ዓለማችን ከክፉ ይልቅ መልካምን ለማድረግ የምንችልና የማንችል መሆናችንን የመፈተኛ መድረክ ናት። በጎ የማድረግ ፍላጎትም ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ የሚመነጭ፣ ለአንዳንዶችም የሕይወታቸው የተሻለ ምርጫ ነው።

በጎነት መገለጫው ብዙ፤ ተግባሩም የከበረ ነው። በጎነት ከትናንሽ ነገሮች በሚጀመር ልምምድ እውን ሊሆን የሚችል ታላቅ ተግባር ነው። ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ በሕገ- ልቦናቸው ሊመሩበት የሚገባ ሰውኛ ተግባር ነው።

ሰዎች አንዳቸው ለአንዳቸው በጎ ማድረግን መልካም መሆንን ቢያዳብሩ በተለይም መስጠትን የኑሯቸው መርህ ቢያደርጉ ተስፋ ለሌላቸው ተስፋን፤ ደስታ ለሌላቸው ደስታን ይፈጥራሉ። ንፍገት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፣ ምቀኝነትና ወንጀል በግልፅ አደባባይ ይሸነፋሉ። ፍቅር ያሸንፋል። የሕይወት ጣዕም ይጨምራል።

በጎነት ከፅንሰተ-ሃሳቡ ጀምሮ በመገንዘብ ተግባራዊ ማድረግ የመጨረሻ ሽልማቱ ሠላምና ደስታ ነው። በጎነት ምላሹ ከፈጣሪ ዘንድ ነው። እርካታን ይሰጣል:: ምርቃት ያሰጣል። በረከትን ያበዛል። ሐሴትን ያጎናጽፋል።

«ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው» እንደተባለው፣ ለመረዳዳትና ለመተዛዘን ዘመድ ወዳጅ አሊያም የሚናውቀው መሆን የለበትም። ደግነት ለማሳየት የግድ ብዙ ወጪ ማውጣት አያስፈልግም። አይጠይቅም። መልካም ለማድረግና ለመርዳትም ሞልቶ የተትረፈረፈው ባለ ሀብት መሆን የግድ አይልም። በብዙ መንገድ ሰዎችን ማገዝ የሚቻል ሲሆን አንደኛው ትንሽ የሚለው በጎ እሳቤና ተግባርም ለሌላኛው ግዙፍ እንደሚሆን መረዳት ግድ ይላል።

‹‹በደግነት የተነገረ አንድ ቃል የሦስት ወሩን ቅዝቃዜ ያስረሳል›› የሚል የሩቅ ምሥራቃውያን አባባል አለ። ታዋቂው ደራሲ ቻርለስ ዲከንስ እንደሚለውም ‹‹ትንሿ ቁልፍ ግዙፉን በር ትከፍታለች››። የበጎነት የቁልፎች ሁሉ ቁልፍ (Master Key) ነው። በበጎነት ቁልፍ የማይከፈት ግዙፍ በር የለም።

ስለ በጎነት ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ለቃሉም ለተግባሩም ባይተዋር አይደሉም። ለኢትዮጵያውያን የተቸገሩን መርዳት ሃይማኖታዊ ግዴታ፣ ሥነ ምግባራዊ መገለጫ ነው። ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ መፋቀር እንዲሁም እንዳቸው ለአንዳቸው መተጋገዝና መደጋገፍን እሴት ያደረጉ ሕዝቦች ናቸው።

የማንነት ልዩነት ላይ የማይመሠረቱና አድሎአዊነትን የሚያወግዙ፣ የሌሎችን ደስታና ኀዘን መካፈልም ብቻ ታሳቢ የሚያደርጉ የኢትዮጵያውያን እሴቶችም በማኅበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ ክብር የተቸሩ፣ ለማኅበራዊ ጥቅም የተፈጠሩ፣ በአብሮነት ውስጥ እየበለጸጉ የመጡ፣ ሰብዓዊ ሞራልን የሚገነቡ፣ የሰብዓዊነትን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር የሀገርንና የወገንን ፍቅር የሚያጎናጽፉ፣ ጥልቅ በሆነ ማኅበረ-ባህላዊ ሥርዓት ዳብረው ተቀባይነትን በማግኘታቸው ዘመናትን እየተሻገሩ በመምጣት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ የማንነት መገለጫዎች ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም በርካታ ኢትዮጵያውያን አቅማቸው በፈቀደ አግባብ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውና እውቀታቸውን ፈሰስ በማድረግ በመልካምነት እሳቤ ደግነትን ሲያጋሩና ሳይኖራቸው ያላቸውን ሲሠጡ ብሎም መስጠትን ሲፈቅዱ እየተመለከትን እንገኛለን። ይህ የመደጋገፍ እሴት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ይበልጥ ጎልቶ መታየት ጀምሯል።

ከዚህ የኅብረተሰብ መልካም ተግባር ባሻገርም የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን አስተባብረውና ከአጋር ድርጅቶች አሰባስበው የአቅማቸውን ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ማዕድ ማጋራትና እጅጉን ያረጁ ብሎም ለመኖር አዳጋች የሆኑ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች የማደስና አፍርሶ የመሥራት ጨምሮ በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በርካታ የበጎነት ተምሳሌቶች በራሳቸው ተነሳሽነትና መልካም ፍቃደኝነት ሃይማኖት ብሔር፣ ዕድሜ፣ ጾታና ማኅበራዊ ደረጃ እንዲሁም መልካ ምድራዊ ወሰን ሳይገድባቸው የበጎነትን መንገድ በመከተል በጎ ምኞትን ተላብሰው በሀገራዊ ስሜት፣ ባህል እና ወግ ከወገን ጎን በመቆም ላይ ናቸው።

ከሁሉም በላይ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ኢትዮጵያውያን ድንበር ሳያጥራቸው ለወገናቸው ድጋፍ ለማድረግ የሚያደርጉት ርብርብ ከአድናቆትም ባለፈ የሲቃ ስሜትን የሚያጭር ነው። ይህ የመልካምነት መገለጫ ለወገን አለሁ የማለት ሩጫ ባለፉት አመታትና ዘንድሮ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ ላይ ይበልጥ ተስተውሏል።

ይሁንና መሰል መልካም ዜጎች የመበራከታቸውን ያህል በአሁኑ ወቅት በየቤቱና ጎዳናው በተለይ ድሃና አቅመ ደካማ ሰዎች ችግራችሁ ችግሬ ብሎ የሚደርስላቸው ተመልካች ዓይንና ሰሚ ጆሮ ከሁሉም በላይ መልካም ሰው ብሎም ተቋም እንደሚሹም እርግጥ ነው።

በተለይም በሕይወት ስንክሳር በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ከሰው በታች የመሆን ስሜት የተጋፈጡና ይህን ስሜት ፍራቻ ከሰው መራቅን ምርጫ ያደረጉ ወንድም እህቶቻችን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

ቀላል የሚባሉ በጋራ የመልካምነት መንገድ በመራመድ ሊቃለሉ ብሎም ሊቀየሩ የሚችሉ ችግሮች ሳይቀር በርካቶችን ሲፈትኑና ከመንገዳቸው ሲያሰናክሉም ይስተዋላል። አንዳንድ ተማሪዎች ወላጅ አልባ በመሆናቸው ከጎናቸው አይዞህ/ሽ ብሎ የሚያበረታታ ወገን ዘመድ በማጣታቸው ሌላው ቀርቶ ዩኒፎርም የሚገዛላቸው በማጣታቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ሲገደዱ መመልከትም ለዚህ በቂ ምስከር ሆኖ መቅረብ የሚችል ነው።

በእርግጥ መሰል ሸክሞችን ለማቅለል ትውልድ ካሰበው እንዲደርስ ለማድረግ በርካቶች እንደግለሰብም ሆነ ተቋም በመልካምነት እሳቤ ደግነትን ሲያጋሩና ሳይኖራቸው ያላቸውን ሲሠጡ ብሎም መስጠትን ሲፈቅዱ እየተመለከትን እንገኛለን።

ከዚህ የኅብረተሰብ መልካም ተግባር ባሻገርም የተለያዩ ተቋማት ካላቸው ላይ ቀንሰው ለነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች አስፈላጊውን ግብአት ማሟላትን ጨምሮ በተለያዩ በጎ ተግባራት በመሳተፍ ላይ ይገኛል። ይሁንና ከችግረኛ ተማሪዎቹ ቁጥር አንጻር በጎነታችን ይበልጥ ሊታይ የግድ ይላል። በተለይ ወቅቱ አዲስ አመትና ትምህርት የሚጀመርበት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ የአብሮነት ድጋፎች ይበልጡን ሊጎለብቱ ይገባል።

በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ረገድ የጀመረውን የበጎነት ተግባር ይበልጥ መደገፍ የሚገባ ሲሆን ችግሩ ሀገር አቀፍ እንደመሆኑም ሌሎች ክልሎችም ይህን የበጎነት መንገድ ተከትለው ሊራመዱ የግድ ይላል።

መታወቅ ያለበት እውነት ቢኖር የእርዳታ ትንሽ የለውም። የደንብ ልብስ ባለመልበሳቸው በርካቶች ከትምህርት ገበታ ለመቅረት ይገደዳሉ። ከጓደኞቻቸው ተለይተው ድህነታቸው እንዲሰማቸው ይሆናሉ። የደንብ ልብስ ድጋፍ በማድረግ ብቻ አንድን ተማሪ ከትምህርት ገበታው እንዳይርቅ ማድረግ ይቻላል።

ይህን የመልካምነት መንገድ በመራመድ ብቻ ሚሊዮኖችን መታደግና የተማረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ይቻላል። ነገ ከነገ ወዲያ ከራስ አልፈው ለሌሎች መትረፍ የሚችሉትን እውን የማድረግ አቅሙም ግዙፍ ነው።

በመደመር እሳቤ በጎ የሚያስብ አዕምሮ መደመርን- መተባበርን፣ መሰባሰብን-መተሳሰብን ይጠይቃል። የመደመር ጎዳና የሠላም፣ የአብሮነትና በጋራ የማደግ ጎዳና ነው። መደመር ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ዕድገት የየበኩላቸውን ዐሻራ የሚጥሉበት፣ ለጋራ ጥቅም በጋራ የሚራመዱበት መንገድ ነው።

ነገን የተሻለ በማድረግ ጉዞ የሀገርንም ሆነ የሕዝብን ችግር በማቃለል ብሎም በማጥፋት ሂደት ሁሉም በበጎነት የአንድነት መንገድ ሊራመድ ይገባል። በዚህ ተሳትፎውም የበርካቶች ሞራልና ደስታ ምንጭ መሆኑን በተጨባጭ ማስመስከር የግድ ይላል።

እንዲህ ያለው በሳል ስብዕና እንደ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ የሀገር ሕዝብ በጋራ ስንኖር ለሚኖሩን ግንኙነቶች የተግባቦት ጤናማነት መሠረት በመሆኑ ግንኙነቶቻችንን ሁሉ ሰላማዊ በማድረግ ጠንካራ ሀገርና ሕዝብ ለመመስረት ዋስትና ይሆናል።

ከሁሉም በላይ የታላላቅ ሞራልና እሴቶች ባለቤት የመሆን ልምምድ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ብልፅግናን እውን የሚያደርግ፣ በአንድነትም የሚያሻግር መሆኑ ጠንቅቆ ሊገባንም ሊያግባባንም ይገባል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You