ለአዕምሮ እድገት ውስንነት ማኅበር የተከፈለ ዋጋ

 ኪሩቤል አንተነህ ይባላል። የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለበት ወጣት ነው። በ‹‹ፍቅር የኢትዮጵያ አእምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር›› ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራል። ሥራውም የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች ማነቃቃት ነው። በተለያዩ ስብሰባዎች ላይም እነርሱን በመወከል ይሳተፋል። ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም አነቃቂ ሥራዎቹን ያቀርባል።

ወጣቱ፤ ወላጆች በየቤቱ የተደበቁ ልጆቻቸውን ‹‹ይችላሉ። ይሠራሉ።›› ብለው አምነውባቸው እንዲሠሩ ቢያደርጉ የተሻለ ቦታ እንደሚደርሱ ይናገራል። ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር እንዳለው የሚገልጸው እርሱ፤ ለወደ ፊት በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገር የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ወጣቶች ማነቃቃት እና የእነርሱ ድምጽ ለመሆን እቅድ አለው።

ብርቱካን የሱፍ የኪሩቤል እናት ናቸው። መኖሪያ ቤታቸው አያት አካባቢ ሲሆን፤ በቀን ሁለቴ ከአያት ወደ 22 አካባቢ የሚገኘው ወደ ብሔራዊ ማኅበሩ ቅጥር ግቢ ይመላለሳሉ። ልጃቸው ማኅበሩን ከተቀላቀለ ከስድስት ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ማኅበሩ ለልጃቸው ሁለተኛ ቤት እንደሆነ እና እንደ እርሳቸው ልጅ የአእምሮ ወስንነት ላለባቸው ልጆች ጥሩ እንደሆነ ይገልጻሉ። የእቤት እመቤት የሆኑት ብርቱካን ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ይሁን እንጂ ‹‹ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ነገር በጸጋ መቀበል ነው። ነገ የተሻለ ነገር ይመጣል። ልጄ ደስተኛ ከሆነ እኔ ደስተኛ ነኝ።›› ሲሉ ይጽናናሉ።

የሸዋጌጥ ክብረት የ‹‹ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር›› ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ከዛሬ 28 ዓመት በፊት የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ያሏቸው ልጆቻቸውን የሚያውሉበት ቦታ ነበር። ዕድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላ ግን ከማዕከሉ ይወጣሉ። ልጆቹም ተመልሰው ቤት ይቀመጣሉ። ስለዚህ ወላጆቹ ተሰባስበው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑትን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ማኅበር ‹‹ለምን አናቋቁምም?›› በማለታቸው ምክንያት ማኅበሩ ተመሠረተ።

በብዛት በማኅበረሰቡ በኩል ‹‹የአእምሮ እድገት ውስንነት የሚመጣው በእርግማን፣ በቁጣ እና በመሳሰሉት ነው።›› ተብሎ የሚታመን ሲሆን፤ ማኅበሩ ሳይንሳዊ መረጃን በመስጠት አመለካከታቸው የተሳሳተ እንደሆነ ግንዛቤ ይሰጣል።

የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ሲገኙ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማስቻልም ሌላኛው የማኅበሩ ዓላማ ነው። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አለባቸው። ማኅበሩ ሲቋቋም ሁለት ትምህርት ቤቶች ብቻ የነበሩ ሲሆን፤ ዛሬ ግን ከ25 በላይ ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ብቻ እንደሚገኙ ዋና ሥራ አስኪያጇ ያብራራሉ። ክልል ላይ ምንም ትምህርት ቤቶች ያልነበሩ ሲሆኑ፤ ዛሬ ግን በመከፈት ላይ ናቸው። እንዲሁም ማኅበሩ ‹‹በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ቢያንስ አንድ ክፍል ለእነዚህ ልጆች መኖር አለበት።›› የሚል ዓላማ አንግቦ እየሠራበት እንደሚገኝም ያክላሉ።

ከግንዛቤ እጥረት፣ ማኅበረሰቡ ‹‹ምን ይለኝ ይሆን?›› አንዳንዶቹም ለራሳቸው ክብር በመጨነቅ፤ ልጆቹ ረዥሙን ዓመት ቤታቸው እንዲቀመጡ ይገደዳሉ። ታዲያ እነዚህ ልጆች ዕድሜያቸው 20 እና ከዚያ በላይ ስለሚሆን ወደ ትምህርት ቤት የመሄዳቸው ዕድል ጠባብ ነው። ማኅበሩም ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የሙያ ማሠልጠኛዎችን በአዲስ አበባ እና በክልሎች በመክፈት የስጋጃ፣ የሽመና፣ የሻማ፣ የቡና ማንጠፊያ፣ የመወልወያ፣ መጥረጊያ እና የመሳሰሉትን ሥራዎች እንዲሠሩ ያደርጋል። ከዚህ ጎን ለጎንም በሙዚቃ፣ በዳንስ እና በሥዕል፣ ማንበብ እና መጻፍ እንዲችሉ በማድረግ እንዲሁም የባንክ ሂሳብ ራሳቸው እንዲያንቀሳቅሱ፣ ትራንስፖርት እንዲጠቀሙ፣ ስልክ ቁጥሮችን መመዝገብ እንዲችሉ መደበኛ ያልሆነ ትምህርት እንደሚሰጣቸው የሸዋጌጥ ይገልጻሉ። ወላጆች ደግሞ መብት እና ግዴታቸውን እንዲያውቁ፤ ልጆቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፤ እንዲሁም፣ በማንኛውም ቦታ ልጆቻቸውን ይዘው እንዲወጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሥራዎች ይሠራል።

ወላጆች በተለያየ ምክንያት ለከፋ ድህነት ይጋለጣሉ። ልጆቻቸውንም ‹‹ይድናሉ።›› በማለት ያላቸውን ጥሪት ያሟጥጣሉ። ከዚህ በተጨማሪም ልጆቻቸው የብዙ ሰዓት ጥበቃ የሚስፈልጋቸው በመሆኑ፤ ጉልበት፣ እውቀት እና ፍላጎት ኖሯቸው ልጃቸውን የሚጠብቅላቸው ብቻ ባለማግኘታቸው ለከፋ ድህነት ይጋለጣሉ የሚሉት የሸዋጌጥ፤ ስለዚህም ወላጆች እርስ በእርስ እንዲደራጁ እና የብድር እና የቁጠባ ተቋም እንዲያቋቁሙ መደረጉን እና 20 የሚሆኑ ወላጆችን በማደራጀት የሥጋጃ መሥሪያ ክር አዘጋጅተው እንዲሸጡ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም ለልጆቹ ስለ ኤችአይቪ/ኤድስ፣ ሥነ ተዋልዶ እና መሰል ጉዳዮች ለእነሱ በሚያመች፤ እንዲሁም በሚገባቸው መንገድ መረጃ ይሰጣቸዋል።

‹‹የእኛ ማኅበር በብዙ ፈተና ውስጥ ያለፈ ነው።›› በማለት የሚናገሩት ሥራ አስኪያጇ፤ ከዚህ በፊት ይሰጠው የነበረውን የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት በገንዝብ እጥረት ተቋርጧል። ሌላው ፈተና ደግሞ ማኅበሩ 28 ዓመት ይቆይ እንጂ እምብዛም በሰዎች አለመታወቁ፣ ጊዜ የሚፈልጉ ሥራዎች መኖራቸው፣ የማስተዋወቁን ዕድል አለማግኘት፣ የገንዝብ እጥረት፣ በቂ የሰው ኃይል አለመኖር፣ በጎ ፈቃደኞችን አለማግኘት እና ለሚሠሩ ሥራዎች የግብአቶች ዋጋ መናር ማኅበሩን እየፈተኑት ይገኛሉ።

በዓለም ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ብዙ ነገር መሥራት እና ማድረግ ችለዋል። ‹‹እኛ ሀገር ግን ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት እና ወላጆችን ጨምሮ ክፍተቶቸ አሉ። እንደ ዕድል ሆኖ ኪሩቤል ላይ የመገለሉ ነገር የለም። የሌላ ሰው ሲታይ ግን ያማል።›› በማለት ያለውን ክፍተት የኪሩቤል እናት ብርቱካን ይጠቁማሉ።

የሸዋጌጥ በበኩላቸው፤‹‹የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች የሥራ ዕድል እያገኙ አይደለም። ሌሎች ሀገራት ለእነሱ የሚሆን ሥራ በኮታ በማስቀመጥ ያሠራሉ። እኛም ጋር መንግሥትም የታክስ ቅናሽና ሌሎች ማበረታቻዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል። ተወዳድረው ሥራ መቀጠር አይችሉም። ብዙ ነገር መሥራት የሚችሉ እና ፍላጎት ያላቸው ይሁን እንጂ መንግሥትም ይሁን ማኅበረሰቡ አላወቃቸውም።›› በማለት ያስረዳሉ።

ሥራ አስኪያጇ እንደሚገልጹት ማኅበሩ ለወደፊት በርካታ እቅዶች አሉት። በአፍሪካ ሊጠቀስ የሚችል ለአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸውም ልጆች እንዲሁም ወላጆች የሚያርፉበት፣ ሆስፒታል፣ ጥናት እና ምርምር የሚካሄድበት የልህቀት ማዕከል የመክፈት ዓላማ አለው። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ ለዜጎች አቅዶ እንደሚሠራው ሁሉ፤ ውስንነት ያለባቸውን ልጆች በማካተት በሁለም ዘርፍ መሥራት አለበት። የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ አስገዳጅ ሆኖ ሲወጣ እና ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ለውጥ እንዲመጣ ያስችላል።

የአእምሮ እድገት ውስንነት እና ኦቲዝም ያላቸው ልጆች እንደ ማንኛውም ልጅ ትምህርት ቤት ገብተው ውጤት አምጥተው፤ እንዲሁም ማኅበሩ ትልቅ ቦታ አግኝቶ የበለጠ ሥራ ሲሠራ ማየት ምኞታቸው እንደሆነ የሚገልጹት የኪሩቤል እናት፤ ወላጅ ያልፋል፤ ነገር ግን ለእነርሱ የሚሆን ቋሚ ማኅበር እንዲሁም የወላጅን ልብ የሚያሳርፍ ነገር ቢፈጠር ደስተኛ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። ‹‹አሁን ብዙ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ማኅበሩን በትልቅ ደረጃ እና በብዙ ቅርንጫፎች እንዲዳረስ ነው እቅዳችን።» ሲሉም ነው አስተያየታቸውን የደመደሙት።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You