• ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከ5 ሚሊዮን በላይ ብር ለግሷል
አዲስ አበባ፡- ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵ ያውያን መብት (ግሎባል አሊያንስ) በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀዬቸው ለመመለስ ብሎም መልሶ ለማቋቋም የ31 ሚሊዮን 400 ሺህ 700 ብር ድጋፍ አደረገ።
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀያቸው ለመመለስ ብሎም መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የፕሮጀክት የመግባቢያ ሰነድ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመ ሲሆን ገንዘቡ ከኢትዮጵያ ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለገሰ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀዬቸው የመመለስ ሥራን ማገዝ ብሎም መልሶ የማቋቋም ሥራን አላማ አድርጎ የተነደፈ ሲሆን፣ ሰብዓዊ እርዳታዎችን እና አካባቢውን ወደሰላም የመቀየር ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ውጥን አለው።
የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ፕሬዚዳንት አርቲስት ታማኝ በየነ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገረው፣ የመግባቢያ ሰነዱ 70 ሺህ 72 ተፈናቃይ ተመላሽ ወገኖችን ማዕከል አድርጎ የሚሰራ ሲሆን በተለይም በመፈናቀል ሂደቱ ተጎጂ የሆኑና የሚያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ በተገቢው ጊዜ ማግኘት ያልቻሉ ላይ ትኩረት ያደርጋል።
በዚህም መሰረት ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በመላው ዓለም ካሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያሰባሰበውን ወደ 1.1 የአሜሪካን ዶላር ወይም 31 ሚሊዮን 400 ሺህ 700 ብር በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀዬቸው የመመለስ ሥራን ለማገዝ እና መልሶ የማቋቋም ሥራ ለመስራት እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ እንዲያግዝ የሚያስችል ሲሆን ወርልድ ቪዥን አሜሪካ ደግሞ 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማለትም 5 ሚሊዮን 717 ሺህ 220 ብር ለሥራ ማስኬጃ መለገሱን አርቲስት ታማኝ ገልጿል።
በፊርማ ሥነሥርዓቱ ለተፈናቃዮቹ መጠለያዎች እና የእርሻ መሳሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ይደረጋልም ተብሏል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ብራውን በበኩላቸው ሊሰራ የታቀደው ፕሮጀክት በግጭቱ የተጎዱትን ወገኖች በመርዳት ወደቦታቸው መመለስና መልሶ ማቋቋምና የግጭቱን መንስኤ ለመመርመርና አስተማማኝ ሰላም በአካባቢው ለማስፈን በተለያዩ አካላት ለሚሰሩ የትብብር ሥራዎች መነሻ ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን በዚህ ወር መጀመሪያ ተግባራዊነቱ ቀጥሎ በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት አስፈላጊውንና ቀዳሚ የሆኑ የጋራ ሥራዎችን ለማቀድ ቅድመ ሥራዎች የሚጠናቀቁበት ሲሆን በታለመለበት ጊዜ ማስፈፀም እንዲቻል ሁለቱ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ይሰራሉ ተብሏል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በጎንደርና አካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮ ጵያውያን መብት ፕሬዚዳንት አርቲስት ታማኝ በየነ ለአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፈንድ ባስረከበበት ወቅት እንደተ ናገረው ገንዘቡ ከኢትዮጵያ ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለገሰ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
በድልነሳ ምንውየለት