ሥልጣኔ የሚለው ቃል የሰለጠኑ ናቸው ከሚባሉት የአውሮፓ አገራት የመጣ የሚመስለው ይኖር ይሆናል፡፡ ይህ ቃል ግን በልማድ ፈረንጅ የምንለው (ነጭ) የሚባል የአውሮፓ ዜጋ እስከመኖሩም በማያውቀው የአገራችን ሕዝብ ውስጥ ይታወቃል፡፡ ‹‹የእገሌ ልጅ ሥልጡን ነው፣ እገሌ ሥልጡን ነው…›› ሲሉ እንሰማለን፡፡ ሥልጡን ማለት በስነ ምግባር የታነፀ፣ ትሁት የሆነ ማለት ነው።
በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ይህ ከሆነ፤ እነዚህ ሥልጡን የሚሏቸው ሰዎች (ልጆች) ድርጊታቸው ሲታይ ሰዎችን በትህትና የሚያገለግሉ ናቸው። ለታላላቆቻቸው የሚታዘዙ፣ ትልቅ ሰው ሲመጣ ከመቀመጫቸው የሚነሱ፣ ትልቅ ሰው ሲያዝዛቸው በትህትና ‹‹እሺ›› ብለው የሚሄዱ፣ ዕቃ ወይም የሆነ ሸክም የያዙ አዛውንቶች ሲያገኙ ተቀብለው የሚሸኙ ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች የአካባቢው ሰው ‹‹ሥልጡን›› ይላቸዋል፡፡ የሰለጠኑ ማለት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በመጣ ትርጉም ደግሞ መሰልጠን የሚለውን ቃል ማህበረሰቡ ከሰጠው ትርጉም ተቃራኒ የሆነ ትርጉም ሲሰጠው ይታያል፡፡ ይሔውም፤ መሰልጠን ማለት አለባበስ፣ አነጋገርና አንዳንድ ውጫዊ ፋሽኖች ላይ ያተኮረ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በነባሩ የማህበረሰባችን ትርጓሜ ግን መሰልጠን ማለት ሰዎችን ማገልገል ነው፡፡
ዛሬ የአገልጋይነት ቀን ነው ተብሏል፡፡ በዚሁ እግረ መንገድ ስለ አገልጋይነት እንታዘባለን፡፡ አገልጋይነትን ያህል ትልቅ ነገር በብዙ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እንዴት እንደሚያራክሱት እንታዘ ባለን፡፡
ተቋማት ስማቸው ራሱ ‹‹አገልግሎት ሰጪ ተቋም›› ተብለው ነው የሚገልጹት፡፡ ገላጪ ትርጉም ነው፡፡ እንደየ አይነታቸው ሕዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት የሚያገኝበት ማለት ነው፡፡ በእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰሩ ሰራተኞች ደግሞ አገልጋይ ናቸው ማለት ነው፤ ሕዝብን እያገለገሉ ነው። እዚህ ላይ ነው ታዲያ ብዙ ነገሮችን የምንታዘበው፡፡
አንዳንዶቹ አገልጋይነታቸውን ይረሱትና ጌታ ይሆናሉ፡፡ ተገልጋዩ አገልግሎቱን የሚያገኘው በእነርሱ መልካም ፈቃድ ብቻ የሚሆን ይመስላቸዋል፡፡ እርግጥ ነው በአገልጋዩ መልካም ፈቃድ የሚገኙ አገልግሎቶች አሉ፡፡ እነርሱ የበጎ አድራጎት አገልግሎቶች ሲሆኑ ነው። ኃላፊነት ተወስደው፣ ከሕዝብ በጀት ላይ ደሞዝ የሚከፈለው አገልጋይ ግን በግል በጎ ፈቃዱ ብቻ አይደለም የሚያገለግል፤ በኃላፊነት ጭምር ነው፡፡ ጌታው ሕዝቡ እንጂ እሱ አይደለም፡፡
አገልጋይነት በግለሰቦች ይጀምራል፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው አገልጋይነት ሥልጣኔ እና ጨዋነት ነው። የታነጹ ሰዎች የሚያደርጉት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ባህል በጣም የቆየ እና ልማድ የተደረገ ነው፡፡ ምናልባትም ለየት ከሚያደርጉን በጎ እሳቶች አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰለጠኑ ናቸው በሚባሉት አገራት የምንሰማው አንድ ነውር ነገር አለ፤ ይሄውም በቆዳ ቀለም ሰዎችን መለየት፡፡ በተለይም ጥቁር ነጭን እንደ ጌታ እንዲያይ የሚያደርጉ አመለካከቶች አሉ፡፡ በአውቶብስና በባቡር መጓጓዣዎች ውስጥ ነጭ ቆሞ ጥቁር አይቀመጥም የሚባልበት ሁኔታ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ የለም፡፡ ትህትና ነው የሚታየው፡፡ በባቡር እና በአውቶብስ ውስጥ ወንበር የሚለቀቀው የቆዳ ቀለም ታይቶ ሳይሆን ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ነባራዊ ሁኔታ ታይቶ ነው፡፡ ለምሳሌ በዕድሜ የገፉ አዛውንት ከሆኑ ነው ወንበር የሚለቀቀው፡፡ ይሄ ሳይንሳዊ ምክንያት አለው። በዕድሜ የገፉ ሰዎች ለረጅም ሰዓት መቆየት አይችሉም፤ እየተወዛወዙ መሄድ አይችሉም፡፡ በሌላ በኩል ለነፍሰ ጡር ነው ወንበር የሚለቀቀው፡፡ ነፍሰ ጡር በሆዷ ውስጥ ሌላ ፍጡር አለ፡፡ መቆም ይከብዳታል፣ መወዛወዝ አትችልም፡፡ ስለዚህ በምክንያት ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አክብሮት አለ፡፡ የዕድሜ አቻ ሆነው እንኳን አንተ ተቀመጥ አንተ ተቀመጥ ይገባበዛሉ፡፡ ይህ ትህትና ነው፤ ሥልጡንነት ነው፡፡
ከተማ ቦታ ትራንስፖርት ምቹ ስለሆነ ነገሩን በደንብ ለማጤን አይመች ይሆናል፤ በአገር ቤቱ ልማድ ግን አንድ የማስተውለው ነገር አለ፡፡ እናቶች ወይም አባቶች ሸክም በትከሻቸው ይዘው ሲሄዱ ወጣት የሆነ ሰው ከኋላቸው ከመጣ ማለፍ ነውር ነው፡፡ ሸክሙን ተቀብሎ እስከሚሄዱበት ማድረስ ባይችል እንኳን ትንሽ ያግዛቸዋል። የሚሄዱበት ቅርብ ከሆነ ደግሞ ያደርስላቸዋል፡፡ ከዚያም በአባቶች ወይም እናቶች ይመረቃል፡፡
በተቃራኒው ግን ምንም አይነት ትህትና ሳያሳይ፣ ዘፈን ወይም ፉጨት ነገር እያንጎራጎረ ባላየ ካለፋቸው ‹‹የማነው አሳዳጊ የበደለው!›› ነው የሚሉ፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የሚያውቁት ልጅ ማደግ ያለበት በትህትና፣ በጨዋነትና በአገልጋይነት ስለሆነ፡፡ እንዲያውም ለወላጆቹ ሁሉ ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ‹‹ገፍትሮኝ ነው እኮ ያለፈ!›› ይላሉ። ‹‹ገፍትሮኝ›› ሲሉ በእጁ ገፍትሯቸው ሳይሆን ትህትና አለማሳየቱን በግነት ለመግለጽ ነው፤ በእጁ ከመገፍተር አያንስም ለማለት ነው፡፡ አገልጋይነት በዚህ ልክ ነው የኢትዮጵያውያን ልማድ የተደረገው።
የተማረ እና ዘመናዊ በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ግን አገልጋይነት እምብዛም ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ መሰልጠን እየተቆጠረ ና፤ መሰልጠን ማለት ግን ሰዋዊ ነገሮችን ማድረግ ነው፡፡ ከሰዋዊ ባህሪያት አንዱ ደግሞ መተሳሰብ ነው፡፡
በጎ ነገር አድርጉ ማለት አስገዳጅ ላይሆን ይችላል፤ ለማገልገል ኃላፊነት ወስደው የተቀመጡት ግን ቢያንሰ ለህግና መርህ ተገዢ መሆን አለባቸው። አገርን ማገልገል ኃላፊነት ነው፡፡ የህሊና ብቻ ሳይሆን የህግ ተጠያቂነትም አለበት፡፡ ግለሰቦችንና ማህበረሰብን ማገልገል ደግሞ ተቋማዊ የህግ ተጠያቂነት አለበት፤ በበጎ ፈቃድ ብቻ የሚሆን አይደለም፡፡ ኃላፊነትን በበጎ እና በቅንነት መሥራት ግን የበለጠ ሥልጡን እና ሰዋዊ ያደርጋል፡፡
አገልጋይነት የህሊና ጤና ነው፣ የህሊና ደስታ ነው፣ የህሊና እርካታ ነው፡፡ እኛ ያገለገልነው ሰው ሲያገኝ ማየት ደስ ይላል፤ አለበለዚያ ምቀኝነት ነው የሚሆነው፡፡ በእኛ ስም ሰውን ማስደሰት የህሊና እርካታ ይሰጣል፡፡ በቅንነት በሰራንላቸው ሥራ ሰዎች ያመሰግኑናል፤ መመስገን ደግሞ የሚሰጠውን ደስታ ሁላችንም ቢያንስ በትንሹም ቢሆን አይተነዋል፡፡ በተቃራኒው መወቀስና መረገም ደግሞ ያስጨንቃል፣ ውስጣዊ ነፃነት ያሳጣል፡፡ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል፤ ያ ደግሞ የህሊና መረበሽን ይፈጥራል ማለት ነው፡፡
ለሚለምኑ ሰዎች 100 ብር ብንሰጥ የህሊና ደስታ ነው የሚሰማን፤ ከኪሳችን 10 ብር ቢጠፋ ወይም የታክሲ ረዳት 5 ብር መልስ አልሰጥም ቢለን ግን ለረጅም ደቂቃዎች እንረበሻለን፤ ከረዳቱ ጋር እንጣላለን፤ ከኪሳችን በጠፋች 10 ብር ልንናደድ እንችላለን፤ በበጎ ፈቃድ በሰጠነው 100 ብር ግን ሙሉ ቀን ልንደሰት እንችላለን፤ ምክንያቱም በበጎነት ነው ያደረግነው፡፡ ስለዚህ ሰዎችን ማገልገል የህሊና ደስታን ይፈጥራል፤ በአጠቃላይ አገልጋይነት ሥልጣኔ ነው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም