አዲስ አበባ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሀገር ደህንነት ሥጋት እየሆነ የመጣውን ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምንጫቸውና አሳሳቢነታቸው በተጨባጭ ከተረጋገጠባቸው ሀገራት ጋር ችግሩን ለመፍታት የዲፕሎማሲ ሥራ መጀመሩን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በዚህ ረገድ ከወራት በፊት ከሱዳን መንግሥት ጋር የተደረሰውን ስምምነት ለአብነት ጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣
ለኢትዮጵያ ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ያህል ሥጋት አልነበረም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ሁኔታ ግን ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር አሳሳቢ በመሆኑ እንደየ አካባቢውና አገራት ተጨባጭ ሁኔታና ትኩረት በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተለያዩ ስምምነቶች በማድረግ ችግሩን የመፍታት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመግታት ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ አንዱ ከሱዳን መንግሥት ጋር የተደረገውን ስምምነት የጠቆሙት አቶ ነብያት ችግሩ በአካባቢው መከሰቱን በሱዳን መንግሥት ታምኖበት በተደረገው ምክክር በህገወጥ የጦር መሣሪያ እንዳይገባ መግባባት ላይ ተደርሶ የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈርሞ ሁኔታውን በጋራ የመከላ ከልና የመቆጣጠር ሥራ ተጀምሯል።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ ሀገርን ከዚህ መሰል ችግር ለመታደግ ስምምነቶች እንደ የሚመለከተው አካባቢና አገር ይፈፀማል። ችግሩ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎችም ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩ በህገወጦች እንደሚከናወን መዘንጋት እንደሌለበት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ተግባራቸውን በመወጣት መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ሥራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መደገፍ እንደሚገባ ቃል አቀባይ ጥሪ አቅርበዋል።
ህገወጥ የተባሉ ዝውውሮችን በሙሉ በሚመለከት በዓለምአቀፍ ደረጃ ስምምነቶች መኖራቸውንና እንደ ሀገር ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ነብያት ህገወጥ የሰዎች፣የአደንዛዥ ዕፅ፣ኬሚካል ዝውውሮች እና ከኮንትሮባንድ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ችግሮች ለሀገር ሥጋት መሆናቸውንና እነዚህን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። በተለይ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
በለምለም መንግሥቱ