‹‹የጤና ጉዳቱ በዓለም ጤና ድርጅት ካልተረጋገጠ አቅርቦቱ ይቀጥላል›› -ንግድ ሚኒስቴር
– መንግሥት ለዘይት፣ለስንዴና ለስኳር ከሚያደርገው ድጎማ ለመውጣት እንቅስቃሴ ጀምሯል
አዲስ አበባ፡- ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ፓልም የረጋ የምግብ ዘይት በሂደት ለከፋ የጤና ችግር የሚያጋልጥ መሆኑን በሳይንሳዊ ጥናት የተረጋገጠውንና ከእህል ዘር የሚዘጋጅ ፈሳሽ ዘይት በማቅረብ የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በህዳር 19 ቀን፣ 2011 ዓ.ም በላከው ደብዳቤ ያሳወቀውን ምክረ ሀሳብ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ የዓለምጤና ድርጅትና በሥሩ ያሉ የምርት ጥራት የሚያረጋግጡ ተቋማትዘይቱ የጤና ጉዳት እንዳለው እስካላረጋገጡ ድረስ ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጿል።
በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አማካሪ ዶክተር ውባየሁ ዋለልኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ፓልም የረጋ የምግብ ዘይት በደም ውስጥ የቅባት መጠን እንዲጨምር፣ የኩላሊት ተግባር እንዲቀንስ በማድረግ፣የደም ሥሮችን በማጥበብ፣በሂደትም ከፍተኛ ለሆነ የጤና ጉዳት አጋላጭ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ በ2016 ባካሄደው ሳይንሳዊ ጥናት አረጋግጧል።
በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የምግብ ዘይቶች የሚመረቱበት ሂደት አደገኛ መሆኑንም ጥናቱ አመላክቷል ያሉት ዶክተር ውባየሁ ጤና ሚኒስቴር ጥናቱን መሰረት በማድረግ የረጋ የፓልም ዘይት በፈሳሽ እንዲተካና በሀገር ውስጥ ምርት ላይም ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ምክረ ሀሳብ ልኮ ምላሹን እየጠበቀ ነው።
ጤና ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ያሳወቀው ምክረ ሀሳብ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲደርሰው መደረጉንና ሚኒስቴሩ ገበያ ላይ ያለውን ዘይት ዋጋ በማጥናት አምራች ኢንዱስትሪዎች ከእህል ዘር ፈሳሽ ዘይት ማምረት እንዲችሉ የሚደገፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት አማራጭ ሀሳብ እንዲያቀርብ አቅጣጫ እንደተሰጠው ዶክተር ውባየሁ አስረድተዋል።
ንግድ ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተልዕኮውን ከተወጣ ምርቱን በሀገር ውስጥ በመተካት እንዲሁም ከኑግ፣ከሱፍ፣ ከተልባ፣ ከበቆሎ፣ ከአኩሪአተር፣ ከሰሊጥና ከሌሎች የቅባት እህል ዓይነቶች የምግብ ዘይት ማምረት ከተቻለ የህብረተሰቡን ጤና መታደግ እንደሚቻል ዶክተሩ ይናገራሉ።
በአሁኑ ጊዜ ከእህል ዘር የሚዘጋጅ ፈሳሽ የምግብ ዘይት ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱንም ጠቅሰዋል። በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለዘይት ግዥ የምታወጣውን 450 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንደሚያስችል ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው የምግብ ዘይት በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ 330ሺ ቶን መድረሱንም አመልክተዋል።
እንደ ዶክተር ውባየሁ ገለፃ የረጋው የፓልም ዘይት የቅባት መጠኑ ከፍተኛ እንደሆነና ቅቤን ለመተካት ሲባል እየተዘጋጀ የሚቀርብ ምርት ነው። በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የምግብ ዘይቶችም የማምረቻ መሣሪያቸው፣የሰው ኃይላቸውና የምርት ግብአታቸው ላይ የጥራት ክትትል ካልተደረገ በአንዳንዶቹ ላይ ጉድለቶች እንደሚታዩ አስረድተዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ እየቀረበ ያለው የፓልም የምግብ ዘይት ኢትዮጵያ ባስቀመጠችው አስገዳጅ የጥራት መስፈርት ደረጃ የተረጋገጠ ምርት ነው። አቅርቦቱ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የመግዛት አቅም ያገናዘበ ነው ብለዋል። በመሆኑም የረጋው የፓልም ዘይት የጤና ችግር የሚያስከትል መሆኑ በዓለም የጤና ድርጅት እስካልተረጋገጠ ድረስ አቅርቦቱ ይቀጥላል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
መንግሥትም ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለዘይት፣ለስንዴና ለስኳር ከሚያደርገው ድጎማ ለመውጣት እንቅስቃሴ ጀምሯል።በመሆኑም ምክረሀሳቡ በረጅም ጊዜ ውስጥ ለመተግበር ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ወንድሙ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣በትግራይ፣በአማራና በሌሎችም በአራት አካባቢዎች ለማምረቻ የሚሆኑ የሼዶች ግንባታ ሥራ መጀመሩንና ባለሀብቶችም በዘርፉ ላይ በስፋት እንዲሰማሩ ሥራዎች ተጀምረዋል። ሚኒስቴሩ ጥራት ያለው ዘይት እንዲቀርብ በጥናት የተደገፈ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ በአነስተኛና በመካከለኛ አማራቾች በወር ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደሚቀርብና አቅርቦቱን አምስት በመቶ ይሸፍናል። በነጻ ገበያ መርህ ደግሞ በተለያዩ አቅራቢዎች አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሊትር የሚቀርብ ሲሆን፣ ይህም 11በመቶ ይሸፍናል። 40 ሚሊዮን ሊትሩ በመንግሥት ድጎማ ከውጭ የሚገባና 84 በመቶ እንደሚሸፍንና ከፍተኛውን አቅርቦት የያዘው የፓልም ዘይት ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
በለምለም መንግሥቱ