እንቁጣጣሽ አብሳሪው ድምፃዊ

 የነሐሴ ጭጋግ በርግጥ ሊለቅ ስለመሆኑ ማረጋገጫው በሀገራችን የሚገኙ አብዛኞቹ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጣቢያዎች መተኪያ ያላገኙለትን አንድ ዜማ በተደጋጋሚ ለአየር ማብቃታቸው ነው። «ስርቅታዬ» የተሰኘው ዘፈን በመገናኛ ብዙኃኑ፤ እንዲሁም በብዙኃኑ አድማጭ ቤት መሰማቱ ለቡሄ መድረስና ለአዲስ ዓመት መቃረብ አብሳሪ ነው። ዘፈኑን በቴሌቪዥን ያኔም ሆነ አሁን ያዩትና የሚያዩት ነጭ የባህል ልብስ ከቢጫ ጥለት ጋር ያደረገ፤ እራሱም አዲስ ዓመት የመሰለ ወጣት ከዘፈኑ እኩል የብዙዎች ትውስታ ሆኗል።

በቄለም ወለጋ፣ ደንቢ ዶሎ የተወለደው ድምጻዊ ሰለሞን ደነቀ ታላቅ እህቱን ተከትሎ ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ በመሆን በ1951 ዓ.ም ይህችን ዓለም ተቀላቀለ። ሰለሞን ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተለየ አስተዳደግ ነበረው። ይኸውም በርካቶች ጥበብን ለመቀላቀል ሲፍጨረጨሩ ኮርኳሚ የሚበዛበት ሕይወት ቢያሳልፉም እሱ ግን ሙዚቃን ለመሞከር ሲጥር አዲስ የሙዚቃ መሣሪያ የመግዛት አቅም ባይኖራቸውም፣ ወላጅ እናቱ በአካባቢው ካገኙት መሣሪያ ክራር ሠርተው ተሰጥኦውን እንዲያዳብር ያደርጉት ነበር።

ያችን ክራር ይዞ ጊቢያቸው ውስጥ ከሚገኝ ዛፍ ላይ ረዥም ጊዜውን ያሳልፍ እንደነበር ታላቅ እህቱ ታደለች ደነቀ ታስታውሳለች። ከትምህርትና ሙዚቃን በግል ከመዝፈን በተረፈ ሰለሞን በልጅነት ጊዜው ከቤተክርስቲያን የማይጠፋ ነበር። ድምጹ በያሬዳዊ ዜማ መቃኘቱ ሰለሞን ለሚታወቅበት ስርቅርቅ ድምጽ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነ ይታመናል። ከተወለደበት የደንቢ ዶሎ ከተማ የሙዚቃ ሥራውን ለማሳደግ ወደ ነቀምት አመራ። በነቀምት ጉደቱ ወለጋ የኪነጥበብ ቡድንን ተቀላቀለ።

የኪነት ቡድኑን የተቀላቀለው በመሣሪያ ተጫዋችነት ነበር። ከልጅነቱ ክራር ይጫወት ነበርና እሱን ቡድኑ አዳበረለት። በሂደት ጊታር መጫወትን አከለበት። ምንም እንኳን የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ ባይማርም መሰንቆ፣ አኮርዲዮን፣ ትራምፔት መጫወት ይችላል። ሁለገብ ዜማ ይደርሳል፤ ግጥም ይጽፋል። በዚሁ ችሎታውም አብረውት የሠሩት ለመድረክ የተፈጠረ ነው ይሉታል። የድምጹማ ነገር ምን ይጠየቃል፤ በርካቶች ድምጹ ስርቅርቅ መሆኑን ተስማምተውበታል። በኪነት ቡድኑ በርካታ ሥራዎችን ከሠራ በኋላ የመጀመሪያ የአልበም ሥራውን ለማውጣት ወደ አዲስ አበባ አመራ። አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላም በበርካታ የሀገሪቱ ትልልቅ መድረኮች ላይ በግሩም ድምጹ አቀንቅኗል። ከአምስት በላይ አልበሞችንም ለአድማጩ አድርሷል።

በርካታ ዘፈኖች ቢኖሩትም የሰለሞን የተለየ መለያው፣ መታወቂያና መታወሻው ግን ስርቅታዬ የተሰኘ ዘፈኑ ነው። ስርቅታ የፍቅር፣ የቡሄ፣ የእንቁጣጣሽ፣ የትዝታ የባህል ዘፈን ሆኖ ሰባት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሀገራችንን አኗኗር፣ የበዓል አውድን፤ ብሎም የልጅነት ትውስታን ማሳየት የቻለ ድንቅ ድምጻዊ ነው።

በዚያች ዘመን አይሽሬ ውብ ዜማ በስቅታ የተቸገረው ሰለሞን ማን እንዳነሳው ለማወቅ ይቸገራል።

ማን አነሳኝ ደግሞ ትዝታ

ትሁን ቆንጅት ነች ስመኝሽ

እያለ ዘፈኑ ሲጀምር የበዓል ልብስ ከመልበሱ በስተቀር ዘፈኑ ወደ መነፋፈቅ ያደላ የፍቅር ዘፈን ይመስላል። አድማጩ የፍቅር ዘፈን ብቻ ቢመስለውም አይፈረድበትም። ሰለሞንና ምናቡ የፈጠራት ስመኝሽ ብዙ የልጅነት ትዝታ ያላቸው ሲሆን፤ እሱም በዘፈኑ ይገለጻል። በስቅታው መነሻነት የትምህርት ቤት ቆይታቸውንና የልጅነት ምኞቱን ተናግሮ ሲያበቃ በአዲስ ዓመት ሲገናኙ የነበረውን ስሜት እንዲህ ሲል ያስታውሰናል።

ከነማስረጃው ስሚ ትዝታ

ትምህርት ቤት ተገብቶ አሀሀሀ

ሁሉም እረፍት ጨርሶ እህህ

ለእንቁጣጣሽ ዝግጅት አሀሀሀ

ቅዱስ ዮሐንስ ደርሶ

ሁሉም ብቅ ብቅ ሲል አሀሀሀ

አዳዲስ ልብስ ለብሶ

ሎሚና እንግጫ እህ

ተይዞ አበባ በዘመድ አዝማድ እህ

ደጃፍ ሲገባ እህ

ሁሉም ሲጋበዝ ጠላና ድፎ

የምግብ ዓይነት ሞልቶ ተትረፍርፎ

ኩታውን አባባ ለብሰው

ጌጡን እማማ

ቤቱ ተጎዝጉዞ በለምለም ቄጤማ

የሰለሞን ስርቅታዬ ሁሉንም የኑሮ ደረጃ በዓል አክባሪ ያማከለ መሆኑ ከሌሎች የበዓል ዘፈኖች ልዩ ያደርገዋል። እሱ የመረጠው ሁሉም ጋ ሊገኝ የሚችለውን ቄጤማ፣ ሎሚ፣ እንግጫ፣ ድፎና ጠላን አጉልቶ ሌሎቹ አንዱ ጋ ተገኝተው አንዱ ጋ ላይገኙ የሚችሉ የምግብና የመጠጥ ዓይነቶችን እያነሳ እንቁልልጭ ከማለት ይልቅ የምግብ ዓይነት «ሞልቶ ተትረፍርፎ . . .» በማለት በጥቅሉ መጥራትን ምርጫው አድርጓል። እሱ የሚጠራቸው ነገሮች የሁሉም ስለሆኑ በሀብታሙም ሆነ በደሃው ዘንድ የበዓል ትዝታና ስሜትን እንደቀሰቀሱ እስካሁን አሉ።

በማኅበረሰባችን የሴትና የወንድ ተብለው የተለዩ የባህል ጨዋታዎች አሉ። እሱ እነዚህን የጨዋታ ሕጎች ማክበርን መርጧል። ዘፈኑ የበዓል ትዝታ እንደመሆኑ በተለምዶ «አበባየሆሽ» በሴቶች የሚጨፈር ነውና እሱ ከማለት ይልቅ በዘዴ በስቅታው እንዳነሳችው የጠረጠራት ስመኝሽ እራሷ እንድትዘፍንልን አድርጓል።

ታስነኪው ነበረ እንዲህ በሚል ዜማ

ሴቷ የምናውቀውን አበባየሆሽ ዜማ ታዜማለች።

አበባየሆሽ ለምለም (2 ጊዜ)

ባልንጀሮቼ ለምለም

ግቡ በተራ ለምለም

እንጨት ሰብሬ ለምለም……..

አበባየሆሽ በሀገራችን የእንቁጣጣሽ ዕለት የሚከበር በዓል እንደመሆኑ የእንቁጣጣሽ ቀን ሰለሞንን መስማት አይደንቅ ይሆናል። ግን ዘፈኑን ለቡሄም ተመራጭ ያስደረገው እሱ ወንዶች ለቡሄ የሚጨፍሩትን ሆያ ሆዬ እንዴት ይጨፍር እንደነበረ በስርቅታው አስታኮ ስለሚያስታውሰን ነው።

ቀሰቀሰኝ እ ቀሰቀሰኝ እ ስርቅታዬ

የልጅነት ጨዋታሽ

ከታወሰሽ ከደጃፍሽ

ጎላ አርጌ ሆዬ ስልሽ ሆዬ ስልሽ

ሆያ ሆዬ ሆ

ሆያ ሆዬ ሆ

እዛ ማዶ ሆ ጭስ ይጨሳል ሆ

አጋፋሪ ሆ ይደግሳል ሆ

ያችን ድግስ ሆ ውጬ ውጬ ሆ

ከድንክ አልጋ ሆ ተገልብጬ ሆ

እያለ ይቀጥላል።

ዘፈኑን በቃ ቀለል ብሎ ከጓደኛ ጋር ትዝ አይልህም ትዝ አይልሽም በሚሉት ዓይነት ስሜት የቀረበ መሆኑ ዘፈኑ ላይ የተዳሰሱት ሀሳቦች በሙሉ እንዲታወሱ አድርጓል። ምንም እንኳን ዘፈን ማጠር አለበት ቢባልም፣ ከጥድፊያ ተነስቶ ለወንድ የሰጠውን ክብርና ሙገሳ ለሴት ሳይሰጥ ማቆምን አይመርጥም። «ስርቅታዬ» ምንም እንከን የሌለውና እስካሁን መተኪያ ያልተገኘለት የበዓል ዘፈን ሆኖ ዘልቋል።

ሰለሞንን መድረክ ላይ ሲዘፍን ያዩት በአንድ ነገር ይስማማሉ፤ ሲዘፍን እራሱ ተዝናንቶ ስለሆነ መዝናናቱ እነሱም ላይ ይጋባል። የተለየ የሚያበራ ፈገግታ ነበረው፤ ደግሞም የሚዘፍነውን ስሜት መግለጽ መለያው ነበር። በዘፈኑ ነፃ ሆኖ ተወዛውዞ ታዳሚውም እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል። እሱ ሲዘፍን ቁጭ የሚል የለም . . . እስኪባል ድረስ ሁሉም ታዳሚ ተወዛዋዥ ይሆናል።

እናቱ በሠሩለት ክራር የተፈታው እጁ ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎችን ለመጫወት አልቦዘነም። ክራርና መሰንቆ ይጫወታል፤ ጊታር ይችላል። እንደውም «ያደ በሌ» የተሰኘውን የኦሮሚኛ ዘፈኑ ቪድዮ የተቀረጸው ከመዝፈን ባሻገር እራሱ ጊታር እየተጫወተ ነው። የሙያ ባልደረቦቹ ሳክስፎንም ይጫወት እንደነበር ይናገራሉ። አማርኛና ኦሮምኛ በደንብ ማወቁ ጠቅሞታል። በሁለቱም ቋንቋዎች ዘፍኖ በርካታ አድማጭ ለማግኘት ዕድል ፈጥሮለታል። ሁለገቡ ሰለሞን በሁለቱም ቋንቋዎች ግጥም ይጽፋል፤ ዜማ ይደርሳል፤ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ይጫወታል፤ እንዲሁም ሙዚቃ ያቀናብራል።

ሰለሞን በሄደበት የሄደበትን ሕዝብና ባህል ያከብራል ይላሉ የቀድሞ ባልደረቦቹ። አንድ ቦታ ለሙዚቃ ዝግጅት ሲሄድ ከቡድን ጓደኞቹ ተለይቶ የሕዝቡን ባህል ለማወቅ ጊዜ ይወስዳል። ለዚህም ከኅብረተሰቡ ጋር ጊዜ ያጠፋል። ከዚያም መድረክ ላይ ሲወጣ ሌላ ቋንቋ ቢያቅተው ሰላምታውንና እንደ አስፈላጊው በአካባቢው የሚገኙ የቦታ ሥሞችን በሙዚቃ ውስጥ ያካትታል። «ባቡሪ ከኤ» እያለ የሚዘፍነው ተወዳጅ የኦሮሚኛ ዘፈኑ ነው። ባቡሩ ተነሳ ሆዴ አልችልም ብሎ ካንቺ ጋር ለመግባት ተነስቷል። አንቺ ቆንጆ ልጅ ነፍሴን ወስደሽብኛል፤ እያለ እንዴት አድርጋ ነፍሱን እንደወሰደችበት ይተርካል። ከዚያ እንዳገባት በመግለጽ በሠርጉ ላይ የታደሙ የተለያዩ አካባቢ ልጆች እንዲጫወቱ የአካባቢያቸውን ሥም እያነሳ ያበረታታቸዋል።

የሥራ ባልደረባው የነበሩት አቶ ወንደሰን ቦጋለ ሰለሞን መድረክ ላይ ወጥቶ ገና ባቡሪ ከኤ ሲል የሸላሚው ብዛት ባቡር የመጣ ይመስላል ይላሉ። ሸላሚው እራሱ የመሸለም ተራ እንዲደርሰው ይሰለፋል። ሰለሞን ካለ ጨዋታና ሳቅ ነው ይላሉ። እሱ ለደስታ ለሳቅ ለጨዋታ ቅርብ ነውና አብረውት ያሉ ሁሉ ሳይወዱ በግድ ያስቃቸዋል። ያለውን ማካፈል መለያው ነው። እንደ ጓደኞቹ አስተያየት ሰለሞን ያገኘውን ኪሱ ማሳደር አይችልም። ከሕፃናት ጋር የተለየ መግባባት አለው። የቸገረው ሰው ሲያገኝ ከእሱ አልፎ ከጓደኞቹ አምጡ ብሎ ይረዳል። የተቸገረ አግኝቶ መርዳት ባይችል አብሮ ቁጭ ብሎ የሚያለቅስ፣ ሩህሩህነትን የታደለ ነበር።

ድምጻዊው መልከመልካም፣ ብሎም ዘናጭ ነበር። ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ለየት ያለ የጸጉር ስታይል ጀምሮ ነበር። ቢያጆ ጸጉሩ ከፊት ሙሉ ቁርጥ ሆኖ ከማጅራቱ በላይ የተወሰነ የጸጉሩን ክፍል ያሳድጋል። አንዳንዴም ያደገውን ጸጉሩን ቁጥርጥር ይሠራዋል። ለዚህች ጸጉሩ የተለየ እንክብካቤ ያደርግላት ነበር። ጓደኞቹ ምግብ መራጭ ነው ይሉታል። አብሶ ጥብሳጥብስ ይወዳል። አትክልትም ሌላው ሰለሞን የሚወደው ምግብ ነው። ሽሮ ግን ነብሱ ናት ይላሉ። ጥበበኛም ብቻ ሳይሆን ዕድለኛ የሆነው ሰለሞን 15ሺህ ብር ብዙ በነበረበት ወቅት የ15ሺህ ብር ሎተሪ ዕድለኛም ሆኗል።

ክራር ሠርተው ከሙዚቃ ያቀራረቡት እናቱን ውለታ መርሳት ያልወደደው ሰለሞን እናቱን «ሞገሴ»፣ «አለኝታዬ» ብሎ ዘፍኖላቸዋል።

ብድር ውለታሽን ከምዘነጋው

የጠባሁት ጡትሽ ልሳኔን ይዝጋው

ጸጸት ያናጋኝ

ሰዎች ሌሎቹን በሚረግሙበት ቃል እራሱ እራሱን የእናቱን ውለታ ከዘነጋ ቅጣት እንዲደርስበት በይኗል።

የቤተሰብ ፍቅር በሰለሞን ዘፈኖች ውስጥ የቅድሚያ ትኩረት ከሚጣቸው ተርታ ይገኛል። እነሱን ከማጽናናት ባለፈ የነሱ ናፍቆት ምን እንዳደረገው ይተርካል። በአብዛኛው በሀገራችን የሚዘፈኑ ዘፈኖች አንዱን የቤተሰብ አካል ነጥሎ ቢሆንም፣ እሱ ግን ሙሉ ቤተሰቡን ቢለያዩም ደህና መሆኑን የሚያበስርበት ዘፈን አለው።

እምባሽ አይፍሰስ

እምዬ እምባሽ አይፍሰስ

አልሞትኩም አለሁ በጤና

አባቴ ሀሳብ አይግባህ

ብርቅም አለሁ በጤና

እህቴም አይዞሽ አይክፋሽ

አልሞትኩም አለሁ በደህና

እያለ መላው ቤተሰቡን የተራራቁ መገናኘታቸው እንደማይቀር ያበስራቸዋል።

ድምጻዊው ሀገሩን «ካንቺ ያስቀድመኝ» ይላታል። የሰለሞን ለየት ያለው ችሎታውና በዚህ ዘፈንም የሚታየው ድምጹን እንደአስፈላጊነቱ መቀያየሩ ነው። በዚህ ዘፈንም የጀግናው አባቱን ኑዛዜ በዜማ ቀይሮ ሲያቀርብ ድምጹን የትልቅ ሰው አድርጎ ነው።

አሁን አርጅቻለሁ ልጄ

ዕድሜዬ እየገፋ ሄደ

ሀገርህን አይዞሽ በላት

ካንተ ወዲያ ሰውም የላት

የሚሉት አባት የሁሉም አባት ያስተላለፉት አደራ ስለሚመስል ሁሉንም አጀግኖ የሀገር ባላደራነት ላይ ያስቀምጣል። ሀገርን ያገለገሉ ጀግና አባት ልጃቸው ኑዛዜያቸው ትዝ ሲለው፤

አርጅቻለሁ በቃ ሲለኝ

ከሞት አፋፍ ቆሞ ሲያየኝ

ወራሼ ነህ አይዞህ ሲለኝ

ክንዴ መክኗል በቃ ያለኝ ……

ውል አለብኝ ቃል አለብኝ (2 ጊዜ)

ለዚች ሀገር ለዚች አድባር

ለዚች መሬት ለዚች ሀገር

እስቲ በሉ በሉ በሉ

ብሎ ለሀገሩ ሀሳቡን የሚገልጽበት ቃል ቢያጥረው፣ ቃላት ቢረክሱበት እናቶች ልጆቻቸውን የሚያስተኙበትንና የሚያጫውቱበትን ቃል ተጠቅሞ ሀገሩን ዳግም ወልዶ እሹሩሩ ብሏታል። ሀገሩ እሱ እያለ ምንም እንደማትሆን ሀሳቧን ጥላ እንድትተኛ ሲያባብላት እሹሩሩ፡-

የከዳሽ ይከዳ የጎዳሽ ይጎዳ

እሹሩሩሩሩ

የጎዳሽ ይጎዳ የከዳሽ ይከዳ

«ዋሄ በሬዴኬ» የተሰኘው የኦሮሚኛ ዘፈኑ ቋንቋውን በማይችሉት ዘንድ ጭምር እጅግ ተወዳጅ የሆነ የሰለሞን ሥራ ነው። በዘፈኑ ‹‹ያ ሻማ ቡሬ ኪያ›› ቡሬ ሻማ የምትለብስው ልጅ ስለ ቁንጅናሽ ከሰፈር ነው የሰማሁት። ዓይን የለውም ይላሉ የሚያሳበድ ነው። የልጅቷ ፍቅር ምኑም አይታወቅ። ለማነው የምነገረው ይህ አስቸጋሪ ነገር ነው። እያለ ፍቅር ዓይን እንደሌለው የገለጸበት ነው።

ሰለሞንና እንቁጣጣሽ ቁርኝታቸው የተለየ ነው። ከስርቅታዬ ውጪ እንደስርቅታዬ ባይጎላም በዓልን ፍቅር በፍቅር እናክብር የሚልበት «ፍቅር በፍቅር» የተሰኘ ዘፈን አለው። በዘፈኑ የድሮው ትዝታውን የአባቶችን ስሜትና ምርቃትንና የልጃገረዶችን «እታበባዬ» ህብረ ዝማሬ አካቷል። ይሄም ዘፈኖች እንደ ስርቅታዬ ሁሉ በሚቀበሉት ሴቶች የታጀበ ነው። ሰለሞን ሀገረኛ ግጥምና ዜማ ከአዲስ ግጥምና ዜማዎች ጋር ማዋሀድ መታወቂያው ነበር። በወጣትነቱ የተለየነው ድምጻዊ ሰለሞን ደነቀ ከሞተ 20 ዓመታትን ተሻግሯል። ግን በሥራው ሕያው እንደሆነ ቀጥሏል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You