ለከተማዋ ቱሪዝም ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን የሚጠበቀው ማኅበር

ኢትዮጵያ የበርካታ ባህል፣ ታሪክ፣ መልክዓ ምድርና ተፈጥሮ፣ አርኪዮሎጂካልና የሥነ ሕንፃ ጥበብ እንዲሁም የአያሌ ቅርሶችና መስህቦች ባለቤት ነች። እነዚህ የቱሪዝም ሀብቶች ሀገሪቱን በዓለም ካሉ ታሪካዊና ቀደምት ሀገራት ተርታ የመጀመሪያዋ ያደርጋታል። የቱሪዝም በረከቶቹን በአግባቡ ማስተዋወቅ መጠበቅና ማልማት ከተቻለም የኢኮኖሚ አቅምንና የሀገር ገፅታን ለመገንባት ሁነኛ አማራጭ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ተርታ መድቦታል። የግሉ የቱሪዝም ዘርፍ አንቀሳቃሾችም የዚህ እቅድ ዋንኛ ተዋንያን በመሆናቸው በትብብርና በቅንጅት ከመንግሥት ጋር እንዲሠሩ ይጠበቃል።

የቱሪዝም ባለሙያዎች ዘርፉ ቀጣይነት ያለው ልማትን፣ ተከታታይ የገበያና ማስተዋወቅ ሥራን ፣ ዘመናዊ የሆስፒታሊቲና አገልግሎት አሰጣጥ፣ የአስጎብኚዎችና ቱር ኦፕሬተርስ ቅንጅትን እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እና የግሉ ዘርፍ ትብብርን እንደሚጠይቅ ይናገራሉ። በተለይ ከትብብር፣ ከመናበብና ከመደጋገፍ ባሻገር በተናጠልም ይሁን በቡድን ለአንድ ግብ መሥራትን እንደሚፈልግ ያስረዳሉ። በተጨማሪም ይህንን ግብ እውን ለማድረግና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የቱሪዝም ዘርፍ ማኅበራት ድርሻ ጉልህ እንደሆነ ያነሳሉ።

የሆቴል፣ የቱር ኦፕሬተር፣ አስጎብኚዎች፣ የቱሪዝም ምርት ተሳታፊዎች፣ የትራንስፖርት አቅራቢዎች እና የዘርፉ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ጥምረት የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሀብት (ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ) ወደ ኢኮኖሚ ጉልበት ለመቀየር ትልቅ አቅም እንደሆነ ይነገራል። ይህን መሰል ጥምረት በሀገራችን በስፋት ባይታይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢንዱስትሪውን መነቃቃት ተከትሎ በማኅበር የመሰባሰብ ፍላጎት እየታየ ነው። ለምሳሌ ከሚጠቀሱ የቱሪዝም የሙያ ማኅበራት ውስጥ ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ የተመሠረተው የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር አንዱ ነው።

የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ ስለማኅበሩ ምስረታና የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤው ሲያስረዱ፤ ‹‹መሥራች አባላት በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ልምድ፣ ብቃት፣ ፍላጎት፣ ልዩ ተነሳሽነትና ለረጅም ዓመታት የአገልግሎት እውቅት ዝግጅት ባላቸው ቀና አባላት የተመሠረተ ነው። በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መዝገብ ቁጥር 6958 የተመዘገበ የባለሙያዎች ማኅበር ነው›› ይላሉ።

ማኅበሩ በአዲስ አበባ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው የላቀ ደረጃን፣ ትብብርን እና ቀጣይነት ያለው ዕድገትን ለማስተዋወቅ ቀዳሚና ተደማጭነት ያለው ማኅበር የመሆን ራዕይን እንዳስቀመጠም የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ይገልፃሉ። ለከተማዋ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት እና የነዋሪዎቿን ሕይወት የሚያበለጽግ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ማኅበር በመሆን የሆቴልና ቱሪዝም ለማሳደግ እንደሚሠሩ ይናገራሉ።

«ልህቀትና ተባባሪነት ማዕረጋችን ነው» የሚሉት ፕሬዚዳንቱ የማኅበሩ ዋና ተልዕኮ የአዲስ አበባን የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎችን ማስተባበር፣ ለአባላቶቻቸው የሥልጠና እንዲሁም የትምህርት ዕድሎች ማቅረብ፣ ጠቃሚ ትስስሮችን (networking) መመሥረትና በሙያዊ ሥነ ምግባር ማብቃት መሆኑን ይገልፃሉ። የአባላትን ሙያዊ ክህሎት እና እውቀት ለማሳደግ፣ የሥነምግባር ልምዶችን ለማስተዋወቅ፣ ፈጠራን እንዲሁም ተወዳዳሪነትን በኢንዱስትሪው ውስጥ ለመምራት በቁርጠኝነት ለመሥራት እንደተነሱም ያስረዳሉ።

«የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከሀገሪቱ አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ከመመደቡ ጋር ተያይዞም የፖሊሲ ግብአቶችን ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ያቀርባል፣ ያወያያል እንዲሁም በቅርበት ለተፈፃሚነታቸው ይሠራል» የሚሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ፤ አዲስ አበባ ከኒዮርክ እና ከጄኔቫ በመቀጠል ሦስተኛዋ የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ በከተማው የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የሚመች እና የሚመጥን ሙያዊ ልህቀት እንዲኖር ከማኅበሩ አባላት ጋር እንደሚሠሩ ገልፀዋል።

«የከተማችንን እና የሀገራችንን ገፅታ በማሳደግ እና ለሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ምቹ ሁኔታን የምንፈጥር ይሆናል» የሚሉት ፕሬዚዳንቱ ማኅበሩ በዘርፉ በጥናትና ምርምር፣ በሥልጠናና በማማከር ሙያዊ አበርክቶን ለመወጣት እቅድ ይዞ የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህም ባሻገር በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ይገልፃሉ። ይህንን ርዕይ ለማሳካትም ከሚመለከታቸው የመንግሥት እና የግል ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ ያስረዳሉ። የቱሪዝም ዘርፍ በትብብር እና ቅንጅት መሥራትን እንደሚፈልግ የሚገልፁት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ይህንን አስመልክቶ ከመንግሥት ተቋማት፣ ኤጀንሲዎች፣ ከኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት እና ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በንቃት በመሳተፍ የዘርፉን እድገትና ልማት የሚደግፉ ፖሊሲዎችና ደንቦች ለመቅረጽ እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ለዘላቂ የቱሪዝም ልምዶች የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎች እና የከተማዋን እንደ መዳረሻ መስህብ የሚያጎለብቱ ጅምር ሥራዎችን ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው አጋዥ ኃይል እንደሚሆኑም ነው የተናገሩት።

በምስረታው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደሚናገሩት፤ የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ለከተማዋና ዘርፉን ለሚመራው ቢሮ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በተለይ ከቱሪዝም ዘርፍ ከተማው ሊሠራና ሊያሳካ ያቀዳቸውን ተግባራት ስኬታማ ለማድረግ ማኅበሩ አጋዥ ኃይል ነው። አባላቱ ረዘም ያሉ ዓመታት በዘርፉ ልምድ ያካበቱና በቂ እውቀት ያላቸው በመሆኑ የከተማዋን የቱሪዝም እድገት ለማፋጠን ከማገዙም ባሻገር ለሀገር እና ለመላው አፍሪካ ተጨማሪ አቅም ይሆናሉ። በተለይ ከሥነ ምግባር እና ዘርፉ የሚፈልገውን ሙያዊ አገልግሎት ከማቅረብ አንፃር በማኅበሩ የተሰባሰቡት ባለሙያዎች የሚኖራቸው አበርክቶና ድርሻ ከፍተኛ ነው።

«በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሉ ማኅበራት ድንበር የላቸውም» የሚሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ የሚታዩ ክፍተቶች፣ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮችን ጨምሮ ዘርፉን ለማሳደግ የሚጠቅሙ ምክረ ሃሳቦችን የሆስፒታሊቲና አገልግሎት ዘርፍ እውቀቶችን መለዋወጥ እንደሚገባ ይናገራሉ። ምስረታውን ይፋ ያደረገው ማኅበርም ይህንኑ ሚናውን እንደሚወጣ እምነታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። አዲስ አበባ በቱሪዝም ሀብትነት የሚገለፁ ሁሉንም ገፀ በረከቶች የያዘች መሆኗን በማንሳትም እነዚህን ፀጋዎች ተረድቶና አልምቶ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገትና ገፅታ ግንባታ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ከዚህ አንፃር ማኅበሩ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንደሚሉት፣ ባለፉት ጊዜያት በቱሪዝም ዘርፍ የደረሱ ጉዳቶችና ጫናዎችን በመቋቋም አሁንም ድረስ ተስፋ ሰንቀው ለኢንዱስትሪው እድገት የሚሠሩ አሉ። በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ በትብብርና በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበርን መመሥረት ተጨማሪ አቅም ይሆናል። በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ቆየት ያሉ ነባር ማኅበራት፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መደጋገፍና አብሮ መሥራት ቱሪዝም ሚኒስቴር እራሱን ችሎ እንዲቋቋምና ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ እንዲሆን የራሱን ድርሻ ተወጥቷል።

«ለቱሪዝም እድገት የግሉ ዘርፍና የሲቪክ ሶሳይቲ ተዋንያን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው» ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ለማምጣት በቀዳሚነት የግሉ ዘርፍ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ። የአዲስ አበባ የሆቴል ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልፀው ይህንን መሰል ማኅበራት መፈጠራቸው በዘርፉ ለማምጣት ለሚፈለገው ስር ነቀል ለውጥ ጉልበት እንደሚሆኑ ይገልፃሉ። በተለይ ማኅበራት ለቱሪዝም ዘርፉ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦን በተመለከተ የነበረውን ሰፊ ክፍተት የሚሞላና ፋይዳውም ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።

የቱሪዝም የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ የሚሳተፈውና በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ውስጥ በመምህርነት የሚያገለግለው አቶ በቀለ ኡማ በበኩሉ የማኅበሩ ምሥረታና ይዞት የመጣውን የትግበራ ሂደት አስመልክቶ አጭር ዳሰሳዊ ጽሑፍ አቅርቧል። በማብራሪያውም ቱሪዝም ከሌሎች ዘርፎች በተሻለ ከፍተኛ የሰው ኃይል የመያዝና የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ይናገራል። ይህንን ዘርፍ በብቃት ለመምራትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከመንግሥት ባሻገር የግሉ ዘርፍና ሲቪክ ሶሳይቲዎች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ይገልፃል። በተለይ በዘርፉ ምስረታውን ይፋ ያደረገው የአዲስ አበባ ሆቴል ቱሪዝም ባለሙያዎች ዓይነት ማኅበራት ጠቀሜታቸው ጉልህ መሆኑን ያነሳል። በዘርፉ ረዘም ላሉ ዓመታት ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች የተመሠረተው የአዲስ አበባ ሆቴል ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበርም በአዲስ አበባ ከተማና ከፍ ሲል በሀገር ደረጃ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያድግ የድርሻውን የሚወጣ እንደሆነ ይገልፃል።

«የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ተወዳዳሪነትን የሚጠይቅና ቀጣይነት ያለው ተከታታይ ለውጦችን የሚሻ ነው» የሚለው አቶ በቀለ ኡማ፤ ይህንን እውን ለማድረግ በዘርፉ ያሉ የሆቴል፣ የአገልግሎት ዘርፍ ተቋማት፣ አስጎብኚዎች፣ ቱር ኦፕሬተርስና መሰል ባለሙያዎች በጥምረት ቢሠሩ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ይናገራል። ለዚህም ጠንካራ ማኅበራት ወሳኝ ድርሻ እንደሚይዙ ይገልፃል። በተለይ በግሉ ዘርፍ አቅም የማይሞከሩ የመሠረተ ልማቶች እና የመዳረሻ ልማት ሥራዎች ላይ መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ ሥራዎችን ሲሠራ ማኅበራቶች በማማከር ሙያዊ ድጋፍ መስጠት፣ ጥናትና ምርምር ላይ ለመሳተፍ፣ የፖሊሲና ሕጎች ላይ ግብአት በማቅረብ ረገድ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚችሉ ይገልፃል። አዲስ አበባን መሠረት አድርጎ የተመሠረተው ማኅበርም ይህንኑ ኃላፊነት እንደ አንድ የሙያ ግዴታው በመቁጠር ኃላፊነት እንደሚወስድ ይናገራል።

«የአዲስ አበባ የሆቴል ቱሪዝም ባለሙያዎች በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ያሉ ንግዶች ራሳቸውን ችለው በጥንካሬ ቆመው መንግሥትን ለመደገፍ እንዲችሉ ያመቻቻል» የሚለው አቶ በቀለ ኡማ፤ በዘርፉ ያሉ ንግዶች እራሳቸውን ከቻሉ መንግሥት ከግብርና ልዩ ልዩ ጥቅሞች በሚያገኘው የኢኮኖሚ ድጋፍ መሠረተ ልማቶችን ለመደገፍ እንደሚያስችለው ይገልፃል። ማኅበረሰቡም የሥራ ዕድል እንዲያገኝ እና እራሱን እንዲለውጥ ከማድረግ አንፃርም የበኩሉን እንደሚወጣ ይናገራሉ።

አዲስ አበባ ከተማ ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙበት በመሆኗ ምክንያት በተለይ በሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የማደግ ዕድል እንዳላት የሚገልፀው መምህሩና የጥናትና ምርምር ምሁሩ በቀለ ኡማ፣ የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር ይህንን ዕድል ተጠቅሞ ኢትዮጵያ ከቱሪዝሙ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማቅረብ፣ የቱሪስት ፍሰቱን የሚጨምር ስልት በመንደፍና ለመንግሥት በማቅረብ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች በኢትዮጵያ እንዲካሄዱና የማይስ ቱሪዝም እንዲበረታታ ለማስቻል ውትወታ (Advocacy) በመሥራት እንደሚሳተፍ እና የዘርፉ አጋዥ ኃይል እንደሚሆን አስረድቷል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You