ወጣት ሱራፌል መዝገቡ በአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻ መናፈሻ የመጀመሪያው ምዕራፍ በሚከናወንበት አራዳ ክፍለ ከተማ ነው የሚኖረው። መኖሪያው በፕሮጀክቱ አቅራቢያ በመሆኑም ተደስቷል።
ሰው በአካባቢው ጥሩ ነገር ማየት እንዳለበትም እምነቱ ነው። የፊታችን እሁድ በዕለተ ሰንበት አዲስ አበባ ከተማን ጠዋት በጽዳት ዘመቻ፣ ማታ ደግሞ አዲስ አበባን ውብ የማድረግ ዓላማ ያነገበው የገበታ ሸገር የእራት ግብዣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መካሄዱ እንደተመቸው ስሜቱን አጋርቶኛል።
የእራት ግብዣው ላይ የመገኘት ዕድል ባይኖረውም በጠዋት የጽዳት ዘመቻው ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነው።ብዙዎች ለቤታቸው የውስጥ ንጽህና እንጂ ለአካባቢያቸው ሲጨነቁ አይስተዋልም የሚለው ወጣቱ ይህ ባህል መቀየር እንዳለበት ያምናል።
ጽዳት ለማጽዳት ቀስቃሽ መጠበቅ የለበትም ይላል። በግሉ የተጠቀመባቸውን ነገሮች በመንገድ ላይ እንደማይጥል ይገልጻል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማን የማስዋብ ጥረት ሁሉንም ባሳተፈ ከቀጠለ በእይታም በበጎአስተሳሰብም ምቹ የሆነች ከተማ እንደምትሆን ተስፋ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጽዳትና የአዕምሮ ንጽህናን በማስተሳሰር ሰዎች ለበጎ ነገር እንዲነሳሱ የገለጹበትንም መንገድ ወጣት ሱራፌል በሀገሪቷ የተፈጠሩትን ሁከቶችና አላስፈላጊ ችግሮች ለማስወገድ ጭምር የተጠቀሙበት ዘዴ መሆኑና የሚደግፈው ሀሳብ እንደሆነ ተናግሯል።
ጥሩ ነገር ማየት አንዱ የአእምሮ ማነቃቂያ መንገድ እንደሆነ ይገነዘባል። ሁሉም የጠቅላይ ሚኒስትሩን በጎ አስተሳሰብ ተቀብሎ ከተባበረ የተጀመረው ሥራ እንደሚሳካም እምነቱ እንደሆነ ገልጿል።
የሲቪል ኢንጂነሪንግ ባለሙያዋ ወጣት አያንቱ ካሳሁን በሙያዋ ድጋፍ ብትጠየቅ ወደኋላ እንደማትል ነው የነገረችን። በሙያና በገንዘብ የህብረተሰብ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የወንዝ ዳርቻዎችን ለማስዋብና በጽዳትም መነቃቃት ለመፍጠር የጀመሩትን ሥራ በመገናኛ ብዙሃን በሰማችበት ጊዜ መደሰቷን ገልጻለች።
አዲስ አበባን ለሚያህል ትልቅ ከተማ ወንዝዳርን የተከተለ መ ናፈሻ መኖሩ አግባብ እንደሆነ የምትገልጸው ወጣት አያንቱ የወንዝ ዳር ልማቱ ሲጠናቀቅ ምን መልክ እንደሚኖረው ዲዛይኑን በማየቷ አልቆ ለማየት እንደምትጓጓ ትናገራለች። በስፍራው መጽሐፍ በማንበብና በመዝናናት የምታሳልፈው ጊዜ ከወዲሁ በምናቧ ታይቷታል።
በምትኖርበት አካባቢ ሲኤምሲም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የጽዳት ጉድለት መኖሩን ማስተዋሏንና አካባቢን የማጽዳት ባህሉ እንደሌለ ታስረዳለች።የጽዳት መጓደል ለሥራ እንደማያነሳሳና የአእምሮ መነቃቃት እንደማይኖር ታስረዳለች። ሰዎች የደስታ ስሜት ሲኖራቸው አስተሳሰባቸውም በጎ እንደሚሆንና ጥቅሙም ለራስ እንደሆነ ትገልጻለች። እርሷን ጨምሮ ከምንአገባኝ ወጥቶ አዲስ አበባ ከተማ የሁላችንም ናት በሚል ስሜት በከተማ ደረጃ ማጽዳት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፋለች።
‹‹ሰዎች አእምሮአቸውን የሚያሳርፉበት፣ ዘና የሚሉበትና ማንበቢያ ቦታ ያገኛሉ።የሚያነብ ሰው ደግሞ አስተሳሰቡ በመልካም ይቀየራል።ጥሩ አካባቢ የሚያይ ሰው በሥነ ልቦናውምጥሩ ይሆናል።
አረንጓዴ ስፍራ መኖሩ ሰዎች ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ለመነጋገርና ሀሳብ ለመቀያየር ዕድል እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።ሀሳብ የሚለዋወጥ ማህበረሰብ መፍጠር ሲቻል አሁን የምናየውን በማህበራዊ ድረ ገጽ ሳይቀር መረጃ በመለዋወጥ እኩይ የሆነ ተግባር መፈጸም ይቀራል›› በማለት የወንዝዳር ልማቱን አስፈላጊነት የገለጹት የተፋሰስና የአረንጓዴ አካባቢዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስለሺ ደገፋ ናቸው።
እንደ ዶክተር ስለሺ ገለጻ የወንዝ ዳር ልማቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉበት። በአዲስ አበባ ከተማ (ፓርክ) መናፈሻ ባለመኖሩ ሕጻናት ስለ አካባቢ ጥቅም ሳያውቁ ነው የሚያድጉት።ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዲያሳልፉ ተገደዋል።አልባሌ ቦታ መዋላቸው የሁከትና ግርግር ተሳታፊ እንዲሆኑና በዘር ፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ እንደ አንድ መንስኤ ሆኗል።
‹‹ወንዞቻችን ጥሩ ምሳሌ ናቸው።ብሔርን መርጠው አይደለም የሚያቋርጡት።በእያንዳንዱ ደጃፍ ነው የሚፈሱት።ወንዞች የምንሰባሰብበት ቦታና ችግሮቻችንንም የምንፈታበት ሊሆኑ ይችላሉ›› በማለት በምሳሌ አስረድተዋል።ህብረተሰቡም ጥቅሙን ተገንዝቦ የአቅሙን ድጋፍ በማድረግ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ለማ በበኩላቸው አካባቢን ጽዱ የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ድርሻ እንደሆነ ያምናሉ።ይሁን እንጂ በአንድ አካል ብቻ ውጤታማ መሆን አይቻልም ይላሉ። ማህበረሰቡ፣ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዓለም አቀፍና ግብረሰናይ ድርጅቶች ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ጥሩ የሚባለው የሕዝብ እሴት ጠብቆ ለማቆየትም ሆነ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ጽዱ አካባቢ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ወንዞች ውስጥ እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል አደገኛ ነገር መኖሩንና በከፍተኛ ሁኔታም የተበከለ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህ ላይ በመረባረብ ጽዱ ማድረግ ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ነው የገለጹት።
የፊታችን እሁድ በሀገሪቱ የሚካሄደውን ጽዳትና አዲስ አበባን የማስዋብ አካል በሆነው የገበታ ሸገር የእራት ግብዣ መርሐ ግብርን አስመልክተው በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ለፋና ብሮድካስቲንግ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጹት፣ የእራት ግብዣ መርሐ ግብሩ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የሚጀምር ሲሆን፣ታሪካዊ በሆነው የምኒልክ የግብር አዳራሽ ውስጥ ነው የሚከናወነው።
እግረ መንገድም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን መስከረም ወር ላይ በሙዚየም ለህዝብ እይታ ክፍት ለማድረግ እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎችን ማሳየትም የመርሐ ግብሩ አካል ነው።የሚከናወነው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ሁሉ ያሳተፈ ሲሆን፣እስከ ግንቦት 9 ቀን 2011ዓም ድረስ ለገቢ ማሰባሰቢያ የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ክፍት በመሆኑ ተጋባዦች ይጠበቃሉ።
ለገቢ ማሰባሰብ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ አቅማቸው ያልፈቀ የተለያዩ አካላትም በሚችሉት የገንዘብ አቅም ድጋፍ በማድረግ የታሪክ አካል በመሆን በመሳተፍ ላይ ናቸው።በቀጣይ ሁሉንም የሚያሳትፍ መርሐ ግብርም ይዘጋጃል።
በጠዋት መርሐ ግብርም በመላ ሀገሪቱ ከጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ የጽዳት ዘመቻ እንደሚከናወንና ሁሉም አካባቢውን በማስዋብ እንዲሳተፍ ቢልለኔ ጥሪ አቅርበዋል።በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሚያዚያ ወር ላይ የተጀመረው የጽዳት ዘመቻ ቀጣይነት በህብረተሰቡ ባህል ሆኖ እንዲቀጥልና ቂምና ጥላቻን በጽዳት የማስወገድ መርህ ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።
ጽዳቱና ሸገርን የማስዋብ እንቅስቃሴ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ፣ የከተማ ቱሪዝምን ለማሳደግ፣ለገጽታ ግንባታ፣ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
52ኪሎ ሜትር ከሚሸፍነው የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻዎችን ለመናፈሻ የማዋል ሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር የጣሊያን ኩባንያ በሆነው ቫርኔሮ መጀመሩን ባለፈው እትም ማስነበባችን ይታወሳል።አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስድስት መቶ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 76 ወንዞች ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
በለምለም መንግሥቱ