ነገን – በጭላንጭል

አዲሱ ዓመት ተቃርቧል፡፡ ሁሉም በየቤቱ ስለጓዳው ማሰብ እየጀመረ ነው፡፡ ዓውደ ዓመት በመጣ ቁጥር ይህን ማቀዱ ብርቅ አይደለም፡፡ በተለይ ጊዜው አዲስ ዓመት ከሆነ ዝግጅቱ ለየት ይላል፡፡ ይህ በዓል ሁሌም የጋራ ነው፡፡ ሀይማኖት፣ ወገን አይመርጥም፣ ሰው ከሰው አይነጥልም፡፡ ሁሉም በእኩል ተቀብሎ በአንድ ያከብረዋል፡፡

እነሆ ! በዚህ ጊዜ እናቶች ጓዳቸውን ያስባሉ። አባወራዎችም ግዴታቸውን አያጡትም፡፡ ስለ ቤታቸው፣ ስለቤተሰባቸው ሲሉ ከበጉ፣ ከቅርጫው፣ መንደር፣ አይጠፉም፡፡ ልጆች ደግሞ የልምዳቸውን ያውቁታል። አዲሱ ዓመት ሁሌም ገዳቸው ነው፡፡ ከአዲስ ልብስ፣ ከአዲስ ጫማ ያገናኛቸዋል፡፡ ይህን ጊዜ ሲጠብቁት በአዲስ መንፈስ ጓግተውና ናፍቀው ነው፡፡

ወይዘሮ ዓለም ድረሴ በእስከዛሬዎቹ ዓመታት ከእነዚህ እውነታዎች አልራቁም፡፡ አዲስ ዓመት ለእሳቸው የአዲስ መንፈስ ጅማሬ ነው፡፡ ዓመቱን ለፍተው፣ ደክመውበት ሲጠናቀቅ የላባቸውን ይቋጥሩበታል፡፡

ይህ ጊዜ የለፉበት፣ የደከሙበትን ጊዜ አሳልፎ ከአዲስ መንገድ ሲያደርሳቸው ኖሯል፡፡ ሁሌም ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ አንደበታቸው በምስጋና እንደተሞላ ነው፡፡ ደጋግመው ‹‹ተመስገን›› ይላሉ፡፡ ዝናቡን፣ ዶፉን፣ ጨለማውን ወስዶ ከብራው፣ ከጸሀዩ ያደረሳቸውን ፈጣሪ አብዝተው ያመሰግናሉ፡፡

ወይዘሮዋና ዘንድሮ

ዓለም ዘንድሮ እንዳለፉት ዓመታት ደስተኛ አልሆኑም። አንድ ጉዳይ ውስጣቸው ገብቷል፡፡ በየቀኑ ሀሳብ ያስጨንቃቸዋል፡፡ አሁን በዓል ዓውደ ዓመቱ ጉዳያቸው አልሆነም፡፡ ከእሱ አልፎ ስለነገ አብዝተው ያስባሉ፡፡ ምን እሆናለሁ? የት እደርሳለሁ? ይሉት ጉዳይ አብሯቸው መዋል ማደር ከያዘ ሰንብቷል፡፡ ይተክዛሉ፣ ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ፡፡

ዘንድሮ እንደቀድሞው ዳቦውን፣ ዶሮውን የሚሉበት አቅም ከእሳቸው የለም፡፡ ጓዳቸውን ሞልተው፣ ጎረቤቱን፣ ወዳጅ ዘመዱን አይጠሩም። ዓመቱን መሻገራቸው፣ ሰላም መድረሳቸው እንደ ሁልግዜው አመስጋኝ አድርጓቸዋል፡፡ የሆነባቸውን ሲያስቡት ግን እጅግ ይከፋሉ፡፡ አሁን ነገሮች ከአቅማቸው በላይ እየሆኑ ነው፡፡

ወይዘሮ ዓለም የጉልት ነጋዴ ናቸው፡፡ ለዓመታት በቤት ኪራይ ኖረዋል፡፡ ሁለቱ ልጆቻቸው ከእሳቸው ጋር ክፉ ደግ ያሳለፉ ናቸው፡፡ ያለ አባት ሲያሳድጓቸው የአቅማቸውን አድርገው፣ የእጃቸውን አሟልተው ነበር። ከጊዜያት በኋላ ግን ትከሻቸው አልቻለም፡፡

አንደኛው ልጅ ከዘመድ ቤት ተጠግቶ እንዲኖር ወሰኑ። እንዲያም ሆኖ ዝም አላሉም፡፡ ሰው እንዳያስቸግር፣ እሱም እንዳይቸገር የአቅማቸውን መሸጎጥ ያዙ፡፡ ለጊዜው በመጠኑ ሀሳብ ቀለለ፡፡ ከሴቷ ልጅ ጋር ህይወት በመልካም ቀጠለ፡፡ ኑሮ ቢከብድም አላማረሩም፡፡ ከጉልታቸው እየዋሉ በምስጋና አደሩ፡፡

ዓለም ጉልት ሲሸጡ የሚይዙት ብዙ አይደለም። የእጃቸው ሲያልቅ በመጠኑ አምጥተው ደንበኞችን ይጠብቃሉ፡፡ እንደሌሎች በርከት ለማድረግ አቅሙ የላቸውም፡፡ እንደምንም የጠረቃቸውን ገቢ አንድ ሁለት ብለው ለቤት ኪራይ ያውላሉ፡፡

አንዳንዴ ገበያ እንደታሰበው አይቀናም፡፡ ከእሳቸው ይልቅ ገበያተኛው የተሻለውን ይመርጣል፣ ያማርጣል። እንዲህ ሲያጋጥም ፀሀይ ሲመታቸው ውሎ የረባ ሳይሸጡ ይገባሉ፡፡ ማግስቱን ከያዙት የጉልት አትክልት የተበላሸውን ይጥላሉ፡፡ የተረፈውን መራርጠው መንገደኛውን፣ ደንበኞችን ይናፍቃሉ፡፡

ሁሌም ዓይን ዓይን የሚያዩበት ገበያ እንደታሰበው ላይቀና ይችላል፡፡ ጠያቂ ከተገኘ ከምርቃቱ ጨማምረው፣ ካለው አክለው ለነገው ያስባሉ፡፡ እንደወጠኑት ከቀናቸው ‹‹እስየው›› ነው፡፡ የያዙትን ይዘው በምስጋና ያድራሉ፡፡

ዓለምና የጉልት ስራ እንዲህ ሲደጋገፉ ዓመታትን ዘልቀዋል፡፡ ከዚህ ቀድሞ ልጆች ለማሳደግ ያልሰሩት፣ ያልሞከሩት አልነበረም፡፡ ከሰው ቤት እየዞሩ ልብስ አጥበዋል፣ እንጀራ ጋግረዋል፡፡ አሻሮ ቆልተዋል፡፡ የሚያገኙት ጥቂት ገንዘብ በወቅቱ ቤታቸውን ደግሞ ልጆችን አስ ተምሯል፡፡

ይህ አይነቱ ሥራ ከብዙዎች አገናኝቶ አስተዋውቋቸዋል። ቆይቶ ግን አቅማቸውን ፈተነው። ከእሳት ጋር ውሎ ማምሸቱ ለጤናቸው ጠንቅ ቢሆን አማራጮች ፈላለጉ፡፡ የኑሯቸው ሁኔታ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ዛሬን ልረፍ፣ ነገን ልተው አይሉበትም፡፡ እያመማቸው፣ እየተቸገሩ ለህይወታቸው ታገሉ፡፡ አንድ ቀን ግን ራሳቸውን ከጉልት ገበያ ውስጥ አገኙት፡፡

ዓለም ስራውን አልጠሉትም፡፡ ካሳለፏቸው የድካም ዓመታት የጉልቱ ውሎ የተሻለ ሆነ፡፡ እንዲያም ሆኖ ስራው ስጋት አለው፡፡ የሚይዙት ዕቃ ከአቅማቸው የመጠነ ነው። ‹‹አብልጬ ልሽጥ›› ካሉ ጥሩ መነሻ ይፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ አይችሉም፡፡ እንዲህ ካልሆነ ደግሞ የቤቱ ነገር ይጎድላል፡፡ የገቢው ጉዳይ ያሳስባል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በየቀኑ ስራው ሕጋዊ አይደለም የሚሉ ደንብ አስከባሪዎች ምቾት አይሰጧቸውም። የያዙትን ዘርግተው ቁጭ ከማለታቸው ቆመጥ የያዘ፣ አንድ አይነት የለበሰ ግብረኃይል ደርሶ ድራሻቸውን ያጠፋዋል፡፡ አንዳንዴ ችግሩ በዚህ አያበቃም፡፡ ደንቦቹ ድንገት ከደረሱ የጉልቱን አትክልት ከመሬቱ፣ ከጭቃው ቀላቅለው ይበትኑታል፡፡ ቀርቦ ልለምን፣ ልማጸን የሚል ካለ ምላሹን ከዱላ ያገኘዋል፡፡

ወይዘሮ ዓለም ይህን አጋጣሚ ደጋግመው አልፈውታል። ብዙ ግዜ ከደንቦች ተሯሩጠው የእጃቸውን ተነጥቀዋል፡፡ አልቅሰው፣ አንብተው፤ ከእግር ወድቀው አስመልሰዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ታግለው ቤት ሲደርሱ ስለ ነገው ይጨነቃሉ፡፡ ዛሬን ካላሰቡ ነገ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህ የጉልት ቸርቻሪዋ ወይዘሮ ዓለም የየዕለት ገጠመኝ ነው፡፡

የቀን ደግ

ከቀናት በአንዱ ይህን ችግር የሚፈታ በጎ ቀን ነጋላቸው፡፡ ለወይዘሮ ዓለም በመሳቀቅ ለሚሯሯጡበት ህይወት መፍትሄው ተገኘ፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ‹‹ህገወጥ ናችሁ›› የተባሉ በሚመለከታቸው አካላት ማረጋገጫ ‹‹ህጋዊ ሆናችኋል›› ተባሉ፡፡ በሁሉም ዘንድ ደስታ ነገሰ፡፡ እፎይታም ሆነ፡፡

እንዲህ መሆኑን ተከትሎ ሁሉም የጉልት ሴቶች በቡድን ተደራጁ፣ የሥራ ቦታም ተሰጣቸው፡፡ ወዲያው በደረታቸው ባጅ አንጠልጥለው፣ ህጋዊ ግዴታን ተከተሉ፡፡ ጊዜ ቆጥረው፣ ግብር መክፈል፣ ኃላፊነት መወጣት ያዙ፡፡ ያለ ችግር ሽንኩርት ቲማቲም፣ ድንች፣ ጎመን መሸጥ፣ መቸርቸር ያዙ፡፡

ዓለም እንደሌሎች ባይሆንም በአቅማቸው ገዝተው መቸርቸር ልምዳቸው ሆነ፡፡ ብዙ ባያተርፉም ለቤት፣ ለጓዳቸው አላጡም፡፡ በምሥጋና ውሎ ማደር፣ ነገን በተስፋ መጠበቅ ልምዳቸው ሆነ፡፡ ኑሮ እንዳሰቡት ባይሞላም አልከፋቸውም፡፡ ያላቸውን አቻችለው፣ ፈጣሪን አመስግነው ህይወትን ቀጠሉ፡፡

«ነበር›› እንደዋዛ!

ቀናት፣ ወራት ዓመታት በጎ ሆነው አለፉ፣ ያለችግር ስጋት የተራመዱባቸው መንገዶች ለወይዘሮ ዓለም ነገን አሻግረው አሳይዋቸው፡፡ የዛሬን ይዘው የትናንቱን አሰቡት፡፡ ስራን አጥብቀው ከያዙት መጪው ጊዜ እንደማይከብዳቸው ገመቱ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ግን ይህን ታሪክ ሽሮ አንገት የሚያስደፋ ክፉ አጋጣሚ ሆነ፡፡ ሰርተው የሚያድሩበት፣ እንጀራ የሚያገኙበት ቦታ ሊፈርስ ስለመሆኑ ጭምጭምታ ሰሙ፡፡ ጆሯቸውን አላመኑም፡፡ ጉዳዩ እያስደነገጣቸው፣ ሁኔታውን አጣሩ። ከጠየቋቸው ሰዎች የጉዳዩን እውነታ አረጋገጡ፡፡ በድንጋጤ ስለራሳቸው አሰቡ፡፡

አሁን እንደቀድሞው ከደንቦች አይሯሯጡም፡፡ ገቢያቸው ብታንስም ህጋዊ ሆነው፣ ግብር እየከፈሉ፣ በአግባቡ እየሰሩ ነው፡፡ ይህን ሲያስቡ ውስጣቸው መለስ አለ፡፡ የሰሙት ዕውን እንደማይሆን ለራሳቸው ነግረው በ‹‹እግዜር ያውቃል›› ልማድ ተጽናኑ፡፡ በእፎይታ አምሽተው አደሩ፡፡

ማግስቱን ስፍራው ሲደርሱ የተባለው እውነት ሆኖ አገኙት፡፡ አሁን የእሳቸውን የጉልት ቦታ ይዞ የሌሎች ገበያ ቦታ እየፈረሰ፣ እየተናደ ነው፡፡ ደነገጡ፣ ጮሁ፡፡ ለምን? ስለምን? ሲሉ ያገኘዋቸውን ጠየቁ። ሰሚ አላገኙም፡፡ እንደሳቸው የሆኑ ሌሎች ሴቶች ተቀላቀሏቸው፡፡

ሁሉም ኑሯቸውን እያሰቡ፣ ቀጣይ ህይወታቸውን ገመቱ፡፡ የአብዛኞቹ ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም ሌላ ገቢ የላቸውም፡፡ ልጆች አሳደጊ፣ ቤተሰብ አሳዳሪ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ በቤት ኪራይ ይኖራሉ፣ ህይወት ስሜታቸው ቢያመሳሳል በእኩል አነቡ፣ አዘኑ፡፡

ለ…… «ይድረስ አቤቱታ….››

ጊዜ አልፈጁም፡፡ ሰብሰብ ብለው ለሚመለከታቸው ህጋዊ መሆናቸውን እየጠቆሙ ሁሉን ሊያስረዱ ሞከሩ። አቤቱታቸው ሚዛን አልደፋም፣ ውሀ አላነሳም፡፡ በሁሉም ዘንድ ፊት ተነሱ፣ ከስፍራው ተባረሩ፡፡

ይባስ ብሎ በወጉ ከስፍራው ያልተነሱ፣ ለመሸጥ የተዘጋጁ አትክልቶቻቸው በመኪና ሲጫኑ ተመለከቱ። የአብዛኞቹ በሳጥንና በማዳበሪያ የተሞሉ ናቸው፡፡ እነሱን ሊያስጥሉ፣ ሊያተርፉ በተማጽኖ ተለማመጡ፡፡ አዲስ ነገር አልሆነም፡፡ ተገፍትረው ከቦታው ራቁ፡፡

እማዋራዋ ዓለም ሌላ ገቢ የላቸውም፡፡ ልጆቹ ቢያድጉም ህይወትን የሚለወጥ ሥራ ላይ አይደሉም፡፡ ከዓመታት በፊት በሞት ካጧቸው አባወራ የወረሱት አንዳች ጥሪት የለም፡፡ በአንድ ጊዜ ሰማይ በእናታቸው የተደፋ ያህል ጨነቃቸው፡፡ በየወሩ እያሰሉ ከሚከፍሉት የቤት ኪራይ የዘለለ ብዙ አይቆጥቡም፡፡ ይህን ካደረጉ ድፍን አንድ ወር ሞልቷል፡፡ አሁን አከራይዋ ከእሳቸው የወር ገቢያቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ ዓለም ይከፍሉት፣ ይቆጥሩት ብር ከእጃቸው የለም፡፡

ዛሬን ሞልተው ነገን በተስፋ በሚያድሩበት፣ ከእጅ ወደአፍ እያደረጉ ጊዜያትን ቆጥረዋል፡፡ በየወቅቱ የሚፈትናቸው የኑሮ ውድነት የየዕለት ሀሳባቸው ነው፡፡ አንዱን ሲሞሉ ሌላው መጉደሉም ብርቃቸው አይደለም፡፡

እሳቸው ቢታመሙ፣ ችግር ቢገጥማቸው ከመሀረብ የሚተርፍ፣ ከዕለት ጉርስ የሚሻገር ተቀማጭን አያውቁም፡፡ ሁሌም ዛሬን ባገኙት ይኖራሉ፡፡ ነገን እንደአመጣጡ ያልፋሉ፡፡ አሁን ግን የገጠማቸው ችግር ከሌላው ዓመት ብሷል፡፡ በዋዛ መፍትሄ የሚሰጡት፣ እንደቀልድ ሰምተው የሚያልፉት አልሆነም። ጨንቋቸዋል፡፡ ሀዘናቸው ከዕንባ በላይ ሆኖ ሲያሳስብ፣ ሲያስተክዛቸው ይውላል፡፡

ዓለም በዚህ ወቅት ብዙ ጉዳይ ያሳስባቸዋል፡፡ የሚሰሩት ከሌለ፣ ገንዘብ አያገኙም፡፡ ገንዘብ ካጡ ቤት ኪራይ መክፈል፣ ኑሮን መቋቋም አይሆንም፡፡ እናም ይላሉ ‹‹ያለኝ ምርጫ ጎዳና ላይ መውጣት፣ ከመንገድ መውደቅ ነው››

ወይዘሮዋ ይህን ቢሉም ሀሳቡ ቀላል እንዳልሆነ ያውቃሉ፡፡ ጎዳና ለእሳቸውም ሆነ ለደረሰች ልጃቸው ፈጽሞ አይበጅም፡፡ ይህ ህይወት እንደ ቤት ኪራይ ፈልገው የሚገቡበት፣ መርጠው የሚኖሩበት ዕድል አይሰጥም፡፡ አሁን ለጊዜው በአስኮ አዲስ ሰፈር አንድ ጥግ ከደንቦች እየተሯሯጡ ያቅማቸውን መሸጥ ይዘዋል፡፡

ይህ አይነቱ ያልተመቸ ውሎ በእሳቸው ዕድሜ ፈጽሞ አይመችም፡፡ ከእጃቸው ያለውን ጥቂት የጉልት ሸቀጥ ሸጦ ለመግባት በየቀኑ አይሆኑት የለም። እሳቸው እንዲህ ባይሆን ይወዱ ነበር፡፡ ሆኖም ምርጫ የላቸውም፡፡ ከክረምቱ ተጋፍተው፣ ከደንቦቹ ተፋጠው ለዕለት ጉርስ ለመያዝ ሽሚያ ጀምረዋል፣ ቀናትን ቆጥረዋል፡፡

ወይዘሮዋ ያሉበት የህይወት ትግል ከዓመታት በፊት ያሳለፉትን ችግር ያስታውሳቸዋል፡፡ ያለፈው ታሪክ ‹‹ ይዤዋለሁ›› ባሉት ህጋዊነት የተፈታ ቢመስላቸው ችግራቸውን ችለው፣ ነገን ተስፋ አድርገው መኖር ችለው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ነገን ስለሚያሻግራቸው ጭላንጭል ተስፋ እርግጠኛ አልሆኑም፡፡

አሁን አዲስ ዓመት ተቃርቧል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም እንደ ቤት እንደ አቅሙ ለመሆን ጓዳውን ያያል፡፡ በዛም አነሰም በዓውደ ዓመት ‹‹አንዳች የለም ›› ተብሎ ቤት አይዘጋም፣ እሳቸው ግን ስለቤትና ኑሮ ስጋት ገብቷቸዋል። ያልሞላው ውሎ የኪራይ ገንዘብ አጉድሎባቸዋል፡፡ ዛሬ ነገ ሲሉ ያቆዩት ክፍያ ቀን እየቆጠረ፣ ጊዜ እየጨመረ ነው።

ዓለም ምን ቢቸግራቸው ለዓውደ ዓመት ቤታቸው ጎድሎ አያውቅም፡፡ የአቅማቸውን አድርገው፣ ያላቸውን ንፁህ ለብሰው በደስታ ያሳልፉታል፡፡ በግ፣ ቅርጫው ቢቀር ለቡና፣ ዳቦው አያጡም፡፡ ለወዳጅ ዘመድ ቀናት የሚጋብዝ ድግስ ባይኖርም ከዶሮው፣ ከጠላው ማለታቸው አይቀርም፡፡

እንዲህ ባደረጉ ቁጥር ጎዶሏቸው ሞልቶ፣ ጨለማቸው በርቶ ይታያቸዋል፡፡ ቤታቸው የኪራይ ቢሆንም በምስጋና ማደር ልምዳቸው ነው፡፡ አቻ ጎረቤቶች ጠርተው፣ ካላቸው አቃምሰው ‹‹እንኳን አደረሰን፣ አደረሳችሁ›› ማለትን ያውቁበታል፡፡ ይህ አይነቱ አጋጣሚ እስከዛሬ ራሳቸውን የሚችል አንገት እንዳላቸው ሲነግራቸው ኖሯል፡፡

አሁን ሴት ልጃቸው አድጋለች፡፡ ዕድሜዋ ሲጨምርና ኑሮ ሲከፋ ከሰው ቤት ተመላላሽ መስራት ጀምራለች። እንዲያም ሆኖ ህይወት አንዳች ለውጥ አላመጣም፡፡ መቼም ቢሆን፡፡ የልጆቻቸው ከፍ ማለት ለእናትዬው ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ሁሌም እነሱን የሚያስቡት ልክ እንደ ልጅነታቸው ልጆች መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡

ወይዘሮ ዓለም ሰርቶ ለማደር፣ አግኝቶ ለመኖር ዛሬም ጉልበታቸው ብርቱና ዝግጁ ነው፡፡ በየቀኑ የት ልሂድ? እንዴት ልኑር ? ይሉት ሀሳብ ግን በየአፍታው ያስጨንቃቸዋል፡፡ እናም ‹‹ዕድል ይሰጠን፣ ሰርተን እንብላ›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ዛሬም የህጋዊነታቸው መፍረስና የእነሱን ተበትኖ መቅረት ህሊናቸው አልተቀበለም፡፡ አንድ ቀን የሚሰበስባቸው አካል፣ ‹‹አይዟችሁ›› የሚል መልካም ልቦናን ይጠብቃሉ፡፡ ተስፋቸው ለምልሞ ኑሯቸው እንደሚቀናም ያስባሉ። ነገን በጭላንጭል የሚያዩት ጉልት ቸርቻሪዋ ዓለም ድረሴ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You