. ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለስራ ማስኬጃ 5 ሚሊዮን 717 ሺህ 220 ብር ለግሷል።
አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀያቸው ለመመለስ ብሎም መልሶ ለማቋቋም የ31 ሚሊዮን 400 ሺህ 700 ብር ድጋፍ አደረገ።
አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀያቸው ለመመለስ ብሎም መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የፕሮጀክት የመግባቢያ ሰነድ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ተፈራርሟል።
ስምምነቱ የተፈረው በአለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት እና በወርልጅ ቪዥን መካከል ሲሆን ገንዘቡ ከኢትዮጵያ ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያውያን የተለገሰ ነው።
ስምምነቱ በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራን ማገዝ ብሎም መልሶ የማቋቋም ስራን አላማ አድርጎ የተነደፈ ሲሆን ሰብዐዊ እርዳታዎችን እና አካባቢውን ወደሰላም የመቀየር ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ውጥን አለው ተብሏል።
የአለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ፕሬዚዳንት አርቲስት ታማኝ በየነ በፊርማ ስነስርዐቱ ወቅት እንደተናገረው የመግባቢያ ሰነዱ 70 ሺህ 072 ተፈናቃይ ተመላሽ ወገኖችን ማዕከል አድርጎ የሚሰራ ሲሆን በተለይም በመፈናቀል ሂደቱ ተጎጂ የሆኑና የሚያስፈልገውን ሰብዐዊ እርዳታ በተገቢው ጊዜ ማግኘት ያልቻሉ ላይ ትኩረት ያደርጋል።
በዚህም መሰረት አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በመላው አለም ካሉ ኢትዮጵያውያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያውያን ያሰባሰበውን ወደ 1.1 የአሜሪካን ዶላር ወይም 31 ሚሊዮን 400 ሺህ 700 ብር በጌዲዮ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራን ለማገዝ እና መልሶ የማቋቋም ስራ ለመስራት እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ ሰብዐዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ እንዲያግዝ የሚያስችል ሲሆን ወርልድ ቪዥን አሜሪካ ደግሞ 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማለትም 5 ሚሊዮን 717 ሺህ 220 ብር ለስራ ማስኬጃ መለገሱን አርቲስት ታማኝ በየነ ገልጿል።
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ብራውን በበኩላቸው ሊሰራ የታቀደው ፕሮጀክት በግጭቱ የተጎዱትን ወገኖች በመርዳት ወደቦታቸው መመለስና መልሶ ማቋቋምና የግጭቱን መንስኤ ለመመርመርና አስተማማኝ ሰላም በአካባቢው ለማስፈን በተለያዩ አካላት ለሚሰሩ የትብብርስራዎች መነሻ ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለአንድ አመት የሚቆይ ሲሆን በዚህ ወር መጀመሪያ ተግባራዊነቱ ቀጥሎ በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት አስፈላጊውንና ቀዳሚ የሆኑ የጋራ ስራዎችን ለማቀድ ቅድመ ስራዎች የሚጠናቀቁበት ሲሆን በታለመለበት ጊዜ ማስፈፀም እንዲቻል ሁለቱ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር በቅንጅት ይሰራሉ ተብሏል።
በድልነሳ ምንውየለት