የጉበት በሽታ፡- ዝምተኛው ገዳይ

የጉበት በሽታ በዓይን በማይታዩ ተህዋስያን በተለይ ደግሞ ‹‹ሄፒታይተስ›› በሚባሉ ጥቃቅን ቫይረሶች ይከሰታል፡፡ የጉበት በሽታን ሊያስከትሉ የሚችሉት ቫይረሶች አምስት ቢሆኑም ዋናዎቹና የተለመዱት ግን ‹‹ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ›› ናቸው፡፡ ይሁንና የጉበት በሽታ በሄፒታይተስ ቫይረስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል፡፡ በተለይ በሽታው በተለያዩ መርዛማ መድኃኒቶችና ኬሚካሎች እንዲሁም ከመጠን በላይ አልኮል በመውሰድ የሚከሰትበት ዕድል ይኖራል። ከአምስቱ የሄፒታይተስ ቫይረሶች ውስጥ በአብዛኛው የረጅም ጊዜ የጉበት በሽታ ሊያመጡ የሚችሉት ‹‹ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ›› ናቸው፡፡ በዓለምአቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያም በአብዛኛው የሚታዩት እነዚሁ ቫይረሶች ናቸው፡፡

የጉበት በሽታ በዓለምአቀፍ ደረጃ፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስርጭቱ እየተስፋፋ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ በዓለምአቀፍ ደረጃ በየቀኑ ከ8ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጉበት በሽታ ይጠቃሉ፡፡ ይህም ምን ያህል በሽታው እየተስፋፋና ስጋቱ እየጨመረ እንደመጣ ያመለክታል፡፡ በየአመቱ ደግሞ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን በዚሁ የጉበት በሽታ ምክንያት እንደሚያጡ መረጃዎቹ ያሳያሉ። ይህም በሽታው ምን ያህል በከፍተኛ ደረጃ የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡

የጉበት በሽታ ከኤች አይ ኤድስ ጋር ሲነፃፀር ዜጎችን የመጉዳት አቅሙ በጣም ከፍተኛ እንደሆነም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ ከዘጠኝ እጥፍ በላይ የዜጎችን ሕይወት የሚጎዳና የመተላለፍ አቅሙም፤ ስርጭቱም ከፍተኛ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራትና በደቡብ አሜሪካ የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ እንደሆነና ስርጭቱም እየጨመረ እንደመጣ የዓለም ጤና ድርጅትና የተለያዩ አጋር ድርጅቶች የሚሠሯቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያም ከጉበት በሽታ ጋር በተያያዘ የተሠሩ ዘርዘር ያሉ ጥናቶች ባይኖሩም እ.ኤ.አ በ2017 በተጠና ጥናት መሠረት 9 ነጥብ 4 ከመቶ የሚሆኑ ዜጎች በሄፒታይተስ ቢ የተጠቁ መሆናቸውንና 3 ነጥብ 1 ከመቶ ያህሉ ደግሞ በሄፒታይተስ ሲ እንደተጠቁ ያመለክታል። ይህም በሽታው አንድ አስረኛ ያህል ስርጭት በሀገሪቱ እንዳለው ያሳያል፡፡ ትኩረት የሚሻ በሽታ እንደሆነም ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

በዚህም የተነሳ በሽታው ‹‹ዝምተኛው በካይ›› የሚል ተቀፅላ ስም ተሰጥቶታል፡፡ ይህም የሆነው አብዛኛው በዚህ በሽታ የተጠቃ ሰው ምንም ምልክት ሳያሳይ ለረጅም ጊዜ ስለሚቆይ ነው፡፡ ተጠቂው ሊድን ለማይችል የጉበትና የካንሰር በሽታ ተጋላጭ ከሆነ በኋላ ራሱን ሊያውቅ ይችላል፡፡ በርካታ ሰዎችም ለሌላ ምርመራ ሲሄዱ ነው ሄፒታይተስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ እንዳለ የሚያውቁት፡፡

ለሄፒታይተስ ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሄፒታይተስ ቫይረስ ተጠቅተው የጉበት በሽታ ካላቸው ሰዎች ጋር ረጅም ጊዜ አብረው የሚኖሩና ከታመሙ ሰዎች ከሚወጡ ደምና ሌሎችም ፈሳሾች ጋር ንክኪ ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህ በሽታ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት ሲኖርም በሽታው በቀላሉ የመተላለፍ ዕድል ይኖረዋል፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቁ እናቶችም ወደ ልጆቻቸው ቫይረሱን የማስተላለፍ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ የጤና ባለሞያዎችም ለዚሁ በሽታ ተጋላጭ ናቸው፡፡ አደንዛዥ እፅ በመርፌ የሚጠቀሙ ሰዎችም ለጉበት በሽታ የመጋለጥ ዕድል አላቸው፡፡ ንፅህናቸው ያልተጠበቀ የስለት መሣሪያዎችን መጠቀምም ለበሽታው ያጋልጣል፡፡

የጉበት በሽታ ስርጭቱንና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ መንገዶች እንዳሉ በሕክምና ባለሞያዎች ይገለፃል፡፡ እነዚህንም አውቆ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የጤና ባለሞያዎች ይመክራሉ፡፡ በተለይ ከታማሚዎች በኩል ያለውን ፈሳሾችና የደም ንክኪ ማስወገድና መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም በዋናነት ያስፈልጋል። ጥንቃቄ የተሞላው የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም፣ በተለይ ደግሞ ጉበትን የሚጎዱ የተለያዩ ኬሚካሎችን፣ ምንነታቸው የማይታወቅ ሕገወጥ መድኃኒቶችን አለመጠቀምና ከልክ በላይ አልኮል መጠጣትን ማስወገድ ያስፈልጋል፤ ንፅህናቸው ያልተጠበቀ ስለታማ ነገሮችን አለመጠቀምም ይመከራል፡፡

ወይዘሮ ሰብለወንጌል አባተ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ የዓለም ጤና ድርጅት የበሽታውን ግዝፈት በመገንዘብ እ.ኤ.አ በ2030 በሄፒታይተስ ቫይረስ ምክንያት የሚመጡ የጉበት በሽታዎች በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጥሩትን የጤና አደጋ ለመቀነስ የተለያዩ ግቦችን አስቀምጧል፡፡ እነዚህ ግቦች አብዛኛው ሰው በምርመራ ራሱን እንዲያውቅ፣ ቫይረሱ በውስጡ እንዳለበት ካወቀም በኋላ በቶሎ ወደጤና ተቋም ሄዶ ሕክምና እንዲያደርግና ከሄፒታይተስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጉበት በሽታዎችንና ያለ ዕድሜ የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ የተቀመጡ ናቸው፡፡

እነዚህን ግቦች ኢትዮጵያም እንደሀገር ተቀብላ እየሠራችበት ትገኛለች፡፡ በዚሁ መሠረት እንደ ዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች ወደሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ተቀይረው እንዲሠራባቸው እየተረደገ ይገኛል፡፡ የጉበት በሽታ መድኃኒቶች ውድ ከመሆናቸው አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለታዳጊ ሀገሮች ዋጋቸው እንዴት መቀነስና መድረስ እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ከመድኃኒት አምራቾች ጋር ይሠራል፡፡

እንደ ተወካዩዋ ማብራሪያ፣ የዓለም ጤና ድርጅት የጉበት በሽታን ለመከላከል ካስቀመጣቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ክትባት ሲሆን ይህም የጨቅላና የሕፃናት ክትባትን ያጠቃልላል፡፡ የሕፃናት የጉበት በሽታ ክትባት ወደሀገር ውስጥ ገብቶ መሥራት ከተጀመረ አስር አመት አልፎታል፡፡ ከ90 በመቶ በላይ ጥሩ ውጤት አምጥቷል። ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ይህን ክትባት ካቀረበ በኋላ የክትባቱን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ሕፃናት ወዲያው እንደተወለዱ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ቢከተቡ የሚል አዲስ መመሪያ አምጥቷል፡፡

በዚሁ መሠረት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጉበት በሽታ ስርጭት አለባቸው በተባሉ ሞቃታማና ቀዝቃዛ አራት ወረዳዎች ላይ የአንድ አመት የክትባት ሙከራ ተካሂዷል፡፡ ይህም ሙከራ ውጤታማ መሆኑ በምዘና ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አኳያ ‹‹ሄፒታይተስ በርዝ ዶዝ›› የተሰኘውን ክትባት ለማስፋት ከዓለም ክትባት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ንግግሮች እየተካሄዱ ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነች ነው፡፡ በቀጣዩ አንድ አመት ክትባቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሰጥ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡

በሽታውን ከመከላከል አኳያ ጥሩ ጅምሮች አሉ። በፖሊሲ ደረጃም የሁለተኛው የጤናው ሴክተር ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ገብቷል፡፡ ራሱን የቻለ የአምስት አመት እቅድ አለው፡፡ ራሱን የቻለ የአምስት አመት መመሪያም ተዘጋጅቶለታል፡፡ በዚሁ መሠረት በትንሽ ጤና ተቋማት ሲሰጥ የነበረው የጉበት በሽታ ሕክምና አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ ወደ ዘጠና ጤና ተቋማት አድጓል፡፡ ሕክምናው በሁሉም ክልሎች እንዲሰጥም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በቀጣይ ደግሞ አሁን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በማጠናከር የሕክምና አገልግሎቱ እንዲያድግ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደሚናገሩት፣ በኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ ሥራዎች በሚዲያዎች በኩል፣ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውስጥ በማካተትና በጤና ተቋማት የተለያዩ የተግባቦት ሥራዎች ውስጥ በማስገባት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ሥራው በቂ ነው ባይባልም በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አብዛኛዎቹ ዜጎች ጋር መድረስ ተችሏል፡፡

በቀጣይም ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ሚዲያዎችም የበሽታውን መተላለፊያ መንገዶችን በተመለከተና መከላከያ ዘዴዎቹ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራውን በአግባቡ ሊሠሩ ይገባል፡፡ በተለይ ኅብረተሰቡ ከታመመ በኋላ ለሕክምና ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣ በመሆኑና ሕክምናውንም በቀላሉ ስለማያገኝ በሽታውን አስቀድሞ የመከላከሉን ሥራ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ምርመራና የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡን ማጠናከር ይገባል፡፡ በተለይ በግልም ሆነ በመንግሥት ጤና ተቋማት ምርመራ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ነገር ግን አሁንም ይህ በቂ ባለመሆኑ በየጊዜው ምርመራውን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለጉበት በሽታ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ በየአመቱ አንዴና ሁለቴ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ ደግሞ የበሽታውን ምልክት ሲያይ በአፋጣኝ ወደጤና ተቋም ሄዶ መመርመር ይኖርበታል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች የጉበት በሽታ እንዳለባቸው የሚያውቁት ለሌላ ሕክምና ሲመጡ ነው። ከዚህ አንፃር በተለይ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በየጊዜው ምርመራ ማድረግ አለባቸው፡፡ በሽታው ሳይስፋፋና ጉበት ሳይጎዳ ከተገኘ ሕክምናው በቀላሉ ሊሰጥና ወደ ካንሰር ሳይቀየር የመዳን አቅሙም ከፍተኛ ስለሆነ እያንዳንዱ ሰው ምርመራ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት፣ የጉበት በሽታ መድኃኒት በቀላሉ የሚገኝ አይደለም፡፡ የመድኃኒት እጥረቱ የሚታየው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የተወሰኑ መድኃኒቶች ብቻ ናቸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት፡፡ የጤና ሚኒስቴርም የተወሰኑ መድኃኒቶችን ገዝቶ ዜጎች መድኃኒቶቹን እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ይህ በጣም ያንሳል፡፡

ስለዚህ በቀጣይ ጤና ሚኒስቴር በግሉ የሚሠራው ሥራ እንዳለ ሆኖ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት በራሳቸው በጀት የጉበት በሽታ መድኃኒቶችን መግዛትና ማስገባት ብሎም ለዜጎች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመድኃኒቶቹን ዋጋ ቀንሶ ለዜጎች ማቅረብ ደግሞ ከጤና ሚኒስቴር ይጠበቃል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡

በሽታውን ከመከላከል ጋር የተያያዘ ቢሆንም የክትባት ፕሮግራሞችም አሉ፡፡ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ከመደበኛዎቹ የክትባት መርሃ ግብሮች ጋር በማያያዝ የጉበት በሽታ ክትባት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ጨቅላ ሕፃናትም በ45 ቀናቸው ክትባቱን ይወስዳሉ፡፡ ክትባቱን በወሰዱት ላይ የበሽታው ስርጭት ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ክትባቱ በጣም ጠቃሚ መሆኑ በጥናትም ጭምር የተረጋገጠ እንደመሆኑ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ እናቶችም ልጆቻቸው ይህን ክትባት እንዲወስዱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በቀጣይ ‹‹ሄፒታይተስ በርዝ ዶዝ›› የተሰኘውና ሕፃናት ገና እንደተወለዱ የሚወስዱት ክትባት አለ። ይህም ክትባት በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ እየተሞከረ ይገኛል፡፡ አዋጭነትና ውጤታማነቱ ጥሩ እንደሆነም ታይቷል፡፡ ይህን ክትባት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋት በጀት ተይዞ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ይህም የጉበት በሽታ እንዳይስፋፋና ስርጭቱን ለመቀነስ ከሚያስችሉ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ የጤና ባለሞያዎችም ለዚህ በሽታ ተጋላጭ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ክትባት እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም ለማዳረስ በቀጣይ ጥረት ይደረጋል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You