ከሴቶች ሁሉ የተለየች

 መልኳን እፈራዋለው..ሴትነቷ ያስደነብረኛል። ማለዳ የትካዜዋ መነሻ እንደሆነ በደጇ በማገድምበት ጠዋት አስተውያለሁ፡፡ ጀምበርን ተከትሎ የምትወድቅበት ትካዜ አላት፡፡ ከማለዳ ፈቀቅ ባለ የሆነ ጠዋት ላይ ስብር..ስብርብር ትላለች። ብዙ ነገሯ ያስኮበልለኛል፡፡ እሷ ባለችበት ደጅ ሳገድም በጥያቄ ነው፡፡ ስለእሷ እያሰብኩ አንዱንም ጥያቄዬን ሳልመልስ መስሪያ ቤት እደርሳለሁ፡፡

በእሷ በኩል ነው እግዜር ምን እንደሚመስል ያወኩት። ልጅነቴን የሰጠኋቸው የኔታ እንኳን የእሷን ያክል እግዜርን አላስተዋወቁኝም፡፡ እሷን ሳይ እሷን የሰሩ የእግዜርን እጆች ባያቸው እላለሁ፡፡ እሷን ሳስብ ውበት የማያልቅበት የእግዜርን ሀሳብ ብደርስበት እላለሁ፡፡ ደሞም ግራ እጋባለሁ፡፡ በህይወት ላይ ሞት፣ በደስታ ላይ ስቃይ ተፈጥሮ ከሰውነት ጋር አብራ የሰጠችን ስጦታችን እንደሆነ አምኜ የተቀበልኩት እውነት ቢሆንም በውበት ላይ ትካዜ የማን እጅ ስራ እንደሆነ ግን ዛሬም ጠያቂ ነኝ፡፡ የእሱ ካልሆነ የማን ስራ ሊሆን ይችላል? ውበትን ከትካዜ ጋር የቀየጠ ጌታ ክፉ ቢሆን ነው አልኩ፡፡

የህይወቴ ትልቁ ግራ መጋባት በእሷ ውበት እና ትካዜ በኩል የወረስኩት ነው፡፡ በዛ ደጅ..በዛ ግድም ነፍሴ ዝም ማለት አትችልም፡፡ ትካዜዋ ተጋብቶብኝ እስከምሄድበት ይከተለኛል፡፡ በውበት ላይ ትካዜን የፈጠረ እግዜር ላይ ጥርሴን እነክስበታለሁ፡፡

አንዳንድ ሴቶች አሉ ባላቸው ውስጣዊ ልዕልና በዝምታ እና በአግራሞት የሚታለፉ..ከቃል መጥቀው፣ ከአንደበት ልቀው እጅን በአፍ የሚያስጭኑ፡፡ በዝምታ የሚለጉሙ፡፡ ከፍ ሲልም የሚያደናብሩ ውበት እና ሴትነቶች፡፡ እሷም እንደዛ ናት። በመንገዴ ላይ ቃል ያጣሁላቸውን ብዙ መልከኞች አይቻለሁ የእሷ በውበት ላይ ትካዜ ግን..ይሄው እኔም ዝም አልኩ..ቃል አጥቼ፡፡

ብዙ ሴት ናት..የትም የማንም መድከሚያ፡፡ አእምሮ አቅም የሚያጣው በእሷ ውበት እና ትካዜ ነው። እልፍ አይቻት ያልደረስኩበት የውበት እንጦሮጦስ አላት፡፡ ከትካዜ ጋር መሳ ለመሳ የቆመ ውበት፡፡ በየቀኑ እንደ ንስር ራሷን እያደሰች ማለዳና ከሰዐቴ ላይ በትካዜ ሳገኛት ፍርሀት እና ግርምትን የቀላቀለ እግዜር ላይ ጥርሱን የነከሰ ሌላነት ያርፍብኛል፡፡

በእሷ ውበት በኩል ፈጣሪን አብዝቼ አደነኩት። ግን ፈጣሪ ይደነቃል? እሷን ካወኩ ወዲህ ግራ የተጋባሁባቸው ብዙ ያልገቡኝ እውነቶች ከበውኛል። ሸክላ ሰሪው በነዛ በተዋቡ እጆቹ (ግን ውብ መሆናቸውን በምን አወኩ?) ሰው የሚለውን ማንነት ሲሰራ..ሲያበጅ..ሲኩልና ሲያሳምር ከእሷ ውበት እየኮረጀ ሌሎችን የሰራ ይመስለኛል፡፡ እንዴት መሰለኝ ግን? መቼም ያ ውበት እና ትካዜ ከአፈር ተሰሩ የሚል ካለ በገዛ አፉ መቅጠፉን እና መቀሰፉን ይወቅ፡፡

እንደዛ አሳምሯት ግን ለምን ትካዜን ጨመረባት? ሰውነት ሙሉ እንዳይደለ ሊነግረን ፈልጎ ይሆን? ወይስ ውበት ሀሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው ሊለን አስቦ? ይሄ ያልገቡኝ እና የማይገቡኝ ባለችበት ሳገድም የሚሰፍርብኝ መልስ አልባ ጥያቄ ነው፡፡ በሴትነቷ ላይ አይረባም የምለውን አንድ ነውር ለማግኘት ወራት ፈጅቻለው፡፡ አልሆነልኝም እንጂ፡፡

በውበቷ መሀል ተሰንቅሮ በማየው ትካዜ ውበት መልክ ብቻ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ፡፡ በተለይ ደግነት ከሌለው፣ በተለይ በስርዐት ካልታጀበ፣ እውቀት እና ጽድቅና በኩሩ ካልሆኑ ውበት የሞት መንገድ ነው፡፡

ሳያት..አንገቴን ሰብሬ ነው፡፡ እሷ ደጅ ስደርስ ዝግ እላለው፡፡ ስፈጥን መጥቼ ዝግ ማያዬ ደጇ ነው፡፡ አፍታ የፈጠረው የአይኖቻችን ንክኪ ቀን ሙሉ የሚታወስ ትዝታን አውርሶኝ የሚያልፍ ነው፡፡ አይኖቼን ወዳለችበት ሳፈናጥር ተፈጥሮን የምትመራ፣ ሙልዐተ አለሙን የምትቆጣጠር እንጂ በትካዜ የምትወድቅ ምናምንቴ በመምሰል አልነበረም፡፡ በዛ ደጅ ለወራት ስመላለስ ሁሌም ሳላውቀው ቃል እንዳወጣሁ ነው..‹አቤት ውበት የሚል፡፡ የውበት ፋብሪካ..ውበትን ለሰዎች ልታድል በፉንጋዎች መሀል የተቀመጠች ትመስላለች፡፡

ዝግ ማያዬ ናት፡፡ አእምሮና ልቤ በእኩል የሚያርፉት እሷ ዘንድ ነው፡፡ በውበቷ ውስጥ ትዕቢት የሌለው የሴትነት ደብር ይታየኛል። የነካውን ሁሉ ከሀጢዐት የሚያነጻ አጥቢያ። እየሄድኩኝ አረምማለው፡፡ በእሷ ስለእሷ የማላርፍበት የሀሳብ ስፍራ የለም፡፡ ሳያት የታየኝን አጥቢያ እየመላለስኩ ስለውበቷ አበስ ገበርኩ ባይ ነኝ፡፡ ትካዜዋ..በዛ ሁሉ ውበት ውስጥ እውነት እና እምነቴን የሚያቆሽሽብኝ የበትረ አጋንቴ ነው። ትካዜዋን ጥርሴን እነክስበታለሁ። እና ደግሞ በእግዜር ላይ፡፡

በበሯ ሳልፍ ተዐምር ለማየት በመዘጋጀት ነው፡፡ በዘመኔ ተዐምር ያየሁት በእሷ ውበት እና ትካዜ ነው፡፡ በደጇ ሳልፍ ግንባሬ ላይ የምትነደው ጸሀይ እንኳን የእሷን ውበት ያህል አትሞቀኝም፡፡ አስተናጋጅ ናት፡፡ ስሟንና የስራ ድርሻዋን ያሰፈረ ባጅ አንገቷ ላይ አንጠልጥላ፣ በዛ ውበት ገላዋን በሚያሳይ አጭር ጉርድ ከነሽርጧ ሳያት የሰውን ልጅ ሁሉ ሲኦል ለማስገባት የተላከች ቆንጆ አጋንት ወይም ደግሞ የሆቴሉ የማርኬቲንግ ቦርድ በውበቷ መንገደኛውን ሁሉ ሳይፈልግ ወደሆቴሉ እንዲተም ልዩ ተልኮ ሰጥቶ ያሰማራት ትመስለኛለች። በዛ መንገድ የሚያልፍ መንገደኛ እሷን አለማየት አይችልም፡፡ መንገዱን በሚያሳይ የሆቴሉ የፊት ለፊት ወንበር እግሮቿን አነባብራ በትካዜ ስትታይ መላዕክና አጋንት ትመስል ነበር፡፡

ፊቷ ላይ የመከራ ተራራ አለ፡፡ ከትካዜዋ በኋላ በሚስቅ ፊቷ እየተናደ የሚቆለል፡፡ ጸሀይ ፍንትው ባለችበት የጸደይ ሰሞን ላይ አንድ ማለዳ በደንብ አየኋት..፡፡ ሲቀርቡት የሚቀርብ፣ ሲርቁት የሚርቅ ውበት እንዳላት አስተዋልኩ። እንደጀምበር ርቃን አተኩረው ሲያዩት አይን የሚያሳምም ውበት ከደስደስ ጋር የፈሰሰበት ጥርት ያለ ፊት አላት። ከወደአፍንጫዋ አካባቢ አመዳይ ነገር ያየሁ ይመስለኛል፡፡ ማዲያት መሳይ ብናኝ ያበጀ ከባቢ። ቆማ ስላላየኋት ቁመቷን መመተር አልቻልኩም። ግን ረጅም ትመስለኛለች። ከወንበሩ ተርፈው ወለሉ ላይ የፈሰሱ ታፋና ባት አይቻለው፡፡ የውሀ ኮለላ እንደተሸከሙ ሰርዶዎች፣ በጠሩና በነጡ በጎህ ጠል እንዳጎነበሱ ጤዛዎች ከውበት ጋር ወደመሬት አጎንብሳለች፡፡

በውበት ላይ ትካዜ..ይሄን አይነቱ ድባቴ የት አገኛት? አልኩ በነፍሴ፡፡ ያን ትካዜ የምታጋራው አንድ ሰው የምትፈልግ መሰለኝ፡፡ ዝቅ ባለችበት ቅጽበት ከጎኗ አረፍ ብሎ የሚያሻሻት፣ የሚያጽናናት እጅ የምትሽት መሰለኝ፡፡ ልቤ ቅረባት ይለኛል። ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገው ፍርሀት አርፈህ ተቀመጥ ይለኛል። የማለዳ ጠል ለጤዛዎች ቁንጮ ውበት እና ደግሞ ወደመሬት የሚያስጎነብስ መከራ እሷንም እንደዛ አሰብኳት፡፡

አንድ ቀን በበሯ ሳገድም አጣኋት፡፡ እየሱስ እንደተሰቀለበት እለት ጸሀይ በቀን የጨለመች፣ ከዋክብት የረገፉ፣ አለቶች የተሰነጣጠቁ መሰለኝ። ደህና ያደርኩት ልጅ በዛ ማለዳ ተለከፍኩ። ሳያት ኖሬ ያልገባሁት ሰው ያን ቀን ወደ ሆቴሉ ሰተት አልኩ። የውበታሟን ሴት ቦታ ወርሳ ፊት ለፊት ቆማ ወደምትታየኝ አስተናጋጅ ቆምኩ፡፡ ቦታ ያጣሁ መስሏት ወደአንድ ባዶ ወንበር አመላክታኝ ቀድማኝ ወደወንበሩ በመሄድ በያዘችው ጨርቅ ጠረጴዛውን ትወለውል ጀመር። እንደጨረሰች ሄጄ ተቀመጥኩ፡፡ ፋታ ሳትሰጠኝ ትህትና በተላበሰ ዝግ ባለ ድምጽ ‹ምን ልታዘዝ? አለችኝ፡፡ የምፈልገውን ነገር ስላልተዘጋጀሁበት ለመምረጥ ትንሽ አልፍቻት የታሸገ ውሀ እንደምፈልግ ነግሬ ከአጠገቤ አባረርኳት፡፡ እንደሄደችልኝ አይኔን እያንቀዋለልኩ ያቺን ሴት ፈለኳት፡፡ የለችም፡፡ ስራ ቀይራ ወይም ረፍት ወጥታ ይሆናል የሚል ሀሳብ አሰብኩ። በሚቀጥለው ቀን ከዛም ቀጥሎ በመጣው ቀን ፈለኳት አልነበረችም፡፡ ዝምታ በዋጠኝ አንድ እለት ወደሆቴሉ ገባሁ። ታስተናግደኝ ከነበረችው ሌላ ልጅ ልትታዘዘኝ አጠገቤ አጎነበሰች፡፡ የምፈልገውን ነግሬ ሸኘኋት። ስትመለስ የመጀመሪያ ጥያቄዬ ‹አንድ አስተናጋጅ ነበረች..እዛጋ በብዛት የምትቀመጥ› ብዬ በጣቴ ወደቦታው እየጠቆምኩ ከመናገሬ…

‹ፍሬ ህይወትን ነው? የሚል ሀዘን የሰበረው ድምጽ ከአስተናጋጅዋ ጉሮሮ አደመጥኩ፡፡

ሀዘንተኛ ድምጽዋን ተከትዬ ቀና አልኩ ወደመልኳ። አይኖቿ እንባ ሞልቷቸው ያመጣችልኝን ቀዝቃዛ ቢራ ጠረጴዛው ላይ ልታስቀምጥ ስትታገል አየኋት፡፡

‹ሞታለች› አለችኝ ሳልጠይቃት፡፡

ከአካሌ ላይ የሆነ ነገር ተጎርዶ የወደቀ ያክል በድን ሆንኩ። በማደንዘዣ ቢወጉኝም ያን ያክል የምደነዝዝ አይመስለኝም።

‹ራሷን አጠፋች..

ከሲቃዋ ጋር እየታገለች ከአጠገቤ ስትሸሽ ጀርባዋ ይታየኛል፡፡ በአንድ ጊዜ ተስፋ ቢስ ሆንኩ፡፡ ከዛን ቀን ጀምሮ ጸሀይ ትፈጀኝ ጀመር፡፡ ‹ምነው ብላት? ያን ሁሉ ጊዜ በትካዜ ሳያት የሆነችውን ጠይቄ ብረዳ› ስል በምንም የማይሽር ጸጸትን አትርፌ ከሆቴሉ ወጣሁ፡፡ እሷን የምረሳበት አንድ ምክንያት አጣሁ፡፡ ለካ በውበት እና በበጎነት ካጌጠች አንድ ነፍስ እልፍ ናት፡፡ ለካ መቼም የምናጣው የማይመስለን እድል ከእጃችን ያመለጠ ቀን ሙት ነን፡፡ ያን መንገድ ሸሸሁት፡፡ ትዝታዋን አርቄ ልቀብረው ስል ያገደምኩበትን ሰርጥ ራኩት፡፡

አንድ ቀን ሌላ ሆነ..

ለብዙ ጊዜ ከራኩት ከዛ መንገድ ላይ ተገኘሁ፡፡ ወደሆቴሉ ማተርኩ..በዛ ቦታ፣ በዛ ወንበር ላይ አንዲት ሳቂታ አስተናጋጅ ተቀምጣ አየሁ፡፡ ትካዜን የማታውቅ ነፍስ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 26/2015

Recommended For You