ወጣትነት እጅግ አስደሳችና አጓጊ የዕድሜ ክልል እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። በወጣትነት ጊዜ የነበረን ጉልበትና ከፍተኛ የሆነ ሁሉን የማወቅ፣ የመዝናናት፣ የመስራት፣ የማደግና የመለወጥ የተነሳሽነት ስሜት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ጊዜው ምንም እንኳን ጨዋታና መዝናናትን አብዝቶ የሚፈቅድ ቢሆንም፤ ይህ ወርቃማ ጊዜ ለቀጣይ ማንነታችን እርሾ የምናስቀምጥበትም ጭምር ነው።
እርግጥ ነው፤ አብዛኞቻችን ይህን ከኃላፊነት ነፃ የሆንበትን ጊዜ ለነገ ህይወታችን እርሾ ከማስቀመጥ ይልቅ በጨዋታ፣ በዋዛ ፈዛዛና በፌዝ አሳልፈነው ይሆናል። በተለይም ከፊታቸው ብዙ ነገር የመሥራት ዕድሉ ተከፍቶላቸው አጋጣሚውን ያልተጠቀሙና በጊዜው እርሾ ያላስቀመጡ ብዙዎች አሉ። “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ አበው ብዙ የሚሰራበትን የወጣትነት ጊዜ እንዲያው በዋዛ ፈዛዛ ያለ እርሾ ብናስቀረው ጥሎብን የሚያልፈው ጠባሳ በቀላሉ የሚሽር አይደለም።
በተመሳሳይም በርካታ ወጣቶች አንዴ ካመለጠ የማይገኘውን የወጣትነት ሞራልና ወኔ በመጠቀም በውስጣቸው ያለውን እምቅ ችሎታ በከፍተኛ ተነሳሽነት አውጥተው በመጠቀማቸው ምክንያት ገና በጠዋቱ ስኬታማ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ በርካቶችም የፈጠራ ስራዎችን ለማፍራት በጥረት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል ለዛሬ ጥረታቸውንና የፈጠራ ስራቸውን አድንቀን ተሞክሯቸውን ልናካፍላችሁ የወደድነው የሁለት ጓደኛሞችን የጋራ ፍላጎትና ዝንባሌ ነው።
ካሌብ ሰለሞንና ሚኪያስ ንጋኒ ይባላሉ። ሚኪያስ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ካሌብ ደግሞ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል። ሁለቱ ወጣቶች ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ሰባተኛ አካባቢ ሲሆን፤ ከሰፈር የጀመረው ትውውቃቸው ውስጣቸው ባለው ተመሳሳይ ፍላጎትና ዝንባሌ ተስቦ ወጣቶቹን ይበልጥ አቆራኝቷቸዋል። ተመሳሳይ ዝንባሌያቸውም የፈጠራ ስራ የሆነውን ስዕል በጋራ መስራታቸው ነው።
ወጣቶቹን ያገናኛቸው የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ ቤት “ለወርቅ እንትጋ አእምሯዊ ንብረትና ስፖርት” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የአእምሯዊ ንብረት ቀን ባከበረበት ወቅት ነበር። ጽ/ቤቱ ዓለም አቀፉን የአእምሯዊ ንብረት ቀን ያከበረው ከሚያዝያ 28 እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ሶስት ቀናት ነው። በነዚህ ቀናት ውስጥ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች፣ አውደ ርዕይና የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዋል።
በፕሮግራሙ ከቀረቡት የፈጠራ ስራዎች መካከል
ካሌብና ሚኪያስ ያቀረቡት የጋራ ስዕል አንዱ ነው። ወጣቶቹ እንደገለፁት ከሆነ በጋራ ሰርተው ያቀረቡት የጥበብ ፍሬ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትን ይወክላል ይገልፃል ብለው እንደሰሩት ይናገራሉ። በስዕሉ የምትታየው በርካታ ሀሳቦችና የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ያሏት አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት ናት። ጽ/ ቤቱ የአእምሯዊ ንብረት የሆኑ በርካታ የፈጠራ ስራዎች ህጋዊ መብቶች ላይ ጥበቃ የሚያደርግና የፈጠራ ስራዎችን ወደ ልማት የሚያስገባ እንደመሆኑ መጠን በርካታ የፈጠራ ስራዎች ያሏት ይህች ኢትዮጵያዊት ሴትም በጽ/ቤቱ እንደተከለለች ይገልፃል።
አጠቃላይ የስዕሉ ሀሳብ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ብዙ ነገሮችን አቅፎ የሚይዝና ለፈጠራ ስራ ከለላ የሚሰጥ ነው። የፈጠራ ስራ የማይገደብ በመሆኑ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በጠይሟ ኢትዮጵያዊት ሴት ስዕል ውስጥ ያሉት የተለያዩ ቀለማት ይናገራሉ። በርካታ የፈጠራ ስራዎች ያሏቸውን ኢትዮጵያውያንም በዚሁ ስዕል ውስጥ ባሉት ቀለማት ሊወከሉ እንደሚችሉ ወጣቶቹ ይናገራሉ።
እስካሁን የስዕል ችሎታቸውን በቅርበት የሚያውቁ የተለያዩ ሰዎች ስዕል እንዲስሉ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹላቸው የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ ለተለያዩ ሬስቶራንቶችና ለፍራፍሬ ቤቶች ተጠርተው እንደሚስሉ ይናገራሉ። ከዚህም ሌላ፤ በርካታ ስዕሎችን በስጦታ በማበርከት ሰዎች ችሎታቸውን እንዲያውቁ ያደርጋሉ። በመሆኑም የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር የወጣቶቹን ችሎታ በቅርበት በማወቁ በአውደ ርዕዩ ላይ የፈጠራ ስራቸውን እንዲያቀርቡ ጋብዟቸዋል።
ጓደኛሞቹ ሰዓሊዎችም የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበለው የኢትዮጵያ አእምሯዊ ጽ/ቤትን ስራ መግለፅ ይችላል ያሉትን ስዕል በጋራ በመሳል በአውደ ርዕዩ ላይ ለዕይታ አቅርበዋል። ለዚህም ስራቸው ጽ/ቤቱ ዓመታዊ በዓሉን ባከበረበት ዕለተ ረቡዕ ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሰርተፊኬት ተሸላሚ ሆነዋል። በዕለቱ የፈጠራ ስራቸውን ላቀረቡና ለበዓሉ መሳካት የተለያዩ ድጋፎችን ላደረጉ አካላትም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ፤ ሽልማት ባበረከቱበት ወቅት “እንደነዚህ ያሉ ወጣት የጥበብ ባለሙያዎችን ማበረታታት መጪውን ጊዜ ብሩህ ያደርገዋል” በማለት መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከተው አካል በሙሉ ወጣቶቹን ቢያበረታታ ሀገሪቷም ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቁመዋል።
ሚኪያስና ካሌብ ለበዓላት ከሚስሉት የልጅነት ስዕል ጀምሮ አሁን እውቅናን ለማትረፍና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት የተለያዩ ስዕሎችን በመሳል በመጠኑም ቢሆን ለሽያጭ ማቅረብ ጀምረዋል። የስዕል ችሎታቸውን አውጥተው የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከቤተሰቦቻቸው የሚያደርግላቸው እገዛ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆኑ እጅግ ጥልቅ በሆነ የደስታና የተነሳሽነት ስሜት ይገልፃሉ። ከዚህም በላይ ወጣቶቹ ባላቸው የውስጥ ፍላጎትና ከፍተኛ ጥረት በሚሰሩት የስዕል የፈጠራ ስራቸው ከገንዘብ በፊት ዕውቅናን ማግኘት ፅኑ ምኞታቸው ነው።
ስዕል ትዕግስትን ይጠይቃል የሚለው ሚኪያስ፤ ከጓደኛው ካሌብ ጋር ባላቸው የረጅም ጊዜ ትውውቅ ውስጥ አንድም ቀን ተጋጭተው እንደማያውቁ ይናገራል። ያላቸውን የስዕል ችሎታ ይበልጥ ለመጠቀም እንዲህ አይነት መድረኮችን በየጊዜው ብናገኝና ከሰዎች ጋር ብንተዋወቅ የበለጠ መስራት እንደሚችሉና ትልቅ ደረጃ እንደሚደርሱም ያለውን ተስፋ አጫውቶናል። የአእሯዊ ንብረት ጽ/ቤትን ይወክላል ብለው የሳሉት ስዕልም በመነጋገርና በመግባባት እንደሆነና ይህም የስራቸውን ጥራት እንደሚጨምር ተናግሯል።
ሚኪያስና ካሌብ በስዕል ትምህርት ቤት ገብተው ስዕልን አልተማሩም። እስካሁን እየሰሩ ያሉት በተፈጥሮ ባላቸው ክህሎት ነው። በስዕል ስራቸው የሚፈልጉትን ዕውቅና ለማግኘትና የተሻለ ስራ ለመስራት በስዕል ትምህርት ቤት ገብተው መማር እንዳለባቸው ያምናሉ። ለዚህም በአሁን ወቅት እየተማሩ ካሉት ትምህርት ጎን ለጎን የስዕል ስራቸውንም በትምህርት የበለጠ ለማዳበር ሀሳብ አላቸው። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ ትልቁን እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የስዕል ስራ ለመስራት የተለያዩ ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉ ይታወቃል። በመሆኑም ከቀለም ጀምሮ ያሉትን የተለያዩ ግብዓቶች ለማሟላት ወጪያቸውን ቤተሰብ እንደሚሸፍንላቸው ይናገራሉ። አልፎ አልፎም ስዕል ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ ለስዕል ስራቸው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ይገዛሉ። አጠቃላይ የስዕል ስራቸውንም የሚሰሩት በየቤታቸው እንደሆነና ለስዕል ስራ ምቹ የሆነና የተለየ ቦታ እንደሌላቸው ወጣቶቹ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ፤ ቦታ የለም ብለን አንቀመጥም፤ በቤት ውስጥ ባለው ቦታ እየሰራን ነው ያሉት ጓደኛሞቹ፤ ዋናው የውስጥ ፍላጎትና የነገን ተስፋ አርቆ ማየት ነውና በእግራችን ላይ አድርገንም ስዕል የሰራንበት ጊዜ አለ ይላሉ።
እነዚህ ተመሳሳይ ፍላጎትና ዝንባሌ ያላቸው ጓደኛሞች፤ በወጣትነት ዕድሜያቸው እየሰሩ ያሉት ስራ ነገ ለጉልምስና ጊዜያቸው የሚጠቅም እርሾ ነው። ወጣትነት ትኩስ ኃይል እንደመሆኑ በርካታ ስራዎችን መስራት የሚቻልበትና የነገ ማንነታችን የሚመሰረትበት ጭምር ነው። ካሌብና ሚኪያስም የወጣትነት ዕድሜያቸውን በውስጣቸው ባለው የስዕል የፈጠራ ስራ ጀምረውታል። ይህ የጥበብ ስራቸውም ይበልጥ ያቀራረባቸው በመሆኑ “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ” እንዲሉ አበው፤ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ስዕልን በጋራ እየሳሉ ይገኛሉ።
በቀጣይም የተሻለ ስራ ለመስራትና ወደፊት ካሰቡበት ደረጃ ለመድረስ ዛሬ ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያምናሉ። ካሌብና ሚኪያስ፤ ወደፊት የራሳቸው ስቲድዮ ቢኖራቸውና አዳዲስ ስራዎችን በመስራት ወደ ህብረተሰቡ መግባት ቢችሉ ፍላጎታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን ምንም ባይኖረንም ወደፊት ስራችንን ጠንክረን በመስራት ወደምንፈልገው ደረጃ እንደርሳለን። ለዚህም ከቤተሰብ ባለፈ ልክ እንደ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ሁሉ የተለያዩ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ዕድሉን ቢሰጡን መልካም ነው በማለት የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ለሰጣቸው ዕድል በእጅጉ ያመሰግናሉ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም፤ የጋራ ዝንባሌ ያላቸው እነዚህ ወጣቶች እያደረጉ ያሉትን ጥረት በማድነቅ በስዕል የፈጠራ ስራቸው ውጤታማ ሆነው ካሰቡበት እንዲደርሱ ይመኛል። ከዚህም በላይ ወጣቶቹን በዚሁ በማህበራዊ አምድ ላይ ማቅረቡ ሌሎች ወጣቶች ከነሱ ተምረው ማትረፍ እንደሚችሉ በማመንም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011
ፍሬህይወት አወቀ