የተቋማት አለመናበብ፤ የመረጃም ድብብቆሽየበረታበት- የመሬት ክፍፍል

መነሻ ጉዳይ

ጉዳዩ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ስለሚስተዋለው የመሬት ወረራ እና አግባብ ያልሆነ የመንግሥት ሀብት ቅርምት ብሎም የመንግሥት ተቋማት ያልተናበቡበት አሠራር ስለመኖሩ ከአካባቢው ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ጥቆማ አደረሱ፡፡ ዝግጅት ክፍሉም የነዋሪዎቹን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በሥፍራው በመገኘት ሁኔታውን ተመልክቷል፤ የነዋሪዎቹን አስተያየት፣ ሰነዶች እና የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሮም ጉዳዩን እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

 ነዋሪዎች ምን አሉ?

 ለዝግጅት ክፍላችን ጥቆማውን ያደረሱ እና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢ ነዋሪዎች፣ በአካባቢያቸው እየሆኑ ያሉ ነገሮች ሁሉ እንግዳ ሆነዋል። በአካባቢያቸው ለአርሶ አደር ልጅ እየተባለ እየተከናወነ የሚገኘው ተግባርም በእጅጉ አሳዛኝ ነው ብለዋል። “አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጆች ናቸው” በሚል ምክንያት ለግለሰቦች የተመራው ቦታ አግባብነት የጎደለውና በአካባቢው ያልነበሩ ሰዎች የተከፋፈሉት ፍንትው ያለ ሙስና የጎላበት ተግባር ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ዝግጅት ክፍሉ በስፍራ ተገኝቶ እንደተመለከተው፣ የአካባቢ ማህበረሰብ በጋራ ከኪሱ ገንዘብ በማዋጣት የሠራው የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ‹‹ኮብል ስቶን›› ሳይቀር በአሁኑ ወቅት ተቆፍሮ ግለሰቦች ግንባታ እያካሄደበት ነው።

ቀደም ሲል በዚህ የኮብልስቶን የመንገድ ዳር እናቶች የጉሊት ችርቻሮ ንግድ ሲያከናውኑ፣ የእግረኛ መንገድ ዘግታችኋል በሚል ሰበብ በደንብ አስከባሪዎች እንዲነሱ መደረጉን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በሂደት አሻጥር በመፍጠር ለአርሶ አደር ተሰጥቷል በሚል ግንባታ እንዲከናወንበት የተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ከዚህ በተጨማሪም ለቅርምት የተዳረጉት ቦታዎች ቀደም ሲል አረንጓዴ ቦታ የነበሩ ቦታዎች በአካባቢው ማህበረሰብ በጋራ የለሙና በተመሳሳይ በጋራ ይጠቀሙበት የነበሩ ናቸው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የፕላን ተቃርኖ የለውም በሚል ሰበብ ለግለሰቦች በመስጠት ግንባታ እየተካሄደበት ነው። ነዋሪዎቹ ግን ይህ በሐተሰኛ መረጃዎች የታጨቀ ነው፤ በአካባቢው ፈጽሞ ያልነበሩ ሰዎች እንደኖሩ ተደርጎ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ቅሬታቸውንና ተግባሩን የሚቃወሙ መሆኑን አስረድተዋል።

የፕላን ተቃርኖ የለም የሚለው ከሞራልም ሆነ ከእውነት የራቀ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ የእግረኛ መንገድ ሙሉ ለሙሉ ታጥሮ እስከ አስፋልት ጥግ ድረስ እየተቆፈረ ነው። ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎችን በግንባታዎቹ ጣሪያ ላይ የሚያልፉ ናቸው። ታዲያ ይህን የፕላን ተቃርኖ የለውም ማለት ከእውነትም፤ ከዕውቀትም ብሎም ከሞራል የራቀ ይልቁንም ለሙስና የተጋለጠ አሰራር ስለመሆኑ ተናግረዋል።

‘አርሶ አደሮች ነን’ የሚሉ ግለሰቦች ምን አሉ?

ምንም እንኳን ይህ የሰላ ወቀሳና ትችት ከአካባቢ ነዋሪዎች የቀረበ ቢሆንም፤ “የሚባለው ሁሉ ውሸት ነው” በማለት አርሶ አደሮች ነን የሚሉት ግለሰቦች ሃሳቡን ተቃውመው ሃሳባቸውን ገልጸውልናል። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል ደግሞ ወይዘሮ አስናቀች ዳባ አንዷ ናቸው።

ወይዘሮ አስናቀች ዳባ፤ ለብዙ ዘመናት ለግብርና አገልግሎት ስንጠቀምበት የነበረው መሬታችን ያለ አግባብ ሲወሰድና ስንፈናቀል ኖረናል። ይህንንም አቤት ለማለት በየፍትህ ተቋማቱ በር እየዞርን ስንጮህ ነበር፤ ግን ሰሚ አላገኘንም። ይሁንና አሁን ድምፃችን ሲሰማና ምላሽ ማግኘት ስንጀምር የማይመለከታቸው አካላት እየከሰሱን ነው፤ ብለዋል።

እኛ የአካባቢው አርሶ አደሮች አሁን የተወሰነ አንገት ማስገቢያ የሚሆን ቦታ ሲሰጠን አያስገርምም የሚሉት ወይዘሮ አስናቀች፤ ይሄ እንዲሆንም ለዘመናት ዋጋ የከፈልንበት ነው፣ ገናስ መቼ በቂ ፍትህ አገኘንና ብለዋል። ከ100 ዓመት በፊት ቅድመ አያቻችን ጭምር ይኖሩበት የነበረ ቦታ በመሆኑ፣ በእኛ ላይ እየተነሳ ያለው ተቃውሞ አግባብነት የጎደለውና ፍትህ እንዳይነግስ ከመፈለግ የመጣ ነው ሲሉ በነዋሪዎቹ የቀረበውን ቅሬታ ተቃውመዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መብራቴ ስንታየሁ በበኩላቸው፤ አካባቢው ከጥንት ጀምሮ የኖርንበት ሲሆን ሌላው ቀርቶ በአያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ስም የሚጠሩ ሰፈሮችና የምንጮች ስም አሁንም ድረስ ያሉ ህያው ምስክር ናቸው ይላሉ። እንዲያውም አሁን ለመኖሪያ ተብሎ የተሰጠን ቦታ ሊሰጠን ከሚገባው በእጅጉ ያነሰ ለዘመናት የተነፈግነውን መብታችንን ‹‹ዓባይን በጭልፋ›› ዓይነት ነው የተሰጠን ሲሉ አሁንም ቅሬታ እንዳላቸው ይናገራሉ።

ሌላው ቀርቶ በአካባቢው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በገዛ መሬታችን ላይ ተገንብተው ለነዋሪዎች ሲተላለፉ የበይ ተመልካች ሆነን ኖረናል፣ ያሉት አቶ መብራቴ፤ በአሁኑ ወቅት ካርታ የተሰጠን በጉልበት ወይንም በሙስና ሳይሆን ከቀጣና ጀምሮ በወረዳ፣ ክፍለ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድረስ በተዋቀሩ ሕጋዊ ኮሚቴዎችና መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነት ላይ በተቀመጡ ሰዎች ተረጋግጦ ነው ብለዋል።

ይሁንና ለዘመናት ዋጋ የከፈልንበት ጉዳይ በእኛ ያላሰለሰ ጥረትና በመንግሥትም ይሁንታ ፍትህ እያገኘን መሄዳችን አሁንም የማይዋጥላቸው ግለሰቦች ዱካችንን እየተከተሉ የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ነው፤ እነሱ ምንም ቢሉ “እኛ በአካባቢው የተወለድን ብሎም ነባር አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች ነን” ብለዋል።

የወረዳ 14 ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምላሽ

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ድሪባ ጉልማ እንደሚሉት፤ በዚህ አካባቢ የሚነሱ ቅሬታዎች በሕግ አግባብ የተከናወኑ ናቸው። ከአቶ ፍቃዱ ዳባ በስተቀር ሁሉም ሰዎች መብት የተፈጠረላቸው ከሁለት ዓመት በፊት ነው። መብት የተፈጠረውም “አርሶ አደር” እና “ምትክ” በሚል ነው። ሊታወቅ የሚገባው ግን በአርሶ አደርም ይሁን በምትክ ስም የመሬት ጉዳይ ለወረዳ የሚመጣው ከክፍለ ከተማ ነው።

በመሆኑም መጀመሪያ ላይ ካርታ አውጥተው የመጡት ከክፍለ ከተማ ነው። ወረዳው የሚሰራው ከሰነድ አልባ ጋር የተያያዘን ጉዳይ ብቻ ነው። በሰነድ አልባ መብት ይፈጠርልኝ የሚሉ ሰዎችን ፋይል አደራጅተን መብት እንዲፈጠርላቸው ወደ ክፍለ ከተማ እንልካለን እንጂ ከአርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጅ ጋር ተያይዞ ወረዳ ላይ የሚሰራ የለም፤ ብለዋል።

ይሄንን ምላሻቸውን መነሻ በማድረግ እና መመሪያ ቁጥር 20/2013ን ዋቢ በማድረግ፤ “በአርሶ አደርነት የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳ መጀመሪያ በቀጣና ኮሚቴ ታይቶ፤ በወረዳው መሬት ልማትና ማኔጅመንት አስተዳደር ተገምግሞ ለወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ሲቀርብ እና ሥራ አስፈጻሚው ካጸደቀው በኋላ ክፍለ ከተማ ለአርሶ አደሮቹ መብት ይፈጥርላቸዋል። አሰራሩ ይህ ሆኖ ሳለ እንዴት ከአርሶ አደር ጋር ተያይዞ ወረዳው የሚያውቀው ነገር የለም ይላሉ?” የሚል ጥያቄ ከዝግጅት ክፍላችን የቀረበላቸው አቶ ድሪባ፤ መጀመሪያ ላይ ወረዳው አያገባውም ያሉ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን አርሶ አደር እና የአርሶ አደርን ልጅ በተመለከተ የይገባኛል ጥያቄ መስተንግዶ ከወረዳ እንደሚጀምር አምነዋል።

አርሶ አደር ለተባሉት ሰዎች የተሰጠው መሬት አለ ስለተባለው ጉዳይም፣ ‹‹ሁሉም ቦታዎች የፕላን ተቃርኖ አያሳዩም›› ሲሉ ነው አቶ ዲሪባ ምላሽ የሰጡት። ካርታው ተሰርቶ የመጣው ከክፍለ ከተማ መሆኑን፤ ክፍለ ከተማ ቦታውን ጠቅሶ ካርታ ከሰራላቸው ደግሞ ምንም እንኳን በቤታቸው ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመር ቢያልፍም ወረዳው ምንም የማድረግ መብት እንደሌለውም ተናግረዋል።

“የወረዳ 14 ነዋሪዎች ይገለገሉበት የነበረ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ‹‹የኮብል ስቶን›› መንገድ አርሶ አደር ናቸው ለተባሉ ግለሰቦች በምሪት ተሰጥቷል። ሕዝብ እና መንግሥት ለመንገድ ብሎ ወጪ ያወጣበትን መሠረተ ልማት ለቤት ግንባታ መስጠት ተገቢ ነውን?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ድሪባ፤ ቦታው በኮብል ስቶን መንገድ እንዳልተሰራበት ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዝግጅት ክፍሉ ስለቦታው በፎቶ ማስረጃ እንዳለው ሲገልጽላቸው፤ መንገዱ በፕላን ላይ አይታይም የሚል ሌላ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህን መልሳቸውን ተከትሎ ቦታው በፕላን ባዶ ቦታ የሚያሳይ ከሆነ ለእግረኛ የኮብል ድንጋይ ንጣፍ ሲሰራ ለምን አልከለከላችሁም ለሚለው ጥያቄ ግን ምላሽ መስጠት አልቻሉም።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአቶ ፍቃዱ ስም የተመራው እና ግንባታ የተጀመረበት ቦታ ቀደም ሲል ካርታ ተሰርቶለት የመከነ ነበር። አሁን ላይ እንደገና ነው ካርታ የተሰራለት። ግንባታ በሚካሄድበት ቦታ ደግሞ ኮብልስቶን መንገድ የነበረ ነው። ዝግጅት ክፍላችንም ይሄንን በሰነድም በአካልም ተመልክቷል።

ይሄን አስመልክቶ የኮብል ስቶን መንገድ የለም ብለው ሲከራከሩን የነበሩት ሥራ አስፈጻሚው፤ ከአስፋልት ዳር የእግረኛ መንገድ አለ፤ ከእግረኛ መንገዱ ቀጥሎ ስለሆነ ኮብል ስቶን መንገዱ የተነጠፈው ለምን ይጠቅማል? ሲሉ ራሳቸው ጠያቂ ሆነው ቀርበዋል። እኛም ጥያቄአቸውን በጥያቄ መልሰን ኮብል ስቶኑ የማይጠቅም ከሆነ ከጅምሩ የመንገዱ ግንባታ ሕገወጥ ነበር? ስንል ጠየቅናቸው። ሥራ አስፈጻሚውም ‹‹ሕገ ወጥ ነው አለላኩም›› የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። ሆኖም ጥያቄ ከሚመስል ምላሻቸውም ጭምር መረዳት እንደሚቻለው በቦታው ላይ የኮብልስቶን መንገድ የነበረ መሆኑን ነው።

ቦታውን የወሰዱት እና ቦታው ይገባቸዋል በማለት ውሳኔ ያስተላለፉት የቀጣና ኮሚቴዎች በትክልል አርሶ አደሮች ናቸው? የወረዳው ነዋሪዎች ናቸው? ለሚለው ጥያቄም ሥራ አስፈጻሚውም ‹‹አዎ የወረዳው ነዋሪዎች ናቸው›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ያለ አግባብ ለቤተክርስቲያን በአስፋልት ዳር ለዚያውም 200 ካሬ የማይሞላ ቦታ ላይ እንዴት ፈቃድ ሊያገኝ ቻለ? የሚል ጥያቄ ለዋና ሥራ አስፈፃሚው ያነሳንላቸው ሲሆን፤ ዋና ሥራ አስፈፃሚውም ይሄ የሆነው ቦታውን ከተመሩት አርሶ አደሮች ተከራይቶት እንጂ በምሪት ተሰጥቶት አይደለም ብለዋል።

ይሁንና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፤ ቤተክርስቲያኑ ከመስጅድ ጎን በመሆኑ የጸጥታ ችግር እንዳያስከትል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ወስኖ የሰጣቸው ቦታ ነው የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።

 የክፍለ ከተማው ምላሽ

አቶ አንዱአለም ይጥና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። እንደ አቶ አንዱአለም ይጥና ገለጻ፤ በ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ነበር። የ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የራሱ የሆነ መቋቋሚያ አዋጅ አዘጋጀ። ይህ መቋቋሚያ አዋጅም ቁጥር 74/2014 ይባላል።

በዚህ አዋጅ መሠረት ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሥር የነበሩ አራት ወረዳዎች ወደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እንዲካተቱ ሆነ። አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እነኝህን ወረዳዎች ከኮልፌ ከቀራንዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሲረከብ አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጆች ጋር ተያይዞ የነበሩ ባለጉዳዮች መረከባቸውን ያስረዳሉ። ከተረከቧቸው አርሶ አደሮች መካከለም 40 ለሚሆኑት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መብት ተፈጥሮላቸው ነበር ይላሉ።

ነገር ግን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር መብት በተፈጠረላቸው አርሶ አደሮች ላይ ምርመራ ካደረገ በኋላ 22 የሚሆኑትን ካርታዎች እንዲመክኑ ማደረጋቸውን ይናገራሉ። ለዚህም በምክንያትነት ያነሱት አንድ ሰው አርሶአደር በተመለከተ ሊስተናገድ የሚችለው መመሪያ ቁጥር 20/2013 በመሆኑ ነው።

በዚህ መመሪያ ሦስት ዋና ዋና ጭብጦች አሉ የሚሉት ኃላፊው ፤ አንደኛ፣ አሁን ላይ አርሶ አደሩ መሬቱ በእጁ ያለና የሚጠቀምበት ከሆነ መብት ተፈጥሮለት ይስተናገዳል። ሁለተኛ፣ ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው ቦታ የፕላን ተቃርኖ ቢኖረውም ይስተናገዳል። ለምሳሌ፣ አረንጓዴ ስፍራ ወይም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሊሆን ይችላል። ይህን መሰል የፕላን ተቃርኖ ሲኖር መሬቱ ለአርሶ አደሩ ልጅ ወጪ ተደርጎ እንደሚሰጥ በመመሪያው ተቀምጧል። ሦስተኛው፣ በ1997 እና 1988 የአየር ካርታ ላይ የማይታይ ቢሆንም ይስተናገዳል የሚል ነው።

እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ጭብጦች መሠረት በማድረግ የሚደርሷቸውን ጥቆማዎች ለማጣራት ክፍለ ከተማው ከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የኦዲት ግብር ኃይል ማቋቋማቸውን ይገልጻሉ። የተቋቋመው የኦዲት ግብር ኃይልም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ብቻ 22 የሚጠጉ በሕገ ወጥ የተወሰዱና ካርታ የተሰራላቸውን ቦታዎች ማግኘቱን ጠቁመው፤ የ22ቱም ካርታ እንደመከነ እና መሬቱም ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል። 18 የሚሆኑት ደግሞ ግብረ ኃይሉ ማጣራት ካደረገ በኋላ እንዲጸድቅ ተድርጓል።

በመመሪያ ቁጥር 20/2013 በአንቀጽ 9 እንደተመላከተው ደግሞ መብት እንዲፈጠርላቸው የጠየቁ ሰዎች አርሶ አደር እና የአርሶአደር ልጅ ስለመሆናቸው ሲጣራ ኮሚቴ ይቋቋማል። ኮሚቴውም የወረዳውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የወረዳው ግብርና ኮሚሽን፣ የወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም አርሶ አደሩን የሚያውቁት የቀጣና ኮሚቴዎች የያዘ ነው። 18 የሚሆኑት መብት የተፈጠላቸው አርሶ አደሮችም በመመሪያው መሠረት ሕጉን ጠብቀው የተስተናገዱ ስለሆነ ግብረ ኃይሉ ጥያቄአቸውን አጽድቆታል። ይሁን እንጂ አሁንም በወረዳው የተለያዩ ቅሬታዎች እንደሚነሱ አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርምራ ክፍል አርሶ አደር ተብለው መሬት የተሰጣቸው ሰዎች የአካበቢው ማኅበረሰብ በጋራ አልምቶ ሲጠቀምበት የቆየውን የኮብል ስቶን መንገድ መሆኑን ከኅብረተሰቡ ጥቆማ ደርሷል። እናም በቦታው ተገኝተን ሁኔታውን አረጋግጠናል። ስለዚህ ምን ይላሉ ብሎ ለኃላፊው ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር። ኃላፊውም፣ የለማ ኮብል ስቶን መንገድ ለአርሶ አደር በሚል መሰጠቱን እንደማያውቁ ገልጸው፤ ስለጉዳዩ በማጣራት ለዝግጅት ክፍሉ ስለሁኔታው እንደሚገልጹ ተናግረዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 በአርሶ አደር እና በአርሶ አደር ልጅ ስም የተሰጣቸው መሬት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ገመድ የሚያልፍባቸው፤ ትልልቅ የኃይል ተሸካሚ ፖሎችም ያሉበት ነው። እንደዚህ ዓይነት ከባድ የኃይል ተሸካሚ መስመሮች በያዙ ቦታዎች እና የፕላን ተቃርኖ ያለባቸው ቦታዎችን መስጠቱ ተጊቢ ነው ብለው ያምናሉ? ቦታው የተሰጡት ሰዎች አርሶ አደር ናቸው ቢባል እንኳን ከባድ የኃይል አስተላላፊ ገመድ በሚያልፍበት አካበቢ መሬት መስጠት ለሚደርሰው አደጋ ተጣያቂው ማን ነው ሲል ዝግጅት ክፍሉ ጠይቋል።

አቶ አንዱአለም በምላሻቸው፤ በመመሪያ ቁጥር 20/2013 መሠረት ለአርሶ አደር የሚሰጡ ቦታዎች የፕላን ተቃርኖ ቢኖርባቸውም ለአርሶ አደሮች እንዲሰጡ ያዝዛል።

ይህ ብቻ ሳይሆን 1988 ዓ.ም ጂ.አይ.ኤስ እና 1997 ላይን ማፕ ላይ ባይታይም እንኳን ለአርሶ አደሮች እንዲሰጥ መመሪያው ያዝዛል ያሉት ኃላፊው፤ ሆኖም መመሪያው የራሱ ድክመት እና ጥንካሬ ስለሚኖረው ይሄን መተቸት እንደማይፈልጉም ጠቁመዋል።

ሌላው በዝግጅት ክፍሉ ለኃላፊው ከተነሱ ጥያቆች መካከል፣ በወረዳው አርሶ አደር ከተባሉት አካላት በተጨማሪ የህይወት ምንጭ ዓለም አቀፍ ቤክርስቲያን ተገንብቷል። ስለዚህ ምን የሚያውቁት ነገር አለ? የሚል ነበር። ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ኃላፊው፤ በወረዳው የብድር መስጅድ እና ቤተክርስቲያኑ ጎን ለጎን ነበሩ። ይህ ደግሞ በሁለቱ አማኞች መካከል የጸጥታ ስጋት የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል።

ይህን ተከትሎ ባለፈው ዓመት የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው የ60 ቀን እቅድ የሁለቱ ቤተ ዕምነቶች ካልተነጣጠሉ ለወረዳውም ብሎም ለክፍለ ከተማ እንዲሁም ለከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ችግር እንዳለው በመረዳት የከንቲባ ጽሕፈት ቤት እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መጥተው ጉዳዩን ከተመለከቱ በኋላ ቤተክርስቲያኑ እንዲነሳ በማድረግ አሁን ቤተክርስቲያኑ የሚገኝበት ቦታ መሰጠቱን አመልክተዋል።

በእርግጥ አሁን ቤተክርስቲያኑ የሚገኝበት ቦታ ግማሽ አረንጓዴ ስፍራ፣ ግማሹ ‹‹ሪዚደንስ›› ነበር የሚሉት ኃላፊው፤ ሆኖም በቦታው የፕላን ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል። በዚህም ቤተክርስቲያኑ በፊት ከነበረበት ቦታ መነሳቱን ገልጸዋል። ኃላፊው ይሄን ይበሉ እንጂ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባደረገው ማጣራት ቤተክትርስቲያኑ እስካሁን ከቦታው አለመነሳቱን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈልጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በተጨማሪ ለቤተክርስቲያኑ የተሰጠው መሬት ሂደቱን ጠብቆ በከንቲባ እና መሬት ልማትና ማኔጅመንት አምኖበት እንደተሰጠ ኃላፊው ቢገልፁም፤ የወረዳ 14 ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰቦች እንደገለጹት፤ ቦታው ለቤተክርስቲያኑ በምሪት አለመሰጠቱን ተናግዋል። ይሄም ሌላው የተቃርኖ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ተችሏል።

ይህ ቤተክርስቲን ባረፈበት ቦታ የመብራት ኃይል ተሸካሚ ፖሎች እና ገመዶች የሚያልፉበት ነው። ይህን ጉዳይ እንዴት አያችሁት? ተብለው የተጠቁት ኃላፊው፤ ‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ገመድ መኖሩን አላየሁትም›› የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። ኃላፊው አክለውም የኤሌክትሪክ ገመዱን በተመለከተ ማንም ሰው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ ጉዳዩን ለኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በማሳወቅ የኃይል ተሸካሚው ምሰሶ እንዲነሳና ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወር ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ምላሽ

ምሰሶው በሚያልፍባቸው ቦታዎች ላይ ሕንፃዎችን መገንባት ይቻላል ወይ? ቤት የሚገነቡ ካሉስ ተቋማችሁ መብቱን እንዴት ያስጠብቃል? ተብለው የተጠየቁት የምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ቁጥር1 ሥራ አስኪያጂ አቶ ወንድወሰን ፈዬራ እንደገለጹት፤ መሬት የሚሰጠው ሌላ አካል ነው። የመብራት ኃይል የሚሰራው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ብቻ ነው። መስመር ከተዘረጋ በኋላ ቤቶች ቢገነቡ የቤት ግንባታ ጋር የሚያገናኘው አካል ነው መጠየቅ ያለበት እንጂ የእኛ ተቋም አይደለም። ሆኖም መስሪያ ቤቱ በሰዎች መኖሪያ ቤት ላይ ከባድ ኃይል ተሻካሚ ገመድ መዘርጋት ይቅርና በአጥር ላይ እንኳን ዝቅተኛ ኃይል ተሻካሚ ገመድ አይዘረጋም ብለዋል።

ከቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መመሪያ ምን ይላል? ተብለው የተጠየቁት አቶ ወንድወሰን፤ መጀመሪያ የኃይል ተሸካሚ መስመር ተዘርግቶ ከነበር እና በኃይል ተሸካሚው ገመድ ስር ግንባታ ማከናወን የሚፈልግ ሰው በመመሪያው መሰረት ማዘዋወሪያ ይጠይቃል። ለማዘዋወሪያው ክፍያ ይከፍላል። በመቀጠልም የኃይል ተሸካሚ መስመር ማዘዋወር ግዴታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

በዚህ አግባብ ለሚመጡ ሰዎች የማዘዋወር ሥራ እየሠራን ነው ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁን ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ግን ማንም አካል ጥያቄ ለተቋማቸው እንዳላቀረበና ስለጉዳዩም ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዝግጅት የምርመራና መልካም አስተዳደር ክፍል መስማታቸውን አስረድተዋል።

ይህን ተከትሎ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል ጋዜጠኞች እናንተ ሳታውቁት እንደዚህ አይነት ግንባታ ሲካሄድ መስሪያ ቤታችሁ ምን ዓይነት እርምጃ ይወስዳል? ተብለው የተጠየቁት አቶ ወንድወሰን፤ መሰል ችግር ሲያጋጥም በቅድሚያ ችግሩ ለተፈጠረበት ወረዳ ጉዳዩን በማሳወቅ ግንባታ ያካሄዱት አካላት ሕጋዊ ስለመሆናቸው ያጣራል። በመቀጠልም በቦታው ችግር ቢከሰት መሥሪያ ቤታቸው ተጠያቂ እንደማይሆን በማሳወቅ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ለወረዳው ያሳውቃል። ችግሩ በወረዳው የማይፈታ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ተቋማቸው ህግ ክፍል በመውሰድ በሕግ አግባብ እንዲታይ እንደሚደረግ ያስረዳሉ። ሆኖም አሁን ላይ ውዝግብ በተፈጠረበት ቦታ ችግር ቢከሰት መሥሪያ ቤታቸው ስለጉዳዩ ስለማያውቅ በማንኛውም መንገድ መጠየቅ እንደማይችል አመልክተዋል።

መመሪያው ምን ይላል?

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደር የመኖሪያ ቤትና የከተማ ግብርና መጠቀሚያ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አሰጣጥና ዘላቂ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጣ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 20/2013 መሰረት፤ በክፍል አንድ በተቀመጠው ጠቅላላ ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር 2.8 እንደሚለው ‹‹አርሶ አደር ማለት›› በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ በከተማ ግብርና ሥራ ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ ራሱንና ቤተሰቡን የሚያስተዳድር ሰው ነው ይላል።

በተጨማሪም ንዑስ ቁጥር 2.10 ‹‹በአርሶ አደር የተያዙ ይዞታዎች›› ማለት በከተማው አስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ አርሶ አደሩ ለተለያዩ የከተማ ግብርና ሥራዎችና ለመኖሪያነት እየተጠቀመበትና እያስተዳደረው ያለው መሬት ነው ይላል። በዚሁ ክፍል ቁጥር 4 ላይ የተቀመጠው የተፈፃሚነት ወሰን በተመለከተ ደግሞ፤ ይህ መመሪያ በከተማው ክልል ውስጥ በአርሶ አደር እና በአርሶ አደር ልጆች ለመኖሪያ እና ለተለያዩ የግብርና ሥራዎች አገልግሎት እየሰጡ ባሉ የመሬት ይዞታዎች ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል የሚል ነው።

ምንም እንኳን መመሪያው ይህን ቢልም፤ ለረጅም ዓመታት የኖሩ አካባቢ ማኅበረሰብ መሬት ላይ ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ መሆኑን ያስረዳሉ። ከወረዳውና ከሥራ ኃላፊዎች የተገኘው መረጃም እነዚህ ግለሰቦች ይህ ስፍራ ትክክለኛ ይዞታቸው ነው የሚል መረጃ ማቅረብ አልቻለም።

ሲቭል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም መረጃዎችን ለማጥራት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 በተደጋጋሚ ቢመላለስም በቂ ማስረጃ ማግኘት አልቻለም። በወረዳው ሲቭል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት እነዚህ ግለሰቦች በወረዳው ነዋሪዎች ስለመሆናቸው መረጃዎችን ለማየት የሞከረ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ የአካባቢው ነዋሪ ስለመሆናቸው ብሎም በቦታው ላይ ግብርና እያካሄዱ ነበር የሚል መረጃ አላገኘም። በአብዛኞቹ ግለሰቦች ሥም የተመዘገበ መታወቂያ ሊያገኝም አልቻለም።

በመሆኑም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራና መልካም አስተዳደር ክፍል በቀጣይ አባሪ መረጃዎችን በማከልና ሌሎች መረጃዎችን በመሰብሰብ ‹‹እውነት ከየት እንደሆነች›› ለአንባቢያን አስፈላጊውን መረጃ የሚያደርስ ይሆናል።

 ሙሉቀን ታደገ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015

Recommended For You