አዲስ ዘመን ድሮ

የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ጉዳይ በንጉሡ ዘመንም ትኩስ አጀንዳ ነበር። “ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋር ተዋሀደች”፤ ዜጎችስ በወቅቱ ስለዚህ ጉዳይ ምን አሉ.. የሚለውን ጉዳይ አዲስ ዘመን ያኔ አስተያየቶችን አካቶ ሲዘግበው ዝና ነበር። ዛሬ ግን ያ ዜና ታሪክ ነውና ዘመን አልፎ ስናነበው የነበረውን ታሪክ የምናይበት ይሆናል። የማናውቃቸውን ጉዳዮች ለማወቅ “የማታውቁት ታሪክ ቢኖር” ከተሰኘው ገጽ ላይ ቀንጭበን፣ ከወይዛዝርት ገጽም አንዱን መርጠን፤ በመጨረሻም በደርግ ዘመነ መንግሥት መሳ ለመሳ ተቀምጠው ይዘመሩ የነበሩትን ሁለቱን ብሔራዊ መዝሙሮች ለማናውቃቸው እንድናውቅ፤ የምናውቃቸውም እንድናስታውሳቸው በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ እንደሚከተለው እናካፍላችሁ።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ በመዋሐድዋ የደረሱ የደስታ መግለጫ ቴሌግራሞች

ኤርትራ ከውድ እናት ሀገርዋ ከኢትዮጵያ ጋር አንድ በመሆንዋ የተሰማኝን ደስታ ለግርማዊነትዎ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ። አገልጋይዎ ሞሐመድ።

አሥመራ

በኅዳር አምስት ቀን በተደረገው ታሪካዊ ሥራ ኤርትራ ፌዴሬሽኑን ሠርዛ ከውድ ሀገርዋ ጋር አንድ በመሆንዋ የተሰማኝ ደስታ ከፍ ያለ ነው።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ አንድ በመሆንዋ የድሮው ሃሳባችንና ድካማችን ስለሆነ እንኳን ሃሳባችን ሆነ እያልሁ የልብ ምኞቴን ለግርማዊነትዎ እገልጣለሁ። (አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 1956 ዓ.ም)

ግለሰቡ በስቅላት እንዲቀጣ ተፈረደበት

መሐመድ ቢላል ጁመር የተባለው ወንጀለኛ

 በመሰላ ወረዳ ግዛት እመት አረጋሽ እንድሮ የተባለችውን ሴት ገድሏል በመባል ሐረር ከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ተከሶ ቀርቦ ስለተመሰከረበትና ራሱም ስላመነ በስቅላት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል። (አዲስ ዘመን መጋቢት 17 ቀን 1958ዓ.ም)

የኮክቴል ግብዣ

ግርማዊ ንጉሠ ነግሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥር 9 ቀን ከምሽቱ 12 ሰዓት ተኩል ሲሆን፤ በአሥመራ ቤተ መንግሥት የኮክቴል ግብዣ አድርገዋል። በግብዣውም ላይ በአሥመራ ከተማ የሚገኙ ቆንስላዎች፣ የኮሚኒኬሽን ሹሞች፣ የቃኘው ሬዲዮ ጣቢያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ ታላላቅ ነጋዴዎች፣ የሀገር ሹማምንትና መኮንንት ተገኝተዋል። (አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 1956ዓ.ም)

የማታውቁት ታሪክ ቢኖር

በአሜሪካ ቻውታውኳ በተባለ አምባ ሁለት ሰዎች የግል ገንዘባቸውን አውጥተው በስምምነት አንድ ተማሪ ቤት አሠሩ። ተማሪ ቤቱ ተሠርቶ ባለቀ ጊዜ በቀለም አቀባቡ ላይ ሁለቱ ሰዎች ሳይስማሙ ቀሩ። አንደኛው ነጭ ቀለም መቀባት አለበት አለ። ሁለተኛው ደግሞ ቀይ ቀለም መቀባት አለበት አለ። ሁለቱ ሰዎች በቀለም አመራረጡ ስላልተስማሙ ተማሪ ቤቱ በነጭና በቀይ ቀለም ተቀባ። አቀባቡም እኩል እንዲደርሳቸው ስለተደረገ ግድግዳው በየመጠኑ ተከፋፍሎ በመቀባቱ የዳማ መጫወቻ መሰለ። (አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 1957ዓ.ም)

በሶማሊያ ምድር ውሃ የሚገኘው ጉድጓድ እየተቆፈረ ነው። ጉድጓዱን የሚቆፍሩት ሴቶች ናቸው። የሚቆፍሩትም በዶማ ወይም ዛቢያ ባለቀለት መጥረቢያ አይደለም። በባዶ እጃቸው ነው። (አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 1958ዓ.ም)

ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ

አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

ከሥራ ወጥቼ እስከ ምሽቱ 6 ሰዓት ድረስ ለማምሸት እፈልጋለሁ። ከጓደኞቼ ጋር መጫወት እፈልጋለሁ። ግን ሚስቴ ከሥራ ወጥተህ እንደ ዶሮ መስፈር አለብህ ትላለች፤ ትጨቀጭቀኛለች። ብመክር ባስመክር አልሰማ አለች። ልፍታት?

– እንደሱ አይደለም ጌታው እኔንም አይቆጡኝና ሚስትዎን በድለዋል። ክሰው ከቤትዎ ማምሸት ይልመዱ። እንደራስዎ ይዩት። ነገሩ ተገላብጦ ሚስትዎ ከውጭ እያመሹ እርስዎ ቤት እንዲጠብቁ ቢደረግ ይወዳሉ ? ተናደው የቤቱን ሳህን ሁሉ ይፈጁ ነበር። የሚያስመሽዎ ጓደኞችዎም መጥፎዎች ናቸውና ይሽሹ። ጨዋ አባወራ ይሁኑ እንጂ ሚስትዎን አይፍቱ። ለመሆኑ እንዲያው ግን ለመሆኑ አመልዎን ሳያስተካክሉ ለምን ሚስት አገቡ? (አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12 ቀን 1958ዓ.ም)

ለፈገግታ ያህል

ሰውየው እብድ ነው። ውሃ ዋና ይችላል። ከወንዝ አጠገብ ቆሞ ሳለ ውሃው እያንገላታ አንድ ሰው ይዞ ሲሔድ አየ። ወዲያውኑ ከዥረቱ ውስጥ ዘልሎ ገብቶ ሰውየውን አወጣው። ይሄን ጀብዱ የተመለከቱ ሰዎች ነበሩ።

እነዚህ ሰዎች ከጥቂት ጊዜ በኋላ በእዚያው መንገድ ሲመለሱ እብዱ ከውሃው ውስጥ ያወጣው ሰውዬ ተሰቅሎና ሞቶ አዩ።

እብዱም በዚያው ሥፍራ ቆሞ ሲመለከት ስለነበረ ወደ እርሱ ዞር ብለው “የዚህን ሰው ነፍስ ለማዳን አንተ ጥረህ ነበረ፤ ከውሃው ብታድነውም ይሄው ተሰቅሎ አረፈው” ቢሉ ጊዜ እብዱም መለስ አድርጎ “ልብሱ እንዲደርቅ እኔ ነኝ የሰቀልኩት” አለ ይባላል። (አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 1956ዓ.ም)

የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ

በኅብረተሰባዊነት አብቢ ለምልሚ!

ቃልኪዳን ገብተዋል ጀግኖች ልጆችሽ

ወንዞች ተራሮችሽ ድንግል መሬትሽ

ለኢትዮጵያ አንድነት ለነፃነትሽ

መስዋዕት ሊሆኑ ለክብር ለዝናሽ!

ተራማጅ ወደፊት በጥበብ ጎዳና

ታጠቂ ለሥራ ላገር ብልጽግና!

የጀግኖች እናት ነሽ በልጆችሽ ኩሪ

ጠላቶችሽ ይጥፉ ለዘላለም ኑሪ!

ኢንተርናሲዮናል

ተነሱ እናንተ የረሀብ እስረኞች

ተነሱ የምድር ጎስቁዋሎች።

ፍትህ በሚገባ ይበየናል!

ሻል ያለ ዓለምም ይታያል።

ከእንግዲህ ባለፈው ይብቃ እሥር፣

ተነሱ ባሮች ጣሉ ቀምበር።

ያለም መሠረት አዲስ ይሁን፣

ኢምንት ነን እልፍ እንሁን።

የፍጻሜው ጦርነት ነው፣

ሁሉም ዘብ ይቁም በቦታው።

የሰው ዘር በሙሉ፣

ወዛደር ይሆናሉ።

የፍጻሜው ጦርነት ነው፣

ሁሉም ዘበ ይቁም በቦታው።

ኢንተርናሲዮናል፣

የሰው ዘር ይሆናል።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 4 ቀን 1971ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 23/2015

Recommended For You