
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስፖርት ትጥቅ እጥረትን ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከጎፈሬ ሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር ተፈራረመ። ስምምነቱ የእግር ኳስ ስፖርት ዘርፉን በዘላቂነት ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በስምምነት መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የስፖርት ትጥቅ እጥረትን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በተፈረመው ስምምነትም ፕሮጀክቱ ያለበትን መሠረታዊ የትጥቅ ችግር ለመፍታት ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን የእግር ኳስን በዘላቂነት ለማሳደግም የሚያግዝ ነው፡፡
አሁን ላይ ለ970 ተጫዋቾች እና ለ135 አሠልጣኞች የትጥቅ ድጋፍ ተደርጎላቸው የምዘና ውድድር እያደረጉ ይገኛሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ስምምነቱም ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ቱፋ እንዲሁም የጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የነገውን የሀገሪቱን ተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾች ለማፍራት አይነተኛ አስተዋጽኦ ስላለው ድጋፉና ስምምነቱ እንደ ውጤታማነት የሚታይ ነው፡፡ በዚህም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ የስፖርት ትጥቅ ወጪውን 70 በመቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ጎፈሬ ትጥቅ አምራች ድርጅት 30 በመቶ ወጪውን እንደሚሸፍን በስምምነቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም